Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝቦች ጥቅም የሚረጋገጠው በዴሞክራሲያዊ አንድነት ነው

0 321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝቦች ጥቅም የሚረጋገጠው በዴሞክራሲያዊ አንድነት ነው

አሜን ተፈሪ

 

ያለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት የአብዮታዊ ዴሞክራቶች ብቃት እና ግለት የቀነሰባቸው ዓመታት ናቸው፡፡ በዚያው አንጻር ጥገኛ ኃይሎች የተነቃቁበት እና የሐገሪቱን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ዓላማዎች ማጨናጎል የሚችሉ ኃይሎች መሆናቸውን በተጨባጭ ለማየት የቻልንባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡ ጥገኛ ኃይሎች የምንላቸው፤ የጠባብነት እና የትምክህተኝነት አጀንዳ ያላቸውን ኃይሎች ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ፖለቲካዊ ኃይሎች ቢያንስ ባለፉት 25 ዓመታት በሐገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሲያነጋግሩ የቆዩና ናቸው፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፀረ ጥገኝነት ትግሉ መቀዛቀዝ በማሳየቱ እና መሪው ድርጅት በመዘናጋቱ ጎልተው መውጣት ችለዋል፡፡

 

እነዚህ ኃይሎች ሰዎችን በብሔራዊ ማንነታቸው ለይቶ የማየት አመለካከት ያላቸው ናቸው፡፡ አንዱ ሌሎችን በንቅት እና በጥላቻ በመመልከት፤ ሌላው ሌሎችን በጥርጣሬ ዓይን የማየት አዝማሚያ ያላቸው ሆነው ሳለ፤ ሁለቱም ሰዎችን በብሔራዊ ማንነታቸው ለይቶ የማየት አመለካከት የያዙ በመሆናቸው በመሠረታዊ ይዘት ተመሳሳይ ይሆናሉ፡፡ አንዱ የራሱን ብሔር የበላይነት በማስፈን የጥገኛ ገዥ መደቡን ፍላጎት በበላይነት ለማስፈፀም ይጣጣራል፡፡ ሌሎችን በጥላቻና በንቀት በማየትና ራስን የበላይ አድርጎ በመውሰድ አባዜ ይኮፈሳል፡፡ ሌላው ራስን በመከበብ እና ተጠቂ በመሆን ስሜት ውስጥ በመክተት የተናጠል መፍትሄዎችን የመሻትና የመከተል ዝንባሌን ያንጸባርቃል፡፡

 

የትምክህተኛው የሁል ጊዜ ህልሙ ተወደደም ተጠላም በአንድነት ስም የተለያዩ ብሔር ብሄረሰቦችን መጠቅለል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የትምክህት አመለካከት ከስልጣን የተወገደ አመለካከት እንጂ ስልጣን ላይ ያለ ገዥ አመለካከት አይደለም፡፡ የአሁኖቹ የትምክህት ኃይሎች አንድም በመሠረቱ ያለፈው ገዥ መደብ ቅሪቶች ወይም ደግሞ አዳዲሶቹ ጥገኞች እና የእነሱ ጠበቆች ናቸው፡፡ ስለሆነም በወሳኝ መልኩ የተሸነፈ አመለካከት ነው፡፡

 

በሌላ በኩል ያለው ጠባብነት ከትምክህት በባሰ አወዛጋቢ ገጽታ ያለው ነው፡፡ ጠባብነት እንደዬ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ በብዙ መልኩ የሚገለፅና ወጥ የሆነ ትርጓሜ ለመስጠት የሚያስቸግር ነው፡፡ ሆኖም ጠባብነት፤ በዋናነት ራሱን ለሥልጣን በተስፈኝነት ከሚያጨው ንዑስ ባለሃብት የሚመነጭ አመለካከት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ጠባብነት ትምክህት ባለበት ሁሉ የሚኖር፤ ብሔራዊ ጭቆናና አድሎ የሚወልደው ነው፡፡ ጠባብነት ያለፉ ቁርሾዎችን በማሰብ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት ጀርባውን በመስጠት መነጠልን የሚያቀነቅን አመለካከት እና ተግባር ነው፡፡

 

ይህ እንዳለ ሆኖ ጠባብነት ራስን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቸኛ ባለቤት እና ጠባቂ አድርጎ የማሰብና ሌሎችን በጥርጣሬ ዓይን የማየት አዝማሚያ ሆኖም ይገለፃል፡፡ ራስን በመከበብና ተጠቂ በመሆን ስሜት ውስጥ በመክተት የተናጠል መፍትሄዎችን የመሻትና የመከተል ዝንባሌ ነው ጠባብነት፡፡ የዚህ አስተሳሰብ አቀንቃኞች፤ ጠባብነት ገዥ የመሆን ፍላጎታችውን የሚያረካላቸው በመሆኑ ለራሳቸው አጥብቀው በመያዝ ሳይወሰኑ በጠባብነት የማይጠቀሙትን የህብረተሰብ ክፍሎችም የአስተሳሰቡ ተሸካሚ ለማድረግ ሌት ተቀን ይጥራሉ፡፡

 

የጠባቦቹ ህልም የእኛ ነው የሚሉትን ህዝብ ለብቻ ገንጥለው የህዝብን ጥቅም ሳይሆን የቡድን ፍላቶችን በአቋራጭ ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህም ካልሆነ አሁን እያደረጉ እንዳሉት ሁሉ በጥላቻ ዘመቻና አንዱን በአንዱ ላይ እያነሳሱ ሐገርን መበተን ነው፡፡

 

ጠባብነት እና ትምክህተኝነት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መሠረታዊ ባህርያት የሚጋጩ ናቸው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ከጠባብነትና ትምክህተኝነት የሚለይበት አንደኛውና ዋነኛው መሠረታዊ ነጥብ አወጋገኑ፣ የወዳጅና የጠላት አፈራረጁ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወዳጅና ጠላትን ከብሔራዊ ምንጭ እየተነሳ አይፈርጅም፡፡ የአገሬ ጅም ይብላኝ የሚል መፈክር የለውም፡፡ ሰዎችን ከማህበራዊ ምንጫቸው፣ ከተጨባጭ ፖለቲካዊ አቋማቸውና ተግባራቸው እየተነሳ ነው የሚፈረጀው፡፡ አንድ ሰው አርሶ አደር ከሆነ ወላይታ ይሁን ኮሬ፣ አማራ ይሁን ጉራጌ፣ በአርሶ አደርነቱ ብቻ ወዳጄ፤ የትግል አጋሬ ነው ብሎ ይወስደዋል፡፡ አንድ ሰው ላብ አደር፣ የከተማ ድሃ ምሁር፣ ወዘተ…ከሆነም በተመሳሳይ መልኩ ይፈርጀዋል፡፡

 

አንድ ሰው ጥገኛ ከሆነ ትግራይም ይሁን ኦሮሞ፣ ሲዳማም ይሁን አገው ጠላት ነው ብሎ ይፈርጃል፡፡ የማንም ጅብ፣ ጅብ ስለሆነ ጠላቴ ነው ብሎ ይደመድማል፡፡ ከበርቴው ከየትም ብሔር ይምጣ ወላዋይ አቋም ያለው ኃይል ነው፤ ከጠላቶች ጋር እንዳይሰለፍ ማድረግ አለብኝ ብሎ ይነሳል፡፡

 

በተቃራኒው ቀደም ሲል እንዳየነው የጠባብነትና ትምክህተኝነት አስተሳሰብ መሠረታዊ ይዘት አንድ ነው፡፡ ሁለቱም ወዳጅና ጠላት ለመለየት የሚጠቀሙበት መስፈርት የየትኛው ብሔር ተወላጅ ነው? የሚል ነው፡፡ ሰዎችን በብሔራዊ ምንጫቸው እና በብሔራዊ ምንጫቸው ብቻ ወዳጅና ጠላት ብሎ የሚፈርጁ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ የትግራይ ጠባብነት፤ ሁሉም የትግራይ ተወላጆችን በብሔራዊ ምንጫቸው ብቻ በወዳጅነት ያሰልፋቸዋል፡፡ የፖለቲካ አቋማቸውና ተግባራቸው ምንም ይሁን ምን የትግራይ ተወላጆች እስከሆኑ ድረስ የኛ ወገኖቻችን ናቸው ይላል፡፡ የሌላ ብሔር ተወላጆችን ግን በብሔራዊ ምንጫቸው ብቻ ሣይሆን በተጨባጭ ወይም በይሆናል ጠላትነት ያስቀምጣቸዋል፡፡ አማራውን፣ ኦሮሞውን ወዘተ… አንድም በተጨባጭ ያለ ጠላት ወይም ነገ ተነገ ወዲያ ጠላት መሆናቸው የማይቀሩ ሰዎች አድርጎ ያስቀምጣቸዋል፡፡

 

የኦሮሞ ጠባብነትም በተመሳሳይ መልኩ ኦሮሞውን በሙሉ በወዳጅነት ሌላውን በተጨባጭ ወይም በይሆናል ጠላትነት ይፈርጃል፡፡ የአማራ ትምክህተኝነትም እንዲዚሁ ሁሉንም አማራ በወዳጅነት፤ የሌላ ብሔር ተወላጅን በተጨባጭ ወይም በይሆናል ጠላትነት ደረጃ ይፈርጃል፡፡ በሌላውም አካባቢ ይኸው ነው፡፡

 

በአጭሩ የጠባብነትና ትምክህተኝነት መለያ ነጥብ ሰዎችን በማህበራዊ ቦታቸው፣ በተጨባጭ ፖለቲካዊ አመለካከታቸውና ተግባራቸው ሳይሆን በብሔራዊ ምንጫቸው ወዳጅና ጠላት ብሎ የሚፈርጅ ከመሆኑም በላይ የወንዜ፣ የአገሬ ጅብ ይብላኝ የሚል መፈክር አንግቦ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

 

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚጠቀምበት መስፈርት ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው፡፡ አንድን ሰው የየትኛው የህብረተሰብ ክፍል አባል ነው በሚል እንጂ፤ ሰዎችን በብሔራዊ ምንጫቸው ወዳጅና ጠላት ብሎ የሚፈርጅ አይደለም፡፡

 

ስለሆነም፤ ሰዎችን ከብሔራዊ ምንጫቸው ብቻ እየተነሳ የሚጣላና የሚወድ፣ የሚያምንና የሚጠረጥር፣ የሚያርቅና የሚያስጠጋ፣ ምንም መፈክር ቢሸከም፣ ምንም ዓይነት ሽፋን ቢጠቀም ጠባብ/ትምክህተኛ ከመሆን በምንም ዓይነት ምክንያት ሊድን አይችልም፡፡ በአንጻሩ፤ ሰዎችን ከማህበራዊ ቦታቸው እየተነሳ የሚፈርጅ፣ የሚጠላና የሚወድ፣ የሚያርቅና የሚያስጠጋ ሌላ ችግር ቢኖርበትም በመሠረታዊ ባህርይው አብዮታዊ ዴሞክራት መሆኑ አይቀርም፡፡

 

አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ከጠባብነት/ትምክህተኝነት የሚለይበት ዋነኛው ነጥብ፤ ከጠባብነት/ትምክህተኝነት በሰዎች ብሔራዊ ማንነት ላይ የሚመሰረት አመለካከት ሲሆን፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲያ ከማህበራዊ ቦታና አሰላለፍ የሚነሳ አመለካከት ነው፡፡ ከዚህ ተለይቶ የማይታየው ሁለተኛው መሠረታዊ የልዩነት ነጥብ፤ የተጨባጭ ፖለቲካዊ አቋምና ተግባር ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ የብሔራዊ ማንነት እና የማህበራዊ ቦታ እና አሰላለፍ ትርጉም የሚኖራቸውና በተግባርም የሚረጋገጡት በተጨባጭ ፖለቲካዊ አቋም፣ ተጨባጭ ሥራና ተግባር ሲደገፉ ብቻ ነው፡፡

 

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያን ህዝብ የዴሞክራሲና የልማት ጥማትን ማርካት የዓላማው አልፋና ኦሜጋ አድርጎ ይወስዳል፡፡ የመንግስት ሥልጣን የጥቂቶች መክበሪያ መሣሪያ ሳይሆን የህዝቦች የዴሞክራሲ መብት ማረጋገጫ፣ ህዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣን ልማት ማምጫ፣ ሙስናንና ግለኝነትን መንቀያ መሣሪያ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለአርሶ አደሩ፣ ላብ አደሩ፣ የከተማው ጭቁን ህዝብ፣ ወዘተ….. የቆመ ነው ሲባል ትርጉም የሚኖረው ይህ በተጨባጭ ፖለቲካዊ አቋምና ተግባር ሲገለፅ ብቻ ነው፡፡ ብሔራዊ ምንጫቸው ምንም ይሁን ምን ከአርሶ አደሮች ጋር የወገነ አብዮታዊ ዴሞክራት በእርግጥ ከእነዚህ ጋር የወገነ መሆኑን ማረጋገጥ የሚቻለው አርሦ አደሮች በየደረጃውና በሰፊው በዴሞክራሲያዊ መብታቸው እንዲጠቀሙ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲኖራቸው ሲያደርግ እንዲሁም ሁሉንም ጉዳይ ከዚህ አንፃር ብቻ እያየ አቋም የሚወስድ ከሆነ ብቻ ነው፡፡

 

ከአርሶ አደሩ ጋር የወገነ አብዮታዊ ዴሞክራት መሆኑ የሚረጋገጠው አርሶ አደሩ በስፋት ተሳታፊና በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ ለሚሆንበት ፈጣን ልማት ሌት ተቀን የሚረባረብ፤ ማንኛውንም ጉዳይ ላይ ከዚህ አንፃር ብቻ እየተነሳ አቋም የሚወስድና ከማንኛውም ፀረ ልማት አቋም በተለይም ከፀረ ዴሞክራሲና ከሙስና የፀዳ መሆኑ በተግባር ሲያሳይ ነው፡፡ ለአርሶ አደሩና ለጭቁኖች ቆሜአለሁ ቢልም በተግባር ግን የአርሦ አደሩን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ካላረጋገጠ፣ ተጠያቂነት እና ግልፅነት በሌለበት ሁኔታ በሙስና እና በፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ውስጥ ከተዘፈቀ፣ ጥርት ያለ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አቋም በተጨባጭ እስካልያዘ ድረስ ምንም ቢደረግ ከጠባብነት/ትምክህተኝነት አመለካከት ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡

 

ስለሆነም የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና የጠባብነት/ትምክህተኝነት አመለካከት ዋነኛ ልዩነት በአወጋገን፣ በአሰላለፍ፣ በተጨባጭ የፖለቲካ አቋምና ተግባር የሚገለፅ አወጋገን ነው ሲባል ሌላ ገፅታም አለው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሁሉን ነገር ከህዝቡ በተለይም ከአርሦ አደሩ ጥቅም እየተነሳ ስለሚያየው የህዝቦች ሰላም፣ ፈጣን ዕድገትና ዴሞክራሲ ሊረጋገጥ የሚችለው በፈቃደኝነት የሚኖሩባት የጋራ የሆነች አዲስ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ስትገነባ መሆኑን ይገነዘባል፣ በጥብቅም ያምንበታል፡፡ ኢትዮጵያ ከተበታተነች የህዝቦቿ የልማት አቅም ተበታትኖ፣ ሰፊ የአገር ውስጥ ገቢ የመፈጠሩ ዕድል ከስሞ፣ ፈጣን ልማት የሚባል ነገር የህልም እንጀራ ሆኖ እንደሚቀር በጥብቅ ይገነዘባል፡፡

 

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮ መኖርን ጠልተው የሚበታተኑት በውስጣቸው የጠባብነት/ትምክህተኝነት አስተሳሰብ የበላይነት ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ የበላይነት ከሰፈነ በፍቅርና በእኩልነት አብረው ይኖራሉ እንጂ አይበታተኑም፡፡ ጠባብነት/ትምክህተኝነት የበላይነት አግኝቶ መበታተን ከመጣ ከፍተኛ ቀውስና መናቆር ይኖራል፡፡ መበታተኑ ሲመጣም በህዝቦች መካከል ለመገመት የሚያዳግት እልቂትና መተራረድ እንደሚኖር አያከራክርም፡፡

 

በመሆኑም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለህዝቦች መናቆር ሳይሆን በእኩልነትና በመብት መከበር ላይ ለተመሰረተ አንድነት፣ ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ይቆማል፡፡ ህዝቦች እኩልነታቸውና መብታቸው ተከብሮ፣ ሠላም ዴሞክራሲና ልማት የሚያገኙት አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በጋራ ሲገነቡ ብቻ እንደሆነ ያምናል፡፡ ይህችን የጋራ ቤት በጋራ ስንገነባ ብቻ ነው የእያንዳንዱ ብሔር ጭቁን ህዝብ መብትና ጥቅም የሚከበረው ብሎ ያምናል፡፡ የጋራ ቤት የሆነችውን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚንድ፣ የሚሸረሽርና የሚያዳክም ነገር በሙሉ የእያንዳንዱ ብሔር ጭቁን ህዝብ መብትና ጥቅምን ያለጥርጥር የሚንድ ይሆናል ብሎ ያምናል፡፡ ስለሆነም ለብሄሮች መብትና እኩልነት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ በዚህ የጋራ ቤት ግንባታ ሥራ ውስጥ ሆኖ የሚፈፀምና የሚሳካ እንጂ ከዚህ ውጭ የእያንዳንዱን ብሄር ጭቁን ህዝብ መብትና ጥቅም በተናጠል ለማሳካትና ለማራመድ በሚደረግ ሙከራ እንደማይሆን በጥብቅ ያምናል፡፡

 

ይልቁንም የእያንዳንዱን ብሄር ጭቁን ህዝብ መብትና ጥቅም በተናጠል ለማራመድ የሚካሄድ ሙከራ ዞሮ ዞሮ የሁሉም ህዝቦች መብትና ጥቅም የሚከበርበት ብቸኛ አማራጭ የሆነውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት በመናድ የሁሉም ብሔሮች ጭቁን ህዝቦች ለእልቂት፣ ለፀረ ዴሞክራሲና ለከፋ ድህነት የሚጋለጡበት፣ የጭቁን ህዝቦችን መብትና ጥቅም ክፉኛ የሚፃረር፣ ስለሆነም የጥገኝነት፣ የጠባብነት/ ትምክህተኝነት አመለካከት መሆኑን በጥብቅ ያሰምርበታል፡፡ ይህን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት አጥብቀን በመያዝ ሐገራችንን ከጥገኞች ፈተና እንታደግ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy