Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን የማክበር ፋይዳ

0 335

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን የማክበር ፋይዳ

                                                       ደስታ ኃይሉ

በመጪው ህዳር 29 ቀን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ታላቅ ፋይዳ ያለው ነው፤ ለተሳታፊውም ይሁን ላዘጋጁ ክልል። ዕለቱን ማክበር መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት፣ ራስን ለማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለሌሎች ጉዳዩች የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ዕለቱን ስናስብ በርካታ ጉዳዩችን ልናነሳ እንችላለን። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ነፃነቷን አስጠብቃ፣ ህዝቦቿም ለማንም ወራሪ ኃይል ሳይንበረከኩ የኖሩባት ሀገር ትሁን እንጂ፣ ከገዥዎቻቸው የአፈና እና የጭቆና ቀንበር ነፃ አልነበሩም። ይህ ሁኔታም መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ያነሷቸው የነበሩትን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎቻቸውን በረጅምና መራር ትግል እንዲመልሱ ምክንያት ሆኗቸዋል።

ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ዕውን ባደረጉት ህገ-መንግስት አማካኝነትም ጥያቄዎቻቸውን በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ ምላሽ ሊሰጡ ችለዋል። በዚህም ብዝሃነታቸውን እንደ ውበት በመቁጠር አንድነታቸውን አጠናክረው ዛሬ የደረሱበት የዕድገት ማማ ላይ ለመውጣት ችለዋል።

እርግጥ አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያዊያን በቀደምት አበውና እመው ዘመን አንድነት ያላቸው በመሆኑ፣ ዛሬ የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም ሊሉ ይችላሉ። በእኔ እምነት ይህ አስተሳሰብ ፈፅሞ የተሳሳተ ነስው። ምክንያቱም ቀደምት ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል ባካሄዷቸው ትግሎች ወቅት የነበራቸውን አንድነት፤ ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና ይሁንታ ለተመሰረተው አንድነት መገለጫ አድርጎ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም።

በእኔ እምነት ባለፉት ስርዓቶች የተፈጠረው አንድነት፤ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነፃ ፍላጎትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አልነበረም። ይልቁንም ገዥ መደቦች ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቃድ ውጭ የመሰረቱት የኃይል አንድነት ነበር በመላ ሀገሪቱ ሰፍኖ የቆየው።

በቀድሞዋ ኢትዮጵያ የነበረው አንድነት በዥዎች የጠብ-መንጃ አፈሙዝ እንጂ፤ በእውነተኛ ህዝቦች ፍላጎትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አልነበረም። እርግጥም አንድነት እውነተኛ ሊሆን የሚችለው የትኛውም ህዝብ የራሱን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብቱን ተጠቅሞ የሚመሰርተውና ሊመሰርት የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲኖር ነው።

ባለፉት ስርዓቶች ታዲያ ይህ ባለመኖሩ ነው—የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዛሬ 23 ዓመት ገደማ ሁሉንም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ያረጋገጠና በተግባር ላይ ውሎ ተጠቃሚ ያደረጋቸውን ህገ-መንግስት ያፀደቁት።

በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት 23 ዓመታት በህገ-መንግስቱ መሰረት ገቢራዊ የሆነው ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንጂ፣ በኃይል ወይም ለይስሙላ ሲባል የተደረገ አንድነት አለመሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተመሰረተው አንድነት ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነፃነታቸውንና እኩልነታቸውን በማወጅ፤ አንዱ የሌላው የበላይ ሳይሆን በጋራ መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ሁኔታም አንዱ ብሔር የሌላውን ብሔርና ህዝብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ትውፊቶችን የማክበር፣ የመተዋወቅና የልምድ ልውውጥ የማድረግ ተግባሮችን ሊፈጥር ችሏል።

ባለፉት ስርዓቶቹ ተገልለውና ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በብሔራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ በእኩልነት የመሳተፍ መብት አልነበራቸውም።

እንዲያውም በአካባቢያቸው አስተዳደር ውስጥ በአመራር ቦታ ላይ የሚሾሙ አስተዳደሮችና ዳኞች ከማዕከላዊ መንግስት የሚላኩ የኋላ ታሪካቸው ያስረዳል። ሌላው ቀርቶ በወቅቱ የነበረውን የመንግስት ሠራተኞችን ሁኔታ ብንመለከት እንኳን፤ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ነበሩ።

የአካባቢው ተወላጆች እንኳንስ መሾም ይቅርና በሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ የመካተት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ ግመል በመርፌ ቀዳዳ እንደ መሽሎክ ያህል እጅግ አስቸጋሪ ነበር። በመሆኑም እነዚህ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መብት ተነፍጓቸው በሌሎች እየተተዳደሩ እንዲሁም ሀብታቸውም እተየመዘበረ ሊኖሩ ግድ ሆኖባቸዋል።  

የየራሳቸውን አኩሪ ባህልና ቋንቋ የሚጠቀሙበትና የሚያበለፅጉበት ዕድል አልነበራቸውም። አዎ! በእነዚያ ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች የአብዛኛዎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል የሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ተደርገው ከመቆጠር ይልቅ፤ ገሚሶቹ “ብረት ሰባሪ…ወዘተ” እየተባሉ የሚጠሩ ነበሩ።

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመዳኘት፣ የመማር…ወዘተ. መብት ስላልነበራቸውም፣ አብዛኛዎቹን ቋንቋዎች እንኳንስ በአደባባይ ለመጠቀምና ስራ ላይ ለማዋል ይቅርና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለመጠቀም እጅግ የሚያሸማቅቅ ሁኔታ እንደነበረም የሚዘነጋ አይመስለኝም። ባህላቸውን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት መብታቸው የተነፈገ እንደነበርም እንዲሁ።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ስርዓቶች ሰብዓዊ መብታቸውንም ተገፈፈው ኖረዋል። የአካል ደህንነት፣ በህይወት የመኖር መብት፣ ክብርን ከሚያዋርዱ አያያዞች የመጠበቅ… ወዘተን. ከመሳሰሉ መብቶች ጋር አይተዋወቁም ነበር። ከዚህም አልፎ በህግ ባልተደነገገ ሁኔታ ኢ-ሰብዓዊ ለሆነ እስር የመዳረግ፣ በስውር የመታገት…ወዘተ. ወንጀሎች እየተፈፀመባቸው ለከፋ ስቃይና እንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸው የታሪክ ድርሳናቸው ያስረዳል። ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩል ዓይን የማይታዩ መሆናቸውም ጭምር።

እርግጥ እነዚህን ዋነኛ የመብት ጥሰቶችን በዚህ አጭር ፅሑፍ ላይ በአስረጅነት አነሳኋቸው እንጂ፤ ስርዓቶቹ በዜጎች ላይ ሲፈፅሟቸው የነበሩትን ሌሎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ‘ቤቱ ይቁጠራቸው’ ብሎ ማለፍ ተገቢ ይመስለኛል—እንግልቶቹንና አፈናዎቹን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልምና።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሲከማቹ የቆዩ ብሶቶች በስተመጨረሻ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግል ዳግም ላይመለስ ስርዓተ-ቀብሩ እንዲፈፀም አድርጓል። ከደርግ ግብዓተ-መሬት በኋላም በሽግግሩ ወቅት የተረቀቀው ቻርተር ቀደም ሲል የገለፅኳቸውንና ሌሎች ተነፍገው የነበሩትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ ዕውን ማድረግ ችለዋል።

እነዚህ መብቶችም እስከ ታች ድረስ በዘለቀ ህዝባዊ ውይይት ታጅበውና ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ መክረውና ዘክረው የዛሬ 23 ዓመት ገደማ ባፀደቁት ህገ መንግስት አማካኝነት፤ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት፣ በራስ ቋንቋ የመጠቀምና የማሳደግ፣ ባህልን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪክን የመጠበቅ እና ሌሎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፍ እንዲረጋገጥ ተደርጓል።

በዚህ ሁኔታ ላይ ተመርኩዞ በህዳር ወር ላይ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአፋር ርዕሰ-መዲና ሰመራ ላይ ይገናኛሉ። ዕለቱ ራሳቸውን ከማስተዋወቅ፣ አንዱ የሌላውን ባህላዊ ትውፊቶች ከማወቅ፣ በየክልላቸው ያላቸውን ፀጋዎች ለኢንቨስትመንት ለማስተዋወቅ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አያጠያይቅም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy