Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስሜታዊነት፣ህዝብን ያጋጫል፤ አገርንም ያፈርሳል!

0 428

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስሜታዊነት፣ህዝብን ያጋጫል፤ አገርንም ያፈርሳል!

አባ መለኩ

ከጥልቅ ተሃድሶው ማግስት ጀምሮ   መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መንግስት በያዘው ቁርጠኛ አቋም መሰረት በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው። መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተለዩትን ጉድለቶች ለማስተካከልና  የህዝብን ፍላጎትን ለማሟላት  የሚያስችሉ እርምጃዎችን ሁሉ በመውሰድ ላይ ነው። በዚህም ተጨባጭ   ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ነው። በየደረጃው ያሉ ካቢኔን እንደገና የማዋቀር፣ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ የሚገኙ አስፈጻሚዎችና ፍጻሚዎችን ህግ ፊት የማቅረብ  እርምጃዎችን መንግስት  ወስዷል። በመውሰድም ላይ ይገኛል። ይሁንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እነዚህ የመንግስት እርምጃዎች ብቻቸውን ውጤት ማምጣት አይችሉም። መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ የመንግስት ሚና ወሳኝ ቢሆንም  ካለህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ግን የታሰበው ዓላማ ሊሳካ አይችልም።  

አንዳንድ ወገኖች የመንግስት ሹማምንቶችን ከኃላፊነት ቦታቸው በማንሳት ወይም በማሰር መልካም አስተዳደርን የሚረጋገጥ መስሏቸው ከራሳቸው ፍላጎት በመነሳት እከሌ ከሃላፊነት ካለወረደ፤ እከሌ ካልታሰረ ወዘተ በማለት  መንግስት  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያደርገውን ትግል ለማኮሰስ የተለያዩ  ውዥንብሮችን  በመንዛት ላይ ነው።  በእርግጥ ጥፋተኛ መጠየቅ ይኖርበታል፤ ነገር ግን ተጨባጭ ማስረጃ  ባለተገኘበት ሁኔታ  ማንንም  ከህግ ፊት ማቅረብ ደግሞ የግለሰቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መጋፋት ነው። ህገመንግስታዊ አካሄድም አይሆንም። መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቁልፉ ነገር በማንኛውም ተቋም ውስጥ የአሰራር ስርዓት  መፍጠር፣ ተጠያቂነትን ማንገስ፣ ህብረተሰቡም አገልግሎት ለማግኘት የሚጠበቅበትን  መብትና   ግዴታ ጠንቅቆ  ተገንዝቦ መብቱን ማስከበር  እንዲችል ተገቢውን ድጋፍ  ማድረግ  እንጂ ፈጻሚን በየጊዜው በመቀያየር የተፈለገውን ውጤት ይመጣል የሚል እምነት የለኝም።   

በአገራችን የሚስተዋሉ ሁሉም ችግሮች የመልካም አስተዳደር ችግሮች አይደሉም።  ይሁንና አንዳንድ ግለሰቦች  የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ  ሁሉንም ችግሮች ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር ለማስተሳሰር የሚያደርጉት ጥረት ሊወገዝ ይገባል። በአገራችን በርካታ ችግሮች አሉ። ለአገራችን የሚበጃት  ሁሉንም  ችግሮች  በየፈርጁ ብንመለከታቸውና   መፍትሄ ብንፈልግላቸው እንጂ  በነውጥና ሁከት መፍትሄ እንፈልጋለን ማለት  ለአገራችንም ለህዝባችንም የሚበጃት አይሆንም። ስሜታዊነት ህዝብ ያጋጫል፣ አገርንም ያፈርሳል።  ስሜታዊነት  ምክንያታዊ እንዳንሆን  ያደርጋል።

ለአገራችን የሚበጃት ለችግሮቻችን መፍትሄ መፈለግ ያለብን በሰከነና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መሆን መቻል ይኖርብናል።  በአሁኑ ወቅት መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር የፊት ለፊት ውይይት በማድረግ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ መድረኮችን በማድረግ ላይ ነው። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ጅምር ቢሆንም፤ መነጋገርና መወያየት  የሚያስችል  ፖለቲካዊ ስርዓት  በመገንባት ላይ ነው።  ይህን መልካም ጅምር ልንጠቀምበት ይገባል። መስማማት ወይም አለመስማማት አንድ ነገር ሆኖ፤  ቁጭ ብሎ መነጋገር  መቻል  በራሱ የመጀመሪያውና ትልቁ መልካም  ነገር ነው።  ሰሞኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ድርድር የአገራችን  ፖለቲካ ሁኔታ  መቀየር መጀመሩን የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ  ነው። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ይህን ያህል ፓርቲዎች ቁጭ ብለው በጋራ ጉዳያቸው ዙሪያ  መነጋገር መቻላቸው በራሱ አንድ መልካም ነገር ይመስለኛል።  

በአገራችን ባለፉት 27 ዓመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት 15 ዓመታት በርካታ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያጎለብቱና የሚያፋጥኑ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። አገራችን እያስመዘገበቻቸው ካሉ  ስኬቶች  ህዝቡ በየደረጃው ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት  እየተደረገ ነው። ተጨባጭ ውጤቶችም ታይተዋል። ይሁንና መልካም አስተዳደር በማስፈን ረገድ ያልተፈቱና ህዝቡን እያማረሩ  ያሉ በተለይ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ይስተዋላሉ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ላይ ነው። መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ  ሁሉም ባለድርሻ አካላት  የበኩሉን አስተዋጽፆ  ማበርከት ካልቻለ  የመንግስት ጥረት ብቻውን ውጤታማ ሊሆን አይችልም።  

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን ያማረሩትን ችግሮች በመለየት የተለያዩ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። በፌዴራልም ሆነ በክልሎች በተካሄዱ ሠፋፊ መድረኮች ከህዝቡ በተገኙ ግብዓቶች መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ ዕርምጃ በመወሰድ ላይ ነው። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።  እርግጥ ግለሰቦችን ከኃላፊነታቸው   በማንሳት፣ በማገድና በማሰር  ብቻ  የመልካም አስተዳዳር  ችግርን ማስወገድ አይቻልም። ይልቁንም ችግሩ እንዳይከሰት የአሰራር ስርዓትን ማበጀት ቁልፍ ተግባር ይመስለኛል።  የተጀመረውን የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ  የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ  ማጋለጥ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።  

ጠባቦችና ትምክህተኞች  የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ስኬት አይፈልጉም። እነዚህ አካላት  የጥፋት ተልኳቸውን  ለማሳካት  ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈጥሩ ኃይሎችንና በችግሩ የሚማራሩ ወገኖችን በመሣሪያነት መጠቀም ነው። ስለሆነም የአገራችንን ስኬቶች ቀጣይነት ለማረጋገጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩትን ጥረቶች ማጠናከር ወሳኝ ነው።በየትኛውም መስክ ለጥፋት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ይገባል። የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በፅናት መታገል ያስፈልጋል። ትግሉንም በህዝብ ድጋፍ በማጀብ ማሳካትም ይቻላል። ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች እነማን እንደሆኑና በዕለት ተዕለት ህይወቱ የሚያጋጠመውን ተግዳሮቶች ጠንቅቆ ያውቃል።

የአሰራር ስርዓት ከተዘረጋ እያንዳንዱ አስፈፃሚ ተግባሩን በስርዓቱ መሰረት እንዲፈፅም ያስገድደዋል። መልካም አስተዳደር በሂደት የሚገነባ ከዴሞክራሲያዊ ባህል ጋር እጅግ የተቆራኘ ነገር በመሆኑ  በአንድ ጀምበር የፈለግነውን  የተዋጣለት  አገልግሎቶችን  ማቅረብ አይችልም። ይሁንና እስካሁን መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው  ባከናወኗቸው አንዳንድ ጥረቶች ተጨባጭ ለውጦችን  ማስመዝገብ  ተችሏል፤ በዚህም በቅርብ ጊዜ እንኳን በዘመቻ መልክ በተካሄደው እንቅስቃሴ  በርካታ የህብረተሰብ  ሮሮዎችን  መቀነስ ተችሏል።  

የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከጊዜና ከሁኔታዎች ጋር የሚቀያየሩ በመሆናቸው አንዴ ፈተናቸዋልና  ዳግም አይከሰቱም  ማለት አይቻልም። ሁሌም ራስን መፈተሽና ማስተካከል ተገቢ ነው። ምዕራባውያንኖችም ቢሆኑ በየጊዜው የመልካም አስተዳደር ችግሮች  እየገጠሟቸው  ምላሽ   እየሰጡ  ናቸው።  በአገራችን ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓትን እንደጀማሪ የዴሞራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ አራማጅ አገር አኳያ  ስንቃኘው  መልካም ጅምሮች ያሉበት ነው።  እነዚህ መልካም  ጅምሮችን  ማጎልበት ተገቢ ነው። ማንም  በጻፈው ወይም በተናገረው ሲከሰስ ወይም ሲታሰር አልተመለከትንም። ይህ ማለት ግን ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ነገር መጻፍ አያስከስስም ማለት አይደለም።  

ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ቁርጠኛ አቋም እንዲይዝና የዘመቻው አካል ለማድረግ  መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት  አሁንም ተጠናክረው መቀጠል መቻል አለባቸው። ገዥው ፖርቲ ራሱን የፈተሸበትን መነጽር በመንግስት መዋቅር ውስጥም  ቢጠቀምበት መልካም ነው።

መልካም አስተዳደርን  ለማስፈን መንግስት  እየወሰደ ያለው እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ይሁንና ሰው መቀያየር  ጊዜያዊ  እፎይታ ይሰጥ እንደሆን  እንጂ ለዘለቄታው  መፍትሄ አይሆንም። በመሆኑም መንግስት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የአሰራር ስርዓትን መዘርጋት፣ እንዲሁም  ህብረተሰቡ መብቱንና ግዴታውን ጠንቅቆ እንዲያውቅና  ለህግ ተገዢ  እንዲሆን  ማስተማር ተገቢ ነው። ጉቦ ሰጪ ከሊለ ተቀባይ አይኖርም።  

በአሰራር ስርዓት የሚመራ ማንኛውም አስፈፃሚ በተቀመጠለት ህግና ስርዓት ብቻ ተግባሩን ይፈፅማል።  በዚህ መንገድ ህዝባዊ አገልጋይነቱን የሚያረጋግጥ ማንኛውም አመራር ይሁን አስፈፃሚዎች ችግር የሚፈጥርባቸውን ቀዳዳዎች ሊያገኝ አይችልም።  ከጊዜ ሂደት ጋር የሚፈጠሩ  ቀዳዳዎችን  ደግሞ ህዝብና መንግስት  በየወቅቱ በመፈተሽ ወይም አሰራሮችን በማሻሻል አገልግሎቶችን  ማዘመንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ  ይቻላል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘለቄታው ለመቅረፍ የአሰራር ስርዓትን መዘርጋትና በየጊዜው ደግሞ መፈተሽ ተገቢ ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy