Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሁንም አልረፈደም

0 854

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሁንም አልረፈደም

ኢብሳ ነመራ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሃከል ድንበርን ሰበብ አድርጎ ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት ተፅአኖ አሁንም አልለቀቀንም። አሁንም በአንዳንድ አካባበቢዎች በንጹሃን ላይ በሚሰነዘሩ ጥቃቶች የሰው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ሙሉ በሙሉ አልቆመም።  የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሞያሌ ባለፈው ሳምንት፣ በጉጂ፣ ቦረናና ባሌ ዞኖች እንዲሁም በሞያሌ ጥቃቶች መሰንዘራቸውንና የሀያ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን አስታውቀዋል አስታውቀዋል።

በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደቆየው በኢትዮጵያ ሱማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው ግጭት ድንበርን ሰበብ ያድርግ እንጂ ትክክለኛ ምክንያቱ ድንበር አይደለም። ግጭቱ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ህዝቦች መሃከል የተካሄደ አለመሆኑን በሁለቱም በኩል ያሉ ነዋሪዎች እየገለጹ ይገኛሉ። ሰሞኑን በነበረው ግጭት ቆስለው ሆስፒታል ገብተው የነበሩ ሰዎችም ይህን አረጋግጠዋል። አዋሳኝ ከሆኑ አካባቢዎች ራቅ ባሉ አካባቢዎችም ግጨቱ ማጋጠሙ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። ሁለቱ ተዋሳኝ ህዝቦች አንዱ ሌላው ላይ ሜንጫ ሰንዝረው፣ ጦር ወርውረው፣ ተመንጃ ተኩሰው እንዳልተጋጩ ከህዝቡ በላይ ዋቢ መጥቀስ አይቻልም።

በሁለቱ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው ግጭት ዋነኛ ምክንያት ህገወጥ የንግድ ስራ ነው። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ወደሃገር ውስጥ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች የሚገባበት ዋነኛው መስመር ነው። በህገወጥ መንገድ ከሃገሪቱ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪም በዚሁ ክልል የሚዘዋወር መሆኑ ይታወቃል። ግጭቱ ተቀስቅሶ የነበረ ሰሞን በተደረገ ክትትል በአንድ ሳምንት ያህል ጊዜ ውስጥ ብቻ 2 ሚሊየን ብር ገደማ የውጭ ምንዛሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ከምእራብና ከምስራቅ ሃረርጌ አካባቢ ተነስቶ ወደውጭ የሚላክ ጫት በዚሁ ክልል ውስጥ ነው የሚያልፈው። በቀን እስከ 1 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ የጫት የወጪ ንግድ በዚህ አካባቢ እንደሚከናወን መረጃዎች ያመለክታሉ።

እንግዲህ እነዚህ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ቀጣየነት እንዲኖራቸው የህግ የበላይነትን ማስከበር የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። እናም ግጭቱ ድንበርን ሰበብ ያድርግ እንጂ ዋነኛው ምክንያቱ የህግ የበላይነትን በማጥፋት ለህገወጥ ንግድ አመቺ የሆነ ሁኔታን መፍጠር፤ እንዲሁም በተለይ ከሃገር የሚወጣውን የጫት ንግድ በሞኖፖል መቆጣጠር ነው።

ያም ሆነ ይህ፤ በዚህ ምክንያት ከሞቱት እስካሁን ቁጥራቸው ያልተገለጸ ዜጎች በተጨማሪ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀለዋል። ኦሮሚያ ውስጥ ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ በመቶ ሺህ የሚቀጠሩ የክልሉ ተወላጆች በጭናክሰን፣ በሃረር፣ ድሬደዋ፣ ሻሸመኔ፣ አዲስ አበባ ወዘተ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። ለእነዚህ ተፈናቃዮች ከአልባሳት ጀምሮ የእለት ፍጆታ እየተደረገላቸው ይገኛል። የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስራ አመራር ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን ሰሞሙን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ነግረውናል። ተፈናቃይ ተማሪዎች ግን ትምህርታቸን መከታተል አልቻሉም።

ለእነዚህ ተፈናቃይ ህዝቡ እርዳታ እያደረገ ነው። በተለይ የኦሮሚያ ክልለ ህዝብ ከህጻናት ተማሪዎቸ አንስቶ በክልሉ ውስጥ እሰካሉ ባለሃብቶች፣ የክለሉ አርቲስቶች፣ በውጭ ሃገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ወዘተ እርዳታ በመስጠት እንደዜጋና ተወላጅ የሚያኮራ ተግባር እያከናወኑ ነው። ይህ ሁኔታ በክልሉ ከፖለቲካ ልዩነት በላይ ያለ የአንድነት መንፈስ ፈጥሯል። ይህ ለክልሉ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ለሃገሪቱ ሰላም የሚበጅ ከክፉ ሁኔታ እንደተገኘ መልካም አጋጣሚ ሊወሰድ የሚችል ነው። ያም ሆነ ይህ የተፈናቀዩቹ ዘላቂ  እጣ ፈንታ አሁንም አልለየለትም።

እነዚህ ዜጎች የተፈናቀሉት የህግ የበላይነትነ ማስከበር ባለመቻሉ ነው። አሁንም በእርግጠኝነት ተፈናቃዮቹን የፈቀዱት ቦታ የመኖር፣ የመስራትና ሃብት የማፍራት ወዘተ ህገመንግስታዊ መብታቸውን በማረጋገጥ ወደቀድሞ ኑሯቸው መመለስ የሚያስችል ሁኔታ ያለ አይመስልም። በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በወንጀል ከተጠረጡ 38 ግለሰቦች መሃከል 5 ያህል ብቻ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ፣ ይህም በፌደራል ፖሊስ የተከናወነ መሆኑ ክልሉ በጉዳዩ ላይ ያሳየው ቸልተኝነት ይህን ያመለክታል። አሁንም ያልቆመው የታጣቂዎች ጥቃትና በዚህ ምክንያት ህዳር 10 ሊካሄድ የነበረው የሁለቱ ክለሎች የሰላም ኮንፈረነስ መካሄድ አለመቻሉም ሌላው ማሳያ ነው።

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በሚገኘው የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩና አዲስ የተመደቡ የኦሮሞ ተማሪዎች ወደሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መዘዋወራቸው፣ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ተማሪዎች ከኦሮሚያ ክልል ውጭ ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲዘዋወሩ መደረጉ የተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት የመመለሱን ጉዳይ ጥያቄ ጥያቄ ላይ የሚጥል መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይህ ሁኔታ የፌደራል መንግስት የህግ የበላይነት የማስከበር አቅሙ ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ ያደረገ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል።

የኦሮሚያ ወይም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስታት ከሌላ ክልል የተፈናቀሉ ተወላጆቻቸውን ወደነበሩበት አካባቢ መልሶ ማቋቋም የሚያስችላቸው ህገመንግስታዊ መሰረተ የለም። ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት መመለስ ቢፈልጉ እንኳን የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንደማይፈጸምባቸው ዋስትና ያለው ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ ተፈናቃዮቹን ከአንዱ ክለለ ወደሌላው አጓጉዞ ማቋቋም የፌደራል መንግስት ሃላፊነት ነው። እስካሁን ይህን ዋስትና ያለው ሁኔታ መፍጠር ስላልተቻለ ተፈናቃዮቹ ወደመጡበት አካባቢ የመመለስ ድፍረት ያጡበት ሁኔታ ይታያል።

እርግጥ የክልሎቹ መንግስታት ከሌላ ክልል ተፈናቀለው የመጡ ተወላጆቻቸውን በክልላቸው ውስጥ ሰፈረው እንደአዲስ ኑሮ የሚጀምሩበትን ስራ ሊያከናውኑ ይችላሉ። በቅርቡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ደህነነታቸው ተረጋግጦ በፈቀዱት አካባቢ እንዲኖሩ ለማደረግ ጠንካራ ስራ እየተከናወነ የገኛል። በዚህ መሰረት ከመኖሪያና ከንብረታቸው የተፈናቀሎ ወገኖች በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ ይደረጋል ብለዋል።

ክልሉ ከዚህ ያለፈ ሊያደርገው የሚችለው ነገር ያለ አይመስለኝም። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሃብትና ንብረታቸውን ጥለው ባዶ እጃቸውን በመጠለያ ለሚኖሩ ወገኖች ቋሚ መኖሪያ ሰጥቶ የማቋቋም ስራ ግን ቀላል ስራ አይደለም። በቢሊየን የሚቆጠር ሃብትና ሰፊ መሬት፣ ሎጂስቲክስ የሚጠይቅ ነው። እስካሁን ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ከደቂቅ እሰከ ሊቅ ያሉ የኦሮሚያ ተወላጆች የእርዳታ ርብርብ እያደረጉ ነው። በቅርብ ጊዜ የሃገሪቱ ታሪክ የዚህ አይነት የእርዳታና የድጋፍ ርብርብ የተደረገው በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት እንዲሁም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብቻ ነው ብል አልተሳሳትኩም። እስካሁን ከ3 መቶ ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰባቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። ይህ የኦሮሞች አቅም የተፈናቀሉ ወገኖቻቸውን በክልላቸው እንዲቋቋሙ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊኖረው መቻሉ ባይካድም፣ ተፈናቃዮቹን የማቋቋም ስራው ግን ለክልሉ የሚከብደው መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በመሆኑም የህግ የበላይነትን በማረጋጋጥ ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት ሊመለሱ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ክፈተት የታየበት የፌደራል መንግስት ሁለቱም ክልሎች ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ይኖርበታል።

በእርስ በርስ ግጭቱ የተፈናቀሉትን ወገኖች ተወላጅ በሆኑባቸው ክልሎች በማቋቋም ችግሩን እንደምንም ማለፍ ቢቻልም፣ ችግሩ በዚህ መንገድ እልባት ማግኘቱ ግን በዘላቂ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ ጠባሳ ጥሎ ማለፉ አይቀሬ ነው። በመሆኑም የፌደራል መንግስት የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት የሚያድስ ስራ በመስራት የህግ የበላይነትን አረጋግጦ ተፈናቃዮቹ ኢትዮጵያውያን ወደነበሩበት ቦታ ተመልሰው በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ አሁንም አልረፈደም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy