Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በህዝቦች ፍላጎትና መስዋዕትነት የተገነባ ሥርዓት

0 418

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በህዝቦች ፍላጎትና መስዋዕትነት የተገነባ ሥርዓት

                                                         ታዬ ከበደ

የአገራችን ጽንፈኛ ሃይል በተለያዩ ወቅቶች ከውስጥ ሆነ ከውጭ ሆኖ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ለማጥላለት ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። የፅንፈኛው ሃይል ፍላጎት ሥርዓቱን በማጥላላት የከሰረ ፖለቲካውን ማራመድ ነው። ሆኖም ይህ ተግባሩ ከሥርዓቱ ስኬቶች ጋር ሆድና ጀርባ ነው። በተጨባጭ ሥርዓቱ ያስገኛቸው ውጤቶች ሌላ የፅንፈኛው አሉባልታ ደግሞ ሌላ ነው። መሰረተ ቢስ የወሬ ድረታ መሆኑን ሥርዓቱን በተግባር ያየ የሚመሰክረው ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት በተወሰኑ ሃይሎች ሳይሆን በመላው የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ፍላጎትና መስዕዋትነት የተገነባ ነው። ባለቤትነቱም እነርሱው ከመሆናቸው በላይ በጽኑ መሰረት ላይ የቆመና ማንም ከመሬት ተነስቶ ሊያፈርሰው የማይችል ነው። ይህንን እውነታ የትኛውም ወገን ሊያውቀው ይገባል።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በህዝቦች ፍላጎት ነው የተገነባው የሚባለው እንዲሁ ለማለት ተፈልጎ አይደለም። ሥርዓቱን ለማምጣት ውድ የህዝብ ልጆች ህይወታቸውን፣ አካላቸውንና ንበረታቸውን መስዋዕት አድርገዋል። ያም ሆኖ ግን ፅንፈኞች ይህን እውነታ ወደ ጎን በማለት ሥርዓቱን ጥላሸት ሊቀቡት ይፈልጋሉ።

እርግጥ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ሀገራችን የተቀዳጃቸውን ድሎች በርካታ ቢሆኑም የቀድሞውን ስርዓት የሚናፍቁ አሊያም ከስሮ እርቃኑን የወጣ ፖለቲካን ያነገቡ ሃይሎች ዛሬም በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ለማሳየት ይጥራሉ። ይህ ግን ከንቱ ምኞች ነው። ከሁሉም በላይ የሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች በትግላቸው ያገኙትን ድሎች ለመንጠቅ የማሰብ ያህል ነው።

ፅንፈኞቹ ከትናንት አስከ ዛሬ ‘የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ወደ አይሆኑ አዘቅት ውስጥ ትገባለች፣ የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቦቿ በየጎራው ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ይበላላሉ ወዘተርፈ’ በማለት የማለት ዲስኩርን ሲያሰሙ ይስተዋላል።

ዳሩ ግን እነርሱ የፈለጉትን ቢሉም መንግስትና ህዝብ በውዠንብራቸው ሳይዘናጉ ብዝሃነታቸውን ውበታቸው በማድረግ አንድነታቸውን አጠናክረው፣ ለጋራ ዕድገት መረባረቡን ነው የመረጡት፡፡

እርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሥርዓቱ ምሰሶ የሆነውን ህገ መንግስት በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያጸድቁት የተጫውተው ሚና በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ ይህችን ሀገር ከአምባገነኑ የደርግ ሥርዓት አገዛዝ ያላቀቀው ኢህአዴግ መራሹ የህዝብ ትግል፤ ስልጣን በህዝብ እና በህዝብ ብቻ የሚረጋገጥ እንደሆነም የሚያምን በመሆኑ በዚህ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ህዝቦች የትግላቸው ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ፅንፈኞች የሚሉትን አይነት በድቡሽት የተገነባ ቤት ሳይሆን፤ በህዝቦች ፍቃድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ስለሆነ ነው። እናም ሥርዓቱን ሲመለከቱበት የነበረው መነጽር የተሳሳተ ዕውነታውን የማያሳያቸው መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል፡፡

እርግጥ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች በዜሮ ድምር የፖለቲካ ስሌት የሚመሩ በመሆናቸው ይጠቅመናል ብለው ካሰቡ ምንም ነገር ከማለት ወደ ኋላ የሚሉ አይደሉም፡፡ ሆኖም የእነርሱ “የኢትዮጵያ ትበታተናለች” የከሰረ ፖለቲካ እውን አልሆነም። መቼም ሊሆን አይችልም።

ባለፉት ሥርዓቶች መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተነፍገው ከነበሩ መብቶቻቸው መካከል የራስን ዕድል በራስ መወሰን አንዱ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ቻርተርና በሌሎች ዓለም አቀፍ ዶክመንቶች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕውቅና እግኝቶ የነበረ ቢሆንም ያለፉት የኢትዮጵያ ገዢ መደቦች ይህንን መብት አፍነውት ኖረዋል፡፡  

በመሆኑም በተለይም ተገልለውና ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና  ሕዝቦች ጋር ሆነው በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በእኩልነት  የመሳተፍ  መብት አልነበራቸውም፡፡

የየራሳቸውን አኩሪ ባህልና ቋንቋ የሚጠቀሙበትና የሚያበለጽጉበት ዕድል ተነፍጓቸውም ኖረዋል፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች የአብዛኛዎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል የሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ተደርገው ከመቆጠር ይልቅ፤ ገሚሶቹ “ብረት ሰባሪ…ወዘተ” እየተባሉ የሚጠሩ ነበሩ፡፡

የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋቸው የመዳኘት፣ የመማር  ወዘተ. መብት አልነበራቸውም። አብዛኛው ቋንቋዎችን እንኳንስ በአደባባይ ለመጠቀምና ስራ ላይ ለማዋል ይቅርና  በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለመጠቀም   እጅግ  የሚያሸማቅቅ ሁኔታ እንደነበረም አይዘነጋም፡፡ ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበር እንዲሁም የማስፋፋት  መብታቸው  የተነፈገ እንደነበርም የኋላ ታሪካችን ያስረዳል፡፡

በእነዚይ ሥርዓቶች የአካል ደህንነት፣ በህይወት የመኖር  መብት፣ ክብርን ከሚያዋርዱ አያያዞች የመጠበቅ…ወዘተ. የሚጣስባቸው ነበሩ፡፡ ከዚህም አልፎ ኢ- ሰብዓዊ ለሆነ እስር መዳረግ፣ እገታ ወዘተ. ወንጀሎች  የሚፈጸምባቸው  በመሆኑ ዜጎች ለከፋ  ስቃይና ስደት ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  እኩል ሆነው የሚታዩበት  ሁኔታዎች ያልነበረባቸው መሆናቸውን የኋላ ታሪካችን ያረጋግጣል፡፡

ሁኔታዎቹን  ግን የደርግ  ሥርዓት በመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግል አካሂደው መብቶቹን ሙሉ ለሙሉ ተጎናፅፈዋቸዋል፡፡

ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተወያይተው ያጸደቁት ህገ – መንግሥት  የራስን ዕድል በራስ  የመወሰን፣ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት፣ በቋንቋ የመጠቀምና  የማሳደግ ፣ባህልን የመግለጽ፣ ማዳበርና ማስፋፋት እንዲሁም ታሪክን  የመጠበቅ እና ሌሎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ አረጋግጧል፡፡

ሆም የአገራችን ፅንፈኛ ኃይሎች ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ አይተው እንዳላዩ መሆንን መርጠዋል፡፡ ይልቁንም  ዛሬም ሥርዓቱን በባዶ ሜዳ ላይ ያለ አንዳች ተጨባጭ አስረጅ እንዲሁም በማኅበረሰቦች ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ጊዜያዊና ነባራዊ ሁነት በማጦዝ ከማጥላላት አልቦዘኑም።

ይሀን እንጂ መላው የሀገሪቱ ህዝቦች በደማቸው የፃፉት ህገ መንግሥት ፀድቆ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም በአንድነት ተሳስረው የእድገት ጉዟቸውን ተያይዘውታል፡፡ አላዛኞችም የሚደልቁት የቆርጦ ቀጥልነት አታሞም ሰሚ አጥቷል፡፡ እናም በሚያስገርም ጨለምተኛ እሳቤያቸው ዓለም የመሰከረውንና ዕድገት ያመጣውን ፌዴራላዊ ሥርዓት “ከሽፏል” ይሉናል፡፡

አንዳንዶቹ ጭራሹኑ በግጦሽ ቦታና በውኃ ምክንያት እንዲሁም በጊዜያዊ አለመግባባቶች ሳቢያ በአንዳንድ የሀገራችን ብሔረሰቦች መካከል ለዘመናት ሲከሰቱ የኖሩ ግጭቶች መኖራቸውን እንዲሁም አማርኛ ተናጋሪዎች ከአንዳንድ አካባቢዎች ተባረሩ በሚሉ  የፌዴራል ሥርዓቱ በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት ከሽፏል እስከማለት ደርሰዋል፡፡

ፅንፈኞቹ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን እያውቁም ወይም ቢያውቁም ለመናገር የሚደፍሩ አይደሉም። ምክንያቱም ለእነርሱ ጥላሸት የመቀባት ሥራ ይህ ሀቅ ምንም ስለማይጠቅማቸው ነው።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሃብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

በየአካባቢው የሚከሰቱ ችግሮችም በሥርዓቱ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ አሰራር እየተፈቱ ናቸው። ወደፊትም ይፈታሉ። እናም ፅንፈኞቹ ያሻቸውን ቢሉምሥርዓቱ በህዝቦች ፍላጎትና መስዕዋትነት የተገነባ በመሆኑ እነርሱ እስካሉ ድረስ ማንም ሊያፈርሰው እንደማይችል መገንዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል።

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy