Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከግጭትም ቢሆን መማር ይቻላል

0 406

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከግጭትም ቢሆን መማር ይቻላል!
ዘአማን በላይ
ግጭት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ሊከሰት የሚችል ተግባር ነው። የዓለማችን ነባራዊ ክስተት ነው። መንግስታት፣ ህዝቦችና ግለሰቦች በተለያዩ ሁኔታዎች ሳቢያ ሊጋጩ ይችላሉ። ሁኔታዎቹ ጊዜያዊ አለመግባባት አሊያም በዓለም ላይ ያለው የተፈጥሮ ሃብት እጥረት ሊሆን ይችላል።

እንኳንስ በህይወት የፍጥነት መዘውር ውስጥ የሚገኘው የሰው ልጅ ቀርቶ ሁለት ግዑዛን ነገሮችም በተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ሳቢያ ሊጋጩ ይችላሉ። እናም ግጭት ‘ማህበራዊ እንስሳ ነው’ ከሚባለው የሰው ልጅ አንስቶ እስከ ማህበራዊ ተግባቦት የሌለው ግዑዝ ፍጥረት ድረስ ሊኖር የሚችል የዓለማችን ክስተት መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ታዲያ ይህ የዓለም ክስተት ከአፍሪካ እስከ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ብሎም እስከ አንታርቲካ፣ ከአውሮፓ እስከ ኤስያ እንዲሁም ከዓለማችን አንዱ ንፍቀ ክበብ ጫፍ እስከ ሌላኛው ድረስ ሊፈጠር የሚችል ነው። ይህ ነባራዊ ክስተት ‘ለምን ተፈጠረ?’ ተብሎ ሊጠየቅ የሚችል አይደለም።
የዓለማችን ሀዝብ የተላመደውና መፍታት የሚችለውም ነው። ቁም ነገሩ ግጭቱ ከመከሰቱ ላይ አይደለም። ዋናው ጉዳይ ግጭቱ በቅድሚያ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ፣ ከተከሰተም በኋላ በስልጡን መንገድ ለመፍታት መሞከርና ከግጭቱም መማር መቻል ይመስለኛል።

ርግጥ ከግጭትም ቢሆን መማር ይቻላል። መማር ለፈለገ ሰው ወይም አካል እንኳንስ ዓለም አቀፋዊና በሰው ልጅ መስተጋብር ውስጥ ከሚከሰተው ግጭት ቀርቶ ከህፃን ልጅም ብዘ ነገር መማር ይቻላል። ህፃን ልጅ በውስጡ አንዳችም ክፋት የለበትም። ፈረንጆቹ እንደሚሉት “tabula rasa” /ታቡላ ራዛ/ (ምንም ያልተፃፈበት ነጭ ወረቀት እንደ ማለት) ነው። እናም ይህን ንፁህ፣ ክፋት የሌለበትን የህፃን ልጅ “ዓለም” በመመልከት ቅንነትንና ያልተበረዘ አመለካከትን ልንማርበት እንችላለን።

ቁም ነገሩ መሆን የሚገባው ምንም ይሁን ማንም ከአንድ ጉዳይ መማር መቻላችን ላይ ነው። ግጭት በባህሪው መጥፎ ቢሆንም ቅሉ፣ ከተግባሩ ግን መማር ይቻላል። በመሆኑም ግጭቱ በምን ምክንያትና እንዴት እንደተከሰተ፣ እነማን እንዲከሰት እንዳደረጉት፣ በግጭቱ ሳቢያ የተፈጠሩ ጉዳቶች ምን ዓይነት እንደሆኑ፣ አስቀድሞ ሁኔታዎችን መቆጣጠር ቢቻል ኖሮ ግጭቱን በምን ያህል መጠን መቀነስ እንደሚቻል…ወዘተ. መረጃዎችን በትክክለኛው ሳይንሳዊ መንገድ በመተንተን በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤን መያዝ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል።
ይህ መደምደሚያ ግጭቱ ዳግም እንዳይከሰት የሚያስችል መረጃን የሚሰጠን መሆን አለበት። እናም ለወደፊቱ በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ግጭት እንዳይከሰት ሁሉንም የይሆናል መንስኤዎችን ከነቀዳዳቸው መድፈን ያስፈልጋል።

ቀዳዳዎችን ለመድፈን እስከ አዋጅ የሚደርሱ ጉዳዩችም ከግምት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ይህን ማድረግ ከተቻለ በሀገራችን ውስጥ እዚህም ሆነ እዚህ በየጊዜው ብቅ ጥልም እያሉ የሚከሰቱ ጊዜያዊ ግጭቶችን ማስወገድ የሚቻል ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው የሚታዩ ጊዜያዊ ግጭቶች እየተከሰቱ መሆናቸውን ማንም የሚክደው እውነታ አይደለም። የቅርቡን በምሳሌነት ብናነሳ እንኳን ወንድማማች በሆኑትና በዘመናት የጋራ እሴቶች በተጋመዱት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ህይወት ያጠፋ፣ ንብረት ያወደመና ዜጎችን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ እንዲፈናቀሉ ያደረገ ግጭት ተከስቷል።

ግጭቱ በሁለቱ ክልሎች ጠያቂነት ፌዴራል መንግስት ጣልቃ በመግባቱ ሳቢያ ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ በእጅጉ ሊቀንስ ቢችልም፤ አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመቆሙን መንግስት በቅርቡ መግለፁ ይታወቃል። ምንም እንኳን ግጭቱ ለዘመናት አብረው የኖሩ፣ ተጋብተው የተዋለዱና የጋራ የሰላምና የመቻቻል እሴቶች ያሏቸው የሁለቱ ክልል ህዝቦች ፍላጎት እንዳልሆነ ቢታወቅም፤ አሁንም ግን ህገ ወጦች ከሁለቱም በኩል ሁከትን የመቀስቀስ አዝማሚያ እየሳዩ መሆኑም ተገልጿል።

ይህም በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ መንገድ የሚጓዘውን የሁለቱንም ህዝቦች ሰላማዊ ፍላጎትን የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ፤ እንደ ሀገር በማይረባው ጉዳይ በግጭት እየታመስን ሀገራዊ ራዕያችንን እንዳናሳካ አሜኬላ እሾህ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። እናም ሁለቱ ክልሎችና ማዕከላዊ መንግስት የችግሩን ፈጣሪዎችና ተዋንያን ወደ ህግ ፊት እንዲቀርቡ እያደረጉት ያለው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁንም ቢሆን ሰላምን የሚያጠናክሩ አጀንዳዎችንና መድረኮችን በመዘርጋት ክልሎቹን ወደ ነበሩበት ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ ይገባል።
ርግጥ ማንም ህሊና ያለው ሰው ግጭትን ሊናፍቅ አይችልም። በየትኛውም ቦታ የሚከሰቱ ችግሮች ባይከሰቱ እሰየው ነበር። ሆኖም ከተከሰቱ በኋላ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። አንድ ግጭት ተከስቶ ሲያበቃ ወደ አልተከሰተበት ኑባሬ መመለስ አይቻልም። ዋናው ነገር ቀደም ሲል እንዳልኩት ግጭቱ ሰዎችን ሳይጎዳ በፍጥነት መከላከልና ከግጭቱ በመማር ዳግም እንዳይከሰት እልባት መስጠቱ ላይ ነው።

በተለይ ግጭት የአንድ ወቅት ክስተት እንደመሆኑ መጠን፤ ስሜት ውስጥ ተገብቶ ማራገብ አይገባም። የእገሌ ብሔር ከዚህ ድንበር ማለፍ የለበትም በማለትም ጉዳዩን ማጎን አስፈላጊ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ዘመን አክትሞለታል። ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን በገዛ ሀገራቸው ‘ወደ ነጮች ሰፈር ድርሽ እንዳትሉ’ ተብለው እጅግ በከፋ የዘር መድልኦ ውስጥ ገብተው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተገፈው እንደነበር ይታወቃል። ግና ጥቁር ደቡብ አፍሪካያኑ ነፃነታቸውን እንደተጎናፀፉ የበቀል ርምጃን አልወሰዱም። በቀል ጠቃሚ ስላለሆነ ብሔራዊ እርቅን ነው በቅድሚያ የተከተሉት።
ታዲያ ይህ እውነታ የሚያስተምረን ነገር የበቀል ስሜት ለበቃዩም ሆነ ለተበቃዩ አላስፈላጊ እንደሆነ ነው። ብቀላ ተጨማሪ ደም መፋሰስን ከመፍጠር ውጭ ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም። በበቀል የሚገኝ ትርፍ የለም—ይበልጥ መቃቃርን ከመፍጠር በስተቀር። እናም በግጭት ውስጥ ያለ የትኛውም ወገን ከብቀላ አዕምሮ ነፃ መሆን ይኖርበታል።

የብቀላ መንገድ እሾሃማ ነው። አንዱ የሌላኛውን ህይወት ያጠፋል፣ ንብረቱን ያወድማል፣…ወዘተርፈ። ሌላኛውም የተፈፀመበትን ለመመለስ ሲል ተመሳሳይ ጥፋት ይፈፅማል። በዚህ መንገድ ውስጥ የሚመላለሱ ሁለት ወገኖች እርስ በርሳቸው ከመተላለቅ ውጭ የሚያገኙት ጥቅም የለም። እናም የብቀላን እሾሃማ መንገድ በሰላም የቄጤማ ጎዳና መቀየር ይገባል። አንዱ ሌላውን እየተበቀለ ራሱን ተጠቃሚ ሊያደርግ ሀገሩንም ሊያለማ አይችልም።
ቂም በቀል እንደ እኛ ያለና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካል- ኢኮኖሚ ማህበረሰብን ለመገንት በህገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ውስጥ ቦታ የለውም። ምክንያቱም ተግባሩ እንኳንስ በፖለቲካና በኢኮኖሚ የተሳሰረ አንድ የጋራ ማህበረሰብ ሊፈር ቀርቶ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ሊያሰናክል ስለሚችል ነው። እናም በቀልን ከማሰብ ይልቅ ግጭቶች ዳግም እንዳይቀሰቀሱ በሰላም አጀንዳዎች ላይ አጠናክሮ መስራት፣ ከተፈጠሩም በኋላ ዳግም እንዳይከሰቱ የሚያስችልን ትምህርት ወስዶ ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት በመፍትሔው ላይ ማተኮር ይገባል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy