Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በትግል የተገኘው ድል፤ በትግል ፀንቶ ይቀጥላል ክፍል አንድ

0 510

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በትግል የተገኘው ድል፤ በትግል ፀንቶ ይቀጥላል

ክፍል አንድ

አሜን ተፊሪ

 

የሐገራችን የፖለቲካ ምህዳር የሙቀት እና የቅዝቃዜ፤ የጥንካሬ እና የመብረክረክ፤ የመድመቅ እና የመደንገዝ ገጽታ አለው፡፡ ምናልባትም፤ ገና መልኩ በግልጽ መታየት ካልጀመረ የታሪክ ጽንስ ጋር ተጋፍጠን፤ በግራ መጋባት ስሜት ተወጥረን የምንገኝ ሆኖ ሊሰማን ይችላል፡፡ ገና የሚከተለውን ጎዳና በውል ለመለየት የሚያስቸግር የታሪክ ፈረስ ጋልበን እየተጨነቅን ያለ ሆኖ ሊሰማን ይችላል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በሳይንሳዊ የትንታኔ መነጽር ሲታይ አደናጋሪነቱ ይቀንሳል፡፡ ከዚያ በኋላ ጎልቶ የሚወጣው ፈታኝነቱ ብቻ ይሆናል፡፡ በሳይንሳዊ ትንታኔ ችግሩ ከተለየ፤ አደናጋሪነቱ ከተወገደ ችግሩን መጋፈጥ ብቻ ነው፡፡ በትግል የተገኘውን ድል፤ በትግል ለማስቀጠል ቆርጦ መነሳት ነው፡፡

 

መሪው ድርጅት የችግሮቹን ምንጮች ያውቃቸዋል፡፡ ታዲያ ለምን ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ ሲሄድ ይሰንፋል? ይህን ጥያቄ አስር ጊዜ አንስቼ፤ አስር ጊዜ መልስ ሰጥቼ፤ ደግሞ አስር ጊዜ መልሼ የማነሳው ጥያቄ ሆኖብኝ አስቼግሮኛል፡፡ ግን ከተስፋ መቁረጥ አላደረሰኝም፡፡ የማይነጥፍ የተስፋ ምንጭ የሆነኝም ኢህአዴግ ለሚያጋጥሙት ችግሮች ውጫዊ ምክንያት ከመስጠት ይልቅ ወደ ውስጥ በመመልከት ራሱን በማረም ላይ የሚያተኩር ህዝባዊ ድርጅት መሆኑ ነው፡፡

 

ኢህአዴግ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በብቃት በመተንተንና ሁነኛ የመፍትሄ አቃጣጫዎችን በመንደፍ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በመተግበር ሐገራችን በቀጣይ የምትደርስበትን የዕድገት ደረጃና በየምዕራፉ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ጭምር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተንትኖ አማራጭ መፍትሄዎቻቸውን በመጠቆም ቀድሞ የሚዘጋጅ የለውጥ ኃይል በመሆኑ፤ ፈታኝና ውስብስብ ሁኔታዎችን በድል የመወጣት ብቻ ሳይሆን ተግዳሮቶችንም ወደ መልካም ዕድልነት በመቀየር ብቃት ያለው ድርጅት መሆኑን አሁንም አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግ ከአንድ ፈታኝ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው ከፍተኛ የስኬት ምዕራፍ እየተሸጋገረ የመጣ ጠንካራ ድርጅት በመሆኑ፤ በዚህች ምድር የፈኘጠቀውን የተስፋ ብርሃኑን እያደመቀ ሊጓዝ የሚችል ህዝባዊ ድርጅት ሆኖ ከፊቱ በተዘረጋው የታሪክ ምዕራፍ በድል አድራጊነት መጓዙን እንደሚቀጥል አልጠራጥርም፡፡

 

በማንኛውም አገር ያለ ህብረተሰብ ከትንሽ ወደ ትልቅ፣ ከቀላል ወደ ውስብስብ እያደገ የሚጓዝ በመሆኑ፤ አገራችንም በዚህ የማይቀር የህብረተሰብ የጉዞ አቅጣጫ ማለፏ የግድ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃና ከገባችበት መድረክ ለሚመነጩ መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች የምትጋለጥ አገር መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህን በመሰለው ሁኔታ ከድርጅቱ አመራር የሚጠበቀው ኃላፊነት መልካም ዕድሎቹን በአግባቡ በመጠቀም፣ ፈተናዎቹን ደግሞ በጥበብና በፅናት በማለፍ፣ አለፍ ሲል ደግሞ ተግዳሮቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አገራችን በማያቋርጥ የዕድገት ሂደት እንድታልፍና ህዝቦቿን በሙሉ እየጠቀመች እንድትጓዝ ማድረግ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ዕድል፣ ሌላ መንገድ የለም፡፡

 

በቅርቡ በአንዳንድ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ለተከሰቱት ወቅታዊ ችግሮችም ሆነ ከዛ በፊት በነበሩት ተከታታይ ዓመታት ህዝባችንን እያስመረሩ ያሉና ለልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ፈተና የሆኑ ችግሮች ዋነኛ መንስዔአቸው የድርጅት እና የመንግስት ስልጣንን ለኅብረተሰባዊ ለውጥ ከማዋል ይልቅ ለግል ጥቅም ማበልፀጊያ የማዋል ዝንባሌ ስር እየሰደደ መምጣቱ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን ችግር ለይቷል፡፡

 

ታዲያ ይህ ችግር አሁኑኑ የማያዳግም መፍትሄ ካልተሰጠው፤ የጀመርነው የሕዳሴ ጉዞ የሚቀለበስበት ዕድል ዝግ እንደማይሆንም ኢህአዴግ ገምግሟል፡፡ ለዚህም ነው፤ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ በውስጡ፣ ከውስጡም ደግሞ ከበላይ አመራሩ ጀምሮ እንዲቀጣጠል በማድረግ ሁሉም የድርጅቱ መዋቅር ራሱን በጥልቀት እየፈተሸ የሚታደስበት አቅጣጫ እንዲቀመጥ ያደረገው፡፡

 

በርግጥም በ2008 ዓ.ም መጨረሻ የተጀመረው እንደገና በጥልቀት የመታደስ ድርጅታዊ ውሳኔ በጣም አስፈላጊ ነበር፡፡ በአስቸጋሪነቱ ለየት ያለ ባህርይ ይዞ እያንገላታን ያለው ችግር ቆራጥ መፍትሔ የሚሻ ነው፡፡ ከዚህ ውሳኔ በፊት በነበሩት ወራት የከፋ ግጭት እና ሁከት የተቀሰቀሰባቸው ወራት ነበሩ፡፡ በብዙዎች ዘንድ “ወዴት እያመራን ነው?” የሚል ጥያቄ ከግራም ከቀኝም ይቀርብ የነበረበት ወራት ነው፡፡ ስለዚህ እንደገና በጥልቀት የመታደስ ድርጅታዊ ውሳኔ፤ በታላቅ የለውጥ መንፈስ፣ ወኔና ዝግጅት ችግሩን ለመፍታት የሚያነሳሳ ውሳኔ በመሆኑ፤ ኢህአዴግ ያሳለፈው እንደገና በጥልቀት የመታደስ ውሳኔ ወቅታዊ እና ነፍስ አድን ውሳኔ ነበር፡፡

 

እንደገና በጥልቀት የመታደስ ውሳኔው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ ውሳኔውን አስፈላጊ ያደረጉ ምክንያቶች ይታወቃሉ፡፡ የአዲሱን የመታደስ ንቅናቄ መሠረታዊ መንስዔዎች፤ የተሐድሶውንም ይዘት እና ባህርይ በውል በመገንዘብ ንቅናቄውን በተቀመጠለት አቅጣጫ አስኪዶ ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት የሚቻለው ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ አሁን ተጨማሪ ሥራ የሚያስፈልገው፤ ቁርጠኝነትን በማጠናከር ረገድ ነው፡፡  

 

በመጀመሪያው ተሃድሶ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለው የቁርጠኝነት መጓደል ባለመታየቱ ነው፡፡ በተለይ የበላይ አመራሩ ሳይታክቱ በመሥራቱ ነው፡፡ እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ለማካሄድ ከመነሳት ጋር ተያይዞ በቀዳሚነት ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ፣ “ከዚህ ቀደም የተጀመረውና እስካሁን የቆየው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ምን ስለሆነ ነው፤ አሁን እንደ አዲስ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ አስፈላጊ ሆኖ የመጣው?” የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ድርጅቱ ይህን ጥያቄ አንስቷል፡፡ ‹‹ለአስራ አምስት ዓመታት በተሃድሶ ላለፈ ድርጅትና መንግስት፤ በመጀመሪያው ተሃድሶ ላይ ምን ሳንካ ቢያጋጥም ነው ሌላ የመታደስ እንቅስቃሴ አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው?›› የሚል ጥያቄ አንስቶ ፍተሻ አድርጓል፡፡

 

ከዚህ መሰረታዊ ጥያቄ በመነሳት ሌሎች ተከታይ ጥያቄዎችን እያቀረበ ጉዳዩን በጥልቀት ለመመርመር ሞክሯል፡፡ በጠራ የሁኔታዎች ግምገማ ላይ ተመስርቶ ለመጓዝ ጥረት አድርጓል፡፡ በጉዳዮቹ ላይ ጥራት ያለው ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ሥራ እና ትግል የሚያግዝ ዕውቀት ለመያዝ ተፍጨርጭሯል፡፡ ሐገራችን ከምትገኝበት ተጨባጭ የዕድገት ደረጃ እና ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር አያይዞ ችግሩን ለመረዳት እና የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ተንቀሳቅሷል፡፡

 

በዚህ ጥረቱ ያገኘው የመጀመሪያ ነጥብ፤ ያለማቋረጥ በዕድገት ጎዳና መራመድን የግድ የምትል ሐገር እየመራ መሆኑን መገንዘብ ነው፡፡ እንደገና በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን አስፈላጊነት ለመረዳት፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የመጣውን ለውጥ በመመልከት ራሱን ለመድረኩ ብቁ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

 

ሐገራችን ኢትዮጵያ እንዲህ እንደ ዛሬው መለወጥ ከመጀመሯ በፊት ለብዙ ዘመናት በአስቸጋሪ ምዕራፍ ውስጥ ለማለፍ የተገደደች አገር ነበረች፡፡ በአገራችን ታሪክ የማያባራ የርስ በርስ ጦርነት ከተካሄደበት ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ የነበረው ታሪኳ እንደሚያሳየው እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የሚዘገንን ዕልቂት ያስከተሉ ጦርነቶችን አስተናግዳለች፡፡ ይህም በአንድ በኩል በእርስ በርስ ጦርነቱ የተነሳ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስታቱ ስልጣናቸውን ለግል ብልፅግና መጠቀሚያ አድርገው ህዝቡን ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዳይበቃ በማድረጋቸው የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ታዲያ ጦርነቱም ሆነ ድህነት እና ኋላቀርነቱ ሐገሪቱን ወደ መበታተን አፋፍ አስጠግቷት ነበር፡፡ ሐገራችን የብዙ ህዝቦች እናት ሆና እያለ ብዝሃነትን በአግባቡ የሚያስተናግድ ስርዓት ባለመገንባቷ፤ በሁሉም ማዕዘኖች ለቅሬታዎች መበራከት፣ ለአመፅ መቀስቀስ እና መበራከት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡

 

ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተረግጠው ዜጎች ለስቃይ በተዳረጉባቸው በነዚያ ዘመናት ወደ ውድቀት አፋፍ ተጠግታ ከዛሬ ነገ ትበታተናለች ተብሎ የተሰጋላት አገር እስከ መሆን ደርሳ ነበር፡፡ በድርቅና ረሃብ፣ በጦርነትና ጭፍጨፋ ሚሊዮኖች እንደ ቅጠል የሚረግፉባት፣ ስደትና መፈናቀል የበዛባት አገር ለመሆን ተገዳም ነበር፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy