Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከአንድነት ሌላ የተሻለ አማራጭ ከወዴት

0 338

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአንድነት ሌላ የተሻለ አማራጭ ከወዴት

ዮናስ

ኢትዮጵያ ብዝኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ  ማስተዳደር ከቻሉና ከተሳካላቸው ጥቂት ሃገራት መካከል አንዷና ዋነኛዋ ነች። ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ የእርስ በርስ መተማመን ፈጥሯል። መተማመኑም መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ የሌላቸው መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ የተስተዋለ ነው።    ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚፈቅድና በህገ መንግስትም የታጠረ ጉዳይ ነው። መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን ደግሞ በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ በማሰብ የሚሰጣቸው እገዛዎች፣ በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ አዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ላይ አገሪቱን ከጫፍ ጫፍ የሚያስተሳስር የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት መስፋፋቱና ይህንንም በተናጠል ሳይሆን በጋራ ለመጠቀም የሚቻልበት እድል መስፋቱ፣ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ሁለት እርምጃ ወደፊት ወስዶናል። ያም ሆኖ ግን እንዲህ ያለው ስርአት ለኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች የማይመች ብቻ ሳይሆን ተመልሶ ለእነርሱው ፍላጎት የሚውልባቸው አግባቦችም ሰፊ መሆናቸው ጥናት ሳያስፈልግ እዚሁ ሃገራችን ባጋጠሙ የሁከት አጀንዳዎች ተረጋግጧል።  

በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት፣ በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ከመፈናቀላቸውም በላይ ውድ የሆነውን ህይወት አጥተዋል። የሁለቱ ክልል ህዝቦች አንዱ ካንዱ ውጭ መኖር የማይችል የአብሮነትና የጠበቀ የጋራ ኑሮ እንዳላቸው የታሪክ ድርሳናትን ጨምሮ የሃገር ሽማግሌዎችና በሁለቱም ክልሎች የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች አረጋግጠዋል። ስለሆነም ግጭቱ ከህብረተሰቡ የቆየ አኗኗር ዘይቤ አኳያና ቀደም ሲል ከሚከሰቱ መጠነኛ ግጭቶች የተለየና ሌላ ጥቅም ፈላጊ አካል ተሳትፎ መኖሩን ያሳያል። የኦሮሞና ሶማሌ ህዝብ ለረዥም አመታት አብሮ ሲኖር፣ አብሮ ሲበላ ሲጠጣ የቆየ ህዝብ በሆነበት አግባብ በርካቶችን ያፈናቀለና የበርካቶችንም ህይወት የቀጠፈ እንዲህ አይነት ግጭት መንስኤው የሚሆነው ኪራይ ሰብሳቢነት ብቻ ነው።  

ከሰሞኑ ጉዳዩን በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው። የግጭቱ መንስኤ ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት የተሳነው አመራር ከበቃኝ እርምጃ ይልቅ በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ተዟዙሮ የመስራት መብት በመጋፋት እኛና እነሱን መምረጡ የመጀመሪያውና ፖለቲካዊ የሆነው መንስኤ ነው። አካባቢው ለወጪ ንግድ የተመቸ በሆነው የጫት ንግድ የበለጸገ መሆኑን የተረዱ የመንግስትና የድርጅት የስራ ሃላፊዎች ከጦር መኮንኖች ጋር ተመሳጥረው አርሷደሩ የምርቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን ማድረጋቸው በጥልቅ ተሃድሶው መረጋገጡና አምራቹን ተጠቃሚ ወደሚያደርግ አሰራር መለወጡ ያነገበገባቸው ኮንትሮባንዲስቶች ጉዳዩን የብሄር መልክ ሰጥተው መፋጨታቸውም ሁለተኛውና ኢኮኖሚያዊ የሆነው ምክንያት መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጻቸው ከላይ የተመለከተውን እና ስርአቱ መልሰው ለኪራይ ሰብሳቢነት አጀንዳ ለሚያውሉ ሃይሎች የተመቸ ነው የሚለውን ያጠይቅልናል።

በመሰረቱ ህገ መንግስታችን የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትህና የእኩልነት ዋስትናችን ነው።  እየተገነባ ያለው ሥርዓት የገበያ መሆን እንዳለበትና ሰዎች ሰርተው የመጠቀም ህጋዊ ዋስትና ሊያገኙ እንደሚገባቸውም ጭምር የሚያረጋግጥ ነው። በዚህ ላይ ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኞቹ ጠላቶቻችን እንደሆኑ፣ ስለዚህም ደግሞ በፍጥነት መልማትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዳለብን አጠቃላይ የጋራ ግንዛቤ ተይዟል፡፡

የህግ የበላይነት መከበር እንዳለበትና ዜጎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል እንደሆኑ ቢያንስ  ግንዛቤ ተይዞበታል፡፡ እዚህ ላይ ከፈጣኑ እድገት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ነባርም ሆኑ አዳዲስ የስርዓት ችግሮችም እንደዚሁ ከሞላ ጎደል የጋራ ስምምነት የተያዘባቸው ሆነዋል፡፡ ያም ሆኖ ኪራይ ሰብሳቢነት ይህንንም የማጨለም ሃይል ያለው ለመሆኑ በነዚህ ክልሎች መካከል ከተፈጠረው በላይ ማረጋገጫ መጥቀስ ግድ አይሆንም። ሃያልነቱ ደግሞ ህዝባዊ ነን የሚሉትን ሚዲያዎች ጨምሮ ጎራ ለይተው እንዲቀጣቀጡ በማድረግም ተገልጿል።  

ከላይ በተመለከቱት የፌደራላዊ ስርአት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረ ቢሆንም፤ ይህ ግን በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑ አሁንም ኪራይ ሰብሳቢው ወጋ ባደረገው ቁጥር የመዋለልና ወደፊትና ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች እያሳየ መሆኑን መቀበል ወደመፍትሄው ያደርሳል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ እንደሆነ ለወትሮው ሲናገር የሚሰማው ህዝብን ጨምሮ ተቋማት ሳይቀሩ ትንሽ በማይባል ደረጃ በዚሁ ዝንባሌ ሲለከፉ ሰሞኑን አይተናል፡፡ የህግ የበላይነትንና ሰላማዊ የትግል አግባብን የተቀበለው ህብረተሰብ፣ ፍላጎቱን በሃይልና በግጭት መንገድ ለማሳካት ሲንቀሳቀስ የታየውም ስለዚሁ የኪራይ ሰብሳቢነት ሃያልነት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አመራሩ ችግሩን ብቃት ባለው መንገድ የማይመራውና ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ በሆነው አቅጣጫ በማያስጉዝ አግባብ በሚሰጣቸው መግለጫዎች ከብሔራዊ መግባባት አኳያ የተሻለ ርቀት የሄድንባቸው ጉዳዮች ሳይቀር ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያ የሚታይባቸው እስከመሆን የደረሱበትን አጋጣሚም ከዚሁ ግጭት ለመታዘብ ችለናል፡፡

ይህም ሆኖ ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ በህገ መንግስቱና የህግ የበላይነት ማስከበር ላይ፣ በልማትና በህዝብ ተጠቃሚነት አጀንዳዎች ላይ እንዲሁም በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ በተነፃፃሪ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የፈጠረች አገር ሆናለች፡፡ህገመንግስታችን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያስከበረ ተራማጅ ህገመንግስት ነው። በአገራችን ዴሞክራሲና ልማት የማይነጣጠሉ የአገራችን የህልውና መሰረት  ሆነዋል።

 

በአገራችን  ዜጎች የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመቃወም፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመጻፍ የመሳሰሉት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በህገ መንግሥቱ ተረጋግጠዋል። ማንኛውም ዜጋ  ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቃወም የሚችልበት አሰራርም በህገመንግስቱ በግልጽ ተመልክቷል። ስለሆነም ዛሬ በየትኛውም  አካባቢ የሚከሰት የድንበር ግጭት  ህዝቦች ጥቅምና ፍላጎት አይደለም። አንድ የጋራ ማህበረሰብ በመፍጠር ላይ ያለመው የፌዴራሊዝም ሥርዓታችን በድንበር ጉዳይ ላይ የታጠረ ሳይሆን በህዝቦች ፍላጎትና የልማት ተጠቃሚነት ላይ ያነጣጠረ ነው። ያም ሆኖ ግን የመረጥነው ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት ለአንዴና ለሁልጊዜ ረግቶ የሚቀመጥ ሳይሆን ከአገሪቱ የእድገት ደረጃ ጋር ተገናዝቦ ሁሌም ቢሆን በታዳጊነት መገንባትና እየዳበረ መጓዝ ያለበት መሆኑን መዘንጋት አይገባም።ከዚህ በመነሳት በአገራችን  ብዝሃነት ያሉዋቸው ማህበረሰቦች እንደሚገኙና እነዚህም የየራሳቸው ልዩ ልዩ ፍላጐቶች ያሏቸው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።  

በቡድን መልክ የሚገለፁ ማህበረሰቦችም የተሟላ እኩልነት ተጎናፅፈዋል፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ሴቶች፣ ሠራተኞች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና የመሳሰሉ ማህበረሰቦች  የቡድን መብቶቻቸውን የተጎናጸፉ መሆኑም እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣይነት ህልውናዋ ተረጋግጦ ልትቀጥል የምትችለው ዜጎቿንና ህዝቦቿን አክብራ ስትይዝ ብቻ እንደሆነ በማመን ተግባራዊ የተደረገው ዴሞክራሲ አገሪቱን ለፅኑ ህዝባዊ አንድነት አብቅቷታል፡፡

በአገራችን እየተገነባ ያለው የፌዴራል ስርአት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት ነው። መንግስት የዘመናት የብሄራዊና የመደብ ድርብ ጭቆና የህዝብ ጥያቄዎች ከመሰረቱ ለመለወጥ ከተከተላቸው ቁልፍ የፖለቲካ አቋሞችና ከወሰዳቸው ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎች መካከል የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን የመገንጠል መብቶችን ማረጋገጥ ቢሆንም ከዚሁ ባልተናነሰ አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር የመጨረሻው ግብ ሆኖ ተቀምጧል። በዚህም አዲሲቷ ኢትዮጵያ በህዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተች፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ዴሞከራሲያዊ አንድነት የሚንፀባረቅባት አገር ለመሆን በቅታለች።  

በአገራችን እየተገነባ ባለው የፌዴራል ስርአት በክልሎች መካከል መነጣጠልና መለያየት ሳይሆን ጠንካራ ትብብርና መደጋገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጎለበተ እንዲመጣ የሚያስችል ነው። ዛሬ ቀድሞ የነበረው በህዝቦች መካከል የተረጨው በመጠራጠርና ቁርሾ ላይ የተመሰረተው ግንኙነት በመሰረቱ ተወግዷል። በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ ሆኖ ፀድቋል። ከዚህ በላይ ያለው ሁሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አጀንዳ ነውና ልንዋጋው ይገባል። የነዚህ ሃይሎች አጀንዳ ሰለባ ለመሆን መቋመጥ መልሶ የሚወጋው እኛኑ መሆኑን በመገንዘብ በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ የሌለን መሆኑ ላይ ሙጥኝ ማለት ይጠበቅብናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy