Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በመልማት መብታችን የማንንም ይሁንታ አንጠይቅም!

0 274

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በመልማት መብታችን የማንንም ይሁንታ አንጠይቅም!

                                                       ደስታ ኃይሉ

የግብፅ መገናኛ ብዙሃንና አንዳንድ ተቋማቶቻቸው በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል የተደረገው ውይይት ያለ ስምምነት መበተኑንና በሌላ ጊዜ እንደሚቀጥል መወሰኑን አስመልክቶ  በህጋሴ ግድቡ ላይ እያቀረቡት ያለው ሃሳብ የተሳሳተ ነው። በተለይም የአገራችንን ህጋዊ የመልማት መብት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተፈጥሮ ሃብታቸው የመጠቀም መብታቸውን ለድርድር የማያቀርቡ፣ የሚያከናውኑት የልማት ስራ የትኛውንም የተፋሰሱን አገር ለመጉዳት ሳይሆን ከድህነት አዙሪት ቀለበት ለመውጣት አይደለም።

የልማት ስራቸውንም ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት መንገድ የጋራ ተጠቃሚነትን ዓለም አቀፍ መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ እያከናወኑ ይገኛሉ። ታዲያ ይህን ተግባር ሲከውኑ የአገራችን ህዝቦች ከድህነት ለመውጣት የተፈጥሮ ሃብታቸውን ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ እንደማይጠይቁ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ የየትኛውንም የተፋሰሱን አገራት ጥቅም የመንካት ፍላጎት እንደሌላት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ ሳይቀር “…ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ፈጣን ዕድገትን ለማሳካት የሚያስችል ስራ ካልሰራች የልማት ስራዎቹ ሊከናወኑ አይችሉም። ይህንንም የግብፅን መሰረታዊ ጥቅም በማይነካ፣ ጥቅሞችን በሚያጣጣም አኳኋን ማድረግ ይቻላል፤ ይገባልም።…” በማለት በግልፅ አስፍራለች። ይህ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም ነው።

ይህ የኢፌዴሪ መንግስት አቋም ሀገራችን የሌሎችን ሀገር ጥቅም ሳትጎዳ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያብራራል። አቋሙም በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ የሚመለከት ነው።

አዎ! የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመገንባት ላይ የሚገኙት የህዳሴ ግድብ የታችኛዎቹን ተፋሰስ ሀገራት መሰረታዊ ጥቅሞችን የሚያስከብር እንጂ የሚጎዳ አይደለም። ምንም እንኳን አገራችን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በፖሊሲዋ ላይ ሳይቀር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የዓባይን ውሃ በፍትሃዊነት ለመጠቀም ቃል የገባች ቢሆንም፤ በተለይም ግብፆች ይህን ግልፅ የሆነ መርህ ሊቀበሉት የሚፈልጉ አይመስልም።

እርግጥ ኢትዮጵያና ግብፅ ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ቁርኝት ያላቸው ሀገራት ቢሆኑም፤ በዓባይ ወንዝ ምክንያት ግንኙነታቸው የሚጠበቀውን ያህል የተጠናከረ ነበር ለማለት አያስደፍርም። ለዚህም ግብፅን ለዘመናት በየተራ ሲመሯት የነበሩት መንግስታት የዓባይን ወንዝ የውስጣቸውን የፖለቲካ ትኩሳት ማብረጃ መሣሪያ አድርገው ሲጠቀሙበት መቆየታቸውን በምክንያት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

እነዚያ የግብፅ ገዥ መንግስታት ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃን መጠቀም ከጀመረች ሀገራቸው ለከፍተኛ አደጋ እንደምትጋለጥ በማስመሰል ህዝቡን ሲሰብኩት መኖራቸው ይታወቃል።

የግብፅ መገናኛ ብዙሃንና ተቋማቶቻቸው አገራቸውና ሱዳን ብቻ እ.ኤ.አ በ1929/ በ1959 ዓ.ም  የተፈራረሙትን የቅኝ ገዥዎች ውል በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ከውሃው አንድም ሊትር መጠቀም እንደሌለባት ለህዝባቸው ሲገልፁ ነበር—ዛቻንና ማስፈራሪያን ጨምሮ “ሆድ አደር” የሆኑ የአገራችንን ተቃዋሚዎች ለእኩይ ፍላጎታቸው በማሰማራት ጭምር።

ታዲያ ዛሬም ይህ ሁኔታ በግብፅ ሚዲያዎችና ባለስልጣናት ዘንድ እየተስተዋለ ነው። በአንድ ጎን እየተወያዩ በሌላው መልኩ ደግሞ የቅኝ ግዛት ውሎችነ ያጣቅሳሉ። ይህ ፈቅሞ ስህተት ነው። ይህ የግብፅ መገናኛ ብዙሃንና ተቋማት አቋም ለዓባይ ወንዝ ከ86 በመቶ የማያንስ ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያን በኢ-ፍትሐዊ አስተሳሰብ ያገለለና “እኛ ብቻ እንጠቀም” የሚል በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

ይህ በተለያዩ ወቅቶች ብቅ ጥልም እያለ የሚከሰተው የግብፅ መንግስታትና የተቋሞቻቸው በጎ ያልሆነ ተግባር አገራችን ካላት ሁሉም ተጠቃሚ ከሚሆንበት አቋም ጋር የሚጋጭ ቢሆንም፤ መቼም ቢሆን የታችኛዎቹን የተፋሰሱን ሀገራት በማይጎዳ መልኩ የተፈጥሮ ሃብቷን መጠቀሟ አይቀርም። ይህ የሀገራችን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት አስተሳሰብ በመርህ ደረጃ ተፈፃሚ የሚሆን በመሆኑ ነገም ቢሆን ከዚህ አቋሟ ልትዛነፍ የምትተችልበት ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም።

ኢትዮጵያ ግብፅን አስመልክቶ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ “…የዓባይ ጉዳይ ጥቅሞችን በማጣጣም መርህ በሰላምና በድርድር የልማት እንቅስቃሴያችንን በማይጎዳ መልኩ እንዲፈታ፣ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች በቂ ጊዜ በሚሰጥ አኳኋን እንዲታዩ ማድረግ ይሆናል።…” የሚል አቋም አስፍራለች። ይህም መንግስት በዓባይ ጉዳይ ፍትሐዊ የሆነ የሁለትዮሽ ጉዳይ ተጠቃሚነትን በሚያስብበት ወቅት፤ ሰላማዊ ተግባሩን በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት እንዲሁም በችኮላ ሳይሆን ጊዜ በሚሰጥ ሁኔታ እንደሚያከናውን የሚያሳይ ነው።

የጋራ ተጠቃሚነትንና አገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቀው ይህ የመንግስት አቋም የህዳሴው ግድብ በሰጥቶ መቀበል መርህና በድርድር እውን ሊሆን እንደሚችል ማረጋገጫ የሚሰጥ ይመስለኛል። ግብፆች ግን አሁንም በቅኝ ገዥ ውሎች ላይ ለምን እንደመንጠለጠሉ ለማንም ግልፅ አይደለም።

እንደሚታወቀው ሁሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት እያደገ በመሄድ ላይ በሚገኘው ምጣኔ ሃብታችን ሳቢያ፣ ግብርና የመሪነት ሚናውን በሂደት ለኢንዱስትሪው ሲያስረክብ ለሚፈጠረው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ነው። ለግብፅ ጭምር ኤሌክትሪክ በመሸጥም የውጭ ምንዛሪ አቅማችን እንዲጎለብት ማድረጉ አይቀርም።

የኢፌዴሪ መንግስትም አገራዊ የፀረ ድህነት ትግሉን በማቀጣጠል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራን ይፋ የማድረጉ ምክንያትም ይኸው ይመስለኛል። እርግጥ የግድቡ ግንባታ ለዘመናት የዘለቀውን የድህነትና የኋላቀርነት ታሪካችንን የመቀየርና ያለመቀየር ጉዳይ አንዱ ምክንያት በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳነቱ ሊያጠያይቅ አይችልም። በመሆኑም የግድቡን ግንባታ የማሳካቱ ጉዳይ የአሁኑን ትውልድ ህይወት የመለወጥና ያለ መለወጥ ጥያቄና ውሳኔ ብቻ አይሆንም— የአሁኑንና የቀጣዩን ትውልድ ህልውና የማረጋገጥና ያለማረጋገጥ ብሎም ሀገራዊ ህልውናን የማስቀጠል አገራዊ ፋይዳ ያለውም አንድ ማሳያ ነው።

የህዳሴው ግድብ ዛሬ ግንባታው 63 በመቶ የደረሰ ህዝባዊ ልማት ነው። ይህ በራስ አቅም የመልማት ስራችን አገራችን ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት አንድ ማሳያ እንጂ የማንንም ጥቅም ለመጉዳት ታስቦ የሚከናወን አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን የማንንም ጥቅም እንደማንጎዳ ሁሉ፤ በውሃ ሀብታችን ለመልማት በምናደርገው ጥረት የማንንም ይሁንታ የማንጠይቅ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። ምክንያቱም የትኛውም አገር የተፈጥሮ ሃብቱን ለማልማትና ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት የማንንም ፈቃድ ጠይቆ ስለማያውቅ ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy