Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶቻችን

0 388

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶቻችን

                                                     ታዬ ከበደ

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ምከፈቻ ንግግራቸው የአገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶች አንስተው ነበር። አገራችን በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፎች ባለፈው ዓመት በርካታ ድሎችን መጎናፀፏን ፕሬዚዳንሩ ገልፀዋል።

እርግጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የአንድ ጊዜ ግኝት አይደለም። ካለፉት ዓመታት እድገቶች ጋር ተደምሮ የሚታይ ነው። በፖለቲካው ረገድ ኢትዮጵያ የምታካሂደውን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከማጎልበትና ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች። በተለይ ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረው ድርድርና ክርክር ተጠቃሽ መሆኑን በማመላከት ሂደቱ በመቻቻል፣ በመደማመጥና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ በመመስረት ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጠናከር የበኩሉን ሚና እያበረከተ ነው።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጋር የተደረጉ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ዴሞክራሲያዊ ባህልን ከማጎልበት አንጻር ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል።

ሆኖም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች የዴክራሲያዊ ስርዓቱ ለማጠናከር ከፍተኛ ስላለው ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።  በየደረጃው ያሉ የህዝብ ምክር ቤቶችና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ለማጠናከር የተደረጉ ጥረቶችም ጎልብተው መቀጠል ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የመደራጀት መብት ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመስርተው ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። በተለይም የሽግግር መንግስቱን ተከትሎ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነ በኋላ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ እስከተካሄደው ምርጫ ድረስ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው ለአምስት ጊዜያት በተካሄዱት ምርጫዎች ተወዳድረዋል።

ሆኖም የምርጫ ጉዳይ በመራጩ ህዝብ ፍላጎት በሚሰጥ ድምፅ ላይ የተመሰረተ እንጂ፣ በገዥው ፓርቲ አሊያም መንግስት በሚያደርጉት ችሮታ ላይ የሚከናወን ባለመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በአብላጫ ድምፅ ተመራጭ ሊሆኑ አልቻሉም።

ሶስት ምክንያቶች ተቃዋሚዎቹ የህዝቡን አብላጫ ድምፅ እንዳያገኙ ምክንያት ሳይሆኑ አልቀሩም። ቀዳሚው ተቃዋሚዎቹ በህገ መንግስቱና በህዝባቸው ከመተማመን ይልቅ በውጭ ኃይሎች የሚዘወር ዴሞክራሲን የሚሹ ሆነው መቅረባቸው ነው።

ቀጣዩ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሳቢያ በህዝቡ ውስጥ የተፈጠሩ ብሶቶችን ከማራገብና ቅንጭብጫቢ የኒየ-ሊበራሊዝን አስተሳሰብ ከማስተጋባት በስተቀር የህዝብን ቀልብና ልብ ሊገዙ የሚችሉ የነጠሩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ማቅረብ አለመቻላቸው ሲሆን፤ ሰላሹ ደግሞ ተቃዋሚዎቹ ራሳቸውን እንደ ፓርቲ ሲመሰርቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን እናጎለብታለን በሚል እሳቤ ይሁን እንጂ፣ ከአወቃቀራቸው ጀምሮ እርስ በርሳቸው የማይተማመኑና የጎዳነና ላይ ተደባዳቢ ሆነው በመራጩ ህዝብ ዓይን ውስጥ በትዝብት ላይ ስለወደቁ ነው። ይህ የግሌ እምነት ነው። ምህዳሩ ግን ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉበት ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን በፖለቲካው ረገድ መንግስት እየተከተለ ያለው የመቻቻል፣ ችግሮችን በርጋታና በበሰለ መንገድ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት እንዲሁም የሁሉም ህዝቦች ድምፅ እንዲሰማ ያለው ፍላጎት ረጅም ርቀት መጓዛችንን ማሳያዎች ይመስሉኛል።

በኢኮኖሚው ረገድም ቢሆን አገራችን በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት በተከታታይ ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ማምጣት ችላለች። በኢኮኖሚው በኩል ግብርና ዛሬም ቀዳሚ ነው፡፡ ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የግብርናን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው 8 በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በ2009 ዓ.ም የተገኘው ከ10 በመቶ በላይ ውጤት የዚህ ማሳያ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በያዝነው የዕቅድ ዘመን (2008 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ) በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ የ11 በመቶ አመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የማረጋገጥ አቅጣጫ መከተል ለአገራችን ህዳሴ መረጋገጥ መሠረታዊ ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በመጀመሪያ የዚህ ዓይነት ፈጣን ዕድገት የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞው አንዱ ምዕራፍ የሆነው ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ላይ በ2017 ዓ.ም ለመድረስ ወሳኝ ነው፡፡

 

ስለሆነም የህዳሴ ጉዟችን አንዱ ምዕራፍ በስኬት ለማጠናቀቅ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ፈጣን ዕድገቱን ማስቀጠል አማራጭ የለዉም፡፡ በተያያዘም ፈጣንና ፍትሃዊ ዕድገቱ ለህዳሴ ጉዞው መፋጠን ይበልጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ዜጐች እያሳዩት ያለው ከፍተኛ ተነሳሽነትና ተሳትፎ ጥረታቸው በርግጥም ፍሬ እያመጣ መሆኑንና ከዚህ ፍሬም ተጠቃሚ መሆናቸውን በተግባር እያረጋግጡ በመምጣታቸው ነው፡፡

 

በመሆኑም በህዳሴ ጉዟችን ዙሪያ እየተፈጠረ የመጣው አገራዊ መግባባት እየጐለበተ ሊሄድ የሚችለው ዜጋው ውጤት እያየና ተጠቃሚ እየሆነ ሲመጣ በመሆኑ ፈጣንና ፍትሃዊ ዕድገቱን ማስቀጠል በቀጣይም መሠረታዊ አቅጣጫ ነው፡፡

ፈጣን ዕድገቱ መሰረታዊ ስትራቴጂ የሆነበት ሁለተኛው ምክንያት ማህበራዊ አገልግሎቶችንና የኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶችን ለዜጐች በጥራት የማስፋፋት አቅማችን ለማጐልበት ያስችላል፡፡ ሦስተኛ ምክንያት የሚታየውን ድህነትና ሥራ አጥነት በመቅረፍ ረገድ ፈጣንና መሰረተ-ሰፊ ዕድገቱ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑ ነው፡፡

 

የያዝነውን የ11 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሰፊ መሠረት ኖሮት እንዲቀጥል የሚጠበቅ ቢሆንም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚመዘገበው ከፍተኛ እመርታ እና በኢኮኖሚው አወቃቀር የሚታየው መሠረታዊ ለውጥ/ትራንስፎርሜሽን ልዩ መለያዎቹ ይሆናሉ፡፡

የ2008-2012 ዓ.ም የኢኮኖሚ ዕድገት ዕቅዱ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ እመርታ በማምጣት በቀላል ማኑፋክቸሪንግ ሀገራችንን ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ማድረግ እና በአጠቃላይ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከመጀመሪያዎቹ ቀዳሚ ሀገሮች ምድብ ለማሰለፍ በተቀናጀና በተደራጀ ጥረት መሳካት ያለበት አገራዊ ራዕይ አካል መሆኑን ታሳቢ ያደርጋል፡፡

ታዲያ ሀገራዊ ራዕዩ መሳካቱን ለማረጋገጥ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እና ጥራት ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገባ፣ መንግሥትና ሕዝብም ከሁሉም የላቀ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚታዩ ዋና ዋና እንቅፋቶችን ለመፍታት ለዘርፉ ድጋፎችን እንዲያመቻቹና ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ይጠበቃል፡፡

በዚህም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አሁን ካለው ድርሻ በአራት እጥፍ እንዲጨምር በማድረግ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የተመራ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ታቅዷል፡፡

በዚህም መሠረት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በ2007 ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የነበረውን የ4 ነጥብ 5 በመቶ ገደማ ድርሻ በአራት እጥፍ በማሳደግ በ2017 ዓ.ም ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ከማድረግ የመነጨ ነው፡፡ በአጠቃላይ በፖለቲካውም ይሁን በኢኮኖሚው ዘርፍ አገራችን እያስመዘገበች ያለችው እድገቶች ባለተስፋነታችንን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy