የመድበለ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ ስርአት
ለሃገሪቱ ህዳሴ
ዮናስ
በርካታ የአላማችን ሃገራት ከበርካታ ጭቆናዎች ለመፋታት ያስቻላቸው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብ ከ1983 ዓ/ም በፊት ለነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባዳ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። የተደራጀና ተቋማዊ ተቃውሞን ማስተናገድ ለቅድመ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ልሂቃን የማይታሰብ የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ። ዛሬ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ከሥርዓቱ መገለጫዎች አንዱ ሆኗል። ስለሆነም ይህንኑ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ በማስተዋወቁ ረገድ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ያበረከተው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ አያከራክርም። ይህን ስርአት በመዘርጋት ሂደት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በአገራችን የፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ላይ ከባድ ልዩነትና ተጠራጣሪነት ሰፍኖ የነበረ መሆኑም ሌላኛው የማያከራክር ጉዳይ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ በኢትዮጵያ ብዙኅነትን ከቀደምት አስተዳደሮች በተለየ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለመያዝና ለማስተዳደር እንደሚፈልግ ባሳወቀ ጊዜ፣ ሰፋ ያለው የከተማ ማህበረሰብ በተለይ ደግሞ የአገሪቱ ልሂቃን አቅጣጫውን በከፍተኛ ጥርጣሬ ተመልክተውታል። ኢትዮጵያ አንድ ሆና እንድትቀጥል የነበራቸው ፍላጎት አደጋ የሚጋረጥበት የሚመስላቸውም ጥቂቶች አልነበሩም። ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ብዙኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዳደር መቻሏና ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ የፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና ስጋት ቀስ በቀስ እያረገበው ሊሄድ ችሏል።
ህገ መንግስታችን የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትህና የእኩልነት ዋስትና መሆኑ በተነፃፃሪ የተሻለ መግባባት ተፈጥሯል። የሚገነባው ሥርዓት የገበያ መሆን እንዳለበትና ሰዎች ሰርተው የመጠቀም ህጋዊ ዋስትና ሊያገኙ እንደሚገባቸው ተመሳሳይ መግባባት ተፈጥሯል። በዚህ ላይ ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኞቹ ጠላቶቻችን እንደሆኑ፣ ስለዚህም ደግሞ በፍጥነት መልማትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዳለብን አጠቃላይ የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል። የህግ የበላይነት መከበር እንዳለበትና ዜጎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል እንደሆኑ ግንዛቤ ተይዟል። እዚህ ላይ ከፈጣኑ እድገት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ነባርም ሆኑ አዳዲስ የስርዓት ችግሮችም እንደዚሁ ከሞላ ጎደል የጋራ ስምምነት የተያዘባቸው ሆነዋል። ኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ እንደሆነና ብዙኀኑን ህዝብ እንደሚጎዳ ከሞላ ጎደል በብዙኀኑ ህዝብ ዘንድ ስምምነት እየተፈጠረ ነው። በዚህ ላይ ሰላማዊና የተረጋጋ ህብረተሰብ የመሆናችን አስፈላጊነት በጥልቅ የሚታመንበት ሆኗል። ዜጎች ከአመፅ ይልቅ ሰላማዊ በሆነ መንገድና በድርድር መብትና ጥቅሞቻቸውን ማስፋት እንዳለባቸው የሚታመንበት ሆኗል።
በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረ መሆኑ እንደተጠበቀ፤ ይህ ግን በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑ አሁንም የመዋለልና ወደፊትና ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች ይታያሉ። ኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ እንደሆነ የሚቀበለው ህዝብ ትንሽ በማይባል ደረጃ በዚሁ ዝንባሌ ሲለከፍ ይታያል። የህግ የበላይነትና ሰላማዊ የትግል አግባብን የተቀበለው ህብረተሰብ፣ አልፎ አልፎ ፍላጎቱን በሃይልና በግጭት መንገድ ለማሳካት ሲንቀሳቀስ ይታያል።
ይህም በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የለም በሚሉና በምርጫ ማሸነፍ ሲሳናቸው ድክመቶቻቸውን ሁሉ ወደ መንግስትና ገዥው ፓርቲ በሚያላክኩ ፓረቲዎች የሰርክ ወሬ የሚረጋገጥ ነው። እነዚህ ፓርቲዎች ባለፉት አመታት በተደረጉ ሃገራዊና አካባቢያዊ ምርጫዎች ተሸንፈው መውጣታቸውን ለመድበለ ፓርቲ ስርአት ማብቃት እንደማሳያነት ይጠቀሙበታል። በዚህ ሳያበቁም ኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ወደኋላ በማለት ወደ አንድ ፓርቲ ሥርዓት ተሸጋግራለች ብለው እስከማሳጣትም መድረሳቸው ይታወቃል።
ገዢው ፓርቲ ከላይ የተመለከቱት መከራከሪያዎች ምክንያታዊ እንዳልሆኑ እያወቀም ዝምታን አልመረጠም። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የአንድ ፓርቲ ሥርዓትን እንደማይፈቅድ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ እና ለመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ብቻ ሳይሆን ያለነሱ ተሳትፎ የትም መድረስ የማይቻል መሆኑን አምኖ በመቀበል እየተጋ ለመሆኑ በርካታ አስረጂዎች መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ መካከልም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ሲደረግላቸው በነበሩ ድጋፎች ታግዘው መንቀሳቀስና መነቃነቅ ያቃታቸው መሆኑን የተገነዘበው መንግስትና ገዥው ፓርቲ ስለመድበለ ፓርቲ ስርአት ግንባታው ሲል ቀድሞ የነበሩ የምርጫ አሰራርና ስርአቶች በፓርቲዎች አቅምና ቁመና ልክ ሆነው ቢሻሻሉ የተሻለ እድል ይፈጥርላቸዋል በሚል እምነት በርክታ ህግጋትን ለመሻር የሚያስችል ድርድር ውስጥ መግባቱ ሊጠቀስ የሚገባው አስረጅ ነው። እስካሁን ባለው ሂደትም የአብላጫ ድምጽ የነበረውን የምርጫ ስርአት ተመጣጣኝ ውክልናን ጨምሮ ቅይጥ የምርጫ ስርአት እንዲሆን በማድረግ ለመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እውንነት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
የኢፌዴሪ ሕገ መነግሥት ሰላማዊና ሕጋዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በፍትሐዊነት በምርጫዎች እንዲሳተፉና እንዲንቀሳቀሱ መሠረታዊ ማዕቀፉን የዘረጋ መሆኑ በሚታወቅበት አግባብ፤ ወደዚህ ድርድር መግባቱ ለመድበለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ መሄድ የሚገባው ድረስ ለመሄድ ዝግጁ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው። ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ የተረጋገጡላቸውን መብቶች ሊጠቀሙባቸው አለመቻላቸው የቀደመ ድክመታቸው ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያሉ እና እድል የሚፈጥሩላቸው አማራጮችም ላይ ማጉረምረማቸው እና ጥላሸት ለመቀባት ማሰፍሰፋቸው ለመድበለ ፓርቲ ስርአት ውድቀት ማሳያ አድርገው የሚያቀርቡት ከላይ የተመለከተ አስረጃቸው ምክንያታዊ እንደማይሆን የሚያረጋግጥ ነው።
ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በመሰረቱ በተቃውሞው ጎራ ያሉትን ፓርቲዎች ባሳተፈ ሁኔታ በገዢው ፓርቱና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ድርድር ለማድረግ መወሰን በራሱ ዴሞክራሲያዊነት ነው። ኢሕአዴግ ቃሉን በማክበር ለሁሉም አገር አቀፍ ፓርቲዎች የውይይትና የድርድር ጥያቄ ለማስቀየስ አልያም ያንን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት ሳይሆን ለሃገሪቱ ህዳሴ የመድበለ ፓርቲ ስርአት ያለውን ወሳኝ ሚናና ፋይዳ ስለሚገነዘብ ብቻ ነው። የመድበለ ፓርቲ ስርአት ለጊዚያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የሚዘረጋ ሳይሆን ዘላቂነት ላለው የዴሞክራሲያዊ ስርአት መጎልበት ብቻ መሆኑም የፖለቲካው ዘርፍ ሀሁ ነው።
የሁሉም ነገር ግብ ስለሆነው የህዝብ ጥቅም ሊደራደር ዝግጁ የሚሆን የትኛውም ፓርቲ ሊከተል የሚገባው መርህ አለ። ሲደራደር አጀንዳዎችን መመዘን የመጀመሪያው መርሁ ነው። ሁሉም የየራሱ ርዕዮተ ዓለም አለው። ከራሱ ርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ በመነሳት የሚቀበለውን ይቀበላል፣ የማይቀበለውን ደግሞ አልቀበልም ማለትም ተያያዥ የሆነው የድርድር መርህ ነው።ስለሆነም ድርድሩ በአገሪቱ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ ለአሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚተላለፍበትን ሥርዓት ይበልጥ ለማስፋት ወሳኝ ምእራፍ መሆኑን የትኛውም ህዝብን ወክላለው የሚል ፓርቲ ሁሉ ሊገነዘብ እና በዚሁ ማእቀፍ ብቻ ሊንቀሳቀስ ይገባል። በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ እንቅፋት ብቻ ሳይሆን በግብዓትነትም መጠቀም በህዝብ ስም የሚንቀሳቀስ ፓርቲ መሰረታዊ መገለጫ ነው። መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ የፓርቲዎችን የዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት፣ ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሐሳብ፣ ያላቸውን ሐሳብ ተገንዝቦ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከየትኞቹም ለዴሞክራሲያዊ መርሆ ተገዥ ነን ከሚሉት ሁሉ የሚጠበቅ ቅድመ ሆኔታ መሆኑንም መገንዘብና በዚሁ አግባብ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።ለብሔራዊ መግባባት፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን የሃገሪቱን ህዳሴ ማረጋገጥ የሚቻለው የተጀመረውን እና ወሳኙን ምእራፍ ያለፈውን ድርድር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እንጂ በማብጠልጠል አይሆንም።
ስለዚሁ ስርአት እውንነት ለሚገጥሙ ችግሮች ኢሕአዴግን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ በራሱ የመጀመሪያው ችግር ነው። እንኳንስ እንደኛ ያለ ታዳጊ ሃገር ይቅርና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ፈር ቀዳጆች ናቸው የሚባሉትም ከችግር ሊጸዱ አይችሉም። ስለሆነም እስከዛሬ በነበረው ሂደት ጨምሮ እየተደረገ ባለው ድርድር ችግር ቢኖር የሁሉም ግብ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እስከሆነ ድረስ ችግሩን ለኢህአዴግ ብቻ መስጠት (ሊሆን ስለማይችል) ተገቢ አይሆንም። ራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሕዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ብዙም ትርጉም ያለው ሚና እንዳይኖራቸው በማድረግ ረገድ ተጠያቂ ስለመሆናቸው አምኖ መቀበል ተገቢና የመፍትሄውም መጀመሪያ ይሆናል።
ባጠቃላይ፣ ህዝብን መሰረት አድርገናል ሲሉ የምናደምጣቸው ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚከሰሱባቸው ጉዳዮች መካከል እጅግ ደካማ መሆናቸው፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉና የተከፋፈሉ መሆናቸው፣ ከሁሉም በላይ ለራሳቸው ክብር ይበልጥ ትኩረት በሚሰጡ ግለሰቦች የሚመሩ መሆናቸው፣ ጠንካራ የድጋፍ መሠረትና አማራጭ ፖሊሲ የሌላቸው መሆናቸው፣ እንዲሁም እርስ በርስ በጥርጣሬ የሚተያዩና የሚገዳደሩ መሆናቸው ተጠቃሾች በሆኑበት አግባብ የችግሮች ሁሉ ባለቤት ገዢው ፓርቲ ነው የሚል ሙግት ውሃ የማያነሳና በህዝብ ስም መቆመር ይሆናል። የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መጎልበት ማንንም የሚጎዳ እና አንደኛውን ጠቅሞ ሌላውን የሚያገል ሳይሆን ተቃዋሚውን ጨምሮ ገዢ የሆነውን ፓርቲ በህግ የበላይነት ስር እንቂንቀሳቀሱ ብቻ በማድረግ የሃገሪቱን ህዳሴ የሚያረጋግጥና በዚህም የህዝብን ዘላቂ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚያስችል እድል የሚፈጥር ብቻ ሳይሆን የሚጠቅምም ይሆናል።