Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከሁሉም በላይ ሰላም

0 283

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከሁሉም በላይ ሰላም

                                                                                          መዝገቡ ዋኘው

ለወራት ያህል በተለያዩ ኦሮሚያ አካባቢዎች ውጥረት፣ ግጭትና የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ የቆዩ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ሁኔታዎች ተለውጠው ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል፡፡ በእነዚህ አቸስጋሪ ግዜያት ውስጥ የክልሉ መንግስት ከአባገዳዎች፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር በመሆን አካባቢውን ለማረጋጋት ሰፊ ስራዎችን ሰርቶአል፤ እየሰራም ይገኛል፡፡

የመጀመሪያው የጉዳዩ ባለቤት ከሆነው ሕዝብ ጋር ሰፊ ውይይቶችና ምክክሮችን እንዲሁም ኮንፈረንሶችን ማድረግ የነበረ ሲሆን ይህንንም ማድረግ ችሏል፡፡ ቀጣይ ሒደቱን አጠናክሮ ችግሩን ከስረመሰረቱ ለመፍታት ተከታታይ ስራዎችን መስራት መሆኑ ታምኖበት በዚህ ደረጃም ያሉት ስራዎች በእቅድ በመሰራት ላይ ናቸው፡፡

በየቦታው ችግሩ በሰላም እንዳይፈታ ለማድረግ የማቀጣጠል ስራ ሲሰሩ የነበሩት ኃይሎች ዋነኛ ተልእኮ ሕብረተሰቡ ሰላም እንዲያጣ፤ በሂደትም አጠቃላዩ ሀገራዊ ሰላም እንዲታወክ፤ መደበኛ የሆነው የሕዝቡ ሰላማዊ ሕይወት እንዲደፈርስ የማድረግ፤ የኢኮኖሚ ተቋማትን የማሽመድመድ፣ ትምህርትን፣ ትራንስፖርትን ወዘተ የማስተጓጎል ስራ መሆኑ በገሀድ ታይቶአል፡፡

በመነጋገር ሊፈታ የሚችለውን ችግር ክፍተቱን በመጠቀምና በማስፋት ሀገራዊ ሰላምን የማደፍረስና የተጀመሩትን የልማትና የእድገት ስራዎች እንዲቆሙ የማድረጉ ስራ  ከጀርባው የጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች እጅ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ በተለይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስቆም ከጅምሩ ጀምሮ ብዙ ርቀት በመሄድ ሲሰራ የነበረው የግብጽና የኤርትራ መንግስት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሕልማቸውን ያሳኩ መስሎአቸው ሲጨፍሩና ሲፍጨረጨሩ ነው የከረሙት፡፡

የታየውን የሰላም መደፍረስ በመጠቀም በአጠቃላይ የሀገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ መጣል በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረውን ቤተሰባዊ በብዙና በማይበጠሱ ድሮችና ክሮች የተገመደውን ሕብረት፣ አንድነት፣ መቻቻልና መከባበር ለመናድ ይህ ቀረው የማይባል ስራ ሰርተዋል፡፡ ዛሬም ይህ እኩይ ድርጊታቸው የከሸፈው በሕዝቡ ታላቅ ርብርብ ነው፡፡

የሀገር ሰላም መደፍረስ ለሕዝቦችዋ የሚያስገኘው ምንም አይነት ጥቅም የለም፡፡ በብዙ መልኩ የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነው፡፡ ኢኮኖሚውንም ይጎዳል፤ የእለት ተእለት ሕዝባዊ መስተጋብሮችን፣ ግንኙነቶችን፣ ማሕበራዊ ሕይወትን ጭምር ያቃውሳል፡፡ ስለዚህም ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው የሀገር ሰላም መረጋገጥና መከበር ነው፡፡ ሌላው ከዚህ በመቀጠል የሚሰራ ስራ ነው የሚሆነው፡፡  ለምን ቢባል፣ የሀገራዊ ሰላምና ደሕንነት መኖርና መከበር ሲችል ነው ስለልማት፣ ስለእድገት፣ ስለተረጋጋ ኢኮኖሚ መነጋጋር የሚቻለው፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠሩት ግጭቶች መፈናቀሎች የሰው ሕይወት መጥፋት አደጋው ያንዣበበው በሁለቱ ክልሎች ብቻ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ ነው፡፡ ችግሩ በሁለቱ ክልሎች ብቻ ተወስኖ ወይንም ተጽእኖው ተገድቦ የሚቀር አይደለም፤ ሰፊ አድማስን ይሸፍናል፡፡ ለዚህ ነው ጉዳዩ የሶማሌ ክልልና የኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን የመላው ሀገሪትዋ ነው የምንለው፡፡ ይህ አካባቢ ለሀገራችን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው የላቀ ሲሆን፣ የኢኮኖሚያችንን ገቢና ወጭ ንግድ የሚስተናግድበት፣ የሚንሸራሽርበት ቁልፍ አካባቢ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ተፈጠረ ማለት የሚጎዳው መላ ሀገሪቱን እንጂ የተወሰኑ ክልሎችን ብቻ አይደለም፡፡

የሀገራችን ጠላቶችም ይህንኑ ስለሚያውቁ በዚህ አካባቢ ያለውን ሰላም ለማደፍረስ የማይቆፍሩት ጉድጓድ፤ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሌላው አካባቢው አሁንም የስጋት ቀጣናና ቀይ መስመር ያለበት መሆኑ ነው፡፡ አክራሪ እስላማዊ ኃይሎች ከዚህ በፊት ሞክረው ባይሳካላቸውም ዛሬም በእቅድና በፕላናቸው ውስጥ ያለ ቀጠና መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተለይ ከወዲያኛው ሶማሊያ ወደ እኛው ሶማሌ ሰፊውንና በቀላሉ ለመቆጣጠር የማይቻለውን ድንበር በመጠቀም ሰርገውም በመግባት እነአይሲስ፣ እነአልቃይዳ የእኛኑም ሶማሌዎች መስለው ቢሆን የተለያዩ ሽብሮችን፣ ሁከቶችንና ግጭቶችን ከመጫርና ቀጠናውን ወደ ጦርነትና ቀውስ ውስጥ ለመክተት ከመስራት አይመለሱም፡፡ የኤርትራ ተላላኪዎች በስፋት  ሰርገው በመግባት ይህንኑ ተልእኮ ሊፈጽሙና ሊያስፈጽሙ ይችላሉ፡፡

አስፍተን ከተመለከትነው ችግሩ እየተቀጣጠለ፣ እየሰፋ እንዲሄድ የሚያደርጉ አካላት ከጀርባ ለዚሁ ስራ የተሰማሩ፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰርገው የገቡ፣ የውጭ አላማን አንግበው የሚሰሩ የኦብነግ፣ የኦነግ ሰርጎ ገቦች ወንጀል እየፈጸሙ፣ ግድያ፣ ዘረፋ እያካሄዱ ሕዝብን ከሕዝብ ከማናከስ ከማባላት ወደኃላ አይሉም፤ አድርገውታል፡፡

እዚህ ላይ ጥንቃቄና ትኩረት መደረግ ያለበት ጉዳዩን ከስሩ በመፈተሸና መፍትሄም ማስቀመጥ ያለበት የአካባቢው ሕዝብ፣ የክልሉና የፌደራል መንግስት ነው፡፡ ጉዳዩ የሁለት ክልሎች ብቻ አይደለም፡፡

ወደ ሀገራዊ የተረጋጋ ሰላማችን እንድንመለስ የተሰሩት ስራዎች የበለጠ ውጤታማ መሆን የሚችሉት ያልተቋረጠ ሰላምና መረጋጋትን የማስፈን ተከታታይ  ስራዎች በህዝቡ ውስጥ መሰራት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡

ሕዝቡ ተረባርቦ የተፈጠረውን ውጥረትና የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋት በክልሉ መንግስት ኃላፊዎች፣ በአባገዳዎች፣ በኃይማኖት መሪዎች፣ በታዋቂ ሰዎች፣ በወጣቱና በሴቶች የተደረገው ርብርብ የሚደነቅ ቢሆንም በዘላቂነት ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ በራሱ ከሕዝቡ ውስጥ እነዚህኑ አካላት ያካተተ በየክልሉ እስከቀበሌ ድረስ በሕዝቡ ተደማጭ የሆኑና የተከበሩ ሰዎችን ያካተተ፣ የአካባቢውን ሰላም የሚያስከብሩ፣ ችግሮች ሲከሰቱ ሕዝቡን ይዘው የሚፈቱ፣ የሚዳኙ ኮሚቴዎች መኖር በቅርበት ችግሮች ከመፈጠራቸውም በፊት ለመፍታት ያስችላል፡፡

ግርግር በተነሳ ቁጥር በአካባቢው ያለውን የመንግስትም ሆነ የግለሰብ ዜጎችን ንብረት በእሳት ማጋየት ማውደም የሕዝብ ቁጣ ማሳያና መገለጫ ነው የሚለው የተሳሳተ አስተያየት ግዜው ያለፈበት ብቻ ሳይሆን ከዘመኑም ጋር የሚራመድ አይደለም፡፡ የሚወድመው ሀብትና ንብረት ዛሬም ነገም የሕዝቡ መጠቀሚያና መገልገያ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

በድሀ ሀገር አቅም የራስን ሀብት መልሶ ማውደም መልሶ የሚጎዳው ሕዝቡን ነው፡፡ ንብረቶቹ አገልግሎት የሚሰጡት በዚያ አካባቢም ሆነ በሌላ አካባቢ ለሚኖረው የራሳችን ወገን ነው፡፡ ንብረት በማውደም የሚገኝና የሚመጣ ምንም አይነት ለውጥ የለም፡፡ ይልቁንም ነገም ከነገ ወዲያም አገልግሎት የሚሰጡት የሚጠቀምባቸው ሕዝቡ በመሆኑ ንብረቱን፣ ሀብቱን የግለሰብም ሆነ የመንግስት ጉዳት ላይ እንዳይወድቁ የመጠበቁ ኃላፊነት የሕዝብና የሕዝብ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በየቦታው የሚከፈቱት ኢንቨስትመንቶች እጅግ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብና እውቀት የፈሰሰባቸው ከመሆኑም በላይ ተጠቃሚ የሚያደርጉት ወደስራ የሚያሰማሩት የአካባቢውን ነዋሪ ነው፡፡ በዚያ በተከፈተ የስራ መስክ በርካታ ዜጎች የገቢ ምንጫቸው ሆኖ ሕይወታቸውንና ቤተሰባቸውን ይመሩበታል፤ያስተዳድሩበታል፡፡

የሀገር ውስጥ ባለሀብትም ሆነ የውጭ ዜጋ የከፈተውን ድርጅት ፋብሪካ ወይም ተቋም ማቃጠል በዜጎች ሕይወትና የእለት ተእለት እንጀራቸው ላይ የሞት ፍርድ የመፍረድ ያህል ነው፡፡ ያ ድርጅት ስራውን ዘግቶ አካባቢውን ለቆ ቢወጣ ስራው በመቆሙ ምን ያህል ቤተሰብ ጉዳትና ችግር ላይ እንደሚወድቅ ተመልሶ ለስራአጥነት እንደሚጋለጥ ከስሜታዊነትና ከጀብደኝነት በመውጣት ደግሞ ደጋግሞ ማሰብን ማስተዋልን ይጠይቃል፡፡

ባጠቃላይ፣ ስለማንኛውንም ጉዳይ፣ የመብት ጥያቄ በሕግ አግባብ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠየቅ፣ መነጋገር፣ መወያየት እየተቻለ ወደ ጥፋት መንገድ መሄድ ንብረትና ሀብት ማቃጠል ነገም ከነገ ወድያም የሚጎዳው ሕዝቡን ነው፡፡ ምንም ባልነበረበት አካባቢ ተጀምሮ የነበረውን  የልማትና የእድገት እንቅስቃሴ መልሶ ማዳፈን የአካባቢውን ነዋሪ ሕዘብ  በረዥም ግዜም ቢሆን ይጎዳዋል፡፡ ከጥፋትና ከውድቀት አስተሳሰብ በመላቀቅ ለአካባቢም ሆነ ለሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት መቆም ግድ ይላል፡፡ ሰላም ይበጃል፤ ሰላም ሁሉም የለም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy