Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከ80 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

0 585

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከ80 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ 7 የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ 9 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ተከሳሾቹ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛው የወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ ተነቦላቸዋል።

1ኛ ተከሳሽ አቶ መስፍን ተፈራ በድርጅቱ የጭነት ማስተላለፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ 2ኛ አቶ ሲሲይ አባፈርዳ በድርጀቱ የኮርፖሬት ምክትል ስራ አስፈፃሚ መስፈርቱን ያልጠበቀ ግዥ ለመፈፀም በመስማማት ተከሰዋል።

እነዚህ ተከሳሾች የራሳቸውን መስሪያ ቤት ጨምሮ በኮሜት ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር፣ በከልቻ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር እና ዕለት ደራሽ ትራንስፖርት ድርጅቶች እያንዳንዳቸው እንደቅደም ተከተላቸው፥ 100፣ 100፣ 60፣ 20 በድምሩ 280 የከባድ ተሽከርካሪ በጋራ በማዕቀፍ ግዥ ለመግዛት መስማማታቸው በክሱ ተገልጿል።

በስምምነታቸው መሰረት ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት አሸናፊው አቅራቢ ድርጅት ያስመጣቸውን ተሽከርካሪዎች በውሉ መስረት፥ አቅራቢው ድርጅት ያስያዘው የመልካም ስራ አፈፃፀም ዋስትና ጊዜ ያለፈበት እና 11 መስፈርቶች ሳያሟላ ቀርቷል።

ባልተሟላው መስፈርት ላይ የቴክኒክ ኮሚቴው ያለአግባብ ማብራሪያ እንዲሰጥ መደረጉን ክሱ ያመለክታል።

በዚህም የጂፒኤስ እና ቶዊንግ ሁክ ጉድለቶች እንጂ ሌሎች ተቀባይነት ያላቸው ነው በማለት፥ በዘጠኝ ጉድለቶች በመንግስት ላይ ከ7 ሚሊየን 546 ሺህ ብር በላይ ጉዳት አድረሰዋል።

3ኛ ተከሳሽ አቶ ሲራጅ አብዱላሂ በድርጅቱ የጅቡቲ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት፥ ድርጅቱ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር በሚደረገው ዝግጅት መመሪያ በመተላለፍ ዋና ስራ አሰፈፃሚው ሳይፈቀድ ወይም በስራ አመራር ቦርድ ሳይፀድቅ ግዥ እንዲፈጸም አድርገዋል።

በዚህም ተከሳሹ የተሰጣቸውን ሹመት ያለአግባብ በመጠቀም፥ ከመመሪያ ውጪ ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው በክሱ ተገልጿል።

4ኛ ተከሳሽ አቶ ደሳለኝ ገብረህይወት በድርጅቱ የወደብ እና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ እና 5ኛ ተከሳሽ ተናገር ይስማው የየብስ ወደቦች ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መምሪያ ዳሬክተር ሆነው ሲሰሩ፥ በሰመራ ደረቅ ወደብ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ግሮቭ ጂኤምኬ የተባለ ክሬን ከመስከርም 2008 ዓ.ም ጀምሮ መበላሸቱንና ለማስጠገን ተሞክሮ ያልተቻለ መሆኑን በመግለፅ በአስመጪው በኩል በዝቅተኛ ወጪ ማስጠገን ሲችሉ በተቃራኒው ተንቀሳቅሰዋል ይላል ክሱ።

ለአንድ ወር ጊዜ ብቻ ክሬኑን እንዲከራዩ ለዋና ስራ አስፈፃሚው በማቅረብ ካፀደቁ በኋላ በደረቅ ወደቡ ከ4 እስከ 5 ሰዓት የማይባል ስራ መኖሩን እያወቁ፥ ውሉን በየጊዜው በማራዘም ስራ ቢሰራም ባይሰራም በስዓት 2 ሺህ ብር ሂሳብ እንዲከፈል ማድረጋቸው በክሱ ቀርቧል።

በዚህም በመንግስት ላይ ከ2 ሚሊየን 225 ሺህ ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ አድረገዋል ነው የተባለው።

6ኛ ተከሳሽ ቺፍ ኢንጂነር አለሙ የሺፒንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ሲሰሩ፥ ድርጅቱ በኮንቴይነር ኪራይ ከ400 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት ድርጅቱ የራሱን ኮንቴይነሮች እንዲገዛ መጠየቃቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በድርጅቱ ፕላን ክፍል ጥናት እንዲደረግበት እና አዋጪነቱ ከተረጋገጠ በኋላ 1 ሺህ 800 ባለ 20 ጫማ እና 780 ባለ 40 ጫማ በአጠቃላይ 2 ሺህ 580 ኮንተይነሮች ከ199 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞ ጨረታ መውጣቱ ተገልጿል።

በጨረታው ጄኔራል ኤክስፖርት ከ6 ሚሊየን 575 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ ስምምነቱ ተፈርሞ የግዥ ክፍሉ የቴክኒካል ይዘት አዘጋጅቶ ቢያቀርብላቸውም፥ ተከሳሹ ውድቅ በማድረግ ድርጅቱ ከ65 ሚሊየን 594 ሺህ ብር በላይ ለኪራይ ወጪ እንዲያደረግ በማድረግ ጉዳት ማድረሳቸው ተነግሯል።

7ኛ ተከሳሽ የድረጅቱ ፋይናስ እና ሂሳብ መምሪያ ዳሬክተር አቶ ሳሙኤል መላኩ ደግሞ ከ4ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን የሞጆ ደረቅ ወደብ መጋዘን ቁጥር አንድ 67 ሚሊየን 989 ሺህ 786 በማሸነፍ፥ በፕሮጅክቱ ውል መሰረት ከአጠቃላይ ዋጋ 30 በመቶ በሶስት ጊዜ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ መከፈሉን ነው ጠቅላይ አቃቤ ህግ በክሱ ያስረዳው።

ሆኖም ቀሪው ክፍያ የተሰራው ስራ በአማካሪ ድርጅቱ ተገምግሞ ጸድቆ መከፈል ሲገባው፥ ተቋራጩ እቃዎችን ከደረቅ ወደቡ ላስወጣው በማለት የጠየቀውን 14 ሚሊየን 100 ሺህ ብር ያለአግባብ እንዲከፈል በማድረግ፥ 4 ሚሊየን 410 ሺህ ብር በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል።

8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች የሞጆ ደረቅ ወደብ መጋዘን 1 እና 2 ሲገነባ፥ አማካሪ ሆነው ሲሰሩ ተገቢውን ክትትል ባለማድረግ መንግስት ላይ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።

ተከሳሾቹ ያቀረቡት ዋስትና በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አላገኘም፤ በክሱ ላይ ያላቸውን መቃወሚያ ለማድመጥ ለህዳር 15 ቀን 2010 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በበላይ ተሰፋዬ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy