Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህግና ስርዓትን የማስከበሩ ስራ ይበልጥ ይጠናከር!

0 302

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህግና ስርዓትን የማስከበሩ ስራ ይበልጥ ይጠናከር!

ዳዊት ምትኩ

በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታትና በሁለቱ ህዝቦች መካከል መቀራረብን ለመፍጠርና ብሎም ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ አቅጣጫ ሰጥተው ነበር። አቅጣጫው አሁን ያለበትን ደረጃ ሰሞኑን በኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኃላፊ ሚኒስትሩ በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ላይ በተከሰተው ግጭት ላይ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር እየዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሆኖም በሁለቱ ክልሎች በተመሳሳይ ደረጃ እየተሰራ አንዳልሆነ መገምገሙንም አስታውቀዋል።

የፌደራል እና አርብቶ አደር ልማት ጎዳዮች ሚኒስቴር ጨምሮ ዘጠኝ የፌደራል መስሪያ ቤቶች የተካተቱበት ግብረ ሃይል በምከትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነት በክልሎቹ የተሰራውን የፀጥታና ህግን የማስከበር ስራ ገምግሟል።

በግምገማው መድረክ በአሁኑ ጊዜ ችግሩ መቶ በመቶ ቆሟል በሚል መደምደም ባይቻልም በምስራቁ አካባቢ የተሻለ የሰላም ሁኔታ መኖሩን የፌዴራል ፖሊስ ሪፖርት መጠቆሙ ተመልክቷል። ሆኖም ግን ባለፈው ሳምንት በቦረና ሞያሌ፣ በጉጂ እንዲሁም በባሌ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች በአዲስ መልክ ግጭት እንደነበረ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል። በግጭቱም ከሁለቱም ክልሎች ከ20 በላይ ዜጎች ህይወት ማለፉ ተመልክቷል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ አካላት ለዜጎች ህይወት ጥበቃ እንዲያደርጉና በዚህ ተግባር የሚሳተፉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ግብረ ሃይሉ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ተፈናቃይ ዜጎች በአፋጣኝ ከመጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው እየተሰራ መሆኑን ግምገማው ያሳያል። የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ላይም ግብረ ሃይሉ ትኩረት ሰጥቶ መገምገሙንና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ ክፍተቶች መስተዋላቸውም ተገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአወዳይ አካባቢ በተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የክልሉ የፀጥታ አካላት እስካሁን 54 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውለዋል። በኦሮሚያ ክልል የፌደራል ፖሊስ ገጭቱ በተከሰተበት አካባቢ በመንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የተጠርጣሪዎች ቁጥር 44 መሆኑም ተወስቷል።

በአንፃሩ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የፌደራል ፖሊስ በራሱ ክትትል ባገኘው መረጃ እስካሁን 38 ተጠርጣሪዎችን መለየቱንና ከእነዚህም ውስጥ 29 ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ወጥቶ እስካሁን 5 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ምንም እንኳን ከዶክተር ነገሪ መግለጫ በመነሳት ህግንና ስርዓትን በማስከበር ረገድ ክፍተት ቢኖርም፤ እስካሁን የተሰሩት ስራዎች ግን አበረታች መሆናቸውን ለመረዳት አይከብድም። ሆኖም አሁንም ቢሆን ህግና ስርዓትን አጠናክሮ ማስከበር ይገባል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ ይሆንበታል።

አገራችን የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ስሆነ ነው።

ከሁሉም በላይ ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህግ የበላይነትን በሚገባ የሚያስከብር ነው። የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠበት ጥፋት ልክ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ይህ አሰራር በማንኛውም ዜጋ ወይም አካል ላይ ገቢራዊ የሚሆን ነው።  

ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል። ህግና ስርዓት ባልተተገበረበት ሁኔታ ዜጎች በሰላም ስራቸውን አያከናውኑም። ይህም የአገራችን እድገት የሚጎይት ነው። ስለሆነም ሁሉም ህግንና ስርዓትን በማስከበር የድርሻውን ተግባር መወጣት አለበት። ህግና ስርዓትን ይበልጥ አጠናክሮ የማስከበር ስራ የሁሉም ዜጋ ድርሻ መሆኑም ሊታወቅ ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy