Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በወ/ሮ አዜብ መስፍን ዕግድ ላይ የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚወስን ተጠቆመ

0 684

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማና አቶ ዓለም ገብረዋህድ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ናቸው

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በማዕከላዊ ኮሚቴ እያካሄደ በሚገኘው ጥልቅ ግምገማ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ለጊዜው ታግደው እንዲቆዩ በተደረጉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጉዳይ ላይ፣ የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚሰጥ ምንጮች ገለጹ፡፡

ምንጮች እንደገለጹት ወ/ሮ አዜብ መስፍን እንዲታገዱ የተወሰነው በአሁኑ ወቅት ግምገማ እያደረገ በሚገኘው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ሲሆን፣ ይህ ግምገማ ከተጠናቀቀ በኋላ የሕወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ እንደሚካሄድና በጉባዔውም የወ/ሮ አዜብ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ይወሰናል፡፡

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሞላ ጎደል ላለፈው አንድ ወር ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ በዚህ ወቅትም ተቀማጭነታቸው በትግራይ ክልል የሆኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ላይ የሰላ ትችት ሲሰነዘር እንደነበር ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በሙስና ከመዘፈቅ አንስቶ የከፋ የዴሞክራሲ ችግር በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ የነገሠ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ ወልዱን የገነነ ኢዴሞክራሲያዊነት እንደሚንፀባረቅባቸው፣ በዚህም የተነሳ በርካታ የሕወሓት አባላት ተቃውሞ እንደሚያቀርቡባቸው፣ እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የነበረውን የወሰን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ በፍጥነት ባለመፍታታቸው የትግራይ ተወላጆችን ለአደጋ እንዳጋለጡ መገምገማቸውን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአቶ ዓባይ ወልዱ ላይ የተሰነዘረውን የሰላ ትችት ለመቃወም ሲሞክሩ እንደነበር፣ በኋላም ስብሰባውን ረግጠው እንደወጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከሕወሓት ነባር ጥብቅ የዲሲፕሊን ሥነ ሥርዓቶች አንዱ የፓርቲውን የስብሰባ ሥነ ሥርዓት ማክበር እንደሆነ የተናገሩት የሪፖርተር ምንጮች፣ የወ/ሮ አዜብ ድርጊት በርካቶችን አስቆጥቷል ብለዋል፡፡ ከወ/ሮ አዜብ በተጨማሪ የኤፈርት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ በየነ ምክሩ በተመሳሳይ የደረሰባቸውን የጎላ ግምገማ ሸሽተው አንድ ስብሰባ ሳይሳተፉ መቅረታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሰኞ ኅዳር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፣ ወ/ሮ አዜብ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው ላልተወሰነ ጊዜ ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑን፣ አቶ ዓባይ ደግሞ ከፓርቲው ሊቀመንበርነት እንዲነሱና ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ እንዲሉ መወሰኑን ይፋ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም አቶ በየነ ምክሩ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ እንዲሉ ሲወሰን፣ ሁለት ማንነታቸው ያልተጠቀሱ አባላትን በከባድ ማስጠንቀቂያ ማለፉን ገልጿል፡፡

እነዚህ ሁለት ግለሰቦች የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር) እና የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ዓለም ገብረዋህድ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ወ/ሮ አዜብን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ማሰናበት እንደማይችል የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ የዚህን ስብሰባ መጠናቀቅ ተከትሎ የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ የሚካሄድ በመሆኑ ወ/ሮ አዜብ ከማዕከላዊ ኮሚቴው ይሰናበቱ ወይስ ይቀጥሉ? የሚለውን እንደሚወስን ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ አዜብ የኤፈርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ በዚህ ሥልጣን ላይ የመቆየታቸውም ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡

የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ አደራጅ ኮሚቴ ቀደም ብሎ መመረጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሕወሓት ስብሰባ ጀርባ አድራጊና ፈጣሪ ናቸው ተብለው ስማቸው እየተነሳ የሚገኘው የሕወሓት መሥራችና ጎምቱው ፖለቲከኛ አቶ ስብሃት ነጋ (አቦይ ስብሃት) ናቸው፡፡

በቅርቡ ጎንደር በተካሄደው የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ኮንፈረንስ ላይ የጥናት ጽሑፍ አቅርበው የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን፣ በአገሪቱ ሲንከባለል የቆየውን ግጭትና አለመረጋጋት ለመፍታት አቶ ስብሃት በግላቸው እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ክብር እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡

አቶ በረከት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ የተገደዱበት ምክንያትንም አስመልክቶ በዚሁ ጉባዔ ላይ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ አገሪቱ በግጭት ውስጥ ልትቆይ አይገባትም ብለው ችግሩ በፍጥነት እንዲቀረፍ ሲያደርጉ የነበረውን ጥረት አመራሩ ከመጤፍ አለመቁጠሩ፣ እንዳደከማቸውና ይህም የግላቸውን ውሳኔ እንዲወስኑ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል፡፡ በአቶ በረከት ግምገማ መሠረት አገሪቱ አሁን ላለችበት ግጭት ምክንያቱም መፍትሔውም አመራሩ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy