የቅማንት ማህበረሰብ አዲስ የራስ አስተዳደር አወቃቀር በዚህ አመት ተግባራዊ እንደሚደረግ የማእከላዊ ጎንደር ዞን አተዳደር አስታወቀ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪው አቶ አየልኝ ሙሉአለም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት የማህበረሰቡን የራስ አስተዳደር ለማዋቀር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
ለዚህም ከውሳኔ ሕዝብ ጀምሮ ህዝቡ በራሱ ፍላጎትና ፍቃድ ህዝባዊ ኮንፍረንሶችን በማካሄድ የጋራ ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
የዞኑ አስተዳደር ከቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በመቀናጀት አስተዳደራዊ መዋቅሩን ሌሎች ዝርዝር የአሰራር የጥናት ሰነዶች ተጠናቀው ለክልሉ መንግስት መላካቸውን ገልጸው “በክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላም በዚህ አመት ተግባራዊ ይደረጋል” ብለዋል፡፡
የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር መብት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት መንግስት ከተሃድሶ ማግስት ጀምሮ የወሰዳቸው እርምጃዎች አካል መሆኑን አመልክተዋል።
“መስተዳድሩ የዞኑን ህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እያደረገ ባለው ጥረትም ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመስራት ላይ ነው” ብለዋል፡፡
ነባሩ ዞን ካለው የቆዳ ስፋት ፤ የህዝብ ቁጥርና መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪነት አንጻር የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በቅርብ ሆኖ ለመፍታት በመንግስት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም ነባሩን ዞን በሶስት የአስተዳደር ዞኖች በማዋቀር አዲሶቹን ዞኖች በሰው ሃይልና በቁሳቁስ የማደራጀት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አቶ አየልኝ አስታውቀዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ