Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በመዲናዋ የኤች አይ ቪ ስርጭትን በተመለከተ ከነገ ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

0 1,095

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ከነገ ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ27 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ አዲስ የሚያዙ ሲሆን፥ እስከ 20 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ከፌዴራል ኤች አይ ቪ መከላከያ እና መቆጣጠያ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።።

በአዲስ አበባም ከ127 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ይኖራሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ግን እራሳቸውን የሚያውቁት ከ65 በመቶ የማይበልጡ ናቸው ተብሏል።

ከ2009 ዓ.ም በፊት በመዲናዋ በየዓመቱ በቫይረሱ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ከ2 ሺህ 200 አይበልጥም ነበር፤ የባለፈው ዓመት መረጃ ግን በዓመቱ ውስጥ አዲስ የተያዙት ሰዎች ከ4 ሺህ 200 በላይ ደርሷል።

ይህም በዓመቱ ከ100 ሰዎች አምስቱ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ያሳያል።

በዚህም የቫይረሱ ስርጭት በመዲናችን ወረርሽኝ በሚባል ደረጃ እየታየ እና እየጨመረ መሆኑን ነው፥ የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፈለቀች አንዳርጌ የሚናገሩት።

በቫይረሱ ባለፈው ዓመት ብቻ እንኳ ከ1 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የፅህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

ተጋላጭ ከሆኑትም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ያሉ ሲሆን፥ በቫይረሱ ከሚያዙት ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች ናቸው።

የስርጭት መጠኑ መጨመርም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ለማወቅ ፍላጎት አለመኖር ወይም የግንዛቤ እጥረት እንዲሁም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚያደርጉ ቦታዎች ቁጥር መስፋፋት ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው ወይዘሮ ፈለቀች የገለጹት።

ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጭዎችም ቢሆን ግንዛቤው ላይ እየተሰራበት አለመሆኑን እና ለቫይረሱ አጋላጭ የሆኑ ቦታዎች መስፋፋታቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ይህን ህብረተሰቡን እያጠቃ እና አምራች ሀይልን እየነጠቀ ያለውን በሽታ ለመከላከል እና ለመቀነስ፥ በዚህ ዓመት ሊሰሩ ከታሰቡ እና ከተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ እና ዋነኛው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ነው ተብለዋል።

ፅህፈት ቤቱም ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄን ሊያካሂድ መሆኑን ገልጿል።

ንቅናቄው “አሁንም ትኩረት ለኤች አይ ቪ መከላከል” የሚል መሪ ቃልን የያዘ ነው።

በዚህ ንቅናቄ የተለያዩ የውይይት መድረኮች፣ የምርመራ ዘመቻዎች እና ሌሎችም ግንዛቤ መፍጠሪያ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።

ይህ መደረጉም ብዙዎች የተዘናጉበትን በሽታ አጀንዳ ለማድረግ እና ህብረተሰቡም ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚረዳ መሆኑ ታምኖበታል።

ግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎንም መከላከልን ትኩረት ባደረገ መለኩ የኮንዶም ሰርጭት እየተሰራበት መሆኑንና በዚህ በጀት ዓመት የመጀመሪያ 3 ወራት ከ2 ሚሊየን በላይ ኮንዶም በነፃ መከፋፈሉን ፅህፈት ቤቱ አስታውቋል።

እስከ ዓመቱ መጨረሻም ከ40 ሚሊየን በላይ በነፃ የሚታደሉ ኮንዶሞች እንደሚገቡ ነው ይፋ የተደረገው።

 

 

በዙፋን ካሳሁን

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy