Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብአዴን 37ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በኦሮሚያ ክልል ተከበረ

0 988

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብሄረ አማራ ዴሚክራሲያዊ ድርጅት (ብአዴን) 37ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በኦሮሚያ ክልል በዛሬው እለት ተከብሯል።

በዓሉ በአዲስ አበባ ኦሮሞ ባህል ማእከል የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና የብሄረ አማራ ዴሚክራሲያዊ ድርጅት (ብአዴን) ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት በተገኙበት ነው የተከበረው።

እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች በበዓሉ ላይ መታደማቸውን የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል።

ANDM_oro_2.jpg

በበዓሉ ላይ ኦህዴድን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ አባ ዱላ ገመዳ፥ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

አቶ አባዱላ፥ “የብአዴንን የምስረታ በዓል ስናከብር ለኛ ለኦህዴዶች የእህት ድርጅትን በዓል ማክበር አይደለም፤ የብአዴንን የምስረታ በዓል ስናከብር ለኛ የድርጅታችንን በዓል ማክበር ነው” ብለዋል።

“ምክንያቱ ደግሞ የኦህዴድ መስራች አባላት መታገያ ስፍራ ባልነበራቸው ዘመን መታገያው ኢህዴን የዛሬው ብአዴን እና የአማራ ህዝብ ስለነበረ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

“37 ዓመት የአንድ ጎልማሳ እድሜ ነው፤ እዚህ ለመድረስ ብዙዎች ተሰውተዋል፤ እኛን ለዚህ ያበቁ ምርጥ ታጋዮች አልፈዋል” ያሉት አቶ አባዱላ፥ “የዛሬውን በዓል ስናከብር እነሱ የሰጡንን አደራ ከግብ ለማድረስ እና ለቀጣዩ ትውልድ ቃል በመግባት መሆን ይገባል” ብለዋል።

ብአዴን፣ ኦህዴድ በአጠቃላይ ኢህአዴግ ከባድ ሀላፊነት አለበት ያሉት አቱ አባ ዱላ፥ ሀላፊነቱ ጠንካራ እና ትልቅ ሀገርን የመገንባት ጉዳይ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

በዚህ ውስጥ ብዙ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ፤ እነዚህን ችግሮች መቋቋም እና ማሸነፍ የሚቻለው ገድሞ አንድ በመሆን ነው ብለዋል።

የብአዴን/ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባልና የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው በበኩላቸው፥ በብአዴን እና በኦህዴድ መካከል ያለው በደምና በአጥንት የተሳሰረ አንድነት ምን ማለት እንደሆነ ነባር ታጋዮች በዝርዝር ነግረውናል ብለዋል።

ስለዚህ አዲሱ ትውልድ ይህንን አጠናክሮ የማስቀጠል አደራ አለበት ብለዋል።

በዓሉ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ላደረጉ የኦህዴድ አመራሮች እና አባላት በድርጅታቸው ብአዴን እና በራሳቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የብሄረ አማራ ዴሚክራሲያዊ ድርጅት (ብአዴን) 37ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “ህዝባዊነትና የአላማ ፅናት ለዴሞክራሲያዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ሲከበር ቆይቷል።

በዓሉ በፌደራል እና በክልል ደረጃ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልሉ ባለስልጣናት እንዲሁም የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት ህዳር 11 2010 ዓ.ም መከበሩም ይታወሳል።

በበአሉ ላይ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ታላቅ መስዋእትን ለከፈሉ ከ8 ሺህ በላይ የድርጅቱ ነባር ታጋዮች እውቅና ተሰጥቷል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy