Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመረጃ ነጻነት፤ የህዝብ የማወቅ መብት

0 578

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመረጃ ነጻነት፤ የህዝብ የማወቅ መብት

                                                                                        ይልቃል ፍርዱ

ኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት ሕግን ካጸደቁትና በስራ ላይ እንዲውል ካደረጉት ሶስት የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ አንደኛዋ ናት፡፡ እንግሊዝን የመሳሰሉ ሀገራት የመረጃ ነጻነት ሕግን ያጸደቁት በ2004 (እኤአ) ነው፡፡ የመረጃ ነጻነት ሕግ ዜጎች በዜግነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢ መረጃ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፕሬስ የመናገር ነጻነት ሕገመንግስታዊ እውቅናና ጥበቃ ካገኘ ግዜ ጀምሮ ሕጉ ቢኖርም በተግባር፣ በአፈጻጸምና በአተገባበር ደረጃ ብዙ ፈተናዎችና ችግሮች ታይተዋል፡፡ ሕግ አስፈጻሚውን አካል በስፋት ስለሕጉ ምንነት ማስተማር ግድ ይላል፡፡

የሕጉ መኖር ብቻ ሳይሆን የችግሩ ትክክለኛ ምንጭ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው መስክ በማደግ ላይ ያለን ሕብረተሰብ ከመሆናችን አንጻር ስለፕሬስና ስለመናገር ነጻነት ሕገመንግስታዊ መብቱን ጠንቅቆ አውቆ የሚጠቀምበት መብቱ መሆኑን በውል ለይቶ የሚከራከረውና ለማያስከበር የሚሞክረው የሕብረተሰብ ክፍል ቀጥር በአነስተኛ ደረጃ መገኘቱም አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 29 በግልጽ ያሰፈረውን ይህንን ፍጹም የሆነ ሰብአዊ መብት የፕሬስ የመናገር የመደራጀት ሀሳብን በጽሁፍም ሆነ በንግግር የመግለጽ፤ ተንቀሳቅሶ ተዘዋውሮ የመስራት መብቶችንና ሌሎችንም በተመለከተ በግልጽ በሕገመንግስትዋ ውስጥ አስፍራ ሕጋዊ  እውቅና የሰጠች ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡

የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብት ድንጋጌም ይሄንን አሕጉራዊና አለምአቀፋዊ ተቀባይነት የሕግ ድጋፍና መሰረት ያለውን የፕሬስ የመናገር መረጃ በነጻነት የማግኘት ሰብአዊ የሆነ መብትን ይደነግጋል፡፡ በሀገራችን የፕሬስ የመናገርና መረጃ የማግኘት ነጻነት ከሕገመንግስታዊ እውቅናው ጋር ተያይዞ የመጣ ሲሆን ይሕን ተከትሎ በርካታ የግል ፕሬሶች ጋዜጦችና መጽሔቶች ሕጋዊ ፈቃድና እውቅና አግኝተው ለአደባባይ በቅተዋል፡፡

በመጀመሪያ በወጣው የፕሬስ ሕግም ቢሆን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ የተቀመጡ የመንግሰት ሹሞች አስፈላጊ መረጃ ከሚዲያው በሚጠየቁበት በማንኛውም ግዜ እንዲሰጡ ይደነግጋል፡፡

በሁለተኛው ተሻሽሎ የወጣውና ሰፊ ሀገራዊ ውይይት የተደረገበት የመገናኛ ብዙሐንና መረጃ ነጻነት ሕጉ በተጠናከረ ሁኔታ የመንግስት ኃላፊዎች በሚዲያው መረጃ በሚጠየቁበት ሰአት በተለይም ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መረጃ የመስጠት የሕግ ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡

ይሄው ሕግ የጋዜጠኞችን ኢዲቶሪያል ነጻነት በበለጠ መልኩ ያሰፈረበት በጋዜጠኞች የኢዲቶሪል መብት ላይ ሶስተኛ ወገን ጫና ሊያደርግ እንደማይችል፤ በሙሉ ነጻነት ሊሰሩ የሚችሉ መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት የመረጃ ነጻነት ሕጉም ሳይጨመር በራሱ በመገናኛ ብዙሐን ሕጉ መሰረትም ጋዜጠኞች ለሕዝብ መረጃ ለማድረስ በጠየቁበት ሰአት መረጃ የማግኘት ሙሉ መብት አላቸው፡፡

በአለም አቀፉ የፕሬስና የመናገር ነጻነት መብት ተከራካሪዎችም ሆነ በእኛም ብሔራዊ ሕጎች ላይ በግልጽ በሰፈረበት መልኩ ሕዝብ መረጃ የማግኘትና ስለሀገሩ ስለመሪዎቹ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ የማወቅ መብት አለው፡፡ ይሄንን መረጃ ለሕዝቡ የሚያደርሱት የሕትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ጋዜጠኞች መረጃ በጠየቁበት ሰአት ማንኛውም የመንግስት ኃላፊም ሆነ የሕዝብ ተወካይ በግልጽ የተጨበጠ መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት፤ ይሄንን በሕግ የተጣለበትን  ኃላፊነት መወጣት ካልቻለ በሕግ እንደሚጠየቅ በግልጽ ሰፍሮ የሚገኝ ነው፡፡

ሆኖም ግን ሕዝብን የሚመለከቱ የተለያዩ ጥያቄዎች በብዙ መልኩ በጋዜጠኞች ሲነሱ  ለምሳሌ ያህል የኮንዶሚኒየም ቤት ድልደላ ችግር፤ የትራንስፖርት፣ የመልካም አስተዳደር፤  የፍትህ ችግር፣ አድልዎና መድልዎ፣ ፍትሀዊነት የሌለው፣ በሕግ፣ በመንግስት መመሪያና ደንብ ያልተደገፈ ሀብትና ንብረትን ያለአግባብ መጠቀም፣ መንግስታዊ ተቋምን በተሰጣቸው ኃላፊነትና የሕዝብ አደራ በመጠቀም ለግል መገልገያ ያደረጉ ሰዎችን በተመለከተ፤ በቤተሰብ፣ በሀገር ልጅነት የተሞሉ የመንግሰት ተቋማትን በተመለከተ፤ ሕገወጥ ጨረታዎችን፤ የመሬት ቅርምትን፤ ሕገወጥ ካርታ ወዘተ ብዙ ብዙ ሊባሉ የሚችሉ የሕዝብን ብሶትና ምሬትን ያስከተሉ ጥያቄዎችን በተመከለተ በዘርፉ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች መረጃ እንዲሰጡ ሲጠየቁ መረጃ መስጠት  የሕዝብ መሰረታዊ መብት መሆኑን በመዘንጋት ወይንም እንደግል ንብረታቸው በመቁጠር መረጃውን የሚከለክሉ ኃላፊዎች ሞልተው ተርፈዋል፡፡

ጋዜጠኛን የሚያስፈራሩ፣ የሚያሸማቅቁ፣ የተጠየቀው መረጃ ለሕዝብ እንዳይደርስ እንቅፋት ሁነው የሚከለክሉ፣ ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለግለሰብ ሹማምንቶች ታማኝ አገልጋይና ጠባቂ የሆኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ኃላፊነታቸውን በቅጡ ለይተው የማያውቁ በዚያ በታ እንዲቀመጡ ስለተደረጉ ብቻ ራሳቸውን ፈላጭ ቆራጭ አድርገው የሚወስዱ ቁጥራቸው የትየለሌ ነው፡፡

እውነቱን መረዳት ቢችሉ ኖሮ የተቀመጡት ሀገርና ሕዝብን ለማገልግል ነው፡፡ በሕጉ መሰረት ተገቢውን የድርጅታቸውን መረጃ ሕዝብ ማወቅ ያለበትን ሲጠየቁ ለሕዝብ ለማሳወቅ ነው፡፡ የሕዝብ ሠራተኛና የሕዝብ አገልጋይ እንጂ የግለሰብ ባለስልጣናት የግል ተቀጣሪ አይደሉም፡፡ የቀጠራቸው የሚያሰራቸው መንግስትና ሕዝብ ነው፡፡ አገልግሎታቸውም ሀገራዊና ሕዝባዊ እንጂ ግለሰባዊ አይደለም፡፡

በምንም መልኩ ቢሆን ሕዝብ የሚፈልገውን ማወቅ የሚገባውን መረጃ አፍኖ መያዝ ለሚዲያ አለመስጠት በተለያየ መልኩ የሚፈጠሩ ችግሮችን ሕዝቡ አውቆ ሌላ የተሳሳተ የፈጠራ ዜናና ወሬ ውዥንብር ውስጥ እንዳይገባ እውነተኛውን ጉዳይ ከሚመለከተው የመንግስት አካል እንዳያገኝ እንዳይሰማ መከልከል ማለት ነው፡፡ ማንኛውም መረጃ የሀገርና የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ ሕዝብ ማወቅ ያለበትን መረጃ መከልከል አይቻልም፡፡

ጋዜጠኛውን መረጃን እንዳያገኝ መከልክል፤ ይህም በመንግስታዊ የሚዲያ ተቋማትም ሆኑ ኃላፊዎች ዘንድ ሕዝቡ አመኔታ እንዲያጣ ስለተነገረውና ስለተዛመተው በየመንደሩ  ስለሚነገር ወሬ እንዲያምን የሚያደርገው ብቻ ሳየሆን፤ ጋዜጠኛው እራሱም የተሳሳተ መረጃን ይዞ አደባባይ እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን ተሳስቶ እንዲያሳስት ጭምርም ያደርገዋል፡፡  የዚህ ሁሉ መነሻው ደግሞ፤ ከላይ እንደገለፅነው፣ ለዚህ ስራ መንግስት መድቦአቸው የተቀመጡት ሰዎች ሚዲያው ተገቢውን መረጃ ሲጠይቃቸው በተገቢው ወቅትና ሰአት መስጠት/ማብራራት ስላልቻሉ ነው፡፡ እንድገመውና፣ ትልቁ ችግር ይሄው ነው።

ይህ ሊታረም ያልቻለ ችግር አሁንም ገዝፎ ይታያል፤ ዋጋም እያስከፈለ ነው፡፡ እውነቱን እውነት ብሎ መቀበልና ስህተትን ለማረም ዝግጁ ሆኖ የመፍትሔው አንድ አካል መሆን መቻል ተገቢ ነው፡፡ መረጃን በተገቢው መንገድ ለሚዲያው መስጠት የሚፈጠሩ ውዥንብሮችን ለማጥራትና ለመከላከል ይረዳል፡፡ ሕዝቡ እውነቱን እንዲረዳ እንዲገነዘብ ያስችለዋል፡፡

የተሰጣቸውን መረጃ አዛብተው የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች ካሉ እንዲያርሙ መጠየቅ ከዚህም ካለፈ በሙያ ስነምግባር ጉድለት ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚህ ባለፍ ሕዝብ ማወቅ ያለበትን መረጃ የሚጠይቁ ጋዜጠኞች ያለአግባብ በየኃላፊዎች ቢሮ ሊጉላሉ አይገባም፡፡ ኃላፊው ለስራ ወጥተዋል የሉም፤ ስብሰባ ላይ ናቸው፤ ክልል ሄደዋል፤ ለስራ ከሀገር ወጥተዋል፤ የአመት ፈቃድ ላይ ናቸው፤ ቤተሰብ እክል ላይ ናቸው ወዘተ የሚሉት አሰልቺና ከሚዲያው ለመሸሽ የሚደረገው ምክንያታዊ ሩጫ ለሀገርና ለሕዝብ አይጠቅምም፤ ለውጥና እድገትም አያመጣልንም፡፡

ይልቁንም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ሲጠየቁ በተገቢው መልኩ መረጃ የሚሰጡ ከሆነ ግልጽነትና ተጠያቂነት ደረጃ በደረጃ እንዲያድግ ትልቁን ድርሻ ይወጣሉ፡፡ ለተተኪውም ባሕል ሁኖ እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡ የመረጃ ነጻነት ሕጉ በግልጽ ያስቀመጠው በአለም አቀፍ ደረጃ ክልክል ተደርገው የሚወሰዱ የማይነኩ ነጥቦች አሉት፡፡ ከዚሁ አኳያም እኛም “መረጃ ይሰጥ” ስንል ሀገራዊ ምስጢሮች፣ በምንም መልኩ መጠበቅ ያለባቸውና በሚዲያ መገለጽ የሌለባቸው ተብለው በቁጥር የተዘረዘሩ ክልከላዎችን የመለከታል እያልን አይደለም፤ እነሱን አይመለከትም፡፡ ከእነዚህ በጥብቅ ከተከለከሉት ውጭ ያሉትን መረጃዎች ለጥናትና ለምርምር ለሚፈልጉ ምሁራን፣ አጥኚዎች፣ ተመራማሪዎች ወዘተ በተለያየ መስክ ያሉ ዶክመንቶችንና  መረጃዎችን አደራጅቶ፣ በሕግ የተቀመጠውን ክፍያ አስከፍሎ፣ መረጃውን እንዲያገኙ ማድረግ የሕዝብ ግንኙነቶች ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡

ዋናው ቸግር ብዙዎቹ መንግስታዊ እድሜ ጠገብ የሆኑ መስሪያ ቤቶች ድርጅቶች ተቋማት ከጥንት ጀምሮ የነበሩትን መዛግብትና ዶክመንቶች በዘመናዊ መልኩ በመረጃ ቋት ውስጥ አላስገቡም፡፡ ይህን ለመስራት በመላው ሀገሪቱ ባሉት በነበሩት መስሪያ ቤቶች ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ያሉትን ሀገራዊ ዶክመንቶች በአግባቡ አደራጅቶና በኮምፒዩተር ተይቦ በየርእሱ ቁጥር ሰጥቶ በከምፒዩተር የዳታ (መረጃ) ማእከል ውስጥ ማስቀመጥን ይጠይቃል፡፡ ይሄ በአብዛኛው (በሙሉም ማለት ይቻላል) የለንም፡፡ ይህ በሌለበት ደግሞ ህዝብ አስፈላጊው መረጃ አለው፤ የማወቅ መብቱም ተከብሯል ለማለት ከቶም የሚታሰብ አይደለም፤ በተቃራኒው “ህዝብ የማወቅ መብቱን ተነፍጓል” እንጂ።

በአብዛኛዎቹ መስሪያ ቤቶች ዘመናት ያስቆጠሩ ጠቃሚ ሀገራዊ መረጃዎችና ዶክመንቶች ለጥናትና ምርምር የሚያገለግሉ፣ ብዙ ሊሰራባቸው የሚችሉ ሁነው ሳለ ሙት ፋይል (ዴድ ፋይል) ተብለው ሰፊ ቤት ውስጥ ታሽገው አቡዋራ እየጠጡ የሚገኙ ናቸው፡፡ የመረጃ ነጻነት ሕጉ የሚጠይቃቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች ለማሟላት እጅግ በጣም ብዙ ወደኋላ ቀርተናል፤ እየታየ ያለው የሀገራችን እውነትም ይሄ ነው፡፡

በጣቃላይ፣ እነዚህ ከላይ በመጠኑ የጠቃቀስናቸው ከመረጃ ነፃነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ሁሉ፣ በተለይም የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች ትከሻ ላይ የወደቁ ናቸው፤ በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ከወዲሁ ቀበቷቸውን ጠበቅ ሊያደርጉ ይገባል እንላለን።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy