Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰከን ብለን ስኬቶችና ድክመቶችን…

0 384

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰከን ብለን ስኬቶችና ድክመቶችን…

አባ መላኩ

በኢትዮጵያ በርካታ ነገሮች በፈጣን የለውጥ ዑደት ውስጥ ናቸው። እነዚህን ፈጣን ለውጦች በመጣንበት ፍጥነት  ማስቀጠል እንዲሁም ለድክመቶች መፍትሄ መፈለግ ከቻልን  በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት አገራችን  ዝቅተኛውን የመካከለኛ አገራት ገቢ  ማለትም  የአንድ ሺህ ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ  ደረጃ መቀላቀል ትችላለች። ከሚሌኒየሙ ወዲህ ባሉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያ እጅግ ስኬታማ የሆነችባቸው ዓመታት ናቸው። ይህ ሲባል ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው፤ምንም ድክመት የለም ማለት ግን አይደለም። ችግሮች ቢኖሩም ስኬቶቻችን ግን የጎሉ እንደነበር  መካድ አይቻልም።

 

በመጀመሪያው  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገራችን  ተጨባጭ ስኬቶችን  ያስመዘገበችበት ወቅት ነበር። በመጀመሪያው ዕትዕ አገራችን ግዙፍ የሆኑ ባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መገንባት የተቻለበት እንዲሁም   በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር መንግስት በርካታ ስራዎችን ያከናወነበት ወቅት ነበር።  ለአብነት ግዙፍ የሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ (የአገር አቋራጭና ቀላል የከተማ ባቡር ሃዲድ ዝርጋታ)፣ ከነእጥረታቸውም ቢሆኑ  ዘጠኝ ግዙፍ የስኳርና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ እንዲሁም ሰፋፊ የአስፋልትና የገጠር መንገዶች ግንባታ፣ ግዙፍ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ማስፋፋያ ተጠቃሽ ናቸው።

 

ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ረገድም ባለፉት አስር ዓመታት በአገራችን ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል። በትምህርትና ጤና ዘርፍ መንግስት እያከናወናቸው የሚገኙት ተግባራት አንጸባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ ችለዋል። ከአንደኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ  በርካታ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።  የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን ከ95 በመቶ በላይ  የደረሰ ሲሆን  ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ህጻናት በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ  የሚያስችሉ ስራዎች  በመከናወን ላይ ናቸው። በአገራችን ከበርካታ የዓለማችን አገሮች የህዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ የሚልቅ ሆኖ እናገኘዋለን።

 

አሁን  ላይ የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ብቻ ከ45 በላይ የደረሰ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጥርም ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ደርሷል። ይህ የሚያሳየው አገራችን በጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ የተማረ የሰው ሃይል ሊኖራት እንደሚችልና ይህ ሃይል ደግሞ አገሪቱ የጀመረችውን  ፈጣን ልማት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሚሆን በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  በጤናው ረገድም ተጨባጭ ድሎች ተመዝግበዋል። መከላከልን መሰረት ያደረገው የአገራችን የጤና ፖሊሲ በገዳይነታቸው የሚታወቁ ተላላፊ በሽታዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። መንግስት በሰራው የማህበራዊ መገልገያዎች የማስፋፋት ተግባር  አገራችን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች አንዳንዶቹን ቀድማ በማሳካት እንደአብነት የምትጠቀስ ለመሆን በቅታለች።

 

መንግስት በዜጎች መካከል ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር መሰረተ ልማቶችንና መሃበራዊ መገልገያዎችን ከማስፋፋተ ባሻገር በከፍተኛ ድጎማ የጋራ የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት  በእጣ እያከፋፈለ ይገኛል። ይህም በሁሉም የአገራችን ትላልቅ  ከተሞች ተግባራዊ ተደርጓል።  በተለይ በመዲናችን  በርካታ የከተማ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያለቸው ነዋሪዎች  በዝቅተኛ  ክፍያ  የቋሚ ንብረት ባለቤት  ለመሆን በቅተዋል።  

 

በምግብ ሰብል ራስን በመቻል ረገድም  አገራችን ስኬታማ መሆን ችላለች። በድርቅና በስንዴ በዕርዳታ ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ ላይ በአገር ደረጃ የምግብ  ፍላጎቷን ማሳካት  ችላለች።  ይህ ስኬት በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ እንዲቻል በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መንግስት ግብ ጥሎ በመስራት ላይ ነው። በዕትዕ ሁለትምግብ ዋስትናን  በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ  መንግስት  ከሚያከናውናቸው ተግባራቶች መካከል የስራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ገቢ ማሳደግ  ተጠቃሽ  ተግባር ነው።

 

በአርሶና እርብቶ አደር አካባቢዎች የግብርና ምርትና ምርታማነትን  ለማሳደግ የሚያስችሉ  ስራዎች ለአብነት ምርጥ ዘር፣ ማዳባሪያና የተለያዩ መደሃኒቶች  አቅርቦት በመከናወን ላይ ናቸው። በዚህም ሳቢያ በዘንድሮው የመኸር ምርት በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ በዕቅድ ከተያዘው ከ345 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማሰባሰብ እንደሚቻል ቅድመ ትንበያዎች ያመላክታሉ። ሥር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን  አካባቢዎች በምግብ ሰብል ራሳቸውን እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎች ከማድረግ ባሻገር ሴፍትኔት ፕሮግራም ተቀርጾ በመተግበር ላይ ነው።

 

ባለፉት 15 ዓመታት በአገራችን በተተገበሩት የሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል። በዚህም ከ3 ሚሊዮን በላይ ቤተሰቦች አቅም በመገንባታቸው የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጣቸው ከፕሮግራሙ ተመርቀው እንዲወጡ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት 4ኛው ዙር የሴፍቲኔት ፕሮግራም እየተካሄደ ሲሆን ከስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በመሆን ላይ ናቸው።  ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረጉ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።  

 

በሁለተኛ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው ነገሮች መካከል  የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ  ማረጋገጥ እንዲሁም ድህነትን  መቀነስ ነው። ለዚህ ዕቅድ ስኬት ለወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል መፍጠር  ቁልፍ ሚና እንዳለው መንግስት በመረዳቱ በከተሞችና በገጠር ለሴቶችና ወጣቶች የተለያዩ የስራ ዕድል ስትራቴጂዎችን ቀርጾ  በመተግበር ላይ ነው። በከተሞች የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች መስፋፋት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕደል በመፈጠሩ  የነዋሪዎች ህይወት እጅጉን በመለወጥ ላይ ነው።

 

ለወጣቶች ስራ ፈጠራ የሚሆን  በፌደራል መንግስት  ብቻ ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር በመፍቀድ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው። ከዚህም ባሻገር ክልሎች እንደየአቅማቸው ገንዘብ በመመደብ እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎችን በማቅረብ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመሰራት ላይ ናቸው። ይህ ስኬታማ የሚሆነው የወጣቶች ጥረት ሲታከልበት በመሆኑ ወጣቱ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል።

 

የፌዴራል መንግስቱ በክልሎች መካከል ተመጣጣኝ ዕድገት ለማምጣት  እንዲሁም  ለዜጎችም የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ  የኢንዲስትሪና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ አካባቢዎች በማቋቋም ላይ ነው።  ወጣቶች በእነዚህ ፓርኮች በሚፈጠረው የስራ ዕድል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎች ከመመቻቸታቸውም ባሻገር በአውት ግሮወር መልክ ተደራጅተው ለኢንዱስትሪዎቹ  ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መጠነ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

 

ባሳለፍነው በጀት ዓመት ለገጠር ወጣቶች በግብርና ሴክተር በተለይ በመስኖ ልማት፣ በዶሮ ርባታ፣ በከብት ርባታና ድለባ፣ ፍየልና በግ ማሞከት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በተፋሰስ ልማት ስራዎች ባገገሙ አካባቢዎች በተካሄዱ ሁለገብ የልማት ስራዎች  ከ1.57 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ የገጠር ወጣቶች ስራ ዕድል  መፍጠር ተችሏል። ይህንን ስራ አጠናክሮ በመቀጠል በ2010 በጀት ዓመት በቋሚ ለ1,200,365 እንዲሁም በጊዜያዊ ደግሞ ለ599,390  በድምሩ ከ1.799 ሚሊዮን በላይ የገጠር ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።

 

የወጣቶች የስራ ፈጠራ ስትራቴጂ ስኬታማ የሚሆነው የወጣቶች ጥረት ሲታከልበት ብቻ ነው። ወጣቶች ነገ የመቀየር፣ ነገ የማደግ እንዲሁም ነገን ተስፋ የማድረግ ስሜት ሊያጎለብቱ  ይገባል። ለዚህ አንዱ ነገር ደግሞ ወጣቶቻችን ስራ የማማረጥ አባዜን  በማስወገድ የተገኘውን ስራ የመስራት እንዲሁም  የቁጠባ  ባህልን ማዳበር ይኖርባቸዋል።  ቁጠባ የመለወጥ  ብቸኛው መንገድ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ነገን ብሩህ ለማድረግ ዛሬ ላይ መጠንከር ይኖርባቸዋል። አገር የምትለማው ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆነው ሁሉም በተሰማራበት መስክ ጠንክሮና በሃላፊነት ስሜት መስራት ሲችል ብቻ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy