Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማኅበራትን ማጠናከር መፍትሄ ነው

0 321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማኅበራትን ማጠናከር መፍትሄ ነው

አባ መላኩ

በቅርቡ ከዶላር አኳያ የብር የምንዛሬ ተመን በመስተካከሉ ሳቢያ በንግዱ ዘርፍ አንዳንድ ህገወጥ  አካሄዶችን እየተመለከትን ነው። አንዳንድ ነጋዴዎች ጽንፍ በወጣ የራስ ወዳድነት ስሜት፤ ሰርቶ ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አጭበርብሮና ነጥቆ  ሃብት ለመሰብሰብ የሚያደርጉትን መሯሯጥ  የሚመስሉ አካሄዶችን  በመመልከት ላይ ነን። ለአብነት  በቂ ክምችት እያለ  በሸቀጦች ላይ እጥረት ለመፍጠር ታስቦና ታቅዶ ሸቀጦችን  የመደበቅ  እንዲሁም የብር ተመን ዋጋ ከዶላር አንጻር 15 በመቶ ብቻ ቀንሶ ሳለ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ እስከ 50 በመቶና ከዚያም በላይ  ዋጋ የመጨመር ሁኔታዎች  ታይተዋል።  

በተመሳሳይ  አንዳንድ  ሸማቾችም ህገወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እየተመለከቱ መብታቸውን ለማስጠበቅ  ወደ ህግ ከመሄድ ይልቅ  በግዴለሽነት የተጠየቁትን  ሲከፍሉ ይስተዋላሉ። ይህ አይነት አካሄድ ለነገ የሚጠቅም አይደለም። የህግ የበላይነትን የሚረጋገጠው በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን በእኛ በዜጎች  ጠንካራ ተሰትፎ በመሆኑ ሁሉን ነገር ወደ መንግስት መግፋት የለብንም።  እንዲህ ያሉ  ህገወጥ ድርጊቶች የሚፈጸሙት  በድብቅ  በመሆኑ  መንግስት እንደነዚህ ያሉ ድርጊቶችን  ለማስተካከል  ብቻውን የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ውጤታማ አይሆንም። በመሆኑም መብታችንን የመጠየቅ፣  ህገወጦችንም ወደ ህግ እንዲቀርቡ  የማድረግ ስራ የሁላችንም ሃላፊነት  ሊሆን ይገባል። የዛሬው አነሳሴ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ባለመሆኑ  እዚህ ላይ ላቁመውና  የዛሬ ርዕሰ ጉዳዬ  ወደሆነው የህብረት ስራ ማህበራት አንዳንድ ጉዳዮችን ላንሳ።  

የሸማቹንና የአምራቹን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እንዲሁም የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት በማዘመን ረገድ የሕብረት ሥራ ማህበራት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አላቸው። በየሰፈሮቻችን የሚገኙ የሸማቾች ማህበራት እንኳን ዋጋ በማረጋጋት ረገድ ያላቸው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለአብነት አሁን ላይ አንድ ኪሎ ስጋ በአማከኝ  በመደበኛ  ገበያ ከሁለት መቶ ሃምሳ ብር በላይ ሲሸጥ ከሸማቾች ግን ከመቶ እስከ መቶ ሃያ ብር በመሸጥ ላይ ነው። ይህ የሚያሳየው  የአገራችን የንግድ ስርዓት የትርፍ  ወሰን  እንደሌለው  ነው። ነጻ የገበያ ስርዓት ማለት እንዲህ ከሆነ እጅግ ከባድ  ነገር ይመስለኛል።  በአገራችን የንግድ ስርዓት ውስጥ  ውድድሩ ደካማ መሆኑና ሸማቹም የተደራጀ ባለመሆኑ  ገበያው እንደተፈለገ  የሚዘወር ሆኗል።  መንግስት ሸማቾች እንዲደራጁና ማህበራት እንዲጠናከሩ  የሚያደርገው  ጥረት  መቀጠል  ይኖርበታል። የተጠናከሩ ማህበራት  ገበያን ለማረጋጋት የሚያበረክቱት አስትዋጽዖ ከፍተኛ ነው።

እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ   በአገራችን ከ79 ሺህ መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበራት በላይ የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚህ ማህበራት ደግሞ  373 ዩኒየኖችን የመሰረቱ ሲሆን፣ እነዚህ  ዩኒየኖች ደግሞ በጋራ በመሆን  አራት የሕብረት ሥራ ፌዴሬሽኖችን መስርተዋል። እነዚህ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ከ15 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ  አባላት  ያቀፉ ሲሆን፤ ከ17 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታልም አፍርተዋል። መንግስት ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖች እንዲጠናከሩ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።  ይሁንና ይህ ድጋፍና ክትትል አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ማህበራት እንደችግኝ ናቸው፤ ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የመንግስትን ድጋፍና ክትትል እጅጉን ይሻሉ።  

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የህብረት ስራ ማህበራት ቢጠናከሩ ተደራሽነታቸው ቢሰፋ የዋጋ ንረትን በመከላከልና  ገበያን በማረጋጋት  ለአገር  ዕድገት ወሳኝ  ድርሻ ማበርከት የሚችሉ ናቸው። የሕብረት ሥራ ማህበራት ሸማቹን ህብረተሰብ በዋጋ ማሻቀብ እንዳይጎዳ ከመከላከል ባሻገር ጥራትን በማስጠበቅ ጉርሻ አላቸው።  ምክንያቱም መንግስት ለማህበራት የተለያዩ ድጋፎችን ስለሚያደርግላቸው ምርቶቻቸው ከማንኛውም በዕድ ነገር ጋር እንዳይቀላቀሉና ጥራታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የቅርብ ክትትል ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ በሚያቀርቧቸው ማንኛውም ሸቀጦች ላይ ችግር ቢገኝ የተጠያቂነት አሰራር እንዲኖር  ተደርጓል። የህብረት ስራ ማህበራት በአምራቹና በሸማቹ መካከል ያሉ ህገወጥ ደላሎችን ስለሚያስወግዱ አምራቹና ሸማቹን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ናቸው። ይሁንና ይህ መልካም ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርባታል።

ማህበራት ገበያ እንዲረጋጋ ከማገዛቸው ባሻገር ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር  ላይ ናቸው። በርካታ ዜጎች  በተለያየ መስክ በመደራጀት የስራ እድል እየፈጠሩ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ያለው የስራ ባህል በመለወጥ ላይ ይገኛል። ከዚህ በፊት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚመረቁ ወጣቶች ተስፋ አድርጋው የሚጠብቁት የመንግስት መስሪያ ቤቶች መቀጠርን ነበር። አሁን ላይ ይህ አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም እጅጉን ቀንሷል። ወጣቶች በማህበራት በመሰባሰብ ስራ መፍጠር ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በተግባር አሳይተዋል። መንግስት ለማህበራት መፈጠርና መጎልበት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል ወጣቱ የስራ ፈጠራ ባህሉን ማጎልበት ይኖርበታል።        

በአገራችን የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በአይነት፣ ብዛትና ጥራት በማሳደግ ረገድ  የኅብረት ሥራ ማህበራት ወሳኝ ሚና አላቸው።  የወጪ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ የመንግስት ትኩረት በመሆኑ በወጪ ምርቶች ላይ የሚሰማሩ ማህበራት ከመንግስት ልዩ ድጋፍ እያደረገላቸው ነው። የአገራችን የወጪ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ጥራታቸው ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። ማህበራት የወጪ ምርቶች ብዛታቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ ጥራታቸውን ዓይነታቸውንም በማብዛት ረገድ የሚኖራቸው  ሚና በቀላሉ የሚታይ  ባለመሆኑ  መንግስት የጀመረውን ድጋፍ ሊያጎለብተው ይገባል።          

ማህበራት የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት የሚያስችሉ የወጪ ምርቶችን  ከማምረት ጎን ለጎን የገቢ ምርቶችን ሊተኩ የሚችሉ ምርቶችን አገር ውስጥ በማምረት ትልቅ ሚና አላቸው። ሁሉም የገቢ ምርቶቻችን የውጭ ምንዛሬ የሚፈልጉ ናቸው። በመሆኑም ጥራታቸው የተጠበቀና በተፈለገው መጠንና ጥራት የገቢ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶች በአገር ውስጥ ማምረት የሚቻል ከሆነ የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ይቻላል።  መንግስት በወጪ ምርቶች ላይ ለተሰማሩ  አካላት የሚያደርገውን ድጋፍ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ጥረት ለሚያደርጉ አካላት ድጋፍ ማድረግ መጀመሩ መልካም ነው። እንደህ ያሉ ድጋፎች  በመጠናከራቸው አሁን ላይ በርካታ አካላት የገቢ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ላይ ይገኛሉ።     

ከላይ ከተገለጹት ጥቅም ባሻገር የኅብረት ሥራ ማህበራት አገራዊ ቁጠባንም  ያሳድጋሉ። ቁጠባ ማንም ሰው ከሚያገኘው ላይ ቀንሶ የሚያስቀምጠው እንጂ ለመቆጠብ የግድ ከፍተኛ ገቢ ሊኖረንና  ሊተርፈን ያስፈልጋል የሚል እሳቤ መኖር የለበትም።  ቁጠባ የሚካሄደው  ፍላጎትን በመግታት ነው።  ቁጠባ  የዕድገት መሰረት ነው፤ ቁጠባን ባህል ካደረግን መለወጥ ጀመርን ማለት ነው። እንዳንዶች ከአነስተኛ ገቢያቸው ላይ መቆጠብ በመቻላቸው በአጭር ጊዜ መለወጥ ሲችሉ በተቃራኒው አንዳንዶች ደግሞ ከፍተኛ ገቢ ኖሯቸው እንኳን ቁጠባን ባህል ባለማድረጋቸው ለውጥ ወይም ዕድገት አይታይባቸውም።

ቁጠባ ከግለሰብ  ጠቀሜታው ባሻገር አገራዊው ፋይዳውም እጅግ ከፍተኛ ነው። ቁጠባን ባህል ማድረግ የውዴታ ግዴታ አድርገን ልንወስድ ይገባል። የህብረት ስራ ማህበራት ለቁጠባ እጅግ ምቹ ናቸው። የአገራችን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚያደረገው የመዋቅር ሽግግር  ቁጠባ ትልቅ ፋይዳ አለው። ምክንያቱም ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት  ካፒታል እጅግ ወሳኝ ነው። ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት  የሚያስፈልገው የካፒታል እርሾው ከአገር ውስጥ ቁጠባ  የሚገኝ  መሆን መቻል ይኖርበታል። ትናንሽ የግብርና ምርቶችን የሚያቀናብሩ ፋብሪካዎች ሊስፋፉ የሚችሉት በአገር ውስጥ ባለሃብት መሆኑ የአገር ውስጥ ቁጠባ  መጠናከር ይኖርበታል። የኅብረት ሥራ ማህበራት አገራዊ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግርን ለማረጋገጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በውጤታማ አመራር መታገዝ ይኖርባቸዋል።

ማህበራት ምርቶችንና አገልግሎቶችን  በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ስለሚያደርሱ ገበያን በከፍተኛ ሁኔታ ያረጋጋሉ፤ የውጪ ምርቶችን በጥራትና በብዛት  ለገበያ  በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት ይችላሉ።  በተመሳሳይ የኅብረት ሥራ ማህበራት  የገቢ ምርቶችን  በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ያስቀራሉ። በመሆኑም አገራችን ለጀመረችው ፈጣን ዕድገት የኅብረት ስራ ማህበራት መጠናከር ወሳኝ በመሆኑ መንግስት ድጋፉን ሊያጠናክር ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy