Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ችግሮች በጥልቅ ተሃድሶው እየተፈቱ ነው!

0 321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ችግሮች በጥልቅ ተሃድሶው እየተፈቱ ነው!

                                                      ደስታ ኃይሉ

መንግስት የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማጎልበት የጀመረው ጥልቅ ተሃድሶ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው። ጥልቅ ተሃድሶው በህዝብ የቀረቡትን እንደ መልካም አስተዳደር ዓይነት ዐብይ ችግሮችን በየደረጃው እየፈታ የህዝቡን ጥያቄዎች በመመለስ ላይ ይገኛል። በሂደቱም ህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆኑ ለውጤታማነቱ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል።

መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ችግሮችን እፈታለሁ ብሎ ለህዝቡ ቃል ከገባበበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተግባሮችን ፈጽሟል። መንግስት ዛሬም እንደ ትናንቱ ቃሉን የማያጥፍና ሁሌም የሚያካሂደው ተሃድሶ በውጤት እየታጀበ ነው።

ይህን ዕውነታም በሚገባ ተፈፃሚ ሆኗል። በዚህም የሁከትና የትርምስ ኃይሎቹ የሀገራችንን ዕድገት እንዲሁም ብልፅግና የማይሹ አንዳንድ የውጭና የውስጥ ኃይሎች እንጂ ከየትኛውም ብሔርና ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ያላቸው አለመሆናቸው ታውቋል።

ያም ሆኖ እነዚህ ሃይሎች ሙስናን ለመከላከልና የኪራይ ሰብሳቢነትን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመናድ የሀገርን ንብረት መዝብረው ለራሳቸው ጥቅም ያዋሉ ባለስልጣናትንና ግለሰቦችን ለመቆጣጠር የወሰደውን እርምጃ ለማኮላሸት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር እናስታውሳለን። በአሁኑ ወቅት ኪራይ ሰብሳቢዎቹ ቅርጻቸውን ቀይረው ዜጎችን በውንብድና ተግባር ወደ ማጋጨቱ ዞረዋል። መንግስትም ተገቢውን የእርምት እርምጃ ወስዷል፤ ወደፊትም ይወስዳል።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልፅ መሆን እንዳለበት፣ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ለህዝብ ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ህዝቡም በማንኛውም ተወካዩ ላይ አመኔታ ሲያጣ በማንኛውም ወቅት ከቦታው የማንሳት መብት እንዳለው ያስቀምጣል። መነሻው የህዝብ የስልጣን ሉዓላዊነት መከበር ነው።

ህዝቡ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ሿሚና ሻሪ የሚሆነው እርሱ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ስልጣን የሚመነጨው ከህዝብ እንጂ ከማንም አይደለም። ተሿሚው በህዝብ በጎ ፈቃድ ወንበሩ ላይ የሚቀመጥና የሚነሳ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ተሿሚው በራሱ ፈቃድ አይደለም ስልጣን ላይ የተቀመጠው። ጥሩ ሲሰራ ጥንካሬውን እንዲያጎለብት፣ ሲደክምም ድክመቱን የሚያሳየውና ከዚያ በላይም በገሃድ በምዝበራ ውስጥ ገብቶ ሲገኝ ካለበት ቦታ የሚያነሳው ህዝብ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ፈላጭና ቆራጩ ህዝብ እንጂ ባለስልጣን አይደለም። ሊሆንም አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ህዝቦች በከፈሉት መስዋዕትነት ባለፉት ስርዓቶች እንዲቀር ያደረጉት ነው።

እናም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ያላመነበትና ያልመከረበት ነገር አይከናወንም። ሰሞነኛው የፀረ ሙስናው ጉዳይ በጥልቅ ተሃድሶው ጅማሮ ወቅት መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚዋጋ የገባው ቃል አንዱ ክፍል ነው ማለት ይቻላል። ህዝቡም ቢሆን ይህ የመንግስትን ቃል በተግባር ተተርጉሞ ማየት ይፈልግ ነበር።

የኪራይ ሰብሳቢነትን የፖለቲካል ኢኮኖሚ በአንድ ጊዜ መናድ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነቱን እንዳይዝ ሁሌም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ኪራይ ሰብሳቢነት በገነነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ልማታዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ መንገድን መገንባት አይቻልም። ኪራይ ሰብሳቢነት ማነቆ ይሆናል። እናም ኪራይ ሰብሳቢነትን ሁሌም መድፈቅ ያስፈልጋል።

በተለይም እንደ እኛ ሀገር ልማት የህልውናው ጉዳይ በሆነ ሀገር ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢነት ልማታዊ አስተሳሰብን ካሸነፈ ችግሩ እጅግ የበረታ ይሆናል። ማንኛውም ዜጋ በሰራው ስራ ልክ ተጠቃሚ አይሆንም። የ“እከከኝ ልከክልህ” የትስስር ሰንሰለት ገቢራዊ እየሆነ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ሊኖር አይችልም። ይህም በግለሰብ ከፍ ሲልም በሀገር ላይ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። እናም የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር ከስር ከስሩ እየተከታተሉ ማምከን የግድ ይሆናል።

ታዲያ በዚህ ሂደት ውስጥ መንግስት አሰራሩን ይበልጥ ለህዝብ ግልፅ ማድረግ አለበት። ይህን ማድረግ ካልቻለ በህዝብ ዘንድ አመኔታን ያጣል። የትኛው ባለስልጣን በምን ዓይነት የሙስና ስራ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር እንደዋለ የመግለፅ ኃላፊነትም ይሁን ግዴታ አለበት። በዚህም ሳቢያ የስራ አፈፃፀሙን የህዝቡ እንደራሴዎች ለሆኑት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ወቅቶች እያቀረበ ይገኛል።

በእኔ እምነት መንግስት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የተሃድሶ ሂደት የመንግስት መዋቅሮችን የህዝቡን እርካታ በሚፈጥሩ መንገድ እየፈተሸ ነው። ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በነበሩ የተሃድሶ መንገዶች የተከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክርና ይበልጥ የሚያሰርፅ ነው።

ታዲያ አሁንም ቢሆን የህብረተሰቡ ሚና የማይተካ በመሆኑ ህዝቡ በጥልቅ ተሃድሶ ስራዎች ውስጥ እንደ ሁልጊዜው የበኩሉን ማበርከት አለበት። እርግጥ ማንኛውም ተሃድሶ ያለ ህዝቡ ድጋፍ ግቡን ሊመታ ስለማይችል በአሁኑ ወቅት ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል በቀጥታ በተሃድሶው ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም ህዝቡ ራሱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኖ ችግሩን ከመግለፅ ባለፈ የማይመጥነውንና የስነ ምግባር ጉድለት አለበት ብሎ የሚያምነውን የመንግስት ስራ ፈፃሚን እየገመገመ ተገቢው እርምጃ የመውሰድ ተግባራት እንዲከናወኑ እገዛ አድርጓል።

በማንኛውም ዴሞክራሲን የህልውና ጉዳይ አድርጎ በሚንቀሳቀስ ሀገር ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ቁልፍ ነው። ለነገሩ መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሠረት ነው። ስለሆነም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ መረባረብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም።

ታዲያ ይህን ዕውነታ በውል የተገነዘበው የኢትዮጵያ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስትም ሃሳቡን ወደ ድርጊት ለመለወጥ በጥረት የታገዙ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ከጀመረ 26 ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት በርካታ ተግባራቶች ዕውን ቢሆኑም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልተቻለም።

በተለይም በፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ አሰራር አልተፈጠረም። በመሆኑም ይህን የአገልጋይነት መንፈስ ለመፍጠርና በመንግስት ስልጣን ያለመገልገል አመለካከትን ፈር ለማስያዝ ለማስያዝ የተደረገው ጥረት አበረታች ነው። ይህም ስራው ወደፊት እየተጠናከረና የተፈጠሩትን ችግሮች በአስተማማኝ መንገድ ለመፍታት አሁንም ተግቶ መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን ያመላክታል።

ርግጥ የመልካም አስተዳደር ስራዎች ከህዝቡ ጋር በቅርበትና በቀጥታ የሚያገናኙ በመሆናቸውና የህዝቡ የእርካታ መለኪያዎችም ስለሆኑ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዩች ናቸው። ህዝቡ በሚሰጠው እርካታ ተገቢ ያልሆነና ህዝቡን ለምሬት የሚዳርግ ከሆነ ቅሬታ ከመፍጠሩም በላይ፤ የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነትን ያደበዝዛል።

መንግስት ለህዝቡ የሚሰጠው አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ እንዳይፈፀምና ህዝብ ከመልካም አስተዳደር ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርጋል። ይህ ደግሞ መንግስት የሚሰጠው የመልካም አስተዳደር አገልግሎት በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ ያደርጋል።

ተግባሮቹ የህዝቡን አመኔታ በመሸርሸር ለሁከትና ለብጥብጥ መዳረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም። በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ የሚኖር ህዝብ ደግሞ ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ሊያደርግ አይችልም። በመሆኑም መፍትሔው አሁንም ቢሆን ጥልቅ ተሃድሶውን አጠናክሮ መቀጠል በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊያበረክት ተግድ ይላል።

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy