የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ አራት ዓመት ከሰባት ወራት ሲታሰሩ የፍትሕ ፍንጭ ስላላሳያቸው ፈጣሪያቸውንም እንደሚጠራጠሩ ገልጸው፣ የተፋጠነ ውሳኔ ማግኘት እንጂ ፍትሐዊ ፍርድ እንደማይጠብቁ ተናገሩ፡፡
አቶ መላኩ ይህንን የተናገሩት ከአራት ዓመታት በፊት የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በመዝገብ ቁጥር 141356 የመሠረተባቸውን ክስ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት እንዲከላከሉ በሰጠው ውሳኔ መሠረት የተከሳሽነት የምስክርነት ቃላቸውን ሲያሰሙ ነው፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና ከእሳቸው ጋር በእስር ላይ የሚገኙትን አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስንና በአሁኑ ጊዜ የዋና ዳይሬክተሩ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው እየሠሩ የሚገኙትን አቶ ነብዩ ሳሙኤልን ጨምሮ፣ የቆጠሯቸውን የመከላከያ ምስክሮች ከማሰማታቸው በፊት የተከሳሽነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡
አቶ መላኩ እንደተናገሩት፣ ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ ያላቸው አቶ ገብረ ዋህድ በጻፉት ደብዳቤ ምክንያት በሚሌ ፍተሻ ጣቢያ ጭነት የያዙ ተሽከርካሪዎች ያለ ፍተሻ እየለፉ መሆኑን እያወቁ ዝም ብለው አልፈዋል፣ በዚህ ምክንያትም አስመጪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንና የጥቅም ትስስር ያላቸው ድርጅቶች በቅርንጫፍ የጉምሩክ ጽሕፈት ቤቶች አይስተናገዱም ሲባሉ በባለሙያዎች ላይ ተፅዕኖ ወይም ጫና እየፈጠሩ በኢንቮይስ እንዲስተናገዱ በማድረግ፣ በሕዝብና በመንግሥት ገቢ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጾ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን ክስ ከመረመረ በኋላ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ይህ የሆነው ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ መሆኑንና በዚህ ጊዜ ውስጥ አቶ መላኩ መጥቀማቸውን፣ መጠቀማቸውንና መንግሥት ገቢ እንዳያገኝ በማድረግ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ መጥቀሱንም አክለዋል፡፡
በሚሌ የፍተሻ ጣቢያ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ሳይፈተሹ የሚያልፉ አስመጪዎች ሲመረጡ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት መመርያን ባላከበረ መንገድ መሆኑ እየታወቀ፣ ዕርምጃ እንዳልወሰዱም በክሱ መገለጹን ተናግረዋል፡፡
ከላይ የጠቀሷቸውን ክሶች የሚከላከሉት አራት ነጥቦችን በማንሳት መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት አቶ መላኩ፣ ‹‹ተከላከል የተባልኩት በተከሰስኩበት ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ለማሰማት ጭብጥ ሲያሲዝ የእሳቸው የሥራ ድርሻ፣ ዕርምጃ ሊወስዱ የሚገባቸውና ዕርምጃ ያልወሰዱበት ምክንያት እንዳልነበረም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንድ ተከሳሽ የተከሰሰበትን ጉዳይ አውቆ ነው ተከላከል ሊባል የሚገባው፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ የተጣለባቸው ብይን ግን ከዚህ ያለፈና ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁዋል፡፡
ሌላው ለክሳቸው ግብዓት የሆነው አቶ እሸቱ ግረፍ (አራት ዓመታት ታስረውና ተፈርዶባቸው የተፈቱ ናቸው) የጻፏቸው ደብዳቤዎች መሆናቸውን የገለጹት አቶ መላኩ፣ ደብዳቤዎቹ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ቢሆኑም እሳቸው ዘንድ ያልደረሱ በመሆናቸው፣ በራሳቸው ምን ማለት እንደሆኑ ገላጭ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ደብዳቤዎቹ በወቅቱ ለኮሚቴ ወይም በዋና መሥሪያ ቤት ለሚመለከተው ዘርፍ የተጻፉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ተቋሙ በአደረጃጀቱ ግልጽ የሆነ ሥልጣንና ተግባሩን ያስቀመጠ መሆኑንና ሁሉም የየራሱ ድርሻ እንዳለውም አክለዋል፡፡
የዋናው ዳይሬክተር ሥልጣንና ተግባር በዋነኛነት ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች፣ በዕቅድና ክትትል ጉዳዮች፣ በሀብት አቅርብት፣ ከሦስተኛ ወገን ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶችና በለውጥ አመራር ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ በኦፕሬሽናል የቀን ተቀን ሥራዎች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን አቶ መላኩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ፍተሻ የቀን ተቀን ኦፕሬሽናል ሥራ መሆኑንና በአደረጃጀቱ በአግባቡ የተቀመጠ መሆኑን ጠቁመው፣ ሊመለከታቸው ቢችል እንኳን ችግር ነው ተብሎ ከማንኛውም ወገን የተገለጸና ወደ እሳቸው የመጣ ጉዳይ አለመሆኑን የተጻፉት ደብዳቤዎቹ እንደሚገልጹ አስረድተዋል፡፡ የተከሰሱት ለአንዳንዶቹ ውክልና ሰጥተሃል ተብለው ቢሆንም፣ ተለይተው ለተሰጡት ውክልናዎች በመመርያ፣ በደብዳቤና በሰርኩላር የተለዩ ስለሆነ ውክልና የመስጠት ሥልጣን እንዳላቸውም አክለዋል፡፡
አቶ መላኩ በሦስት የክስ መዝገቦች ክስ እንደተመሠረተባቸው አስታውሰው፣ በመዝገብ ቁጥር 141354 ላይ፣ ‹‹ውክልና ከሰጠህ መቆጣጠር የለብህም›› ተብለው መከሰሳቸውን፣ በ141352 መዝገብ ደግሞ፣ ‹‹የሰጠኸውን ውክልና በአግባቡ አልተቆጣጠርክም›› መባላቸውንና በ141356 መዝገብም በተመሳሳይ፣ ‹‹በሰጠኸው የሥራ ዝርዝር ላይ ዕርምጃ አልወሰድክም፤›› መባላቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ዕርምጃ መውሰድ እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ወደ እኔ የመጣ ጉዳይ አይደለም፡፡ ተከስሼም ተከላከል የተባልኩበትም ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በነበረ ወንጀል ላይ ዕርምጃ አልወሰድክም ብሎ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠበት ጉዳይ፣ ወንጀል በሌለበት መሆኑን አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከናወኑ ተግባራትን በትክክል ማስቀመጡንና የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችም በትክክል መመስከራቸውን አቶ መላኩ ገልጸው፣ የፍርድ ቤቱ ድምዳሜ ግን ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት ከገቢዎችና ጉምሩክ ተጨማሪ ሰነድ እንዲመጣ ትዕዛዝ ሲሰጥ ጊዜ ይፈጃል በማለት መቃወማቸውን አስታውሰው፣ ፍርድ ቤቱ በትዕዛዙ ፀንቶ ያስመጣው ሰነድ ‹‹ምንም ጉዳት አልደረሰም፣ መንግሥትና ሕዝብም ያጡት ነገር የለም፤›› በማለቱ ፍርድ ቤቱን ሊያመሰግኑ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በሒደቱ እሳቸውም ሆኑ ሌሎች ባልደረቦቻቸው የተጠቀሙት እንደሌለ ሰነዱ ማሳየቱን አክለዋል፡፡
ከአሠራር አንፃር የፍተሻ ማሽን ሲበላሽ በመረጣ ሥራ መሠራቱን በሚመለከት በተቀመጠው መሥፈርት አማካይነት መሥራቱ ትክክል መሆኑን አረጋግጠው፣ በመመርያ ቁጥር 58/2003 መሠረት በመረጣ የተስተናገዱት ዝቅተኛ የጉዳት ደረጃ ያላቸው የመንግሥትና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ መመርያው፣ ‹‹ዝቅተኛ የሥጋት ደረጃ ያላቸው አይፈተሹም›› ስለሚል፣ የመረጣ ኮሚቴውም የተመረጡለትን ጭነቶች መርጦ ካስቀመጠ በኋላ ፈታሾች የሠሩትን ሥራ፣ ማመሳከር ያለባቸውን ከናሙና ጋር በማመሳከርና በማገናዘብ ‹‹ሳይከፈት የታየ›› በማለት ለትራንዚት ቁጥጥር እንደሚያስቀምጥ አስረድተዋል፡፡ ዝርዝር ፍተሻ በመዳረሻ ጉምሩክ እንደሚካሄድም አስረድተዋል፡፡ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችም የተናገሩት ይህንኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም በብይኑ ይህንኑ ማስቀመጡን አክለዋል፡፡
የፍርድ ቤቱ ድምዳሜ ላይ ግን የጉምሩክ ወንጀል ውስብስብና ከሌሎች ወንጀሎች የተለየ በመሆኑ በመረጣ በሚስተናገድበት ወቅት፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት መጣሱን ገልጾ ተከላከል እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ተከላከል የተባሉት ወንጀል በሌለበት ጉዳይ መሆኑን ደጋግመው አስረድተዋል፡፡ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ተጥሷል ሲባል፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ማለት ምን ማለት እንደሆነና የትኛው የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት እንደተጣሰ ማወቅ የግድ እንደሆነ የተናገሩት አቶ መላኩ፣ እያንዳንዱን በመዘርዘርና አፈጻጸማቸውን በመተንተን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
የሚሌ ጉምሩክ ጽሕፈት ቤት ፍተሻ ጣቢያ ሚናና ድርሻ በመመርያ ቁጥር 16/2001 መሠረት ሚሌ የፍተሻ ጣቢያ በጂቡቲ ለሚደረግ የገቢና ወጪ ዕቃዎች ማስተላለፊያና መቆጣጠሪያ የፍተሻ ጣቢያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዝርዝር ሥራ የሚከናወንበት ጣቢያ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ሚና ምን ምን እንደሆነም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ በየቦታው ፍተሻ ይደረግ ቢባል የንግድ እንቅስቃሴውን መግታት መሆኑን ጠቁመው ኢንቨስትመንትንም እንደሚያዳክም ገልጸዋል፡፡ በየቦታው ፍተሻ ሳይሆን የትራንዚት ቁጥጥር እንደሚካሄድና የሚሌ ፍተሻ ጣቢያም ሚና ይኸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከትራንዚት አንፃር የተጣሰ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓትም እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
የመፈተሻ ሚና ምን እንደሆነ፣ በወቅቱ በሚሌ ብቻ የነበረው አንድ ማሽን እንደነበርና በቀን የመሥራት አቅሙ ከ80 እስከ 120 ተሽከርካሪዎችን ብቻ መሆኑን፣ በቀን ግን ከጂቡቲ ከ1,000 በላይ ተሽከርካሪዎች ስለሚመጡ በአማካይ ፈትሾ ለማሳለፍ ዘጠኝ ቀናት ይፈጅ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ መመርያ ቁጥር 58/2003 ከማሽን መጠቀም አንፃር የሚለውንም በዝርዝር ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ መመርያው በአንቀጽ 5 በማሽኑ ውስጥ የማያልፉ ሕይወት ያላቸው እንስሳትን የጫነ፣ ያልታሸገ ኮንቴይነር ዝቅተኛ የሥጋት ደረጃ ያላቸው መሆናቸውን ለይቶ ማስቀመጡን በመጠቆም ወንጀል እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ተቋማቸው በሪፎርም የሥጋት ሥራ አመራር የሚል ኮሚቴ ማቋቋሙንና ይህም በዓለም ደረጃ ንግድን የሚያቀላጥፍ መንገድ መሆኑን አስረድተው፣ ከ2001 ዓ.ም. በፊት የነበረውን ‘ጌት ኪፐር አፕሮች’ የተካ አሠራር መሆኑን በዝርዝር ገልጸዋል፡፡
በሁሉም ቦታ ቁጥጥርና ፍተሻ ላድርግ የሚል ‹‹የፊናንስ ፖሊስ›› እየተባለ ይጠራ የነበረንና ብዛቱም ከ176 በላይ የነበረን የኬላ አሠራር ያስቀረ መሆኑን አክለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም ልፈትሽ የምትለው አሜሪካ ብቻ መሆኗን ጠቁመው፣ እሷም ለንግድና ለልማት ብላ ሳይሆን ከመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ለደኅንነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የሥጋት ደረጃን ለመለየት 15 ነጥቦችን በማስቀመጥ መሥፈርት ወጥቶለት እየተሠራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹አስመጪው ማን ነው? ዕቃው ምንድነው? ትራንዚተሩ ማን ነው?›› የሚለውን በመለየት፣ አስመጪው መንግሥትና የመንግሥት ልማት ድርጅት ከሆነ ታክስ ስለማይከፍል የሥጋት ደረጃው ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ በአንደኛው ደብዳቤ የተጻፈው መንግሥት ባዘዘው መሠረት በወቅቱ ተከስቶ በነበረው የዘይትና የስኳር ችግር ሳቢያ በአፋጣኝ ለሕዝብ እንዲዳረስ መርጠው እንዲያልፉ መደረጉንና መመርያ ቁጥር 16/2001 እና መመርያ ቁጥር 58/2003 የተላለፈ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከወቅቱ የዘይትና የስኳር ችግር አንፃር በየመዳረሻው ሊቆም አይገባምም ነበር ብለዋል፡፡ ወደብ ላይም አንድ ቀንም ማደር እንዳልነበረበትም አክለዋል፡፡ የተሠራው ሥራ በወቅቱ ትልቅ የአገርን ዓላማ ያሳካ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ አስመጪውም መንግሥት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ ከጉምሩክ አንፃርም ዝቅተኛ የጉዳት ደረጃ የነበረው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ መሠራት የነበረበት መሠራቱን፣ የተጣሰ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት እንዳልነበረና ጉዳትም አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
ደብዳቤውም የውስጥ ደብዳቤ በመሆኑ እሳቸውም ጋር አለመድረሱን ጠቁመው፣ ማኔጅመንቱም በወቅቱ በአግባቡ የሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በደብዳቤዎቹ አማካይነት የተሰጠ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡
የተሠራው በሕግና በመመርያ መሆኑን፣ በብይኑም መገለጹን፣ እንዲያውም ጥቅም መገኘቱንና ገቢ ማደጉን ነገር ግን የደረሰ ጉዳት እንደሌለ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡ በ2002 ዓ.ም. የተቋሙ ገቢ ከተለያዩ ቅርንጫፎች (ሳይቀላቀሉ) እስከታሰሩበት 2005 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ከፍተኛ ዕድገት እንደነበረው ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ ባልተከሰሱበት ጉዳይ ተከላከል መባላቸውንና በወቅቱ በአደረጃጀቱና በተመደቡት ኃላፊዎች ላይ የአሠራር ችግር እንዳልነበር ገልጸው፣ ኃላፊዎቹ በወቅቱ ካስገኙት ውጤት አንፃር ‹‹ጎበዞች›› ሊባሉ እንደሚገባ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ወንጀል በሌለበትና በሕዝብም ሆነ በመንግሥት ላይ ጉዳት ባልደረሰበት ሁኔታ ተከላከል መባሉ ተገቢ ባይሆንም፣ የሚያቀርቡትን መከላከያ ፍርድ ቤቱ አይቶና ከማስረጃዎች ጋር አገናዝቦ የተፋጠነ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
‹‹እንግልቱና ድካሙ ስለበዛብኝና አቅሜም እየተሟጠጠ ስለመጣ፣ የተከበረውን ፍርድ ቤት የምጠይቀው የተፋጠነ ውሳኔ እንዲሰጠኝ ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡