Artcles

ፌዴራላዊ ስርዓቱ ችግር የለውም!

By Admin

October 20, 2017

ፌዴራላዊ ስርዓቱ ችግር የለውም!

አሜን ተፈሪ

የሐገራችን የፌዴራሊዝም ስርዓት ለሐገራችን ተጨባጭ ችግር መፍትሔ ሆኖ የተቀረጸ እና በተግባራዊ ሂደቱም አንፀባራቂ ድሎችን ያስመዘገበ ስርዓት ነው፡፡ ይህ ስርዓት ገና ከመነሻው ጀምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት ሲሆን፤ አሁንም የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ አንዳንዶቹ በየትኛውም የፌዴራል ስርኣት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ከሐገራችን ልዩ ሁኔታ ተያይዘው ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ወሰን ከማከለል ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች፤ ሐገራት ከአሃዳዊ ወደ ፌራላዊ ሰርኣት ሲሸጋገሩ በየትኛውም ሐገር ሊጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የችግሮቹ መከሰት ሳይሆን፤ ችግሮቹን በተቻለ ፍጥነት አጥንቶ መፍትሔ የማስቀመጥ እና የተቀመጡትን መፍትሔዎችም በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ መቻል ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ የተከሰቱት ችግሮች ገና ከመነሻው ህገ መንግስታዊ መፍትሔ የተቀመጠላቸው ሆኖ ሳለ፤ የወሰን ክርክሮች እና ግጭቶች ሲከሰቱ፤ የችግሩን መንስዔ እና ባህርይ በአግባቡ በመረዳት ለመፍትሔ በመንቀሳቀስ ረገድ የነበረው ዳተኝነት ለግጭቶች መንስዔ ሆኗል፡፡

ፌዴራሊዝንም በመላው ዓለም በተለይም በኢትዮጵያ ተመራጭ ያደረገው የመሪዎች ፍላጎት አይደለም፡፡ ይልቅስ የተጨባጭ ሁኔታዎች ግፊት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ አንድ አውራ ብሔር የአገሪቱን ተቋማት በመቆጣጠር የራሱን ማንነት እያሳደገ ሌሎች አናሳ ብሔሮች እንዲገለሉ ማድረጉ ቅሬታዎችን እና በመፍጠሩ፤ ይህን ችግር በመፍታት ሐገሪቱን ለእርስ በእርስ ግጭት የዳረገውን እንቅፋት ለማስወገድ ታስቦ የተቀመጠ መፍትሔ ነው፡፡

የምዕራቡ ዓለም ‹‹የኔሽን ስቴት›› ጽንሰ ሐሳብ አንድ ብሔር በሰፈረበት የአገር ግዛት ያስፈልጋል የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህም አንድን ብሔር ታሳቢ ያደረገ መንግሥት የማቋቋም ፍላጎት ማኅበረሰብ ወይም ፖለቲካን የሚተነትነው ግለሰብን በመሥፈርትነት በመጠቀም ነው፡፡ ይህም አስተሳሰብ ከሊበራል ሞዴል ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ይህ ሞዴል በበርካታ ምዕራባዊ አገሮች ለዘመናት የተተገበረና ከቅኝ ግዛት ዘመን ማክተም በኋላም በአፍሪካ የተቀዳ ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ባልተገዛችውና ረዥም የፖለቲካ ታሪክ ባላት ኢትዮጵያም የተተገበረ ሞዴል ነበር፡፡ በዘመናዊ የሐገሪቱ ታሪክ የምናየው አስተዳደርም፤ የተማከለ፣ አሃዳዊ፣ ከክርስትና እና ከአማርኛ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የ‹‹ኔሽን ስቴት›› ባህርይ ያለው ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም፡፡

እንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ የታየው ‹‹የኔሽን ስቴት›› ግንባታ ሂደት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አልነበረም፡፡ አናሳ ብሔረሰቦችን በመጨፍለቅ የተካሄደው የአገር ግንባታ ሒደት ብዙዎችን ያገለለ በመሆኑ፤ የመገፋት ስሜትን ፈጥሯል፡፡

አንድ ‹‹ኔሽን ስቴት›› ሊበራልና ዴሞክራሲያዊ ከሆነ፤ እንዲሁም ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ልማትን ካረጋገጠ፤ አናሳ ብሔሮች ወደ አውራው ባህል፣ ልማድና ቋንቋ መቀላቀላቸውና መጥፋታቸው የማይቀር መሆኑን የሚገምቱ በርካቶች ነበሩ፡፡ በ1960ዎቹ የነበረው አስተሳሰብ እንዲህ ያለ ነበር፡፡ ይሁንና በተግባር የታየው ተጨባጭ ሁኔታ ይህን የሚመሰክር ባይሆንም ‹‹የኔሽን ስቴት›› አስተሳሰብ አሁንም ገዥ ሐሳብ ሆኖ ይታያል፡፡

ሆኖም ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› የሚል መፈክር የሚያቀነቅኑት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከነበረው አስተሳሰብ የወጣ ጎዳና የሚከተሉ ይመስላል፡፡ ይህን አስተሳሰብ በግልጽ ለማስፋፋት እየጣሩም ነው፡፡ አሜሪካን ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከሁለትዮሽ ስምምነቶች ለማውጣት እየሰሩ ይታያሉ፡፡ የአሜሪካ ኅብረተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተከፋፍሎ ይታያል፡፡ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከፖለቲካ ሂደቱና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የተገለሉ እና ማንነታቸውም ዕውቅና የተነፈገው ቡድኖች ‹‹ኔሽን ስቴቱን›› እየተገዳደሩት ይገኛል፡፡

አሁን የካታሎኒያ ህዝብ በስፔን፤ ኩርዶች በኢራቅ፤ ቀደም ሲል ስኮትላንዳውያን በዩናይትድ ኪንግደም፤ እንዲሁም የኪዩቤክ በካናዳና ለማድረግ የሚሞክሩት ይኼንን ነው፡፡ የኢትዮጵያ የነፃነት እንቅስቃሴዎች በዚሁ አንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ክስተቶች የ‹‹ኔሽን ስቴት›› አስተሳሰብ አግላይ ባህርይ እንዳለው መረዳት የሚያስችሉ ተጨባጭ ምስክሮች ናቸው፡፡

ኅብረ ብሔራዊ የአስተዳደር ሥርዓት በአንድ አገር ከአንድ በላይ ማንነቶች እንዳሉ ዕውቅና በመስጠት የተገለሉ ቡድኖች፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያኙ እንደሚያደርግ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበት ዘመን የብሔር ማንነት ያንሰራራበት እና ኅብረ ብሔራዊ የአስተዳደር ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን የሚናገር ዘመን ነው፡፡

በርግጥ በሊበራል የመንግሥት ስርዓት በሚተዳደሩና የተከፋፈሉ ማኅበረሰቦች ባሏቸው ሐገሮች ውስጥ ማኅበረሰቦች ራሳቸውን በመደብ፣ በፆታ ወይም በሲቪል ማኅበራት አደራጅተው ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ማንነት ወሳኝ የመታገያ አጀንዳ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በሊበራሉ ዓለምም አዲስ አመለካከት ብቅ እያለ ነው፡፡ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁም አዲስ አስተሳሰብ እየተጠናከረ ነው፡፡ ሐገራችን ከራሷ ችግሮች በመነሳት የቡድንና የግለሰብ መብቶችን ጎን ለጎን ለማስኬድ የሚያስችል ፌዴራላዊ ስርዓት አቁማለች፡፡

እንደሚታወቀው፤ ሁለት ዓይነት የፌዴራል ሥርዓቶች አሉ፡፡ ለምሣሌ፤ አሜሪካ፣ ጀርመንና ኦስትሪያ የሚከተሉት አካባቢያዊ ፌዴሬሽን ሲሆን፤ የዚህ ዓይነት የፌዴራል ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ ሥልጣን ከአንድ ማዕከል ወደ ተለያዩ ማዕከሎች እንዲሠራጭ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ አደረጃጀት፤ ክልሎች አካባቢያዊ አስተዳደሮችን መሠረት አድርገው እንዲዋቀሩ ያደረጋል፡፡ ‹‹ኔሽን ስቴት ፌዴሬሽኖች›› በሚል የሚጠቀሱትም እነዚህ ናቸው፡፡

በሌለ በኩል፤ እንደ ኢትዮጵያና ህንድ ያሉ ፌዴሬሽኖች አሉ፡፡ እነዚህ ፌዴሬሽኖች ሥልጣንን ከማሠራጨት በተጨማሪ የብሔሮችን ጥያቄ መመለስን ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡ የብዝኃነትን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ፌዴሬሽኖች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት፤ የተለያዩ የብሔር ቡድኖች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩና በፌዴራል ተቋማት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይህ የተቋማቱን ተቀባይነት ይጨምራል፡፡ የተለያዩ ቡድኖች በብሔራዊ ደረጃ በሚከናወነው የፖሊሲ ማውጣት ሂደት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ዕድል እንዲያገኙም ያደርጋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ጥያቄ ከመመለስና የፖለቲካና የአስተዳደር አካላትን ከመገንባት አኳያ ብዙ ርቀት መጥተናል፡፡ ከ25 ዓመታት በፊት፤ ክልሎች ዝቅተኛውን አገልግሎት ለመስጠት እንኳን የሚያስችል ተቋማዊ አቅምና የሰው ኃይል አልነበራቸውም፡፡ አሁን ክልሎች ከሰው ኃይል አንፃር በአግባቡ የተደራጁ ናቸው፡፡ በተወሰነ መልኩ የገንዘብ አቅምም አዳብረዋል፡፡ ይሁንና ችግሮችም እንዳሉብን ግልጽ ነው፡፡

ሐገሪቱ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም የገጠማት ችግር የሚጠቁመን አንድ ነገር ቢኖር፤ ፌዴራሊዝሙን እንደ አዲስ የማኅበረሰብ ግንባታ መሣሪያ አድርገን አለመጠቀማችንን ነው፡፡ ስኬታማ ፌዴሬሽኖች አዲስ ማንነት ለመፍጠር ፌዴራሊዝምን በአግባቡ ይጠቀሙበታል፡፡ ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የዘለቀው አንዱ አከራካሪ ጉዳይ በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔር ማንነት መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በእነዚህ ክርክሮች ሁሌም የሚስተዋለው ነገር በሁለቱ መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዳለ መታመኑ ነው፡፡ ይኼ ግን ስህተት ነው፡፡ በፌዴሬሽን የተለያዩ ማንነቶች ይኖራሉ፡፡ የሆነ ቦታ ትወለዳለህ፡፡ የአንድ የሙያ ማኅበር አለያም ሃይማኖታዊ ቡድን አባል ልትሆን ትችላለህ፡፡ ሆኖም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ የተለየ የብሔር ማንነትም ይኖረናል፡፡ እነዚህን የተነባበሩ ማንነቶች አስታርቀን እና አስማምተን መሄድ የምንችልበትን ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ያሉ ጉድለቶችን ማረም ያስፈልጋል፡፡

በማናቸውም የተሳኩ ፌዴሬሽኖች ውስጥ የተለያዩ ማንነቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ማንነቶች ግን ሁሌም ግጭትን አያስከትሉም፡፡ የብሔር ማንነቱ በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ይገለጣል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም የሚያቅፈው ኢትዮጵያዊነት ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት በብሔራዊ ማንነቶች ኪሳራ የሚገኝ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ወይም የብሔር ማንነት ከሌሎች ሁሉ ማንነቶች በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም አረዳድ ነው፡፡ በተለያየ ደረጃ የሚገኘው የፖለቲካ አመራር ይህን ቁም ነገር ተገንዝቦ፤ የፌዴራል ስርዓቱን በመጠቀም የተለያዩ ማንነቶችን እና ህልሞችን ለማስታረቅ አልቻለም፡፡

በተመሳሳይ በራስ በማስተዳደር ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተሳሳተ እይታ መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር በክልላዊ ወይም አካባቢያዊ የፖለቲካ ተቋማት መተዳደር፤ የራስን ቋንቋ እና ባህልን መጠቀም እና ማሳደግን የሚመለከት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የሐገሪቱ አካባቢዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የጎጥ አመለካከትን ለመገንባት ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ በዚህ የተነሳ ክልላዊ ብሔርተኝነት እየገነገነ ሲሄድ ይታያል፡፡ ይህ አደገኛ ነገር ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፤ ለሌላው ማንነት ክብር የመስጠትና የማስተናገድ ብቃትን የሚጠይቅ ነው፡፡ የተለያዩ ማንነቶች ንግግርና ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ክልላዊ ብሔርተኝነት ፅንፍ እየያዘ፤ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ሽብር ውስጥ የሚያስገባበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በርካታ ሰዎች በጠቅላላ የሥርዓቱ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚጨነቁበት አጋጣሚ ይታያል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች የጋራ ትስስሩን ያዳክማሉ፡፡

በሌላ በኩል፤ የፌዴራሉና የክልል መንግሥታት ግንኙነት ተደጋጋፊ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ አንዱ ያለ ሌላው አይኖርም፡፡ በአንዱ ክልል ቀውስ ሲፈጠር ችግሩ የዚያ ክልል ብቻ ተደርጎ ሊታይ አይችልም፡፡ በአንድ ፌዴሬሽን ባለ አንድ ክልል ውስጥ ችግር ሲከሰት፤ ሌሎች ክልሎችን እና የፌዴራል መንግሥቱን መንካቱ የማይቀር ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ችግር በገጠማቸው ወቅት መጀመሪያ ማንንም ሳይጠብቁ ምላሽ መስጠት የነበረባቸው ክልሎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሌሎች ክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት መርዳት አለባቸው፡፡ እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሉ የፌዴራል ተቋማትም ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ስለዚህ በፌዴራል ሥርዓታችን በተለያየ ደረጃ ያሉ ተቋማት ተመጋጋቢ ሆነው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕዝቡም የስርዓቱ ባህርይ እንዲህ ያለ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ተቋማቱ የገዥውን ፓርቲ ምላሽ ሳይጠብቁ የሚጠበቅባቸውን ሚና በወቅቱ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ጣልቃ በመግባት ችግሮቹ የፖለቲካ መፍትሔ እንዲያገኙ መስራት እና ህዝቡ በስርዓቱ ላይ ያለው እምነት እንዳይሸረሸር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡