Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መልካም ተሞክሮዎች ይጠናከሩ!

0 250

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መልካም ተሞክሮዎች ይጠናከሩ!

ዳዊት ምትኩ

በአማራና በኦሮሚያ ህዝቦች መካከል ሰሞኑን የተካሄደው ሕዝባዊ ኮንፍረንስን ተገቢና ትክክለኛ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ህዝቦችን የሚያቀራርቡ ኮንፈረንሶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ይገባል። የሁለቱ ክልሎች ኮንፈረንስ ችግሮች ሲከሰቱባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች ሁኔታውን ለመለወጥም አስፈላጊ ነው። በመሆኑም እንዲህ ዓይነት መልካም ተሞክሮ በሌሎች ክልሎችና ህዝቦች መካከልም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ይመስለኛል።

ይህን መሰሉ ህዝባዊ ኮንፈረንስ የህዝቦችን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ወሳኝ ነው። ህዝብ እንደ ህዝብ እንዲከበር፣ በያለበት ቦታ ሁሉ ሳይሸማቀቅ ለአገሩ የበኩሉን እንዲያበረክት ያስችላል።

በመሆኑም የአማራውና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል እንደ ተካሄደው ዓይነት ህዝባዊ ኮንፈረንስ በየክልሎቹ ቢካሄድ አንደኛው ለሌላኛው ያለውን ቀና አመለካከት ለማጎልበትና የትውውቅ መድረክ ለመፍጠር እገዛው በቀላል የሚታይ አይደለም።

እንዲህ ዓይነቶቸቹ ኮንፈረንሶች ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ ሃይሎችን ህልም የሚያመክን ጭምር ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ኮንፈረንሶች ተቀጣጥለው ሲካሄዱ አንድነት ይጠብቅና የህዝቦች የጋራ መግባባት ለአገራዊ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። የግጭት መንገዶችን ያስወግዳል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ግጭት በር የሚከፍት አይደለም። ሥርዓቱ ለሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮች እንደ መፍትሔ የሚሰጥ ነው። በተለይም በአጎራባች ክልሎች ውስጥ ሰነከባለሉ በመጡ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችና በግጦሽ ሳቢያ የሚፈጠቱ ችግሮችን በህገ መንግስቱ አግባብ መፍታት ይገባል።

እርግጥ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ አይችልም። ሆኖም እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በሥልጣኔ በበለፀጉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ አይቀርም። ነባራዊ ክስተት ነው። ለነገሩ የሰው ልጅ ሰው ከራሱ፣ በአቅራቢያው ካለው ማህበረሰብና ከተፈጥሮ ጋር መጋጨቱም አይቀሬ ነው።

ይህ በየትኛውም ዓለም ሊኖር የሚችል ግጭት ደግሞ በህግና በስርዓት መመራት ይኖርበታል። በተለይም ዜጎች በሙሉ ፈቃዳቸው ዕውን ባደረጓቸው መሰረታዊ የህገ መንገስት ድንጋጌዎች መፈታት ይኖርባቸዋል።  

እርግጥ ለአብዛኛዎቹ ግጭቶች መነሻ ምክንያት በዓለማችን ላይ ያለው የተፈጥሮ ሀብት እጥረት ነው። ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየች አይደለችም— እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሀብት እጥረት አለባት። እናም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ ነው። ዋናው ነገር የተከሰተውን ግጭት በችግርነት መዝግቦ መፍትሔውን ከህገ መንግስት መሻት ተገቢ ነው።

እርግጥ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ህብረ ብሔራዊ ሆኖ መዋቀሩ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የተመቸ ከመሆኑም በላይ፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ማንነቶችንና የጋራ እሴቶችን እያጎለበቱ መምጣታቸውን ያሳያል፡፡

አዲሱ ሥርዓት ከተመሠረተ ወዲህ በተወሰኑ አካባቢዎች በጎሣዎች መካከልና በአንዳንድ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ግጭቶች ፌዴራል አወቃቀሩ የፈጠራቸው አይደሉም፤ ሊሆኑም አይችሉም፡፡

አንዳንዶቹ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ የጎሣ ግጭቶች ናቸው፤ የተወሰኑት ደግሞ ከልምድ ጉድለት፣ ከመልካም አስተዳደር እጦትና ይህንን ተንተርሰው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ጥቂት ግለሰቦች የሚያባብሷቸው ወይም የሚቀሰቅሷቸው ግጭቶች እንደነበሩ እሙን ነው፡፡

እነዚህ ግጭቶች በሂደት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ ፌዴራል ሥርዓቱ ከተመሠረተ ጀምሮ ለተከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ መንስኤዎች ካለፉት ሥርዓቶች የተወረሱ ችግሮች ነበሩ፡፡

ዛሬ በመላ አገሪቱ የተረጋገጠው ሠላም የተረጋጋ ማኅበረሰብ እንዲኖር በማስቻሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት መላ አቅማቸውን አቀናጅተው በድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ መዝመታቸው የሥርዓቱ ስኬቶች አንዱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙ መብቶች ስለተመለሱላቸው ሀገራቸውን ለመለወጥ እንደ አንድ ማኅበረሰብ በልማት አጀንዳዎች ላይ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ህገ መንግስቱ የሰላም ዋስትና መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡  

እርግጥ እዚህ ሀገር ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት ሀገራችን የምትከተለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል።

የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሃብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የተገነባ አይደለም። በሂደቱ ውስጥ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። እናም በሂደቱ ውስጥ ጥቃቅን ስንክሳሮች ሊያጋጥሙት ይችላል። ዋናው ነገር እነዚህ ጊዜያዊ ችግሮች ህገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ በብቃት እየተፈቱ የመሄዳቸው ጉዳይ ነው።

ከዚህ አኳያ በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ 23 ዓመታትን ተሻግሯል።

በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ችሏል።

ላለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታት የተጎናፀፍናቸው ድሎች በርካታ ናቸው። የሀገራችን ህዝቦች አንደኛው የሌላኛውን መብት የማክበርና የመቻቻል ተግባሮች ተጠቃሽ ናቸው። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተጎናፀፉት ህገ መንግስታዊ መብት ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን ማሳለጥ ችለዋል።  

ያም ሆኖ ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም— ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ። ኮንፍረንሶችን በተከታታይ ማካሄድ የአስተሳሰብ ለውጥን ለማጎልበት ወሳኝ ነው።

እናም ኮንፈረንሶች በሀቦች መካከል እንዲኖር የሚፈለገውን ጠንካራ አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር በመሆኑ ሊቀጥሉ ይገባል። የኦሮሚያና የአማራ ክልል ህዝባዊ ኮንፈረንሶች ዓይነት የህዝብ ትስስር የሚፈጥሩ መድረኮች በየጊዜው መበራከት ይኖርባቸዋል። መልካም ተሞክሮዎች ይጠናከሩ!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy