Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመልማት መብታችንን ያረጋገጠ ሜጋ ፕሮጀክት

0 277

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመልማት መብታችንን ያረጋገጠ ሜጋ ፕሮጀክት

ስሜነህ

በከፍተኛ የህዝብ መነሳሳትና ተሳትፎ የታጀበው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እየተከናወነ ነው፡፡ በዚህ የግንባታ ሂደት ደግሞ በርካታ እና ውስብስብ የሆኑ ችግሮች ከውስጥም ከውጭም እየገጠመው ነው። ከውጭ የግብጽ አይነቶቹ መርህ የለሽ ተቋማት ከሶስትዮሽ ስምምነት ውጭ የሆኑ አፈንጋጭ ፕሮፖጋንዳዎችን በመንዛት፤ ከውስጥ ደግሞ ስትራቴጂካል የሆነውን የግብጽ ፕሮፖጋንዳ ተከትለው የሚፈሱ ሚዲያዎችና በህግ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጭ ቴክኒካል በሆኑ የፕሮጀክቱ ጉዳዮች ላይ ገብተው የሚፈተፍቱ ተቋማት ለፕሮጀክታችን ፈተና ሆነዋል። የግድቡን የግንባታ ሂደት ሥፍራው ድረስ ሄደው የጎበኙ ኢትዮጵያውያንም ስለግንባታው ፈታኝነት እና የገንቢዎቹ ቁርጠኝነት የነበራቸውን ምልከታ በተለያየ መልኩ እና በጋለ ስሜት እየገለጹ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከ4መቶ ሺ በላይ ዜጎች ግድቡን ስለመጎብኘታቸው ሰሞንኛ ከነበረው ስድስተኛ ዙር ጉብኝቴ ማረጋገጥ ችያለሁ። ይህም ለሃገራችን ህዝብና ገንቢዎቹ ከፍተኛ መነሳሳትና መነቃቃት ከፈጠሩ ምክንያቶች መሃል  በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡

10∙5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የኮንክሪት ሙሌት የሚያስፈልገው ዋናው ግድብ የ7∙7 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሙሌት ተከናውኖለታል። የባለኮርቻ ቅርጽ የሆነው ሁለተኛው ግድብ ከ5∙2 ኪሜ ርዝመትና 50 ሜ ቁመት የኮንክሪት ልባጥ የቀረው የተወሰነ ብቻ ሲሆን፤ ይህም በራሱ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ አብሳሪ ነው፡፡ በግንባታው ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ሽንጣቸውን ገትረው ሌት ተቀን በመትጋት ላይ ናቸው፡፡ በራስ አቅም ለሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያውያንም ምናልባትም ከአቅማቸውም በላይ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በንቃት እየተሳተፉ ነው፡፡ ስለሆነም ፕሮጀክቱ ጀምሮ ከመጨረስ ባሻገር ብዙ አስተሳሰቦችን የያዘና የአስተሳሰብ ልዩነትን ያመጣ ነው።

በውጭም ሆነ በውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እንደቤተሰብ ያስተሳሰረልን ፕሮጀክት ከመሆኑ አንፃር፤ አሁን ዋጋ መሰጠት ካለበት ለመጀመራችን ነው። ታላቁ ግድባችን በኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስክም ተጽእኖ ፈጣሪ ፕሮክት ከሆነ ሰንብቷል።

የዚህ ግድብ መገንባት አላማ የተሻለን ነገ ለመፍጠር ሲሆን፤ ግቡም የተሻለ ኑሮ ለዜጎች ማምጣት ነው። ይሄን ዘመን የማየት ራእይ የነበራቸው ህዝቦች በከፈሉት መስዋእትነት የተገኘ ውጤት ነው። በየሴክተሩም እድገት ለማምጣት መነሻ የሚሆን ፕሮጀክት ሆኗል።

በዚህ ፕሮጀክታችን ላይ ታዲያ ባሳለፍናቸው ስድስት አመታት ሁሉ በግብፅ በኩል የተለያዩ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ የግድቡ መገንባት በግብፅ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር እና ይልቁንም ህልውናቸውን እንደሚፈታተን ጭምር በመግለጽ ተቃውሟቸውን  በተደጋጋሚ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡ እውነታው ደግሞ የዚህ ተቃራኒ መሆኑ በተጨባጭ መረጃዎች ተረጋግጧል፡፡ ግድቡ የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በባለሙያዎች ጥናት ተረጋግጧል፡፡ ፍትሃዊ የአባይ ውሃ ክፍፍልን መሰረት ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑም ተወስቷል፡፡

የግድቡ መገንባት በተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ አለመኖሩ በኢትዮጵያ በኩል ቀድሞ የታወቀና በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የተከናወነው ኢትዮጵያን ጨምሮ ቅሬታ አለን ሲሉ በነበሩት ሀገራትም ነው። በሶስቱ የተፋሰሱ አገራት (ኢትዮጵያ፤ ግብፅ እና ሱዳን) ትብብር  የተመራው ይህ የአዋጭነት ጥናት በእነርሱ ይሁንታ ከተመረጡና ከየአገራቱ የተውጣጡ ስድስት ባለሙያዎችና በሶስቱ አገራት በጋራ የተመረጡ አራት ዓለም ዓቀፍ ባለሙያዎችንም ያካተተ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የጥናትና የዲዛይን ሰነድ በመመርመር፣ በግንባታው ቦታ በመገኘትና ሂደቱን በመቃኘት፣ በሶስቱ አገሮች ውስጥ ለስድስት ጊዜ ያህል በመሰባሰብና በተነሱ ጉዳዮች ላይ በመወያየት እንዲሁም ከግድቡ የግንባታ ተቋራጮችና አማካሪዎች ጋር በመመካከር የደረሰበትን የመጨረሻ የጥናት ውጤት ለሶስቱም  ሃገራት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በተደጋገሚ በስፍራው ላይ የተገኙ የሶስቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ታላላቅ ዲፕሎማቶችም እውነታውን አይተው መስክረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የዲዛይን ስራ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የዲዛይን መመዘኛና መርሆዎች ላይ የተመሰረተ፤ ለሶስቱም አገራት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ፤ እንዲሁም በሁለቱ ተጋሪ አገራት (ግብፅና ሱዳን) ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን ቡድኑ በጥናቱ አረጋግጧል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም በተፋሰሱ አገራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማያስከትል፤ በአንፃሩ ልማትን የሚያፋጥን ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ የመልማት መብቷን ተጠቅማ የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨት  የኃይል ፍላጎቷን ለማሟላት የጀመረችው ጤናማ ፕሮጀክት መሆኑም ተረጋግጧል። የዓለማችን  ትልቅ ስጋት እየሆነ የመጣውን  የአየር ብክለትን ለመዋጋት አገሪቷ እየሄደችበት ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስኬትም ያረጋገጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል የኤልክትሪክ ኃይልን በማመንጨት የዜጎቿን ፍላጎት ለማሟላትና ኢኮኖሚውን የሚሸከም ኃይል ለማቅረብ እየተጋች የመሆኗ ትልቁ ማሳያም ነው ታላቁ  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፡፡

በእነዚሁ  እና ቅሬታ ሲያቀርቡ በነበሩ  ሃገራትም የሚኖረው ጠቀሜታ እጅጉን የላቀ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በቀላሉ የሚያገኙበት ዕድል በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሚፈጠር መሆኑም ላይ ግልጽ እምነት መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከጎርፍ ስጋትና ከደለል ሙሌት ይታደጋቸዋልና፣ በተለይም የተፋሰሱ የታችኛው አገራት ለሆኑት ሱዳንና ግብፅ ጥቅሙ ቀላል አይደለም፤ የውሃውን ትነት መጠን በመቀነስ ረገድም ድርሻው ጉልህ ነው፡፡  

ስለሆነም የግብጽን ስትራቴጂካል የሚዲያ አያያዝ ተከትለን ካልጮህን የሚለው የሚዲያ ፉከራ የማያዋጣና ከመንገድ የሚያስወጣ አካሄድ መሆኑን መገንዘብ፤ እንዲሁም የፕሮጀክቱን የግንባታ ጉዳዮች ለፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ መተው ይገባል። የህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤቱ ህዝብን ከማነቃነቅ ባሻገር ቴክኒካል በሆኑ የምህንድስና ጉዳዮች ላይ እየገባ የሚሰጠው መግለጫ ዋጋ እንዳያስከፍለን መጠንቀቅ ይገባል። በህግ የተሰጠው ስልጣን የህዝብ ተሳትፎን ማረጋገጥ እንጂ ስለውሃ አሞላሉ እና ኮንክሪቱ አልያም ደግሞ የማመንጨት አቅምና የደረሰበትን ደረጃ ማብራራት አይደለም። ይህ ሃላፊነት የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ አልያም ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ብቻ ነው። የሶስትዮሽ ጉዳዮችን የተመለከተው ስልጣንም የአለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ነው። በእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ ያለሙያ እና ያለድርሻ መግለጫ መስጠት ለእነግብጽ ሁነኛ የፍርድቤት የመከራከሪያ ዶሴዎችን ማበጀት ነው። ትውልድን እያነጸ በሚገኘው ፕሮጀክታችን ላይ ሻምፒዮን ለመሆን እየተደረገ ያለው ሩጫ ሊያበቃ ይገባል። የማይነቃነቅ ደፋር ትውልድ ፈጥሮልናልና ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሆኑት ቁመራዎች አንደራደርም። ከድሮ ጀምሮ ወንዙም ተራራውም ነበር፤ ብዙዎችም ግድቡን ተግባራዊ ሊያደርጉት ብዙ ጥረዋል። የሆነው ግን በእኛ ዘመን ነው። ስለሆነም በማናቸውም መልክ አንደራደርም። መተጋገል ካለብንም በውስጥ ካሉና ለሻምፒዮንነት ከሚሯሯጡ አላዋቂ ሳሚዎች ጋር ይሆናል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ፣ በበርካታ መረጃዎች የተደገፈና ግድቡ አሁን ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሳይ ፅሁፍ በቅርቡ ይዥ በመምጣት እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy