Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሁለንተናዊ ፋይዳ

0 841

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሁለንተናዊ ፋይዳ

                                                                                    መዝገቡ ዋኘው

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር ናት፡፡ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕሎችና ኃይማኖቶች የሞሉባት፤ ልዩነቶችን አቻችላ የምትኖር ሰፊ ሀገር ናት፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦችን አቅፋ ለዘመናት የዘለቀች፤ ዛሬም እኩልነታቸውን አረጋግጣ የጋራ ሀገራቸውን በሕብረትና በአንድነት ተሳስበው እንዲያለሙ፤ እንዲያሳድጉ ለማድረግ የቻለች ሀገር ነች፡፡

ብዝሐነት ውበት ነው። በአንድ ሀገር ላይ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖራቸው የብዝሐነት መገለጫ ሲሆን፤ ይህም በአግባቡ ከተያዘ ዜጎች ሁለንተናዊ መብታቸው እንዲከበር፤ በጋራ በመቆምም እንዲሰሩ፤ ሀገራቸውን በጋራ እንዲያገለግሉ፤ እንዲጠብቅዋት ጉልበት ሁኖ ያገለግላል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች መብት በእኩልነት ካልተከበረ ለሚከሰቱት መሰረታዊ ችግሮች ሁሉ፣ ብዝሐነት ውበትነቱ ቀርቶ ዋነኛው የችግር/ግጭት መነሻ ነው የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገመንግስት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያረጋገጠ በመሆኑ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ሕገመንግስታችን አብሮነትን፣ መቀራረብን፣ መተዋወቅን፣ በራስ መተማመንን አሳድጓል፡፡ ይህ ከሚገለፅባቸው አውዶች አንዱ ህዳር 29 የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች አመታዊ በአል ነው።

በአሉ በሚከበርበት ሰሞን ሁሉም በአንድ አካባቢ ከተለያዩ  የሀገሪቱ ክልሎች መጥተው በጋራ ስለሚያሳልፉ የበለጠ መቀራረብ መግባባት መተዋወቅ እንዲፈጠር አድርጎአል፡፡ አንዱ ስለሌላው በሰፊው እንዲያውቅ፤ እንዲረዳ፤ የበለጠም በጋራና በእኩልነት መንፈስ እንዲቆሙ ያስቻለም ነው፡፡

በአሁኑ ሰአት ለዘመናት ተዘንግተው ይኖሩ የነበሩ ብሄሮችና ብሔረሰቦች ከማህበራዊውም ሆነ ከኢኮኖሚው እድገት ተካፋይ የሚሆኑበት መደላድል ተፈጥሯል፡፡ ከትምህርት፣ ከጤና አገልግሎት ወዘተ ተጠቃሚነት፤ ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደር፣ በቋንቋቸው ከመማርና ከመዳኘት ርቀው ይህንንም ሳያውቁት ኖረው ብዙ ዘመናትን ገፍተው የነበሩ ብሔረሰቦች በመብታቸው ተጠቃሚ በመሆን ቋንቋቸውን ለማበልፀግ፤ ባሕላቸውን ለማሳደግና ለማስተዋወቅ ወዘተ በቅተዋል፡፡

ይሄ ትልቅ ውጤትና ድልም ጭምር ነው፡፡ በክልሎች አስተዳደር ውስጥ የየራሳቸው ውክልና ያላቸውና ድምጻቸው የሚሰማበት፤ ለመብታቸው የሚከራከሩበትና የሚቆሙበት ወንበርም አላቸው፡፡ በእርግጥ ይህ ይበልጥ እየተከበረ የሚሄደው እድገትም የሚያሳየው በግዜ ሂደት ውስጥ እየጎለበተና እየጠነከረ ሲሄድ ቢሆንም አሁን ባለንበት ደረጃም ቢሆን ሰፊ መሻሻሎችንና እድገቶችን አሳይቶአል፡፡

በእርግጥ መሰራት የሚገባቸው ስራዎች በየክልሉ ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ አንዳንድ ከማእከላዊው የሀገሪቱ ክፍል ርቀው ያሉ ብሔረሰቦች ዘንድ መሰረተ ልማትን የማስፋፋት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረጉ ስራ ዛሬም ካለው በላይ ብዙ ሊሰራበት የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የከብቶቻችውን ጭራ ተከትለው ውሀና መኖ በሚኖርበት አካባቢ አመት ከአመት በመንከራተት ሲኖሩ የነበሩትን በአንድ አካባቢ ተሰባስበው በሰፈራ እንዲኖሩ፤ በዚህም የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

አርብቶ አደሮች እርሻን እንዲለምዱ በዚህም ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ከሚሆነውም ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ልጆቻቸው የትምሕርት እድል እንዲያገኙ፣ የንጹህ መጠጥ ውሀ፣ የጤና አገልግሎት . . . ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች ዛሬም እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም የእኩልነት መብታቸውን (እኩል የመልማት ህገመንግስታዊ መብት) ከማረጋገጥ የዜግነት መብታቸውን አክብሮ ከማስከበርም የመነጨ ነው፡፡

የብሔር ብሔረሰቦችን መብትና እኩልነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማክበር፤ በፍቅር፣ በአብሮነት፣ በመቻቻል፣ በመከባበር እንዲኖሩ፤ በጋራም ሀገራቸውን እንዲጠብቁና እንዲያለሙ ለማድረግ የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ በጋራ ሀገር ላይ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሁኖ የሚታይበት/የሚኖርበት ዘመን አልፎአል፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ያገባቸዋል፤ ይመለከታቸዋል፡፡ ያለአድልዎ ተጠቃሚም መሆን አለባቸው፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ይህ መብታቸው በሕገመንግስቱ የተረጋገጠ ነው፡፡

ባለፉት ስርአታት እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ጭርሱንም የተረሱ፣ ከስልጣኔውም ሆነ ከእውቀት አለም ሙሉ በሙሉ የራቁ፤ ከአካባቢያቸው ውጭ ሌላ የሚያውቁት ነገር የሌላቸው፣ የትምሕርት፣ የጤና አገልግሎት የማያገኙ ነበሩ። ዛሬ እነዚህን ሁኔታዎች ለማስተካከልና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡

በሀገራችን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ በየአመቱ የእኩልነትንና የመብት ተጠቃሚነትን፤ የዜግነትን ክብር እየስታወሰ ፍቅር፣ ሕብረትና አንድነቱን እያጎለበተና እያጠነከረ የሚሄድ ነው፡፡ ከቀኑ መከበር ጋር ተያይዞ መነሳት የሚገባው ሌላው ነጥብ በአሉ በመዘዋወርና በፈረቃ በተለያዩ ክልሎች የሚከበር መሆኑ ሲሆን፤ ይህም አንዱ የሌላውን ባሕል ሕዝቡን ጭምር በጥልቀት እንዲያውቅ ትልቅ መሰረት የጣለና መቀራረብን ያጎለበተ፤ ያሳደገ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በየክልሎቹ በአሉን ለማክበርና እንግዶችን ለመቀበል በሚደረገው ዝግጅት በየአካባቢዎቹ ከተሞች መንገዶችን አስፋልቶችን አስፍቶ የመስራት፤ ሆቴሎችን የመገንባት ስራዎች ቀድሞ ባልታየ መልኩ ሲሰራበት ታይቶአል፡፡ ይህም አንድ ራሱን የቻለ እድገትና ለውጥ ነው፡፡

በላቲን አሜሪካ እኛ ከምናከብረው ቀን ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው በስፋት የሚከበሩ፤ የቱሪስት ገበያዎችንም ወደሀገራቱ በስፋት የሚስቡ፤ ሀገራዊ ገቢንም የሚያሳድጉ፤ ካርኒቫሎች ይከበራሉ፡፡ እኛም ከዚሁ አንፃር ብናስብ አየከፋም፤ በስፋት ማሰብና ማቀዱ ለሀገር ገቢም ሆነ ገፅታ ግንባታ ፋይዳው በርካታ ነው፡፡ በሂደት እለትና ሁነቱንም በዩኔስኮ ማስመዝገብ ይቻላል፡፡

ቀደም ሲል እንዳልነው፤ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሀገራችን መከበር ሕዝብን ከሕዝብ ባሕልን ከባሕል በማስተዋወቅና በማቀራረብ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቶአል፤ መቀራረብን አሳድጎአል፤ በየአመቱ በናፍቆት የሚጠበቅና የሚዘከር ቀን ለመሆንም ችሎአል፡፡ በየአመቱ ቀኑን ለማክበር ተረኛ የሆነው ክልል እንግዶቹን ለመቀበል አስቦበት፣ እቅድ አውጥቶ፣ ከቀደመው አመት በተሻለ ደረጃ የጎደሉትን በማሟላት ረገድ የሚፈጽማቸው ስራዎች ከበአሉ አከባበር በኋላ ለክልሉ የሚቀሩ ትሩፋቶች ስለሆኑ ይሕም በየግዜው ከፍተኛ ለውጦችና መሻሻሎች እንዲገኙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ አድርጎአል፤ በማድረግም ላይ ነው፡፡

ከብሔር ብሔረሰቦች ቀን ጋር በተያያዘ በሚሰሩ በርካታ  ስራዎች ብዙ የክልሎች ዋና ከተሞች በአስገራሚ ፍጥነት ሲለወጡና ሲያድጉ ታይቷል፡፡ ይህ ለውጥና እድገት የተገኘው በየአመቱ ከበአሉ መከበር ጋር በዙርና በፈረቃ ከሚሰራው ስራ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በተለይ የመንገዶችና የሆቴሎች መሰራት፣ የመብራትና የውሀ አገልግሎት እንዲኖር የማድረግ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ቀድሞ ባልነበሩባቸው አካባቢዎች የባጃጆችና የአነስተኛ ታክሲዎች፣ የሚኒ ባሶች መበራከት፣ የሆቴሎች ቁጥር መጨመርና ማደግ ሌሎቹ የበአላ ፋይዳና የእድገቱ መገለጫዎች ናቸው፡፡

ክልሎቻችን በአድገትና በልማት ደረጃ ሲመዘኑ ገና ብዙ ይቀራቸዋል፤ ኋላቀር ተብሎ በሚጠቀስ ደረጃ ያሉ ናቸው፡፡ የመብራት፣ የንጹህ መጠጥ ውሀ፣ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ትምሕርት ቤቶችን፣ የመንገድ ልማትን የማስፋፋት ስራዎች ወዘተ በሰፊው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወደተሻለ ሀገራዊ ልማትና እድገት ሊያደርሰን የሚችለው በሀገር ደረጃ ተቀራራቢ በሆነ መልኩ ሁሉንም ክልሎች ለማልማትና ለማሳደግ ሲሰራ ብቻ ነው፤ በመሆኑም የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲታሰብ አብሮ ሊታሰብ፤ ከቶም ሊረሳ የማይገባው ጉዳይ ቢኖር ይሄው የክልሎች የመልማት ህገመንግስታዊ መብት ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy