Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አበረታቹ ድርድር

0 323

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አበረታቹ ድርድር

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

መንግስት ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ ቃል መግባቱን በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይትና ድርድር እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ እየተካሄደ ነው። በፖለቲካ ፓርቲዎቹ የእስካሁን ድርድር መግባባት፣ አንዱ የሌላኛውን ሃሳብ ማዳመጥ፣ የራሱንም ማቅረብና አለመግባባትን ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ በመፍታት በቀና ሁኔታ ተካሂዷል።

ለወራት በዘለቀው በዚህ ድርድር በርካታ መግባባቶች ላይ ተደርሷል። ሰሞኑን በሀገር አቀፍ የምርጫ ህግ ላይ ፓርቲዎቹ የደረሱበት ስምምነት የዚህ አባባሌ ማስረጃ ነው።  በእኔ እምነት፤ ከድርድሩ አጀንዳ ቀረፃ ጀምሮ አሁን እስከተደረሰበት እስከ ምርጫ ህጉ ድረስ ፓርቲዎቹ የተጓዙበት መንገድ የሚያስመሰግናቸው ነው። የሀገራችን የፖለቲካ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን ያህል እየጎለበተ እንደሄደም የሚያረጋግጥ ነው። አዲሲቷ ኢትዮጵያ በሰፊው የዴሞክራሲ መንገድ እየተራመደች መሆኑንም የሚያሳይ ተግባር ነው።

በሰጥቶ መቀበልና ሃሳቦችን በማክበር እየተካሄደ ያለውን አበረታች ድርድር፤ ከሰሞኑ በምርጫ ህጉ ላይ ፓርቲዎቹ አላስፈላጊ የሆኑ ጉዳዩችን በመሰረዝ፣ ጠቃሚ ናቸው ያሏቸውን ደግሞ በመጨመር እንዲሁም መሻሻል የሚገባቸውን በማሻሻልና መቀጠል አለባቸው ብለው በጋራ ድምዳሜ ላይ የደረሱባቸውን አንቀፆችን ባሉበት እንዲቀጥሉ በማድረግ ከደረሱበት ስምምነት አኳያ እንዲህ መመልከት እንችላለን።

በድርድሩ ላይ ገና ከመነሻው የ11 የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ አዋጅ ላይ 11 የሚሻሻሉ፣ አራት የሚሰረዙ እና ሁለት በአዲስ የሚካተቱ አንቀፆች ነበሯቸው። የፓርቲዎቹ አባላት የቀረቡት የድርድር ሃሳቦች፤ ፍትሃዊ፣ ነፃ ምርጫ ውጤት ስለማሳወቅ፣ ስለ የጋራ ምክር ቤት አመስራረትና አደረጃጃት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ስብስቡ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እስከ ዞን ድረስ እንዲቋቋም፣ የምርጫ ውጤት ከመቀበል ጋር ተያይዞ የጋራ ምክር ቤቱ መሳተፍ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ማሻሻያዎቹን አቅርቧል።

ስብስቡ እንዲሻሻሉ ካቀረባቸው የአዋጁ አንቀፆች በተጨማሪ የግል እጩ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ባለመሆናቸው ከጋራ ምክር ቤቱ በታዛቢነት መገኘት ቀጣይነት የሌለው በመሆኑ ስለማይመለከታቸው ከአዋጁ እንዲሰረዝ ሃሳብ ቀርቧል።

በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ “ኢራፓ” 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ በድርድሩ ያቀረቧቸው የማሻሻያ ነጥቦችን ጨምሮ በ8 ገጽ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ላይ መሻሻልና መሰረዝ ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዩች አቅርቧል። የምርጫ አዋጅ ስነ ምግባርና ጥሰት ላይ ስለሚወሰዱ ርምጃዎች፣ ቅድመና ድህረ ምርጫዎችን ያካተተ እንዲሆን የሚለውም ጉዳይ አንዱ ነው።

ከተደራዳሪዎቹ አንዱ የሆነው የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ እስክ ወረዳ ድረስ እንዲቋቋም የሚልና ሌሎች የማሻሻያ ሃሳቦችን አቅርቧል። በሌላም በኩል መኢብን በበኩሉ በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድር የተገለፁትን ጨምሮ በሌሎች ቀዳሚ አዋጆች የተገለፁ አንቀፆች ከአዋጁ ይስረዙ እንዲሰረዙ ሃሳብ አቅርቧል። ፓርቲው ከአዋጁ እንዲሻሻል፣ እንዲሰረዝና በአዲስ እንዲተኩ ያላቸው 13 የመደራደሪያ ነጥቦችን በማስቀመጥ ተደራድሯል።

በዚህ ሁሉም ሃሳቡን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሚገልፅበት መድረክ ላይ ገዥው ፓርቲ በተደራዳሪው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አማካኘነት የበኩሉን ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ኢህአዴግ በፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ላይ ከፓርቲዎቹ የቀረቡ የመደራደሪያ ነጥቦች ላይ በሰጠው አስተያየት፤ በተደራዳሪ ፓርቲዎች የተነሱ ማሻሻያዎች ብዙ ልዩነት የሌላቸው እንደሌላቸው በመግለፅ፤ የፍትሃዊና የነፃ ምርጫን ውጤትን መግለፅ የሚገባው የተወዳደረው አካል እንጂ፤ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ታዛቢ አለመሆኑን ገልጿል።  የሀገር ውስጥም ይሀን የውጭ ታዛቢ እንደ ስያሜው ተግባሩ መጫወት የሚገባው የታዛቢነት ሚና ብቻ መሆኑን አስረድቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢህአዴግ በዋናነት በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምርጫ አስፈፃሚዎች ተሳትፎ በሁለት ሶስተኛ ስምምነት ድምፅ ይወሰናል በሚል ከተቃዋሚዎች በኩል የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጿል። ኢህአዴግ በምክንያትነት ያቀረበው የአስፈፃሚዎች ተሳትፎ ዓለም አቀፍ አሰራርን የተከተለ እንደሆነም አመልክቷል። እናም ባለበት ሊቀጥል ይገባል ብሏል።

ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት እስከ ምርጫ ክልል ድረስ ቢዋቀር ለሁሉም ፓርቲዎች ጠቃሚው የጎላ ስለሚሆን በማሻሻያነት ቢካተት ኢህአዴግ እንደሚቀበለው ተገልጿል። እንዲሁም የጋራ ምክር ቤቱን በጀት አስመልክቶ በድርድሩ ወቅት በወጣው ህግ መሰረት መፈፀም እንደሚኖርበት ገዥው ፓርቲ አስታውቋል። ይህም በድርድሩ ወቅት የተነሱትን ሃሳቦች ገቢራዊ ለማድረግ የሚረዳ ነው።

የፓርቲዎች የጋራ ምክር የሚወክሉ በየፓርቲዎቹ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ያሉ ግለሰቦች በመሆናቸው ጉዳይም የጋራ ስምምነት የደረሱበት ጉዳይ ነው። እናም በዚህ ሃሳቦች በነፃነትና ዴሞክራሲዊ መንገድ በተገለፁበት መድረክ ላይ በአዋጅ ቁጥር 662/2002 የተደነገገውን የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ላይ የተለቀ ክርክርና ድርድር ተካሂዶ ሁሉም ፓርቲዎች ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ድርድር አካሂደውም ሰባት አንቀፆች እንዲሻሻሉ፣ ሁለት አዲስ አንቀፆች እንዲጨመሩና ሁለት አንቀፆች ደግሞ እንዲሰረዙ ተስማምተዋል።

ከዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር መገንዘብ የሚቻለው ድርድሩ በሰጥቶ መቀበልና የሁሉንም ፓርቲዎች ፍላጎት ማሟላት የቻለ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የሚያሰፋው፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ የሚያደርገው፣ ፓርቲዎች የሚወክሉት ህዝብ ድምፅ እንዲሰማ የሚያደርግ እንዲሁም ጅምሩ ዴሞክራሲያችን ስር እንዲሰድ የሚያደርግ ነው።

በእኔ እምነት ይህን መሰሉ ዴሞክራሲያዊ ድርድር መነሻው ህገ መንግስቱ ነው። እንደሚታወቀው በህገ መንግስቱ አንቀፅ 31 ላይ “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ የመደራጀት መብት አለው። ሆኖም አግባብ ያለውን ህግ በመጣስ ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ናቸው” የሚል ሃሳብ ተደንግጓል።

በዚህ ድንጋጌ መሰረት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ነው። ድንጋጌው ማንኛውም ዜጋ ባሻው ማህበር ወይም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ታቅፎ መንቀሳቀስ እንዲችል ያደረገ ነው። የቁጥሩ መጠን ይለያይ እንጂ ተቃዋሚዎችን የሚደግፋቸው የህብረተሰብ ክፍል መኒሩ አይካድም—እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ነባራዊ ሁኔታ ነው።

እናም ህጋዊ ተቃዋሚዎች የሚወክሉትን የህብረተሰብ ክፍለ የሚወክሉ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ በማናቸውም ሀገራዊ ጉዳዩች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ዴሞክራሲውን ማስፋት ይመስለኛል። ሰር በመስደድ ላይ የሚገኘውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይበልጥ በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ የሚያስችል ይመስለኛል። ሀገራዊ ዴሞክራሲው አቅም በፈቀደ መጠን እንዲሰፋ የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

እናም ለዴሞክራሲው መጎልበት ወሳኝ ሚና ካላቸው አካላት አንዱ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድር ውስጥ አልፈው የእኔ የሚሏቸውን አዋጆች እስከ ማሻሻል፣ ማካተትና መሰረዝ ድረስ እንዲዘልቁ ማድረግ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ሀገራችን ውስጥ ዴሞክራሲን የህልውና ጉዳይ ማድረጋቸውን የሚያረጋግጥ ክስተት ይመስለኛል። ድርድሩ አበረታች ከመሆኑም በላይ አናሳ ድምፆች (Minority Voices) ተደማጭ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy