Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግ ያለበት መንታ መንገድ እና የሀገራችን እጣ ፈንታ!

1 902

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

                                                                                      

ኢህአዴግ ያለበት መንታ መንገድ እና የሀገራችን እጣ ፈንታ!

ቀን 05/03/10

ኢትዮጵያችን ላለፉት ሶስት እና አራት አመታት ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው ኢህአዴግም በዚህ ባለንበት ሠዐት መንታ መንገድ ቆሞ የትኛውን መምረጥ እንዳለበት ግራ ተጋብቶ እያየነው ነው፡፡ ግንባሩ የሚመርጠው መንገድ የሀገራችንን እና የህዝባችንን መፃዒ እጣ ፈንታ የሚወስን ነው፡፡ ስለነዚህ መንታ መንገዶች ምንነት ከመግለፄ በፊት በቅድሚያ የተወሰኑ ነባራዊ ያልተደበላለቁ እውነታዎችን ለማንሳት እፈልጋለሁ፡፡

የህዝባችን መገለጫ

የሀገራችን ህዝብ እንድማንኛውም የአለማችን ጭቁን ህዝብ ኢፍታሓዊነትን ይጠላል፡፡ ጥላቻውንም በተግባር በመግለፅ እስከ አሁኗ ሰከንድ ድረስ ቀላል የማይባል እርምጃ ተጉዟል፡፡ ያብራኩ ክፋዮች በሆኑት ልጆቹ እየመሩ ኢትዮጵያ ሀገራችን ገነት ሆናለት መኖር አጥብቆ የሚመኝ እና ዛሬም ተስፋ ያልቆረጠ ህዝብ ነው፡፡ የትናንት ሀያልነቷን ለመመለስ ዛሬም እየተጋ ነው፣ ማን ካልን ህዝቡ፡፡ ነገር ግን በአብራኩ ክፋዮች ለህዝብ እና ለህዝብ ተቆርቋሪነት የመጓደል ሀልዮት ዛሬም በሚገባው መጠን ያልተካሰ ታጋሽ ህዝብ!!!

ታሪካችን ከአሁን ወደሗላ– ከሗላ ወደፊት

ሀገራችን ኢትዮጵያ የአራት ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች በመሰረቱት እና መጠሪያውንም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ኢህአዴግ) መመራት ከጀመረች እነሆ ሀያ ሰባተኛ አመቷን አስቆጥራለች፡፡ ፓርቲው የሚከተለውን ሪዕዮተ አለም ከግንባሩ መጠረያ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ይሀውም አንድም አብዮታዊ ሲሆን አንድም ዲሞክራሲያዊ የሚለው ነው፡፡ ግንባሩ በዚህ ሪዕዮተ አለም እመራለሁ ብሎ ሀገር ማስተዳደር በሚጀምርበት ወቅት ከራሱ ከፓርቲው ግለሰብ አባላት፣ ከሀገራችን ሙሁራን እንዲሁም ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀላል የማይባል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የተቃውሞው መነሻ የተለያየ የነበረ ቢሆንም ዋነኛው እና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ (በተለይ የምዕራቡ አለም ተቋማትና ግለሰቦች) ያነሱት የነበረው ጥርጣሬ ግንባሩ የሪዕዮተ አለሜ መሰሶዎች ናቸው ብሎ መጠሪያው ላይ ጭምር ያሰፈራቸው አብዮታዊነት እና ዴሞክራሲያዊነት ጥምረት ነበረ፡፡ እነዚህ አካላት አብዮታዊነት እና ዲሞክራሲያዊነት በተናጥል እንጂ በጋራ ሊሆኑ የማይችሉ ፍፁም በተቃራኒ የቆሙ ሪዕዮቶች ናቸው ብለው ተከራክረዋል፡፡ አብዮት ብሎ ዲሞክራሲያዊነት ሊኖር አይችልም ብለው በአለም ላይ የተደረጉ አብዮቶችን ከፈረንሳይ አብዮት ጀምረው እንደምሳሌ እያጣቀሱ ሞግተዋል፡፡ መሞገት ብቻ አይደለም የኢህአዴግን ሀሳብ ለማስቀየር ትልልቅ ሚድያዎቻቸውን ጨምሮ የተለያዩ ተቋሞቻቸውን በመጠቀም ተፅዕኖ ለማሳደር ሞክረዋል፡፡

ኢህአዴግ በበኩሉ የራሱን መከራከሪያዎች በማቅረብ ለማሳመን ጥረት አድርጓል፡፡ ይሀውም የምመራው ህዝብ በከፍተኛ የድህነት አረንቋ ውስጥ በመሆኑ ፈጥኜ ይህንን ህዝብ ከድህነት ማውጣት አለብኝ በመሆኑም  አብዮታዊ ባህሪ የግድ ያስፈልገኛል ያለ ሲሆን  የምመራው ሀገር የተለያየ ማንነት፣ቋንቋ፣እምነት እና እሴት ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ በመሆኑ ይህንን ብዝሃነት የሚያስተናግድ ሥርዐት መገንባት የምችለው በዲሞክራሲያዊነት ብቻ በመሆኑ ድሞክራስያዊነት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የግድ መላበስ ያለብኝ ባህሪ ነው ብሎ ተከራክሯል፡፡ ማን ነበረ ትክክል? ሰፊ ጥናት ለሚያደርጉ ምሁራንና ለአንባቢዎች ትቼዋለሁ፡፡ እዚህ ጋር ይህንን እናቁም እና ኢህአዴግ ሀገራችንን ማስተዳደር በጀመረበት ወቅት የነበረውን የህዝባችንን እና የሀገራችንን ናባራዊ ሁኔታ በወፍ በረር ለማየት እንሞክር፡፡

የሀገራችን ህዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የምመራበት ሪዕዮተ አለም አለኝ ብሎ ህዝቡን ማስተዳደር የጀመረው ከ1966 ዓ.ም ህዝባዊ አብዮት በሗላ ስልጣን የተቆጣጠረው ደርግ ነበረ፡፡ ደርጉ የሶሻሊስት ሪዕዮተ አለም መመሪያው እንደሆነ ለህዝቡ አውጆ እና ወደህዝቡ የማስረፅ ስራ ለመስራት ጊዜ አልፈጀበትም ነበረ፡፡ ነገር ግን ሪዕዮተ አለሙን በማቀንቀን አብዮቱን አስነስቶ የዘውድ አገዛዙን የጣለው የተማረው ክፍል ሳይሆን በሗላ ባጋጣሚ የመጣው የወታደሩ ክፍል ስልጣን በመቆናጠጡ ምክንያት የሪዕዮተ አለሙ መሰረታዊ እና በተነፃፃሪ ለመተግበር ቀለል ያሉ ትግበራዎችን ሳይፈፅም ሀገሪቱ ወደማያባራ የርስ በርስ ጦርነት የገባችው፡፡ በአጭሩ ሪዕዮተ አለሙ በደም ስራቸውና ጠንቅቀው የሚያውቁት ተገፍተው ያልገባቸው እንዲፈተፍቱ እና ሀገራችንን ወደለየለት ቀውስ እንዲያስገቡ ሆንዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ለማንሳት የፈለኩት ነጥብ ይህንን አይደለም፡፡ ለማንሳት የተፈለገው ነጥብ ህዝባችን በሪዕዮተ አለም ላይ ያለው አመለካከት ንቃት ምን ያህል ነው? የሚለው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ህዝብ እንደ ህዝብ ሊሳሳት አይችልም፡፡ ህዝብ ተሳስቶ አያውቅም ለወደፊትም አይሳሳትም፡፡ የሚሳሳተው እንመራሃለን ብሎ መንበረ ስልጣኑን የጨበጠው የስልጣን ባለቤት ነው፡፡ በመሆኑም ከደርግ በፊት ለብዙ ዘመን የሀገራችን አርሶ አደር እና ሀገራችን ኢትዮጵያ በገባሪ እና አስገባሪ አሰራር እንጂ ምንም አይነት ሪዕዮተ አለም አልነበረም፡፡ የነበረው ሪዕዮተ አለም በሰፊው በህዝባችን እና በገዥዎቹ ይታይ የነበረው በገባሪ እና በአስገባሪ እይታ ነበረ፡፡ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን መልካም ግንኙነት ተጠቅመው ሀገሪቱን በሪዕዮተ አለም የማስተዳደር ዕድል የነበራቸው የወቅቱ የሀገራችን መሪ  ቀዳማዊ ኃይለሥላሰሴ ከሳቸው አስቀድመው እንደነበሩት መሪዎች መጓዝ በመምረጣቸው አጨራረሳቸው እንዳያምር ሆንዋል፡፡ ሪዕዮተ አለሙን ትተን በመንግስት መዋቅር ሊኖር የሚገባ የስራ ክፍፍል በየዘርፉ ሚኒስትሮች መሾም የጀመሩት ዳግማዊ ዐፄ ሚኒሊክ ነበሩ፡፡ እንጂ ከዛ በፊት አንድን አካባቢ የሚያስተዳድር ባላባት ራሱ የግብርና ሃላፊ፣ ራሱ የፀጥታ ሃላፊ፣ ራሱ ዳኛ እና ወዘተ የነበረበት እውነታ ነው የነበረው፡፡ ሄዶ ሄዶ ንጉሠ ነገስቱን ጨምሮ፡፡

ደርግ ከ1966-1983

ስለዚህ ደርግ በገባው መጠን የሶሻሊዝም ሪዕዮተ አለምን በህዝቡ ውስጥ ለማስረፅ ማስተማር ሲጀምር የነበረው የህብረተሠብ ምን አይነት ነበረ የሚለው ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ መልሱም ባጭሩ አይደለም ሰብዓዊ መብቱ ይቅርና ማወቅ ያለበትን በገዥዎቹ መልካም ፍቃድ እያገኘ እንዲኖር እና እንዲገዛ ተፈርዶበት የኖረ ህዝብ ነበረ፡፡ ታዲያ ደርግ በገባው መጠን የሶሻሊዝም/ኮሚኒዝም ሪዕዮተ አለምን ህብረተሠቡን ማስተማር እና ማስረፅ ሲጀምር ህዝባችን ከኖረበት ዕሣቤ ፍፁም የተለየ ነገር በመሆኑ ለማስረፅ ከፍተኛ ልፋት እና ያላሰለሰ ጥረት ይጠበቅበት ነበር፡፡ ደርጉ ግን ሪዕዮተ አለሙ መጀመሪያም ቢሆን የራሱ ውጥን ያልነበረ በመሆኑ( አብዮቱን ያስነሱ ሙሁራን እና ተማሪዎች ነበረ) ከህዝቡ ቅራኔ ሲገጥመው ለማፈን በሚያደርገው ጥረት የህዝቡን ተቃውሞ አባብሶ ሀገሪቱን ወደለየለት የርስ በርስ ጦርነት ዳርጎ አልፏል፡፡ ባጠቃላይ ለደርጉ ባለስልጣናት ሶሻሊዝም ለህዝባችን መልካም ነው ብለው አስበው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ መልካም የሆነን ነገር ማወቅ እና መተግበር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ደርጎች መልካም ያሉት ሪዕዮት ለመተግበር በሚያደርጉት ጥረት የገጠማቸውን ተቃርኖ የሚቋቋም ወይም ደግሞ የዚህን ታላቅ የሀገራችን ህዝብ ለመምራት ብቃቱም ሆነ ዝግጁነቱ ስላልነበራቸው እጃቸውን በህዝብ ደም አጨማልቀው አልፈዋል፡፡ ህዝብን በማስተዳደር ሂደት መልካም መመኘት እና መልካም መተግበር እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ መልካም መመኘትህን ለህዝብህ የማሳመን እና የማሰለፍ ችሎታ ሲጎልህ እንዴት መልካም እያሰብኩለት አይረዳኝም ወደሚል ጥሬ ንዴት ገብተህ ወገንህን በአደባባይ መጨፍጨፍ ትጀምራለህ፡፡ መልካሙ ነገር ያለ ህዝብ ተሳትፎ ወደመሬት ማውረድ ስለማይቻል ህብረተሠቡን ማሳመን ምንም አማራጭ የለውም፡፡ የማንን ህይወት ለመቀየር ነው ህዝቡን ከጎንህ ሳታሰልፍ የምትዋትተው፡፡ ዕውቀት፣ብስለት እና የጠልቅ ህዝባዊነት ያልተካተተበት መሪነት መጨረሻው ልክ እንደደርግ ነው፡፡

ኢህአዴግ 1983 ጀምሮ

አጠቃላይ ቅኝት ከኢህአዴግ ሥርዓት ጋር በማዋሀድ

ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር በሚጀምርበት ወቅት ደርግ ከገጠመው ህብረተሠብ የሚለየው እንኳን ደርግ ኢህአዴግ ራሱ ዛሬም ድረስ ሊደመሰስ ያልቻለው የገባሪ እና አስገባሪ ፊውዳል አስተሳሰብ እና ያልጠራ እና ድብልቅልቁ የወጣው ደርግ ለማስረፅ የሞከረው ኮሚኒዝም ቀመስ የሆነና ሚናውን ያለየ ህብረተሰባዊ እሳቤ ነው፡፡ ዛሬ 2010 ዓ.ም ላይ  በአንድ ጎልማሳ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካዊ ንግግር ውስጥ ሶስት አይነት ነገሮችን በተለያየ አጋጣሚ ሲናገር መስማት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በሙስና የተቸገረ አንድ ዜጋ ስለሌብነት አምርሮ ሲናገር ትሰማውና አንድ ቤተሠቡ ወይም የቅርብ የሚለው ሰው የመንግስት ሹመት ሲያገኝ ሰርፆ አልነቀል ካለው የፊውዳል መንፈስ አጣቅሶ የድርሻውን እንዲወስድ መክሮ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ብሎ ያስረግጣል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሌላ ብሄር ወይም እምነት ተከታይ በመሆኔ መድልዖ ተደርጎብኝ የሚገባኝን አገልግሎት ሳላገኝ ቀረሁ ሲል ልትሰማው ትችላለኽ፡፡ ያው አንድ ግለሠብ፡፡

የሆነ ሆኖ ደርግ ሊያሰርፅ ከሞከረው አዲስ ሪዕዮተ አለም በተጨማሪ ኢህአዴግ የተረከበው ህዝብ በባሰ የድህነት አረንቋ፣ጭቆና እና ውርደት ውስጥ የተዘፈቀ ነበረ፡፡ መንበረ መንግሥቱን የጨበጠው ኢህአዴግ ደግሞ በምታምነው እመን፣ በቋንቋህ እደር፣  ራስህን አስተዳድር የሚል አዋጅ በማወጅ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሪዕዮቴን ጀምሬያለሁ ብሎ ከሽግግር መንግስቱ በሗላ በይፋ ስራውን ጀመረ፡፡ በነዚህም አመታት ልክ እንድደርግ ባይሆንም ስልጣን የሰጠው ህዝብ በበቂ ሁኔታ ሪዕዮተ አለሙን አስታትቋል ማለት አንችልም፡፡ አላማውን ለህዝቡ አስታጥቆ በማዝምትና ውጤት በማስመዝገብ ደረጃ እንደማይታማ ከመግለፅ ወደሗላ አልልም፡፡ ለምን ቢባል በተባበሩት መንግስታት እንኳ የሚሊኒየሙ አለማዊ እቅዶች ተብለው የተያዙ ነጥቦችን በማሳካት እውቅና ያገኘ ግንባር ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ታማምኖና አሳምኖ ህዝቡን ከጎኑ ማድረግ ባይችል ኖሮ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ከላይ በጠቀስነው ለሀገራችን መልካም ማሰብ እና በመተግበር መኻከል በሚኖረው ክፍተት ምክንያት ታስበው ያልተሞከሩ ውጥኖችን ሁላ ኢህአዴግ ለማሳካት ችሏል፡፡ እንደምሳሌ የአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማንሳት ይቻላል፡፡ እዚህ ጋር ስለመልካም እሣቤ እና ተግባር ልዩነት በግልፅ ማየት እንችላለን፡፡ ዐፄ ኃይለሥላሴም ሆነ ኮለኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም አባይ ላይ ግድብ የመገንባት እቅድ እና ፍላጎት አልነበራቸውም ማለት ታላቅ ታሪካዊ ክህደት ነው፡፡ ሁለቱም ሥርዓቶች ይህንን መልካም ህልም ለመፈፀም እቅድ ነበራቸው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት መልካም ነገር ለወገንህ ተመኝተህ ማቀድ እና ያንን እቅድ መተግበር እኩል ክብደት የላቸውም፡፡ ጥልቅ የሆነ ማሰብ እና ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም አለማዐቀፍዊ ሁነቶችን ወደግንዛቤ ያስገባ ፖለቲካዊ አመራር መስጠት ያስፈልግ ነበር፡፡ አልቻሉም እንጂ አልፈለጉም ማለት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን መፈለግ ሌላ መቻል ሌላ፡ ፡ ፡ ፡ ለማንኛውም ኢህአዴግ ስላሳካቸው መልካም ነገሮች እና ስለፈጠራቸው ድፍርሶች ማውራት አላማዬ እይደለም፡፡

 

የሆነው ሆኖ ኢህአዴግ በተነፃፃሪ ስላሳካው  አብዮታዊነት እና ዲሞክራሲያዊነት ለማወደስ እኔም እናንተም ጊዜ የለንም፡፡ ለዛ ቢበላ ቢበላ እንደቀጨጨ ወይም አልጠረቃ ያለው የመንግስት ሚዲያ በቂ ይመስለኛል፡፡ እውቀት እንዲገበይ እድል እያለው እውቀት የማይገባውን እንድዚህ ነው የማየው፡፡ የቀረፃ ስቲድዮ እንጂ አእምሮ ብቃትን መኮረጅ የማይችሉ የሚድያ ተቋማት ባለቤት ነው ግንባሩ፡፡ እዚህ ጋር ርዕስ ለቀሀል አትበሉኝ እና የኢህአዴግ ሚድያዎች የሰሩትን ለህዝቡ ከማስረዳት ይልቅ ከነሱ በተቃራኒ ቆመው የሀሰት ወሬ ያሶሩባቸውን ፕሮፓጋንዳ በመከላከል የተጠመዱ መሆናቸውን ሳላነሳ ማለፍ አልፈልግም፡፡

የዛሬው ሁኔታ

ኢህአዴግ ያለበት መንታ መንገድ እና የሀገራችን ዕጣ ፈንታ  

ወደፊት አራማጅ መንገድ ብለን መውሰድ የሚገባን የተሳኩ ነገሮችን ማወደስ ሳይሆን በላቀ ሁኔታ ማጎልበት፤ በተፈጠሩ ችግሮች መብሰልሰል ሳይሆን እየቀረፉ መሄድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ዋናው ነገር ሀገራችን  ቀውስ ውስጥ ናት፡፡ ያ ቀውስ በምን መጣ? ሀገሪቷስ ከዚህ ቀውስ እንዴት ትውጣ? ማንስ ነው የሚያወጣት? የሚሉት ጥያቄዎች በአግባቡ መነሳት ይኖርበታል፡፡

አሁን ሀገሪቱ ያለችበት ቀውስ በምን መጣ?

ኢህአዴግ የ1994ቱን የውስጥ ክፍፍሉን ተከትሎ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሪዕዮተ አለም የበላይነት በተረጋገጠበት ሁኔታ በህዝባዊና ዴሞክራሲያውያን የበላይነት ተጠናቋል በማለትና የተለያዩ ሴክተሮች የሚመሩበት ራሱን የቻለ መሪ ሰነድ (የግብርና ፖሊሲ፣ የእንደስትሪ ፖሊሲ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ሌሎች) አዘጋጅቼ ወደስራ ገብቼያለሁ በማለት ለሚያስተዳድረው ህዝብ አወጀ፡፡ ነገር ግን በነዚህ መሪ ሰነዶች የተባለው ለውጥ ህዝቡ ማጣጣም እና ማየት ሳይጀምር ቀጥሎ የመጣው ምርጫ 97 ግንባሩ ፈፅሞ ያልጠበቀው ኪሳራ አመጣበት፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ፡፡

የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ ሀገሪቷ ወደአለመረጋጋት ምህዋር እንድትገባ ሆነ፡፡ ተቋዋሚዎችም በተለይም ቅንጅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መቀመጫ እንደማይገባበት በማወጅ የተለያዩ የተቃውሞ አይነቶችን ህዝቡን መጥራት ጀመረ፡፡ በስተመጨረሻም  በርከት ያሉ ወገኖቻችንን ህይወት በመቅጠፍ እና በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እስር ምርጫው ያመጣው ማዕበል እንዲቆም ሆነ፡፡ እዚህ ጋር ከምርጫ 97 ጋር ተያይዞ አንድ የሚቆጨኝን ነገር ሳላነሳ ማለፍ አልፈልግም፡፡ ያገኙት ወንበር አንወስድም ያሉት ፓርቲዎች በተቃራኒው ቢያደርጉ ኖሮ ለሀገራችን የዲሞክራሲ እድገት ያደርጉት የነበረው አስተዋፅኦ ሳስበው ያንገበግበኛል፡፡ የሆነ ሆኖ ዋናው መነሻችን አሁን ያለንበት ቀውስ ነውና ኢህአዴግ ከምርጫ 97 በሗላ እስከአሁኑ ሀገራዊ አለመረጋጋት የመጣበትን መንገድ በወፍ በረር ለመቃኘት ነውና እዛ ላይ ለማተኮር እሞክራለሁ፡፡

ከምርጫ 97 ማግስት ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ሀገር ከማረጋጋት ባለፈ የህዝቡን ልብ ለመመለስ ከ97 በፊት ከነበረው ብዙ እጥፍ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ የዚህ ስራ መሪ የነበሩት ደግሞ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት 95 ዓ.ም ፀድቀው ወደ ትግበራ የገቡት መሪ ሰነዶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ስራዎች በዋነኝነት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነበረ፡፡ በተለይ ግንባሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የቀድሞውን የኢህአዲግ ሊቀ መንበር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሩ በስፋት እንዲሰራው የተደረገው ህብረተሠቡን በቀርብ የማወያየት ተግባር ከፍተኛ ፖለቲካዊ ድል አስመዝግቦበታል፡፡ ድሉን ያፈጠነው ደግሞ የፖለቲካ ስራውን ያጀበው በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መታየት የጀመረው የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ነበረ፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ስኬት ግንባሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ፖለቲካዊ ድል እንዲያስመዘገብ አድርጎት ምርጫ 2002 በተረጋጋ ሁኔታ በድል እንዲወጣ ረድቶታል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ለዛሬው ቀውስ ከፍተኛ የሚባለውን ስህተት የሰራው ከዚሁ ምርጫ 97 ማግስት ነበረ፡፡ ይሀውም በየደረጃው የአባላት ምልመላ ማድረግ ጀመረ፡፡ ጭራሽ ከ7 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት በይፋ ማወጅ ጀመረ፡፡ በወቅቱ ከሀገራችን ህዝብ ቁጥር ወደ አስር በመቶ የሚጠጋ ህዝብ አባሌ ነው እንደማለት ነበረ፡፡ ይሄ ደግሞ ላይ ላዩን ሲታይ ትልቅ ስኬት መስሎ ታይቶ ነበረ፡፡ ክፋቱ ገና ነው ወይም ደግሞ ፈረንጆቹ እንደሚሉት the worst yet to come በሚል ንግርት ብዙዎቻችን በትዝብት አልፈነዋል፡፡ ትዝብቱ የሚመነጨው ከሌላ ሳይሆን ከፓርቲ አባልነት መርህ፣ ስነምግባር እና ሂደት የሚመነጭ ነበረ፡፡

በመሠረቱ በብዛት አባላትን መመልመል በራሱ ችግር አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ጥያቄው ሊሆን ይገባ የነበረው አመላመሉ ምን አይነት ሂደትን የተከተለ ነው የሚለው ነው፡፡ ከአለም የፖለቲካ ታሪክ መረዳት እንደምንችለው የፓርቲ አባልነት እንዲሁ በቀላሉ ከጎዳና የሚገኝ ዳረጎት ሳይሆን በጥብቅ ስነ ምግባር እና መርህ የሚመራ መሆኑን ነው፡፡ ኢህአዴግም ከ97 ምርጫ በፊት ባለው ታሪኩ በዚህ አኪያሄድ ብዙም የሚታማ ግንባር አልነበረም፡፡ ከ97 ምርጫ በሗላ የህዝቡ ምላሽ በፈጠረበት መደነባበር ሊሆን ይችላል መርህን ባልተከተለ መልኩ ያደረገው የአባላት በገፍ ምልመላ ለብዙ የሀገራችን ሊሂቃን የራስን ምቹ ሜዳ ወይም comfort zone ከመፍጠር ባለፈ ዘላቂ ሀገራዊ ውጤት እንደማይኖረው የብዙዎች ግምት ነበረ፡፡ ይህ ምቹ ሜዳ የመፍጠር ሂደት ለጊዜው እንጂ የሚዘልቅ ጠቀሜታ እንደማይኖረው የብዙዎቹ የሀገራችን ሙሁራን ቢገነዘቡትም ኢህአዴግ ሊያምን ፍቃደኛ አልነበረም፡፡

አንድ ሪዕዮተ አለም አለኝ የሚል ፓርቲ ከየትኛውም የማስፈፀም ስራ በፊት የፖለቲካ ፕሮግራሙን በአባላቱ የደም ስር እንደሚከተሉት ሀይማኖት ሊያሰርፅ ይገባል፡፡ ለሪዕዮተ አለሙ አለሙ አምኖ ለመሞተ የተዘጋጀ እስኪሆን ድረስ አንድ ግለሠብ የዛ ፓርቲ አባል ሊሆን አይችልም፡፡ አይገባምም፡፡ አለበለዚያ መርህ እና አመክንዮ( Principle and logic ) ተጥሰው ላልተገባ አላማ ውለዋል ማለት ነው፡፡ በኢህአዴግ ሁኔታ ደግሞ ምርጫ 97 የፈጠረበት መወናበድ ለዚህ መርህ እና አመክንዮ መጣስ ዳርጎታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግ እንዳደረገው ከላይ በተጠቀሱት የአባልነት መስፈርት በሁለት እና በሦስት አመታት ውስጥ አባላትን መሰብሰብ የማይቻል እና ተደርጎ የማያውቅ ነው፡፡ ግንባሩም ለዚህ ታሪካዊ ስህተቱ የሚገባውን ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡ ለዚህም ምስክራችን ባለንበት ወቅት ከፓርቲው ሪዕዮተ አለም ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ መግለጫዎች ሲሰጡ የሚዉሉ ከፍተኛ የፓርቲው እና የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በቂ ምስክራችን ናቸው፡፡ በተለይ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሪዕዮተ አለም ለምናውቅ ሰዎች፡፡ ማንኛውም ዜጋ የፈለገውን ሪዕዮት የማራመድ መብት አለው፡፡ ነገር ግን አባልነቱ ሌላ ሪዕዮቱ ሌላ ሲሆን የዛን ፓርቲ የንቅዘት ደረጃ የሚያሳይ ይሆናል፡፡ አባል የሆነበትን እንጂ የሪዕዮተ አለሙን ባለቤት ፓርቲ ንቅዘት እንደማያሳይ ሳንዘነጋ፡፡

ጭቁኑ የሀገራችን ህዝብ እና ኢህአዴግ ከዚህ የእውር ድንብር የአባላት ምልመላ ምን ተረፈው ብለን መጠየቅ ወደዛሬው የቀውስ ምንጭ በቀላሉ ይመራናል፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት በተቀመጠው የፓርቲ አባልነት የስነ ምግባር ደረጃ የአባላት ምልመላ ሳያደርግ ኢህአዴግ የአባላት መጠኑን 7 ሚሊዮን እንደደረሠ ሲገልፅልን ለራሱ የደገሰውን አሜኬላ ገብቶት አልነበረም፡፡ ከነበረው የእድሜ ደረጃ በሚጠበቀው መጠን የመለመላቸውን አባላት ለሪዕዮተ አለሙ ታማኝ እና ነብሳቸውን የሚሰዉ የማድረግ ልምድ እና መዋቅራዊ ብቃት ነበረው ለሚለው ጥያቄ መልሱ አልነበረውም የሚል ነው፡፡  የኢህአዴግ ቀደምት መስራቾች ህውሃት እና ኢህድን    ( ኢህድን በሗላ ኦህዴድን እና ድኢህዴን የመሰረቱ ነባር ታጋዮችን በመለየት ብአዴን ሖኗል) ከ5 መቶ ሺ አባላት በላይ አስተዳድረው የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በአባልነት አይያዙት  እንጂ ህዝቡን ከጎናቸው አሰልፈው እንደነበረ ግን መካድ አይቻልም፡፡ በአባል ምልመላ ግን ያልተገባ ሂደት ከ97 ምርጫ በሗላ ይቅር የሚባል ስህተት ኢህአዴግ እንደሰራ ማመን አለብን፡፡ የቀደመ ታሪኩን መርሳት ያስከፈለው ዋጋ ነው፡፡ ካላመነ 7 ሚሊዮን አባል፣ 20 አባልን የፖለቲካ ትምህርት አስተምረህ እና አንፀህ ማሰለፍ ራሱ ለምን ያህል ድል እንደሚያበቃ ስለአለም የፖለቲካ ታሪክ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ከግንባሩ መስራቾች መኸከል ህውሃት በዚህ የምልመላ ሂደት ተካፋይ እንደመሆኑ ምስረታው በ5 ያመኑ አባላት መጀመሩን መረሳቱ ራሱ አስገራሚ ነበረ፡፡

ኢህአዴግም ያንን ያህል አባል መለመልኩ ብሎ ሲያበቃ እንኳን ሪዕዮተ አለሙን ሊያሳምናቸው ይቅርና መረጃቸው በተሟላ መልኩ ማጠናቀር የሚችልበት ደረጃ አልነበረም፡፡ የይጠጌ አይነኬ አመራሮቹ እንኳን የአባሎቻቸውን ሁኔታ ሊከታተሉት ይቅርና ሪዕዮተ አለሙ ላይ ያላቸው የራስ ቁርጠኝነት በተለይ በዚህ ወቅት ለሰፊው የሀገራችን ህዝብ ግልፅ ሆንዋል፡፡

የዚህ የአባላት ምልመላ ለዛሬው ቀውስ ያደረገው አስተዋፅዖ ምንድነው?

እንግዲህ አባሉን በዚህ መልኩ ያጋበሰው ኢህአዴግ በሂደት መንግስታዊ መዋቅሩን በዚህ መልኩ ለተፈበረኩ አባላቱ በብዛት ለማስረከብ በቃ፡፡ እንኳን እንደዚህ ለበዙ አባላቱ ሪዕዮተ አለም በብቃት ሊያስታጥቅ ይቅርና መላው አባላቱ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑበት ደረጃ ላይ መድረስ የጀመረው ከ2002 ምርጫ ማግስት ነበረ፡፡ በትንሹ እንኳ ወርሃዊ የአባልነት ክፍያ በጥብቅ ዲሲፕሊን ማስፈፀም የማይችልበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡

በእንደዚህ አኳሃን የመጡ አባላቱ ናችው እንግዲህ ከቀበሌ እስከ ፌደራል መንግስቱ ያሉ መዋቅራት ውስጥ በሂደት አብላጫ እየወሰዱ የመጡት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ይሄ አካሄድ እንደማያዋጣ የተረዱ እውነተኛ የሪዕዮተ አለሙ ታማኞች አባልነታቸውን እየተዉ ፓርቲውን በብዛት መልቀቅና ከፖለቲካው መራቅ ጀመሩ፡፡ በፅናት እንታገላለን ያሉት ደግሞ በፍጥነት ስልጣን በስልጣን ላይ እየደረቡ የመጡት እነዚህ ሰርጎ ገቦች የተለያየ ምክንያት እየተፈለገ በስፋት እንዲመነጠሩ ተደረገ፡፡ አስቀድሞ ይጠበቅ እንደነበረው ሪዕዮተ አለምህን አስቀድመህ ያላስታጠከው አባል ሪዕዮተ አለምህን ሊያስፈፅምልህ አይችልም፡፡ ኢህአዴግ በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሁ ብዙ ፖሊሲዎች ማውረድ ቢጀምርም የሚያስመስል እንጂ የሚፈፅምለት አባል በስፋት ሊባል በሚችል ደረጃ ማግኘት ተሳነው፡፡ ጭራሽ በግንባሩ ታሪክ ባልተለመደ መልኩ የፓርቲው መርህ የሆነውን ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እየተጣሰ ሁሉም በየፊናው በስሜት ወደመነዳት ሁኔታ የተገባበትን እውነታ መመልከት ከጀመርን ውለን ማደር ጀምረናል፡፡

ይሄኔ ነው እንግዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኩ ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል እያየ የነበረው ህዝባችን ወደምሬት እና የለየለት ጭቆና ውስጥ መግባት የጀመረው፡፡ ተወደደም ተጠላም ከምርጫ 97 በሗላ ኢህአዴግ ህዝቡ በግልፅ የተመለከተው የተለያየ ኢኮኖሚያዊ ድሎች ማስመዝገብ ችሎ ነበር (ግንባሩ እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ድሎች መመዝገብ የጀመሩት ከ95 አመተ ምህረት ከፓርቲው ተሐድሶ በሗላ ነው ይላል) ፡፡ እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች በስፋት ሀብት መፍጠር ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ይህ ሀብት ፈጠራ በመጀመሪያዎቹ አመታት እየሄደበት የነበረው ፍጥነት እንዲቀዘቅዝ እና ጠፍቷል የሚባልበት ደረጃ ላይ ያደረሱ ሁኔታዎች ተፈጠሩ፡፡

የስራ ዕድል እና የሀብት ፈጠራ ሲቆም ደግሞ ሀገር በሰላም ውላ ታድራለች ማለት አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ አርቆ ማየት አቃተው እንጂ ከ97 ዓ.ም በሗላ የፈጠረው የስራ ዕድል በምርጫው ወቅት በስራ አጥነት እና በመልካም አስተዳደር ምሬት ብጥብጡ ውስጥ ሲሳተፍ የነበረ እና ሳይሳተፍም የሀሳቡ ደገፊ እንዲሁም ኢህአዴግን ምንም ጠብ ሳያረግለት ግን ይደግፈው ለነበረው ወጣት ነው፡፡ በአለም ላይ ህይወት እስከቀጠለ ድረስ ሁልጊዜ ወጣት ይፈጠራል፡፡ የሀገራችን እውነታ ከዚህ የማይሻር ህግ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ ከ97 በሗላ በአስር አመት ውስጥ ሊገጥምህ የሚችለውን የወጣት ሀይል ማሰብ እና ለዚህም በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተህ መጠበቅ እንደ ኢህአዴግ ላለ ራሱን በተራማጅነት ለሚቆጥር ፓርቲ ነጋሪ የማያሻው የሞት ሸረት ሃላፊነት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ ይቅርና በሌቦች(ይህንን ሌቦች የሚል ቃል የምጠቀመው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የሚጠቀምበት ክራይ ሰብሳቢ የሚል ቃል እጅግ ለዘብተኛና ያለንበት ሁኔታ ይገልፃል ብዬ ስለማላምን ነው፡፡ ካሁን በሗላም ይህንን ሌቦች የሚል ቃል መጠቀሜን እቀጥላለሁ) የተጥለቀለቀውን መዋቅሩን በቁርጠኝነት ለማፅዳት ዳተኛ የሆነ ፓርቲ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ የሀገሪቷ አለመረጋጋት ከተነሳ ጀምሮ በዋነኝነት ተሳታፊ የሆኑት ባብዛኛው በአስራዎቹ መጨረሻ እና በሀያዎቹ መጀመሪያ ላይ ያሉ ወጣቶች ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በ97 ዓ.ም ገና ህፃናት የሚባሉ እና ገና ነገር አለሙን ያለዩ ታዳጊዎች ነበሩ፡፡

ኢህአዲግ መራሹ መንግስት ለትምህርት በሰጠው ትኩረት አና ከአለም ነባራዊ ሀሊዮት በፈጣን ሁኔታ መለዋወጥ በተለይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋት ምክንያት አሁን በሀገራችን የሚኖሩት ወጣቶች በብዙ መልኩ ከ10 አመት በፊት ከነበሩት ወጣቶች በአመለካከትም ሆነ በፍላጎት እጅግ የተለዩ እንደሚሆኑ አስቀድሞ በሳይንሳዊ መንገድ መተንተን እና መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደገለፅኩት ከምርጫ 97 በሗላ የተጀመረው የጅምላ የአባላት ምልመላ በአግባቡ እንኳ ሪዕዮተ አለሙን ሳየሰርፅ እከተለዋለሁ ከሚለው ለሰፊው ህዝብ የወገነ ሪዕዮተ ዐለም በተፃራሪ ህዝቡን በስፋት የሚበድሉ የስልጣን ባለቤቶች እንደአሸን መፈልፈል ጀመረ፡፡ የታቀደው የልማታዊ ፐብሊክ ሰርቫንት ወደሌባዊ ፐብሊክ ሰርቫንት ቀላል በማይባል ደረጃ ተዋጠ፡፡

ለአርሶ አደሩ አንደኛ ጠበቃ ነኝ የሚል ግንባር አርሶ አደሩን በስፋት እያፈናቀለ ተገቢውን የማቋቋምና የካሣ ሁኔታ በአግባቡ ሳይፈፅም አርሶ አደሩን በገዛ መሬቱ ባልሀብቱ በገነባው የሆነ ነገር ( መጋዘን፣ ፋብሪካ ወይም ታጥሮ የተቀመጠ) ላይ ዘበኛ ሲደረግ በዝምታ መመልከት ጀመረ፡፡

የነገዱ ሳይሆን በመንግሥት ስልጣን የከበሩ ሌቦችን በአካባቢው የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ የህግ ያለህ ቢልም ምንም እርምጃ እንደማይኖር በማወቁ ቀላል የማይባል ህብረተሠብ ብቸኛ የመክበሪያ መንገድ ወይ የመንግስት ስልጣን መያዝ ወይ ከመንግስት ባለስልጣን መጠጋት ወደሚል እሳቤ እንዲገባ የመንግስት አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የዕሣቤ መንቅዝ ነበረ፡፡ ለዚህም ሙሉ ሀላፊነቱን ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት መውሰድ አለበት፡፡

የኮንትሮባንድ እና የጥቁር ገብያ ንግድ በስፋት የመንግስት መዋቅር በመጠቀም ጭምር ይከናወኑ ጀመር፡፡

ሀገሪቷ እየፈጠረች በመጣችው ሀብት ምክንያት በራስ አቅም የተወጠኑ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የታለመላቸው ግብ ሩቡን እንኳ ሳይመቱ ፕሮጀክቱ የተመደበለት የሀገሪቱ እና የህዝቡ ሀብት እንደጉም ተኖ ሲጠፋ ሀላፊነቱን ወስዶ የሚጠየቅ አለመኖሩ እና መቀጣጫ አለመሆኑ ብዙ ፕሮጀክቶች ተመሳሳይ ጎዳና እንዲከተሉ አድርጓል፡፡ በዚህ ወቅት ያልተጓተተ የመንግስት ፋብሪካ፣ መንገድ እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በጀታቸው ባክኖ እንኳ የሚጠይቅ አካል የለም፡፡ የዚህ ምንጭ ደግሞ በስፋት የመበስበስ ውጤት ነው፡፡ አንድ የህዝብ ፕሮጀክትን የሚመራ ዜጋ በሱም ሆነ በሌላ ምክንያት የተሰጠውን ህዝባዊ አደራ መወጣት ካልቻለ ሌላው ቢቀር በራሱ ሀላፊነቱን የማስረከብ ባህል ሊኖር ይግባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መስመር ይልቅ የሌቦች ፍላጎት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት በማሳየቱ ይህ ህዝባዊ መስመር የበላይነት ተወስዶበት መላዎስ አቅቶት በመፈራገጥ እንዲወሰን ተደርጓል፡፡ ለምን ቢባል በ97 ምርጫ ቤተ ክርስቲያን ሂዶ የኢህአዴግን መውረድ እንዲያይ ሥዕለት ገብቶ የነበረን ግለሠብ ባግባቡ ሪዕዮተ አለሙን ሳያስታጥቅ እና ሳያሳምን የኢህአዴግ አባል ከሆነ በሗላ በስልጣን ላይ ስልጣን እየደረበ ምን ያህል የተግማማ እና የሌባ ኔትወርክ የዘረጋን ግለሠብ እንደማውቅ እኔ ጥሩ ምስክር ነኝ፡፡

ይህን ስል ለዛሬው የመግማማትና የሌቦች ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማገንገን ሊጠየቅ የሚችለው ከ97 ዓ.ም በሗላ ግንባሩን በስፋት የተቀላቀለው አርትዖት ያልተደረገለት የሰፋ የአባላት ምልመላ ብቻ አይደለም፡፡

ከዛ በፊት በሽግግር መንግስቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ የሰፋ ሀብት ባልተፈጠረበት ሁኔታ በሰሩት ሌብነት መቀጣታቸው የሚረሳ ታሪክ አይደለም፡፡ ቀጣይ ያልሆነበት ሁኔታ ግን የአቶ ታምራት ላይኔን የስኳር ታሪክ በህዝባችን እንዳይረሳ ሆኖ አልፏል፡፡ ከዛ በሗላ ግን ኢህአዴግ ሀብት በሀገሪቱ መፍጠር ከቻለ በሗላ እንኳ የመዘበሩትን ቱባ ባለስልጣናቱን ግል ሂሥ አድርጎ ታርሟል በሚል ትንኝ ወሮት የበሽታ ምንጭ እንደሆነ ኩሬ ፀረ ተባይ ተረጭቷል በሚል ተራ ምክንያት ለሰሩት ስህተት ህዝባዊና የማያዳግም ዕርምጃ ሳይወሰድ ባሉበት የስልጣን እርከን እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም እንዲሉ፤ ኢህአዴግ አባላት ያለምንም አስተማማኝ ወንፊት መመልመል ሲጀምር ለነዚህ ቂም ለቋጠሩ እና ግለ ሂሳቸውን አጎንብሶ ለማለፍ ለተጠቀሙበት አባላት ለህዝቡ ሳይሆን ለራሳቸው በስፋት የሚጠቀሙበት መረብ ለመዘርጋት ችለዋል፡፡ ይህን ስል ከነዚህ መስራች አባላት በሗላ የበሰበሰ መስራች አባል የለም ማለት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ኢህአዴግም ከህዝብ፣ ህዝብ መሽተት ወደሌቦች እና ወደግማት ምንጭ የተቀየረው ወደማይነኩ የማይጠጓቸው የመንግስት  ከፍተኛ ባለስልጣናት የጡት አባትነት ከዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ወደ ሌባ ከፍተኛ ባለስልጣን ማዕከላዊነት የዕዝ ሰንሰለት ወደመሸጋገር መጣ፡፡ ሊያውም በነዚህ ሌቦች እቅድ ያለመርህ ተመልምለውና የመንግሥትን መዋቅር በተቆጣጠሩት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት፡፡

የሀገራችን ህዝብ አንድ የሚያውቀው እውነታን ልንገራችሁ፡፡ ጀግንነትም ሆነ መፍራት የአንድ ህዝብ መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ህዝብ ለመልካም ይመራል እንጂ ለሌብነት ሊመራ አይቻልም፡፡ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ይህን የመሰለ ፖለቲካዊ ምዕራፍ አጓጉቶ አያውቅም፡፡

አህአዴግን በመሰረቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ውስጥ በሌባውና በዲሞክራሲ ሀይሎች መሀከል የሞት ሽረት ትግሉ ውስጥ ተገብቷል፡፡ ለሀገራችን ህዝብ በሚገባው ቋንቋ አይገለፅለት እንጂ  የኢህአዴግ የውስጥ ትግል ከህዝባዊነት እና ከፀረ ህዝባዊነት የሚመነጭ ነው፡፡ በመግቢያዬ ላይ እንደገለፅኩት ኢህአዴግ በ4 የሀገራችን ክልሎች የተመሰረቱ ፓርቲዎች የመሰረቱት ግንባር ነው፡፡ በዚህም ያለብሄር ልዩነት አብዮታዊ ዲሞክሪያሲ ሀይሎች እንደሌቦቹ ባይሆን እንኳ አሁንም ህዝባዊ ተቆርቋሪነታቸውን በፅናት ይዘው የሌቦችን ግብዐተ መሬት ለማረጋገጥ እና ዛሬ የአርሶ አደሩን ነገ በሚኖረው የኢንደስትሪ ሽግግር የላብ አደሩን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ እየተጉ ነው፡፡ ግን አንሰዋል፡፡ በሌባው ተበልጠዋል፡፡ ለህዝቡ ተቆርቋሪነት በሌብነት ተበልጧል፡፡ የሌቦች እና የሰርጎ ገቦች ፖለቲካል ኢኮኖሚ(ለጊዜውም ቢሆን የበላይነቱን ያረጋገጠበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡) ህዝባችንም መሮታል፡፡ ሪዕዮተ አለም ሳይነቅዝ የማያውቁት ግለሠቦች በተዘበራረቀ የሪዕዮተ አለም ዝቅተት ውስጥ ሲዋልሉ እንድማየት በሺ አመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተስፋ የተጣለበት ግንባር ላይ እንደማየት የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡

ሌቦቹም አልተኙም አልያም አይነኬ ሆኑ፡፡ ሌብነቱ የተረጋገጠበት ሀይል ከነባር እስከጥርቃሚ(በገፍ ሂደቱን ሳይከተል የገባውና መዋቅሩን በስፋት የተቆጣጠረው ምልምልን ጨምሮ) የበላይነቱን አረጋግጦ ይገኛል፡፡ እንደሚባለው ሌቦች በየትኛውም የህዝብ ዋጋ ራሳቸውንና ከነሱ ጋር ያለውን የመከላከል ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነሱን ከሚነካ በስተቀር ጥቅማቸውን ለማስከበር የትኛውንም መስዋዕትነት እንዲከፈል ያደርጋሉ፡፡ ደህነታቸውን ለማስጠበቅ የትኛውንም አስቀድሞ የተቋቋመ የመንግስት ቢሮክራሲ እንደየአስፈላጊነቱ እና እንደሚያገኙት ጥቅም ይጠቀሙበታል፡፡ ሌቦች በየትኛውም ዋጋ እንዳይነኩ እንጂ ህዝባዊነት የሚባል ነገር ከነንድፈ ሀሣቡ የማያውቁት የጭቁኖች ሪዕዮት ነው፡፡ ድል ለሠፊው ህዝብ ሞት ለሌቦች፡ ሳልል ማለፍ አልፈልግም

የአርሶ አደሩ ዘላለማዊ ዘቦች ነን ብለው በንፅህና የሚኖሩት ደግሞ በሚከፍሉት አብዮታዊ ዋጋ የሚታገለውን የበሰበሰ እሳቤ እና ድርጊትን  እንጂ ህዝቡ እንዳይነካ ወይም እንዳይጎዳ ይተጋል፡፡ ህዝብ ምንግዜም ከህዝባዊነት ጋር እንጂ ከግለሠባዊ ጥቅም ጋር ጉዳት እንዲደርስበት ፈፅሞ አይፈቅዱም፡፡ ስለዚህ በሀገራችን በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ በህዝባዊነት እና በፀረ ህዝብነት ከፍተኛ የትግል ሁኔታ ውስጥ ተገብቷል፡፡ የአርሶ አደሩና ላብአደሩ አሸናፊነት የሰፊውን ህዝብ ድል ያረጋግጣል፡፡

አሁንም ሞት ለሌቦች እና ያላግባብ ለከበሩ ነቀዞች  

ቀውሱ በምን መጣ የሚለውን ከመለስን ዘንዳ ሀገሪቷስ ከዚህ ቀውስ እንዴት ትውጣ? ለሚለው የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቅመጥ እንሞክራለን፡፡

ኢህአዴግ ብዙ ስኬቶችን በሀገራችን ላይ ማስመዝገብ የቻለ ፓርቲ ነው፡፡ የሀገራችን ህዝቦች እነዚህ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዲቀጥሉ ይፈልጋል፡፡ የሀገራች ገበሬ እንደሚለው አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነውና ኢህአዴግ በስፋት የወረረውን አረም መንቀል መጀመር አለበት፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ሌቦቹን በስፋት እና በቁርጠኝነት ጠርጎ የጠራ እና የተስተካከለ ቁመና ሊይዝ ይገባል፡፡ ግንባሩ ሁለት መንታ መንገድ ላይ ይገኛል፤ በሌብነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ዘቅጦ መጥፋት ወይም በአብዮታዊነት ሀገሪቷን ለላቀ ድል ማዘጋጀት፡፡

ስለዚህ እኔም እንደ አንድ ዜጋ የሚከተሉትን አምስት ነጥቦች ኢህአዴግ ቢተገብር ቶሎ የመዳን እድል ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ወይ መጥረግ ወይ መጠረግ የሚለው ሰዐት ላይ ተደርሷል

  1. የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነቱን በየትኛውም ዋጋ ማረጋገጥ እና የግንባሩን ልዕዋላዊነት ማረጋገጥ፡፡ ይሄን ማድረግ ጊዜ የማይሰጥ እና ሌቦችን በማባበል ለማስቀረት ከታቀደው ቀውስ መፃኢው የሚያስፈራ ነውና ባፋጣኝ ወደስራዐቱ አደጎች ሌቦች ላይ መብረቃዊ እርምጃ  ሊወስድ ይገባል፡፡
  2. የሀገሪቱን ሚዲያዎች በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ቁጥጥር ስር በማዋል ሌቦችን የመታገሉን ሂደት ህዝቡን በስፋት እስካሁን ባለው ሳይሆን የእውነት በማሳተፍ እና ሌቦችን አጋልጦ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ፡፡ በዚህም ትክክለኛ ለህዝብ የወገኑ አባላቱን ለይቶ ዋነኛ ተዋናይ ማድረግ፡፡ በእስካሁኑ ሂደት በሌብነት የሚታወቁ በየደረጃው ያሉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጥልቅ ተሀድሶ ተብሎ የተጀመረውን ማልያ ገልብጠው ሲመሩት እያየን ነው፡፡
  3. የግንባሩን አባላት በ1 ሚሊየን መገደብ እና የአባልነትን ክብር ወደነበረበት መመለስ፡፡ እያንዳንዱ የግንባሩ አባላት ፓርቲዎች 250 ሺ እንዲሆኑና ሌላውን በደጋፊነት መያዝ ይቻላል፡፡ በዚህም ሂደት አባልነት አጓጊ ማድረግ እና ክብሩን መመለስ፡፡
  4. በአባላቱ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ስራ መስራት እና እንዚህን አባላቱ በተለይ ወጣት አብዮተኞችን መፃኢ የሀገሪቷ መሪዎች እንዲሆኑ ማድረግ ሰይዋል ሳይታደር ሀላፊነቱን መስጠት፡፡ የወጣቱን ችግር በወጣት አብዮተኞች ለመፍታት መመረሽ
  5. ያለንበትን የአለም ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ ቀምሮ ሀገራችን ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በመቀመር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ካለፉ በሗላ ለህዝቡ መስጠት ያቃተውን አዲስ ራዕይ ለህዝቡ ማስታጠቅ፡፡ ራዕይ ሁልጊዜ መታደስ ስላለበት፡፡ ለምሳሌ በቻይና የሲልክ ሮድ silk road ፕሮጀክት የሀገራችን ተጠቃሚነት እስከምን መሆን እንዳለበት እና የሚኖረንን ድርሻ ኢህአዴግ እስካሁን የነገረን የለም፡፡ ይሄ ለኔ አሳፋሪ ነው፡፡ የመካከላኛው ምስራቅም የጂኦ ፖለቲካል ሁኔታ በፍጥነት ተቀያይሯል፡፡ ስለዚህም ምንም እየሰማን አይደለም፡፡

 

እንግዲህ ኢህአዴግ ያለበት መንታ መንገድ ከሞላ ጎደል ይህንን ይመስላል፡፡ የህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች የበላይነት ተረጋግጦ ኢትዮጵያን ለላቀ ስኬት ማብቃት ወይም የሌቦች የበላይነት ባለበት የሀያልነት ደረጃ አሸናፊነቱን አረጋግጦ ሀገራችንን ወደማያባራ ቀውስ መክተት፡፡ ለሁሉም ሁላችንም አብረን የምንታዘበው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጨው ለራስህ ስትል ጣፍት ሳልል ማለፍ አልፈልግም፡፡

ባጠቃላይ ቆራጥ አማራርነት መስጠት ግንባሩን ከሚመሩ አካላት ይጠበቃል፡፡ አለበለዚያ የሚፈጠረውን ለመገመት ጠንቋይ መሆን አያስፈልግም፡፡

ድል ለሰፊው ህዝብ!

ሀብቶም ገ/እግዚያብሄር

(ይህ ፅሁፍ እንደዜጋ ለሀገሬ ማበርከት በሚጠበቅብኝ አስተዋፅኦ ለመከወን የተፃፈ የግሌ አተያየት እና አቋም ነው እንጂ የማንንም አቋም የማይወክል መሆኑ እንዲታወቅልኝ እጠይቃለሁ፡፡)

አድራሻ:- nahat143love@gmail.com

 

   

 

    

   

 

አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ

97 የአባላት ምልመላ

ይህን መንገድ ከመረጠ ያለው ነባራዊ እና ሊፈፅመው የሚገባው እውነታ

ሲልክ ሮድ

ሁለት መንገዶች አሉ፡፡

  1. ermias says

    አሪፍ ነው። ከመጨረሻው ብነሳ እንደ ቀድሞ መሪ ልበ ሙሉ አመራር ያስፈልጋል። ከዛ የላቁ ጉዳዬች ግን አሉ። እንደኔ የድርጅቱ ትልቁ ያሳካው ስራ ግድብ ሳይሄን ፤አንድ ለገበሬውና ቤተሰቡ የመሬት ማረጋግጫ መስጠቱ ቀጥሎ ጠንካራ የሀገር መከላያ ሰራዊት እንብዛም የክደት ውሬዎች ማይሰሙበት ሽንፍትም ያልደረሰበት እንዲሁም ብዙም ያልደፈረሰ ከባቢያዊ ሰላም መኖሩ ነው።
    ድክመቶቹ ደግሞ ጥራት ያነሰው ለስነ ምግባር ብቃት በአግባቡ ትኩረት ያልሰጠ ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ መለቀቁና ድርጅቱ ስነ ምግባር በሌለው ህገመንግስቱን በሚጠላ መርህን በናቀ ሀይል እየተረታ መምጣቱ ነው። የድርጅቱ መሳሪያዎች ጭምር ኪራይ ሰብሳቢነት ለመሸፈን መጠቀሚያ ናቸው። ይህ ቀስ በቀስ የድርጅቱ ሙሉ መለያ እየሆነ ነው። በዚህ ሰአት ኢሃዴግ ቀድሞ ከነበሩት መንግስታት የነበረውን ብልጫ እንዳያጣ በተለይ በደቡቡ ክፍሎች ስጋት አለኝ። ለዚ ምሳሌ ሚሄነው አሁን እየተናፈሰ ያለው ድርጅተን አስጠይ ለማድረግ ሚደርገው ነገር ነው። ህዝብ የተጨቆነው በፓርቲው ምክንያት እንደሆነ እንዲያምን እየተደረገ ነው። እኔ እስከሚገባኝ ግን የአመራሩ ጉድለት ነው እንጅ ፓርቱው የመጮቄንም የመለያየትም አላማ የለውም።
    ስለዚህ እንዳልከው ለጥቂት ግዜም ቢጎዳ ድርጅቱ ከነዚ አመራሮች ዞር ብሎ ጠቃሚ አባላትንና አመራሮችን መመልመል አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy