Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የባለስልጣናት ከስራ የመልቀቅ ምክንያቶች

0 331

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የባለስልጣናት ከስራ የመልቀቅ ምክንያቶች

                                                      ይልቃል ፍርዱ

በፖለቲካው አለም መሪዎች ይፈጠራሉ፡፡ ይሰራሉ፤ ያልፋሉ፤ ይተካሉ፡፡ በተለይም ከረዥም ግዜ አገልግሎት በኋላ በስራቸው ለመቀጠል ወይንም ለመልቀቅ የሚያስችላቸው የተለያዩ ሁኔታዎችም አብረው እንደሚፈጠሩ ይታወቃል፡፡ በጤና በእድሜ በአገልግሎት ጣሪያ መንካት በውስጥ በራሳቸው መስማማትና አለመስማማት ጭምር ከያዙት የመንግስትም ሆነ የፖለቲካ ስልጣን ሊለቁ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ተከስተው ታይተዋል፡፡ ወደፊትም ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ የለፉት የደከሙት የሰሩት ስራ በታሪክ መዝገብ ሰፍሮ ይኖራል፡፡

የፖለቲካ መሪዎች በተፈጥሮ ሕመም በድንገተኛ አደጋ በሞት ወይንም አገልግሎቴ በቃኝ ብለው በክብር የሚለቁበትም ሁኔታ በብዙ አጋጣሚዎች ታይቶአል፡፡ ሁሉም ግለሰብ በቆመበት መስመር መስራት የሚችለው በሙሉ እምነትና ነጻነቱ በሙሉ የስራ ፈቃድ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ በአመለካከትና በአስተሳሰብ ልዩነት ከተፈጠረም ስራውን በፈቃደኝነት የመልቀቅም መብት አለው፡፡

ይህ እንዲያውም በአውሮፓ የተለመደ ስልጡንና ዘመናዊ አካሄድ ነው፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ በመሰረቱ በተለያየ ደረጃ የነበሩ ነባር መሪዎች ረዥም ግዜ በማገልገላቸው የገነቡት ተክለ ሰውነት የስራና የካበተ የትግል ልምድ አላቸው፡፡ ከመምራትም ባለፈ በስራው ሂደት ሺዎችና ሚሊዮኖችን አፍርተዋል፤ አሰልጥነዋል፤ አስተምረዋል፤ የትግል ተሞክሮና ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

ነባር አመራሮች ለኃላፊነት ብቁ የሚሆኑ ሰዎችን ቀርጸዋል፡፡ ይሄ ታላቅ ሀገራዊ አስተዋጽኦ ነው፡፡ በፖለቲካ መስመራቸው ቀጣይነት ላይ አላማውን የሚያራምዱ በብዙ ሺዎችን ሚሊዮኖችን አስተምሮ ማሰለፍ መቻል የመስመሩ ቀጣይነት የማእዘን ድንጋይ ዋልታና ምሰሶ ሁኖ የሚቀጥል ስራና ተግባር ነው፡፡ ልዩነትንም ማክበር ስልጡንነት ነው፡፡

በቅርቡ ከነበሩበት የመንግስት ኃላፊነት ለመልቀቅ ደብዳቤ ካስገቡት ሁለት ታላላቅ ሰዎች በፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ ከኃላፊነታቸው በመተካካት ሂደቱ የለቀቁ ነባርና መስራች ሰዎችንም አይተናል፡፡ የነባሩ ታጋይና የፖለቲካ ሰው የርእዮተ አለሙ መሪ ተደርገው የሚወሰዱት በረከት ስምኦንም ሆኑ የተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤ የነበሩት አባዱላ ገመዳ ከስልጣናቸው ለመልቀቅ ያስገቡት ደብዳቤ በመንግሰት በኩል ተቀባይነት ቢያገኝም ከፖለቲካ ድርጅቶቻቸው ለመልቀቅ ወይንም ላለመልቀቅ ወሳኙ ድርጅቶቻቸው ናቸው የሚሆኑት፡፡

እነዚህ ሰዎች እጅግ የላቀና የገዘፈ ሀገራዊ አስተዋጽኦ ያደረጉ የለፉ የደከሙ የተሻለችና ከድሕነት የተላቀቀች ሀገር ለመፍጠር በተደረገው ትግል ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ሲመሩ የቆዩ የኢህአዴግን ፖሊሲ በመቅረጹም ሆነ በማስፈጸሙ ረገድ የጎላ ድርሻ የነበራቸው በግላቸውም ሰፊ የትግል ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡

በተገኙት ሀገራዊ ስኬቶች ድሎች ውስጥም የየራሳቸው ስፍራ አላቸው፡፡ ይህንን በፍጹም መካድ አይቻልም፡፡ በተለይ በአመለካከትና በአስተሳሰብ ልዩነት ከተከሰተ በቃኝ አገልግዮአለሁ አልቀጥልም ማለት ዲሞክራሲያዊ መብትም ነው፡፡ ማንም በግድ ተጭኖ ስራ ስሩ ሊላቸው የሚችል አይኖርም፡፡

ግለሰቦች በየትኛውም አይነት ስራ ቢሆን ስራን መልቀቅ አለብን ብለው ከወሰኑ መብታቸው በሕግም የተከበረ ነው፡፡ አንዱ በሀገራችን የግራና የቀኝ ፖለቲካ አራማጆች አማካኝነት በሕዝቡ ውስጥ ለበርካታ አስርት አመታት እንዲሰፍን ሰርጾ እንዲገባ የተደረገውና ሊወገድ የሚገባው እንደ ባህልም እየተቆጠረ ያለው የስም ማጥፋት ዘመቻ አሉባልታና የጥላቻ ፖለቲካ ነው፡፡ አስሩን የፈጠራ ወሬ ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ ድረስ ከመንዛት ስም ለማጥፋት ከመሮጥ ይልቅ ግለሰቦቹ ያደረጉትን ሀገራዊ አስተዋጽኦ ማየት ማመዛዘን፣ ተገቢ ክብርም መስጠት ይገባል፡፡

የሴራና የጥላቻ ፖለቲካ የፈጠራ ወሬና አሉባልታ አንዱ በሌላው ላይ ማሴር የመጠፋፈት የመባላላት ፖለቲካ ሀገሪቱንም ትውልዱንም አልጠቀመም፡፡ የኋሊት እንድንጓዝ ነው ያደረገው፡፡ በሀሳብ ልዩነት የመከባበር ባህል አልተገነባም፡፡ ልዩነትን በልዩነት ይዞ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ በአንድነት ጸንቶ ስለሀገር ስለሕዝብ ሰላም ፍቅርና ሀገራዊ ጥቅም የመቆም ባሕል ጨርሶውንም የለንም፡፡

ሀገር ሲገድል የኖረው ትውልድን ያደነበሸው መርዝ ነዝቶ ዘርቶ ያለፈው መተማመን መከባበር መቻቻል እንዲጠፋ ትልቅ በር የከፈተውና ዛሬም ወደተረኛው ትውልድ እንዲሸጋገር ያደረገው በሸር በተንኮል በጥሎ ማለፍ ላይ የተመሰረተው ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ራስ ወዳድነት የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክር የበዛበት የቀደመው ዘመን ጽንፈኛ አክራሪ ፖለቲካ ነው፡፡

ዛሬ ነፍስ ዘርቶ ሲያተራምሰን እያየነው ነው፡፡ የሠለጠነ አስተሳሰብና ስልጡን የፖለቲካ አካሄድ ገና አልተገነባም፡፡ የመከባበር ባሕል ገና አላደገም፡፡ ብዙ ይቀረናል፡፡ መናናቅ ከእኔ በላይ አዋቂ የለም የሚለው የእብሪት የአምባገነናዊነት ፖለቲካ ነው ከጥንት ጀምሮ በሀገራችን ሰፍኖ የኖረው፡፡

በኢህአዴግ ዘመን ዲሞክራሲውን በማስፋት ረገድ ከሁሉም ግዜያት የተሻሉ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር፡፡ የውስጥ ችግሮች እንዳሉ ሁነው በአግባቡ መጠቀም አልተቻለም፡፡ መልካምና ጥሩ ጅምሮች ነበሩ፡፡ የእነበረከት አስተዋጽኦ ግዙፍና የጎላ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የጥልቁ ተሀድሶ ቀማሪ የጸረ ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው ትግል ግንባር ቀደም መሪ ሁኖ ኪራይ ሰብሳቢነት በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ መንሰራፋቱን ተተብትቦ መያዙን ለዚህም ሕዝባዊ ትግል ማድረግ እንደሚገባ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ሀገራዊ አደጋ መሆኑን በአደባባይ የተናገረ የተከራከረ ሰው ነው በረከት፡፡

በረከት ለርእዮተ አለማዊ እምነቱ በታማኝነት የኖረ ልምዱን እውቀቱን ያሰረጸ ሺዎችና ሚሊዮኖችን በመስመሩ ያፈራ፤ ለራሱም ለቤተሰቡም ያልኖረ ሰው ነው፡፡ በአሉባልታ የሚናጠው ጀሌና ምንዝር አስሩን እየፈጠረ ቢያወራ አይደንቅም፡፡ እሱም ሆነ መለስ በውጭ ኃይሎች ተጽእኖና ጫና ያልተንበረከኩ አዋጪ የሆነውን ኢትዮጵያዊ መስመርና ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውን የሚበጀውን ብቻ የሚከተሉ የነበሩ ናቸው፡፡

ሀገሪቱንም በመሪነት ቦታቸው ሁነው ኢሕአዴግን በመምራት ከተደጋጋሚ የቀውስና የትርምስ የጥፋት አደጋ የታደጉ ናቸው፤ እጅግ በሳል ፖለቲከኞች፡፡ እነዚህን ሰዎች በቀላሉ ማፍራት አይቻልም፡፡ በእንደዚህ አይነቱ ቀውስ በገነፈለበት ወቅት መለስን በሞት በረከትን በስራ መልቀቅ ማጣት ሀገራዊ ጉዳቱ የገዘፈ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ለማረጋጋትም እኮ ፖለቲካ አዋቂነትን ይጠይቃል፡፡ ወንበር ላይ የተቀመጠ ሁሉ የመሪነት ብቃት አለው ብሎ ለማለት አይደፈርም፡፡

ከአክራሪው ፖለቲከኛ የከፋ በሽታ በመውጣት ሀገራችንን ወደተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር ከዚህ ትውልድን ካመከነ ሀገርን ከገደለ የነበረንን መልካም የመተሳሰብ፣ የመከባበርና ተቻችሎ የመኖር ባሕል አውልቆ ከጣለና ካራገፈ እጅግ የመከነ አመለካከት ተስፈንጥረን መውጣት አለብን፡፡

የሀገር ውስጡም ሆነ የዲያስፖራው አክራሪና ጽንፈኛ ፖለቲከኛ እድሜ ዘመኑን የሚያመነዥገው ጥላቻን እብሪትን ከእኔ በላይ ለሀገር አሳቢና ተቆርቋሪ የለም አይፈጠርም እኔ ያሰብኩትና የማስበው ብቻ ትክክል ነው የሚል እጅግ ኋላቀርና ደካማ ለሀገርና ለሕዝብ አብሮነት አንድነት ፈፅሞ የማይበጅ አስተሳሰብ ነው፡፡

ማንም ለሀገር የሚበጅ የረባ ቁምነገር ያልሰራ ሎሌ ሁሉ እየተነሳ እንደፈለገ የሚናገርበት (ስድብ ነቀፋ ሽሙጥ በዋልጌነት የተሞላ ልቅነት ሀሜት) አሉባልታ የሚነዛበት እራሱን ከምሮ ትልቁ ሰው እኔ ነኝ እያለ የሚውረገረግበት የቆሸሸ ፖለቲካ ለሀገር እድገት ለሕዝብ አንድነትና አብሮነት አይጠቅምም፡፡ ለደከሙ ለለፉ ሰዎች የቱንም ያህል የሀሳብ ልዩነት ቢኖር ከጥላቻ ወጥቶ በአክብሮት ማየት ተገቢም ጨዋነትም ነው፡፡

በሀሳብ መከራከር የተሻለውን ሀሳብ መቀበል ለሁሉም በጋራ የሚበጀውን መውሰድ  የሀሳብ ልዩነትን በጸጋ መቀበል እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ከሚለው ግትርና ጽንፈኛ ሀሳብ መውጣት፤ በሰለጠነ እሳቤ ስለሀገርና ስለሕዝብ ሰላም ማሰብና ለህዝብም መቆም ነው ለሁሉም የሚበጀው፡፡

ከዚህ ባለፍ ያለው መንገድ ሁሉ ከጥፋትና ከውድመት ውጪ ለሀገር አይበጅም፡፡ ግለሰቦች ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም እድገትና ልማት ላደረጉት መልካም አስተዋጽኦ ሁሉ ሊመሰገኑ እንጂ ሊሰደቡ አይገባቸውም፡፡ ሰው የሆነ ሁሉ ጠንካራና ደካማ ጎን አለው፡፡ ይሄ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ሁሉን ወንጅለን ሁሉን ነቅፈን ሁሉን ተሳድበን ሁሉን ኮንነን ሁሉን ጥላሸት ቀብተን እኛ ብቻ ነን ትክክል ብለን የምናምን ከሆነ ትልቁን የሰውኛ መመዘኛ መስፈርት ረግጠነዋል ማለት ነው፡፡

አክራሪና ጽንፈኛ ፖለቲከኛው ዛሬም ጥፋት እንደናፈቀና በቀል እንደጠማው ይገኛል፡፡ ከሀገር ጥፋትና ውድመት የሚገኝ ትሩፋት የለም፡፡ ከዚህ ድኩም እሳቤ ሊወጣ ካልቻለ ባሕር ማዶ ቁጭ ብሎ የቆጡን የባጡን በመዘላበድ የሀገርን ችግር መፍታት አይቻልም፡፡

እሳት በማንደድ ሀገርን የማትመለስበት አረንቋ ውስጥ ለመክተት መክለፍለፍም ለማንም አይጠቅምም፡፡ በአሉባልታና በፈጠራ ወሬ በስም ማጥፋት የተበከለው የቆሸሸው የተመረዘው የባሕር ማዶው ጽንፈኛ ፖለቲከኛ በፖለቲካ ዳፍንት ውስጥ የሚባጅ የሀገርን ሰላም ሳይሆን ጥፋትና እልቂትዋን የሚመኝ መሆኑን ሕዝብ ተረድቶታል፡፡ የሻእቢያና የግብጽ ቅጥረኛ መሆኑንም ያውቃል፡፡ ገንዘቡም ከእነሱው እንደሚሰፈርላቸው በበቂ ማስረጃ ይታወቃል፡፡

በፖለቲካው አለም ግለሰቦች ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ፡፡ ማንም ቋሚ የለም፡፡ ለሰሩት መልካም ስራ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ ከጥላቻ መውጣት መልካሙን ማሰብ ነው ሀገርን ሊታደጋት የሚችለው፡፡ ግለሰቦች በታሪክ ውስጥ የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸውም መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ጥላቻ ስድብ የፈጠራ ወሬ አሉባልታ በአልተጨበጠና በሌለ መነሻ ስም ማጥፋት ለሀገር ለሕዝብም አይበጅም፡፡

አክራሪውና ጽንፈኛው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ከዚህ ስር የሰደደ በሽታው መቼ እንደሚላቀቅ መቼ ሚዛናዊ ሁኖ የተሻለ ለማሰብ እንደሚበቃ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ዛሬም እየተርመጠመጠ ያለው እዛው ላይ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ቀድሞት ሄዶአል፡፡ የጥላቻ መርዙን የመጠፋፋት የመናቆር የመባላት የስም ማጥፋት ባሕሉን ተቻችሎ ተከባብሮ ለመኖር የማይበጅ ስለሆነ ነቅሎ ይጥለዋል፡፡ ለሀገር እድገትና ሰላም ስለማይጠቅም፡፡ ቸር እንሰንብት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy