Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለፌዴራል ስርዓቱ ትሩፋቶች መበልጸግና ለተሻለች ኢትዮጵያ ትግሌን አጠናክራለሁ—ህወሓት

0 674

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌደራል ስርዓቱን ቱሩፋቶች በማበልጸግ ለተሻለች ኢትዮጵያ የጀመረውን ትግል ከእህትና አጋር ድርጅቶች ጋር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ / ህወሓት/ አስታወቀ።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በ35 ቀናት የጥልቅ ግምገማው ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ድርጅቱ በትጥቅ ትግልና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አኩሪ ተጋድሎ ቢፈጽምም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለያዩ ችግሮች እየገጠሙት ነው።

ከፍተኛ አመራሩ እየተዳከመ ተልእኮውን ለመወጣት የሚያስችል ቁመናው በየጊዜው እየተሸረሸረ፣ ህዝባዊነቱ እየቀነሰና በትናንሽ ድሎች የሚረካ ሆኖ መገኘቱን መግለጫው አመልክቷል።

በነዚህ ምክንያቶችም አመራሩ የመፍትሄው አካል ከመሆን ይልቅ የችግር ምንጭ መሆን የጀመረበት ሁኔታ በስፋት መታየቱን ገልጿል።

በተለይም ስትራቴጂካዊ አመራሩ ለህዝብ ያለው ወገንተኛነት የተሸረሸረ፣ ከአገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደተገልጋይ እየቆጠረ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ እንቅስቃሴዎች ከመጠመድ ይልቅ በተደማሪ ለውጦች የሚረካ እየሆነ መምጣቱን መግለጫው አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በተዛባ ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነና ራሱን ወደ ጥገኛ ገዢ መደብ የመሸጋገር አዝማሚያ እየተጠናወተው እንደነበርም መግለጫው ጠቁሟል።

በእህትና አጋር ድርጅቶች መካከል የነበረው በመርህና በትግል የተመሠረተ የአመለካከትና የተግባር አንድነት በየጊዜው አየተሸረሸረ እንደመጣና በጋራ አላማ ዙሪያ በአንድ ልብና መንፈስ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በንትርክና ጥርጣሬ መተያየት ያጠላበት እንዲሆን በማድረግ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ እንደነበረውም አስታውሷል፡፡

በድርጅቱ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር የድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴ በአጠቃላይ ተጠያቂ ቢሆንም የችግሩ የከፋ መገለጫ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እንደ ግለሰብና እንደ አካል እንደነበር አመልክቷል፡፡

በመሆኑም የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ከገባበት አዙሪት ለመውጣት ያለው ብቸኛ አማራጭ በድርጅቱ በቆየው ሳይንሳዊ የትግል ባህልና ታሪክ መሠረት በቁጭት ተነሳስቶ ጥልቀት ያለው የአመራር ግምገማ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ያጋጠሙትን ፈተናዎች መርምሮ በማያዳግም ሁኔታ ወደ ትክክለኛ መስመሩና ህዝባዊ ወገንተኛነቱ ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ራሱን መፈተሹንም ገልጿል።

ህወሓት ፈተናዎች ባጋጠሙት ቁጥር ከህዝብና አባላቱ ጋር በመሆን ችግሩን እየፈታ በርካታ አስርት ዓመታት መዝለቁን ያመለከተው መግለጫው አሁንም ህዝባዊ አመኔታውን አስጠብቆ የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy