Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ዘረፋን መዋጋት

0 522

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ዘረፋን መዋጋት

ብ. ነጋሽ

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ሰሞኑን 7ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በአዳማ ገልማ አባ ገዳ አዳራሸ አካሂዷል። እየሰራን እንታደሳለን፤ እየታደሰን እንስራለን በሚል መሪ ሃሳብ ነበር ጉባኤው የተካሄደው፤ በጉባኤው ላይ የድርጅቱ አመራሮችን፣ የህብረተሰብ ተወካዮችን፣ ምሁራንንና ደጋፊዎችን ጨምሮ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል። የጉባኤው ዋነኛ የትኩረት ነጥብ፣ በጥልቅ ተሀድሶ የተገኙትን ድሎች ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማጽደቅ ነበር።

የኦህዴድ ሊቀመንበርና የከልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በድርጅታዊ ጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኦሮሞን ህዝብ ጨምሮ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚፈልጉትን አንድነት ለማረጋገጥ ሁሉም የድርጅቱ አባላትና ህዝቡ በጋራ ሊሰሩ ይገባል፤ ሲሉ አሳስበዋል። ኦህዴድና የኦሮሞ ህዝብ ጠንክረው በአንድነት መንፈስ መስራታቸው ለሃገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመልክተዋል። በተጨማሪም፤ የህዝቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለመመለስ ኦህዴድ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት የጉባኤ መክፈቻ ንግግር፤  “ጉባኤው የክልሉንና የሀገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የሰላም ስጋቶችን ለመታገል በአንድነት የምንስራበት ነው!” ብለዋል።

የድርጅቱን ውስጣዊ መዋቅር ማጠናከርና ወደፊት በማራመድ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና እኩልነት ለማጠናከር የሚረዱ ስልቶችን ማስቀመጥ ከጉባኤው አጃንዳዎች መካከል ቀዳሚው ነበር። በኦሮሚያ የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ብልሹ አሰራርና ኪራይ ሰብሳቢነት ከመሰረቱ ማስወገድ፣ ህገ ወጦችን አንገዋሎ ለማራገፍ የተጀመረው ዘመቻ እስካሁን የመጣበት ፍጥነት ሳይበርድ እንዲቀጥል ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታም ድርጅታዊ ጉባኤው ካተኮረባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል። የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የህገ ወጦችንና የኪራይ ሰብሳቢዎችን ሴራ በመበጣጠስ የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት አጠናክረው ለማሰቀጠል የሚያግዙ ገዳዮች ተነስተው ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

ድርጅታዊ ጉባኤው በማጠናቀቂያው ላይ ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። በዚህ ጽሁፍ ላይ ከአቋም መግለጫዎቹ መካከል የተወሰኑትን ጠቅለል አድርጌ ለመመልከት እሞክራለሁ።

ኦህዴድ በክልሉ የተፈጠረውን ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ህዝቡን በማሳተፍ ከመሰረቱ በመፍታት የዜጎች ሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ መብቶች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ እንዲጠበቁ እንደሚሰራ፤ እንዲሁም ህገ-ወጦችና ኪራይ ሰብሳቢዎች የሸረቡትን ሴራ ለመበጣጠስና በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እንደሚሰራ በአቋም መግለጫው ላይ ተመልክቷል። ህዝቡ ለሚያነሳቸው ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት የመፍትሔው አካል ሆኖ እንዲሰራም ጠይቋል።

ሁላችንም እንደምናውቀው በኦሮሚያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር ተፈጥሮ ሰንብቷል። እርግጥ አሁን በመላው ኦሮሚያ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል። ይህን የሰሞኑን የጸጥታ ችግር የፈጠረው የህዝብ ብሶት አልነበረም። ልብ በሉ! ህዝብ ብሶት የለበትም፣ ጥያቄዎቹ በሙሉ ምላሽ አግኝተዋል እያልኩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አሁን ክልሉን እያስተዳደረ የሚገኘው የተሃድሶ አመራር፣ የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲገኙ ለማደረግ ቁርጠኛ አቋም በመያዙ፣ እስካሁን በወሰዳቸው እርምጃዎቹ ቁርጠኝነቱን በተጨባጭ በማሳየቱና ህዝቡም ይህን ስለተረዳ የፀጥታ ችግር ሊያስከትል የሚችል ተቃውሞ የሚያስነሳ ተጨባጭ ምክንያት አለመኖሩን እየገለጽኩ ነው።

የጸጥታ ችግሩ መንስኤ ህገወጦችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው። የክልሉ መንግስት የህዝቡን የመልካም አሰተዳደርና የልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የኪራይ ሰብሳቢነትን ድርጊት ከነአመለካከቱ ማስወገድ ይኖርበታል። የክልሉን ሃብት ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሚዘርፉና ኢኮኖሚያዊ እድገቱን የሚያቀጭጩ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችንም መግታት ይኖርበታል። የተሃድሶው አመራር በዚህ ረገድ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። ይህ ሁኔታ ያሰጋቸው ዘራፊዎችና ኪራይ ሰብሳቢዎች በክልሉ ውስጥ ሁከት በመቀስቀስ የተሃድሶውን አመራርና ጉዞ ለማደናቀፍ፤ እንዲሁም ለህግ ማስከበር አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ በመፍጠር ዝርፊያቸውን ለማጧጧፍ የክልሉን ለጋ ወጣቶች በማደናገር የፈጠሩት ሁከት ነው። በመሆኑም በድርጅታዊ ጉባኤው የአቋም መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ኪራይ ሰብሳቢዎችና ህገወጦች የሸረቡትን ሴራ መበጣጠስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው።

ይህ ብቻውን ግን ዘላቂና አስተማማኝ የሰላም መፍትሄ አይደለም። ዘላቂው መፍትሄ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር፣ እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሀገወጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ህዝቡንም የልማት ተሳታፊ በማድረግ ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ያሻል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተሃድሶ አመራር የእስካሁኑ ጅምር ይህን ማሳካት የሚችል መሆኑን ያመለክታል። በሰሞኑ የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ የአቋም መግለጫም ላይ ይህ ጅምር ቀጣይነት እንደሚኖረው ተገልጿል። ህዝቡም የዚህን ተግባር ቀጣይነት በተስፋ ይጠብቃል።

በአቋም መግለጫው ላይ የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ፣ በአዋሳኝ አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ላይ የሚያተኩር ነው። በድንበር አካባቢ የነበሩ አለመግባበቶችን ሽፋን በማድረግ አፍራሽ ሃይሎች ህገወጦችና የኮንትሮባንድ ንግድ ተዋናዮች በፈጠሩት እንቅስቃሴ የዜጎች መፈናቀልና ጉዳት መድረሱን የሚያስታውሰው የአቋም መግለጫው፣ ድርጊቱ የህዝቦች አብሮነት ያሰጋቸው ሃይሎች ሴራ መሆኑንም አመልክቷል።

እንግዲህ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከወሰን ጋር በተገናኘ ጥያቄዎችና አለመግባባቶች መታየት ከጀመሩ ከአንድ አስርት ዓመት በላይ ተቆጥሯል። አልፎ አልፎ ከረር ያሉ የግጭት ባህሪይ ያላቸው ችግሮች ቢፈጠሩም፣ ከድንበር አካባቢ አልፈው ብሄራዊ ማንነትን መሰረት ላደረገ የሰብአዊ መብት ጥሰት – ድብደባ፣ ዘረፋ፣ ከመኖሪያ አካባቢ መፈናቀልና ሞት ምክንያት ሆኖ ግን አያውቅም። በተደራጀ ትጥቅ ወደሚወሰድ ጥቃት፤ እንዲሁም ከድንበር አካባቢ ርቀው ወዳሉ አካባቢዎች ነዋሪዎችም ላይ ወደሚሰነዘር ጥቃትነት የተቀየረው በ2009 ዓ.ም. ነው። አዲሱ የተሃድሶ አመራር ኦሮሚያ ውስጥ የተሃድሶው አመራር ወደስልጣን ከመጣና በህገወጦች፤ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች፣ በመሬት ወራሪዎችና በጥገኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ ህዝቡን የልማት ተሳታፊና ፍትሃዊ ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማና ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች መውሰድ ከጀመረ በኋላ  ነው። የሚገርመው ይህ በግለሰቦች እጅ በማይገኝ መካከለኛ የጦር መሳሪያ ጥቃት ሲሰነዘር በነበረበት 2009 ዓ.ም. ሃገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ነበረች።

ይህ ሁኔታ፤ ግጭቱ በድንበር አካባቢ በሚኖሩ የሁለቱ በሄሮች አባላት መካከል በወሰን ይገባኛል ጥያቄ የተነሳ ሳይሆን፣ በአካባቢው ግጭት በመቀስቀስ ለህገወጥ ንግድ በተለይ ለኮንትሮባንድ ንግድ አመቺ ሁኔታ የመፍጠር ዓላማ ያለው በዘራፊዎችና በኪራይ ሰብሳቢ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጥምረት የተፈጠረ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። የተሃድሶ አመራሩ በኦሮሚያ ውስጥ የፈጠረው የህዝብ አንድነትና ከመንግስቱ ጋር መግባባት የመንግስት ሙሉ ትኩረት ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋትና በልማት ላይ እንዲያተኩር ስለሚያደርገው ሁከት በመፍጠር የህዝቡን አንድነት የማፈራረስና የመንግስትን ትኩረት የመበተን ዓላማ ያለው ነው።

በመሆኑም በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸውን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ከማቅረብና መልሰው እንዲቋቋሙ ከማገዝ ጎን ለጎን ግጭቱን የቀሰቀሱትን ቡድኖች ህዝብ እንዲያውቃቸው የማጋለጥ ስራ፤ እንዲሁም በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረግ ይኖርበታል። በኦሮሚያ ውስጥ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን የሚቻለው የችግሩ ምንጭ የሆኑ ዘራፊዎችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ተጋልጠው አደብ ሲይዙ ብቻ መሆኑም መታወቅ አለበት።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy