Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴ ግድቡ የተሻለ ህይወት አለያም በድህነት የመማቀቅ ጉዳይ ነው

0 630

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዳሴ ግድቡ የተሻለ ህይወት አለያም በድህነት የመማቀቅ ጉዳይ ነው

ብ. ነጋሽ

ኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመሩ ሰባት ዓመት ሊሞላቸው ወራት ቀርቶታል። ቁልቁል የግድቡን መሰረት በመቆፈር የጀመረው የግድቡ ግንባታ ስራ አሁን በአባይ ወንዝ ግራና ቀኝ ያሉትን ተራራዎች እየታከከ ጎልቶ የሚታይ ግዙፍ አካል ለመሆን በቅቷል። እስካሁን ይፋ በተደረገ መረጃ የግድቡ ግንባታ ከ60 በመቶ በላይ ተከናውኗል። በግዙፍነቱ በዓለማችን እስከ 10ኛ ባሉ ደረጃዎች ውስጥ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሃብት ነው የሚገነባው። ከኢትዮጵያውያን ውጭ በብድርም ይሁን በድርሻ በግድቡ ግንባታ ውስጥ እጁን ያስገባ የውጭ አካል የለም። ይህ ግድቡን ፍጹም ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል።

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ልዩ የሚያደርገው በዓለም በርዝመቱ የቀዳሚነትን ደረጃ በያዘው ወደግብጽና ሱዳን የሚፈሰው የአባይ/ናይል ወንዝ ላይ መሰራቱ ነው። በተለይ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት የሆኑት ሱዳንና ግብጽ፣ ለወንዙ 80 በመቶ ውሃ የምታበረክተውን  ኢትዮጵያን ጨምሮ የሌሎቹን የወንዙ ተጋሪ ሃገራት ስምመነት ሳያገኙ ውሃውን ሲጠቀሙ የቆዩ መሆናቸው ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ የተፋሰሱን ሃገራት  ሳያሳውቁና ስምመነታቸውን ሳያገኙ ከመጠቀም ባሻገር የሌሎቹን ሃገራት የመጠቀም መብት ሲቀናቀኑ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ በአባይና በአባይ ገባር ወንዞች ውሃ ለመጠቀም የምታደረገው የትኛውም እቅድና ሙከራ በግብጽ ጥብቅ ተቃውሞ ሲገጥመው የቆየው ለዚህ ነበር። ግብጽ በተለይ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝና በገባሮቹ ወንዞች ውሃ ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት ስታደናቅፍ ቆይታለች። ይህን የምታደርገው ለፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና መንግስታት እንዳታገኝ በማድረግ ነበር።

በተለይ በግብጽ በኩል ኢትዮጵያ በድንበሯ ውስጥ የሚፈሰውን የአባይና ገባር ወንዞች ውሃ እንዳትጠቀም የማደረግ አቋም በራሱ ኢትዮጵያን ከመጠቀም አግዷት ቆይቷል ማለት አይቻልም። ኢትዮጵያ የአባን ወሃ ሳትተቀም የቆየችው ውሃውን ለማልማት የሚያስፈልግ ሃብት በማጣቷ ብቻ እንጂ ተግብጽን ፍላጎት አክብራ አልነበረም። ለግብጽ ጉልበት የሰጣት የኢትዮጵያ ድህነት ነበር። ግብጽ አበዳሪ መንግስታትና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ላይ ጫና በማሳደር ኢትዮጵያ የበይ ተመልካች ሆና እንድትኖር የማድረግ እድል አግኝታ ቆይታለች።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በድህነት የተሸበበ የኢትዮጵያ እጅ መፈታት ጀምሯል። በመሆኑም በአባይ ተፋሰስ ወንዞች የመጠቀም መብቷ በግብጽ ፍላጎት ሊገደብ እንደማይችል በተጨባጭ አሳይታለች። በመጀመሪያ ድህነት ሸብቦት የነበረው የኢትዮጵያ እጅ የተፈታው በ2001 ዓ/ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት በጀመረው የተከዜ የሃይል ማመንጫ ግድብ ነበር። 300 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ሃይል የሚያመነጨው የተከዜ ግድብ በ360 ሚሊየን ደላር ወጪ ተደርጎበታል። ይህ በወቅቱ የዓመቱ ድንቅ ፕሮጀክት ለመባል በቅቶ የነበረ ግድብ የአባይ ተፋሰስ ወንዝ ላይ የተሰራ የመጀመሪያው የልማት ፕሮጀክት ነው።

በመቀጠል በ2004 ዓ/ም በዚሁ የአባይ ተፋሰስ ላይ የተሰራው የጣና በለስ ፕሮጀክት ተመረቀ። የጣና በለስ ሁለገብ ፕሮጀክት 460 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ሃይል ከማመንጨት ባሻገር እስከ 200 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አገልግሎት የሚውል ነው። ይህ በአባይ ተፋሰስ ላይ ኢትዮጵያ የሰራችው ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

ኢትዮጵያ እነዚህን ሁለት ፕሮጀክቶቸ የሰራችው ሙሉ በሙሉ በራስዋ አቅም ነበር። በዚህም የግብጽ ፍላጎት ሊገድባት እንደማይችል አሳይታለች።

ኢትዮጵያ መጋቢት 24፣ 2003 ዓ/ም በአባይ ወንዝ ላይ ሊሰራ የሚችለውን ትልቁን ግደብ መገንባት ጀምራለች፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ16 ዩኒቶች 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት የኤለትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም አለው። ግድቡ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ሲኖረው፣ ገንብቶ ለማጠናቀቅ 80 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል። የታላቁ የኢተዮጵያ ህዳሴ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በግዙፍነቱ በአፍሪካ ቀዳሚ ነው። የግድቡ ግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ነው የሚሸፈነው። በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያውያን ፕሮጀክት ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዓላማ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጨት ነው። የውሃ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ውሃን እንደፍጆታ ስለማይጠቀም በውሃ ፍሰት መጠን ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ አያሳድርም። በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ማለትም ሱዳንና ግብጽ ቀደም ሲል ሲያገኙት የነበረው የውሃ ፈሰት መጠን በግድቡ ምክንያት አይቀንስም። ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በይፋ ሲጀመር ይህን አሳውቃለች። ሱዳንና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ምክንያት የውሃ ፍሰት መቀነስ የገጥመናል የሚል ስጋት ውስጥ እንዳይገቡ መተማመኛ ይሆን ዘንድ ከሶስቱም ሃገራት የተወጣጣና ዓለም አቀፍ ሙያተኞችን የያዘ ቡድን ግድቡ የሚኖረውን ተጽእኖ እንዲያጠና ሃሳብ አቅርባ ይህ ተግባራዊ ተደርጓል። የሶስትዮሽ አጥኚ ቡድኑ የግድቡ ግንባታ የአባይ የውሃ ፍሰት ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ እንደማያስከትል አረጋግጦ፣ ይሁን እንጂ በተለይ ከግድቡ ውሃ አሞላልና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሊያሳድር የሚችለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተፅእኖን በተመለከተ ሞያዊ ጥናት እንዲካሄድ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

በዚህ ምክረ ሃሳብ መሰረት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በጋራ ቢ አር ኤል የተባለ አጥኚ ቡድን ቀጥረዋል። ለአጥኚ ቡድኑ የጥናት መመሪያ ለማዘጋጀት ሶስቱ ሃገራት በውሃ ሚኒስትሮቻቸው ደረጃ ውይየቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሶስቱ ሃገራት እስከአሁን 17 ግዜ ተገናኝተው ተወያይተዋል። በቅርቡ በካይሮ በተካሄደው 17ኛው ስብሰባ ላይ ግን ግብጽ ኢትዮጵያን የማይመለከተው እ ኤ አ በ1959 ዓ/ም ከሱዳን ጋር ያደረጉት የውሃ ድልድል ስምመነት የጥናቱ መመሪያ መነሻ እንዲሆን የሚል ሃሳብ አቅርባለች።

አንድ ስምምነት በግለሰቦች፣ ህጋዊ ሰውነት ባላቸው ተቋማት፣ በመንግስታት ላይ የገዢነት ጉልበት የሚያገኘው እነዚህ አካላት ስምመነቱ ውስጥ ሲኖሩበት ብቻ ነው። ወደሱዳንና ግብጽ ለሚፈሰው የአባይ ውሃ ከ80 በመቶ በላይ የምታበረከተው ኢትዮጵያ በ1929 እና በ1959 ዓ/ም የተፈረመው የውሃ ድርሻ ስምምነት ውስጥ የለችበትም። በመሆኑም ለዚህ ስምመነት ተገዢ እንድትሆን ማድረግ የሚያስችል ምንም አይነት የህግ መርህ የለም። እስካሁን በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መሃከል ወይም በሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት መሃከል የተደረሰ አንድ የውሃ ድርሻና አጠቃቀም ስምመነት የለም። እናም ግብጽ የህዳሴውን ግድብ ተጽእኖ አስመልክቶ የሚደረገው ጥናት ኢትዮጵያን የማይመለከተው የ1959 ዓ/ም የውሃ ድርሻ ስምምነት መነሻ ያድርግ በሚል ያቀረበችው ሃሳብ ተቀባይነት የለውም። ኢትዮጵያ ይህን የግብጽ ሃሳብ እንደማትቀበለው በይፋ አሳውቃለች። ይህ ተገቢና ህጋዊ አቋም ነው።

በተባበሩት መንግስታት ተቀባይነት ያገኘው የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የውሃ አጠቃቀም መርህ ሁለት ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ነው። የመጀመሪያው ሁሉም የተፋሰስ ሃገራት ፍትሃዊ (equitable) የውሃ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚል ሲሆን፣ ይህነኑ መነሻ በማደረግ የላይ ተፋሰስ ሃገራት የውሃ አጠቃቀም በታችኞቹ ላይ ጉልህ ጉዳት (substantial injury) የማያደርስ መሆን አለበት የሚል ነው።

እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ በመሆኑ በግብጽ ላይ ጉልህ ተጽእኖ አያሳድርም። ከኢትዮጵያ የሚወጣውን ውሃ የአንድ ዓመት ፍሰት ያህል ማለትም 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ወሃ የሚይዘው ግድብ በሚሞላበት ወቅት ግብጽ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ተጽእኖ ለማስቀረት የግድቡ አሞላል ጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ኢትዮጵያ ፍቃደሽነቷን አሳውቃለች።

እንግዲህ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ እውነታዎች በአጭሩ ይህን የሚመስሉ ናቸው። ሰሞኑን አንዳንድ የግብጽ መንግስት ባለስልጣኖችና ሚዲያዎች የሚያሰሟቸው የአባይ ውሃን አናስነካም የሚሉ ፉከራ ቀመስ አስተያየቶች መሰረተ ቢስ ናቸው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀድሞውኑም ወደግብጽ የሚፈሰውን ውሃ አይነካም። ምናልባት ከግድቡ ውሃ አሞላል ጋር ተያይዞ የሚኖር ተጽእኖም ካለ ይህን ለመቀነስ ሳይንሳዊ ስርአት ማበጀት ይቻላል።

ግብጾች ሁሌም ማስታወስ ያለባቸው በቅድሚያ የ1929 እና 1959 ዓ/ም የቅኝ ግዛት የውሃ ድርሻ ስምመነቶች ኢቶዮጵያን የማይመለከቱ መሆናቸውን ነው። የህዳሴው ግድብ ወደግብጽ የሚፈሰው ውሃ ላይ ተጽእኖ የማያሳድር ከመሆኑ በተጨማሪ ለኢትዮጵያውያን በልማት የተሻለ ህይወት የመኖር ያለመኖር ጉዳይ መሆኑንም ማስታወስ አለባቸው። ይህ ደግሞ የህልውና ጉዳይ ነው።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy