Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዘላቂ ሰላም ያሻናል

0 256

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዘላቂ ሰላም ያሻናል

                                                                     ይልቃል ፍርዱ

ሀገራችን የተረጋጋ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ በየቦታው እየተቆሰቆሰ ያለው አመጽና ሁከት ይሄንንም ተከትሎ እየታየ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትና ንብረት መወድም ፈጥነን ልንገታው የችግሩንም ፈልገን መፍትሄ ልናበጅለት ግድ ይላል፡፡

የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ሞልቶ በተረፈ ሁኔታ መከሰቱ መንግስታዊ የሕዝብ የሆኑ ሀብቶች በኪራይ ሰብብሳው ኃይልና በራሱ በመግሰት ውስጥ በመሸገው ኃይል መዘረፉን ተከትሎ ሁኔታውን ለማስተካከል ችግሩንም ለመፍታት ኢህአዴግ የጥልቅ ተድሶ ንቅናቄ እንዲደረግ በጉባኤ ደረጃ ወስኖ ወደ ተግበር በመግባት ሰፊ ለውጦችን ስመዝግብ ችሎአል።

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባና በክልል መስተዳድሮችም ጭምር ሰፊና ጥልቅ ተሀድሶ ተደርጎ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ በተለያየ ደረጃ በተገኙ አመራሮች ላይ ሰፊ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከዚሁጋር በተለያየ ደረጃ በተካሄድ ግምገማ በድርጅት ደረጃ ኢሕአዴግ ራሱ 50ሺህ የሚገመቱ አባላቱን ማሰናበቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ጥፋታቸው ቀላል የሆኑትና ታርመው መስራት የሚችሉት በተሀድሶው እንዲቀጥሉ ጥፋታቸው ከባድ የሆኑት ደግሞ ጉዳያቸው ወደ ፍርድቤት ተመርቶ እየታየ ይገኛል፡፡

ጥልቅ ተሀድሶው የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አስጠብቆ ሀገሪቱ የጀመረቻቸውንና የተጎናጸፈቻቸውን ታላላቅ የኢኮኖሚ ድሎች ጠብቆና አስጠብቆ መዝለቅ ነው ዋነኛ አላማው፡፡ እንደ ሀገር ከድሕነት ተላቃ ያደገችና የበለጸገች ሀገር ለመሆን ሰፊ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላም በአለማችን እጅግ ውድና በምንም ነገር ሊተካ ሊለወጥ የማይችል ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ምንም የለም፡፡ ስለዛሬም ሆነ ስለነገ ማሰብ አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው ሀገራችን በቅድሚያ በሁሉም አቅጣጫ ሰላም የሚያስፈልጋት፡፡

በየቦታ የተቆሰቆሰውና መልኩን እየቀያየረ የሚከሰተው አመጽ መነሻ የኪራይ ሰብሳቢው የጥገኛውና የሙሰኛው ኃይል የጥበትና የትምክሕት ኃይሎች በአንድም ሆነ በሌላው መልኩ ተቀናጅተው የሚቀሰቅሱት ሲሆን ለዚህ ማሳያ የሚሆነውም መንግሰት በኪራይ ሰብሳቢው ላይ የከፈተውን የተጠናከረ ዘመቻ እንዲገታ ብሎም ተድበስብሶ እንዲቀር ለማድረግ የሚያደርጉት የማይሳካ ጥረት ነው፡፡

ሰላምን የማደፍረስ ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት የመንግስትና የሕዝብን ሀብትና ንብረት የማውደም ስራዎችን ሆን ብለው የሚያቀጣጥሉና የሚያስፋፉ ክፍሎች  ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንቅፋት የሆኑ መሰናክሎችን በየቀኑ እየፈጠሩ  የምናይበት ሁኔታ ሊቆም ይገባዋል፡፡

ይህ አይነቱ መንገድ ስርአተ አልበኝትነትን የሚያስፋፋ የሕዝብና የሐገርን ሰላምና ደህንነት ጭምር አደጋ ላይ የሚጥሉ የማናከስ  አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱት የኪራይ ስብሳቢውና የትምክህት ኃይሎች ከጀርባቸው የሀገሪቱን ሰላም ለማናጋት የጀመረችውን የልማትና የእድገት አቅጣጫ የጨበጠቻቸውንም ታላላቅ የኢኮኖሚ ልማት ድሎች ለማሰናከል ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው የሚንቀሳቀሱ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ የውስጡ ችግር በሰላምና በውይይት ሊፈታ የሚችል ሁኖ ሳለ እነዚህ ኃሎች በአቀጣጣይነት የሚጫወቱት የጀርባ ሚና ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡ ይህም የግብጽንና የኤርትራን እጅ ያካትታል፡፡  

የሀገሪቱ ሰላም መደፍረስ የሚጠቅመው ለጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ብቻ ነው፡፡ የሀገርና የሕዝብ ሰላም ከምንም በላይ ወሳኝ በመሆኑ የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ፈጥኖ መንቀሳቀስ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር በመሆኑ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከሁከት ከትርምስ ንብረት ከማውደምና ከማቃጠል የሚገኝ ሀገራዊም ሕዝባዊም  ጥቅም ከቶ የለም፡፡

ይህ አይነቱ ሁኔታ ሀገራዊ ኢኮኖሚን በማዳከም የወጪና የገቢ ንግዱ እንዲሁም በአጠቃላይ በንግድ ዝውውሩና በገበያ ልውውጡ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያሳድር በመሆኑ ዞሮ ዞሮ ተጎጂ የሚሆነው ሕዝቡ ነው፡፡ የገበያ ውድነትን በመፍጠር ውጥረትን የማባባስ ድርጊት ሕብረተሰቡን ለማስመረር የሚደረግ በመሆኑ በሚፈጠረው ስርአተ አልበኝነት አሁንም ተጎጂው ሕዝብ ነው የሚሆነው፡፡ በሌሎች ሀገራትም ያየነው ይሄንኑ ነው። ሕግና ስርአት ካልተከበረ ሕዝቡ ለዘራፊዎችና ለቀማኞች ይጋለጣል፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ ከመንግስት ጎን ሁኖ ሰላሙን ማስከበር መጠበቅ አለበት የሚባለው፡፡

ሸቀጦች ወደከተማ እንዳይገቡ ከከተማም ነጋዴው ወደ ክፍለሀገር ሄዶ እንዳያመጣ የሚደረጉት ትራንስፖርት መዝጋትና መኪኖችን አላሳልፍም ማለት የሸቀጦች ዝውውርን ግብይትን መግታት የከፋ ችግር ላይ የሚጥለው ሕዝቡን ነው፡፡

በዚህ መልኩ የኪራይ ሰብሳቢውና የጥገኛው የትምክህትና የጥበት ኃይሉ የፈጠረውን ትርምስ ለመግታትና ሕዝቡ ሰላሙንና አካባቢዊ ደሕንነቱን የማስከበር ኃላፊነቱን በተለያዩ ቦታዎች በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ በረዥሙ ሲታይ በዚህ ግርግር ተጠቃሚ እሆናለሁ ፖለቲካዊ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ የሚያስበው ኃይል ያሰበውን ለማሳካት አይችልም፡፡ የተፈጠሩት ግዜያዊ ችግሮች በሰላማዊ ውይይት በቆየውና በኖረው የሕዝቡ ባሕል መሰረት በመነጋገር በመደማመጥ በአዛውንቶችና በሀገር ሽማግሌዎች በመፈታት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሕዝቡ ቅሬታውን ብሶቱን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መግለጽ፣ ለሚመለከተው አካል ማሰማትም ሕገመንግስታዊ መብቱ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሰላምን የሚያናጉ አብሮነትን የሚያፈርሱ ግጭትን የሚጋብዙ ንብረት እንዲወድም የሰው ሕይወት እንዲጠፋ የሚያደርጉ ኃላፊነት የጎደላቸውን ግለሰቦች ሕብረተሰቡ በዝምታ ማለፍ አይችልም፡፡

ኢትዮጵያዊነት በማይናድ ጠንካራ አለት ላይ የተገነባ የማይነቃነቅ የማይፈርስ ሕዝቦችን በማይበጠስ ክር ያስተሳሰረ በመሆኑ በየቦታው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚደረጉት ሴራዎች ሁሉ አሁንም እየከሸፉ እየመከኑ ያሉት በሕዝቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ በአራቱም ማእዘናት ሄደው ቢኖሩ ቢሰሩ ሀብትና ንብረት ቢያፈሩ ቢወልዱ ቢከብዱ ሀገራቸው ናት፡፡

ክልልህ አይደለም ለቀህ ውጣ፤ ሀብትህን ትተህ ሂድ ወይንም እናቃጥለዋለን የሚለው አካሄድ የዜጎችን ሕይወት ማጥፋት ንብረታቸውን ማውደም የመጨረሻውን የድህነት ኑሮ ለፍተው ጥረው ግረው በሚኖሩ ከድህነት ጋር ትንቅንቅና ትግል በሚያደርጉ ዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ መዝመት በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ ሕዝብ ከሕዝብ (ለዛውም የአንድ አገር) አይጋጭም፤ ሊጋጭም አይችልም፡፡

ይህንን የሚቀሰቅሱትንና የሚጭሩትን መግታት በየአካባቢው ሰላምን ማስፈን ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ስራ ነው፡፡ ተጋብቶ ተዋልዶ በክፉውም በደጉም ሁኔታ ውስጥ ብዙ ዘመናትን ያሳለፈ አብሮነቱን በብዙ ማሕበራዊ ድሮች በማይበጠሱ ግንኙነቶች አጥብቆ ያሰረና ጠብቆ የኖረውን ሕዝብ ማናከስ ማባላት መቸም ሰላምን አይፈጥርም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢው ጥገኛው የጥበትና ትምክህት ኃይሉ የፈጠሩት ቀውስ በመሆኑ በቀላሉ የሚታለፍ አይሆንም፡፡

በዚህ ረገድ ሰላምና መረጋጋቱን የማስፍን ስራዎች በሁሉም የኃይማኖት አባቶች በሲቪክ ማሕበራት ሰፊ ማሕበራዊ መሰረት ባላቸው እድሮች ጭምር መሰራት ይገባዋል፡፡ ሁከቱን ለማስፋት የሚንቀሳቀሰው አክራሪና ጽንፈኛ ኃይል ባሕር ማዶ  ሁኖ በማሕበራዊው ሚዲያና በፌስ ቡክ ጭምር የሚያደርገው ዘመቻ ለሀገሪቱና ለሕዝብ በፍጹም የሚበጅ አይደለም፡፡

በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን በግልጽ በመወያየት ልዩነትን በልዩነት ይዞ በጋራ በሚያቆሙ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመቆም ሀገርን የህዝብን ሰላም መጠበቅ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ዙሪያገባዋን ከጥንትም ግዜ ጀምሮ ሰላምዋንና መረጋጋትዋን በማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች እይታ ስር መሆንዋን ከዚህ ትርምስ ጀርባም ዋነኛው ኪራይ ሰብሳቢው የጥበትና ትምክህት ኃይሉ ቢሆንም እነሱም ከጀርባ እንዳሉ መታወቅ አለበት፡፡

የፈለገው ይምጣ የሚለው የአክራሪውና የጽንፈኛው ኃይል የሀገርን ውድመትና ጥፋት ናፋቂነት ሀገርን ከማውደም ሕዝብን ለእልቂትና ለትፋት ከመጋበዝ ውጭ ምንም አይነት የተሻለ ነገር ለሀገር አያመጣም፡፡ በዚህ መልኩ ስልጣን እንይዛለን ብለው የሚያስቡ የዲያስፖራው አክራሪ ኃይሎች በትክክል የኢትዮጵያን ሁኔታ አላነበቡትም ወይንም አያውቁትም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሕልማቸውን ለማሳካት አይችሉም፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀውና ተደጋግሞም እንደተገለፀው፤ ዋነኛው የሀገራችን ጠላት ድሕነትና ኋላቀርነት ነው፡፡ ከድህነት ለመውጣት አሁን የተጀመሩትን ሀገራዊ የልማትና የእድገት ስራዎች አጠናከሮ መቀጠል፣ የበለጠ መትጋትና መስራት፣ በሚገኘውም ውጤት ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እየተሄደበት ያለውን ጉዞ ለማሳካት ታላቅ ርብርብ ማድረግ ሲገባ ሀገራዊ ትርምስና ሁከት አመጽ ውስጥ መግባት ኢኮኖሚውን ለማሽመድመድ መንቀሳቀስ ያልተጠበቀ ጥፋት ከማስከተሉ ውጪ የተረጋጋ ሰላም ያላት ሀገርን ጠብቆ ለመዝለቅ አያስችልም፡፡ ለዚህም ነው ዘላቂ ሰላም ያሻናል ይምንለው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy