Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ልብ ያለው ልብ ይበል!

0 324

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ልብ ያለው ልብ ይበል!

ኢብሳ ነመራ

ግርግር ለሌባ ይመቻል። ሰላምንና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ልክ ሌብነት ስፍራ ያጣል። የሌቦች ዋነኛ መደበቂያ ጫካ ሳይሆን የህግ የበላይነት ያልተረጋገጠበት፣ ሰላም የሌለው ማህበረሰብና የፖለቲካ ሥርአት ነው ነው። እናም ሌቦች ለመኖር ሁሌም ረብሻና ግርግር ይሻሉ። ዓለም ላይ በእርስ በርስ ግጭት ሁከትና ግርግር የነገሰባቸው ሃገራት ዋነኞቹ የህገወጥ ተግባራት ማዕከሎችና መተላለፊያዎች ናቸው። አፍጋኒስታን የአደንዛዠ ዕጽ ንግድ ማዕከል ሆና ነበር፤ አሁንም ከዚህ አልጸዳችም። ሊቢያ አውሮፓን ያጨናነቀውና በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ሃብት የሚገላበጥበት የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ማዕከልና መተላላፊያ ነች። ታዲያ በእነዚህ ጸያፍ ህገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማረተው የደለቡ ባለጸጎች በአካባቢዎቹ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አይፈልጉም። ሰላምና የህግ የበላይነት ህገወጥ ተግባራቸውን ስለሚያከሽፈው።

በሃገራችን ኢትዮጵያም በህገወጥ መንገድ መከበር የተለመደ ነው። በኮንትሮባንድ ንግድ፣ በህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር፣ በመሬት ወረራና ቅብብሎሽ ብዙዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢሊየነሮች ለመሆን በቅተዋል። እነዚህ በህገወጥ ተግባር በድንገት ቢጠሯቸው የማይሰሙ ዲታ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች በሃገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አይፈልጉም። ሁሌም ስጋት፣ ሁሌም በተለመደው የህግ ማስከበር ስርአት በቁጥጥር ስር ሊውል የማይችል ሁከት እንዲኖር የፈልጋሉ። በተለመደው ህግን የማስከበር ሥርአት ሊጠበቅ ያልቻለ አካባቢ ለህገወጥ ንግድና ዘረፋ አመቺ ነውና።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኦሮሚያ ውስጥ የምንመለከተው ሁከትና ግርግር ምንጭ ይህ የሌቦች የህግ የበላይነትን የመቅጨትና ሁከትን የማንገስ ሴራ ውጤት ነው። ኦሮሚያ ሰፊ ክልል ነው። ክልሉ የሃገሪቱ ዋነኛ ምርቶች በተለይ በአነስተኛ መጠን ትልቅ ጥቅም የሚገኝበት ቡናና ወርቅ የመሳሰሉ ምርቶች ዋነኛ መገኛና መዘዋወሪያ ነው። የሃገሪቱ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ/ፊንፊኔም በዚሁ ክልል ማዕከላዊ አካባቢ ስለምትገኝ በተለይ ወደአዲስ አበባና ወደማዕከላዊው የሃገሪቱ አካባቢ የሚገባው የኮንትሮባንድ ሸቀጥ በኦሮሚያ ውስጥ ነው የሚዘዋወረው። አዲስ አበባ/ፊንፊኔ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች መሬቶች ምናልባትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድ የሚባለውን ዋጋ የሚያወጡ ናቸው። የሃገሪቱ የንግድና የፖለቲካ ማዕከል ከሆነችው አዲስ አበባ ተነስቶ በህገወጥ መንገድ ከሃገር የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ የኦሮሚያን ክልለ ያቋርጣል።

በእነዚህ ለማሳያነት የጠቀስኳቸውና ሌሎችም በቢሊየን ብር የሚለካ ሃብት በህገወጥ መንገድ ሊንቀሳቀስባት የምትችለው ኦሮሚያ ሌቦችንና ኪራይ ሰብሳቢ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ምራቅ የምታስውጥ ክልል ነች። ታዲያ ኦሮሚያ ሌቦችና ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲበለጽጉባት የህግ የበላይነት አልቦ መሆን ይኖርባታል። ዙሪያዋ በሁከት የሚታመስ፣ በተለመደው ህግን የማስከበር ሥርአት ልትጠበቅ የማትችል፤ ከተቻለም ሁሌም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምትተዳደር መሆን ይኖርባታል። ኦሮሚያ ይህ ሲሆን ለሌቦችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ሲሳይ ትሆናለች። ለወጣቶቿ ደግሞ የስራ አጥነት፣ የድህነት፣ የተስፋ መቁረጥና የሞት አውድማ ትሆናለች።

ኦሮሚያ ባለፉት ዓመታት የዘራፊዎች መፈንጫ ሆና መቆየቷ ይታወቃል። በአዲስ አበባ ዙሪያና በሌሎች ትላልቅ የሃገሪቱ ከተሞች አቅራቢያ የተቸበቸበውን መሬት ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። በርካታ የኦሮሞ አርሶ አደሮች በካሬ ሜትር 2 ብር ከ50 ሳንቲም ካሳ ተብዬ ክፍያ የኑሯቸው መሰረት የሆነውን መሬታቸን አሳልፈው እንዲሰጡ ተገደው አሁን በከተሞች ውስጥ ከነልጆቻቸው የበይ ተመልካች ሆነው ይገኛሉ። ራሳቸው ያስተዳድሩኛል ብለው የወከሏቸው ወገኖቻቸው ከቀማኛ ደላሎችና ጥገኛ ባለሃብቶች ጋር ተመሳጥረው ነው መሬታቸውን በጠራራ ጸሃይ የዘረፏቸው። እጅግ ለም በሆኑና ለአዲስ አበባ እንዲሁም ለሌሎች የሃገሪቱ ክልሎች ዋና ከተሞች፣ ለወደብ ቅርብና አመቺ በሆኑ አካባቢዎች በኢንቨስትመንት ሥም በመቶ ሄክታር የሚለኩ ቦታዎች በወራሪዎች ተይዞ ታጥሮ የተቀመጠበት ሁኔታ አለ።

እነዚህ በኢነቨስትመንት ሥም ተገቢ ባለሆነ ዋጋ፣ ከመሬቱ ላይ ለተነሳው አርሶ አደር ከአንድ ዓመት የዕለት ጉርስ በማያልፍ የካሳ ክፍያ የተወሰዱ መሬቶች ለኢንቨስትመንትም አልዋሉም። አርሶ አደሩ መሬቱን ኢንዳያጣ ያደረጉት ኢንቨስትመንቶች ተከናውነው አርሶ አደሩና ቤተሰቦቹ ከስራ እድልና ሌሎች የኢንቨስትመንት ትሩፋቶች ተጠቃሚ መሆን  አልቻለም። በአብዛኛው መሬቶቹ ታጥረው የተቀመጡበት ሁኔታ ይታያል። አንዳንዶቹ ከአርሶ አረደሩ ባነሰ የምርታማነት ደረጃ በበሬ እየታረሱ ጥቅም ላይ የሚውሉበት ሁኔታ አለ። አርሶ አደሩ ግን ከበቶቹን እንኳን በዚህ መሬት ላይ ማሰማራት እይችልም።

ከአርሶ አደሩ በተወሰደ መሬት ላይ የሚከናወኑ የኮንስትራክሽን ማዕድናት የማውጣት ሥራዎች እሴት ጨማሪ ያልሆኑ ናቸው። በተፈጥሮ ያለውን አሸዋ፣ ጠጠርና ኖራ እየዛቁ ከመቸብቸብ ያለፈ በምርቶቹ ላይ ምንም እሴት አይጨመርባቸውም። ይህ በአርሶ አደሩ ሊከናወን የሚችል ከፍተኛ ካፒታል የማይጠይቅ ስራ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ እሴት የማይጨምሩ የኮንስትራክሽን ማዕድን የማውጣት ስራዎች፣ ከመሬቱ ላይ ያለበቂ ካሳ ለተፈናቀሉት የአርሶ አደሩ ልጆች የስራ እድል አልፈጠሩም። አርሶ አደሩ መሬቱን አጥቶ የበይ ተመልካች ከመሆን ባሻገር በቁፋሮው የሚቦነው አቧራ ኑሮውን አመቺ እንዳይሆን አድርጎበታል።

ይህ ሁኔታ የኦሮሞሚያን ወጣቶች አስቆጥቷል። በድንገት ገንፍለው ለተቃውሞ አደባባይ አስወጥተዋቸዋል። ይህ የአደባባይ ተቃውሞ ተገቢ ምክንያት ቢኖረውም ህገመንግስታዊ ሥርአቱን ማፍረስ በሚፈልጉ በውጭ ሃገራት ባደፈጡ ለኦሮሞም ሆነ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ደንታ የሌላቸው ጽንፈኛ ፖለቲከኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ተጠልፎ ወጣቱን ለአላስፈላጊ መስዋዕትነት መዳረጉ ግን ሁሌም በሃዘን የሚታወስ ነው።

የወጣቶቹ ተቃውሞ ተገቢ መሆኑን የተረዳው የክልሉ መንግስትና ገዢ ፓርቲ ኦህዴድ እነዚህን ከላይ የተገለጹ ችግሮችና መዘዛቸውን፣ እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነት ሌላኛው ገጽታ የሆኑትን የመልካም አስተዳደር እጦትና የፍትህ መጓደል ለማቃለል ለህዝብ ቃል ገብተው መንቀሳቀስ ጀምረዋል፤ ከ2009 ዓ/ም መግቢያ አንስቶ። ከዚህ ጊዜ በኋላ የክልሉ መንግስት ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያስገኙ በረካታ እርምጃወችን ወስዷል። ለወደፊትም እንደሚወስድ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል።

በህገወጥ መነገድ በወረራ የተያዙ መሬቶችን እንዲሁም በኢንቨስትመንት ሥም ተወስደው ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን ነጥቆ ለስራ አጥ ወጣቶችና ለአርሶ አደሩ መልሷል። የከተማ ቦታዎቹን ወደመሬት ባንክ መልሷል። በአርሶ አደሩ መሬት ላይ አፈር እየዛቁ ምንም እሴት ሳይጨምሩ የበለጸጉ ኢንቨስተር ተብዬዎችን ቦታ ነጥቆ ሥራ አጥ የአርሶ አደሩ ልጆች እንዲሰሩበት አድርጓል። በመሬት ወረራ ላይ የተሰማሩ በየደረጃው የነበሩ የክልሉ መንግስት የስራ ሃላፊዎች ላይ አስተዳደራዊና የህግ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል። ተጀምረው ያለአግባብ የተጓተቱና የተቋረጡ የማህበራዊ ልማት ተቋማትና የመሰረተ ልማት ግንባታቸው እንዲፋጠኑና ግንባታቸው እንዲቀጥል የማደረግ እርምጃ ተወስዷል። የክለሉ የህዝብ ሚዲያዎች የህዝብን ብሶት አንድም ሳይሸሽጉ ለሌሎች የሃገሪቱ ሚዲያዎችም አርአያ መሆን በሚያስችላቸው ደረጃ ይፋ ማወጣት ጀምረዋል። አሁንም ይህን እያደረጉ ይገኛሉ። የOromiya Broadcasting Network (OBN) ቴሌቪዥንና ሬድዮ የየእለቱን ስርጭት መመልከት ለዚህ አስረጂ ነው።

እነዚህ ሁኔታዎች በህዝቡና በክልሉ መንግስት መሃከል ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መተማመንና መግባባት መፍጠር አስችለዋል። መግባባትና መተማመኑ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም ጥሩ መደላድል መሆን ጀምሯል። ሰላም ካለ የህግ የበላይነት ይኖራል። የህግ የበላይነት ካለ ህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የልማት ስራዎችን ማከናወንና የህዝቡን ኑሮ ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋጋር ይቻላል። ይህ ሁኔታ በተቃራኒው የክልሉን ሃብት ለመዝረፍና ክልሉን የህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ መሽሎክሎኪያ በማደረግ እንደከዚህ ቀደሙ ለመክበር  ላሰፈሰፉና በዚህ መንገድ ሃብት ላጋባሱ ሌቦችና ኪራይ ሰብሳቢዎች አልተመቸም። ካሁን በኋላ ሊያገኙ ያሰቡትን የሚያሳጣ ብቻ ሳይሆን እስካሁን የዘረፉትንም መትፋታቸው እንደማይቀር አመላክቷቸዋል።

ሌቦቹ ይህን ሁኔታ በቀላሉ መቀበል አልሆነላቸውም። አናም በተለያያ መንገድ ክልሉን የማተራመስ ርምጃ መወሰድ ጀምረዋል። ገሚሱ በድንበር ሰበብ የአካባቢውን ህዝብ ከለላ አድርገው በወሰዱት እርምጃ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ ሰዎቸ እንዲፈናቀሉና ንብረት እንዲወድም በማደረግ በተለመደው የህግ ማስከበር አሰራር መቆጣጣር የማይቻል ሁኔታን ለመፍጠር ሞክረዋል። የተቀሩት ደግሞ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ወጣቶችን በማደናገር አውዳሚ ሁከት እንዲቀጣጣል እያደረጉ ነው። ይህ ሁከት በመላው ኦሮሚያ እንዲስፋፋና በኦሮሚያ ህግ ማስከበር እንዳይቻል፣ በዚህም ከክልሉ መንግስት ቁጥጥር እንድትወጣ የማድረግ እቅድ ነው ያላቸው። መሳሪያቸው ደግሞ የዚህ ሁከት ዋነኛ ተጎጂ የሆኑ የዋህ የኦሮሞ ወጣቶች ናቸው።

እናም የኦሮሞ ወጣቶች ባንዲራና አርማ ውጭ ሃገር አሳትሞ ኮንትሮባንድ በሚዘዋወርበት መንገድ ወደሃገር ውስጥ አስገብቶ ለሁከት የሚያነሳሳችሁ ሁሉ ተቆርቋሪያችሁ አይምሰላችሁ። አሁን ክልሉ ባለበት ሁኔታ ለሁከት የሚያነሳሳችሁ፣ ክልላችሁን በማተራመስ የህግ የበላይነትን ሊያጠፋ የሚፈልግ ሌባ መሆኑን ተረዱ። ኦሮሚያ ከዳር እስከዳር ተተራምሳ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንድትወድቅና ለልማት አመቺ እንዳትሆን፣ የሌቦች መፈንጫ እንድትሆን የሚፈልግ ነው። ራሳችሁን በራሳችሁ እንዳትበሉ ልብ በሉ። ልብ ያለው ልብ ይበል!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy