የኢንዱስትሪ መንደሮች—ለመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር
ደስታ ኃይሉ
በአሁኑ ወቅት ስራ የጀመሩትንና በመገንባት ላይ ያሉትን የኢንዱስትሪ መንደሮች ለአገራችን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ከመፍጠር አኳያ ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው። ለዚህም መንደሮቹ ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አኳያ ወደ 20 በመቶ እንዲያድጉ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል።
የኢንዱስትሪ መንደሮቹ (ፓርኮቹ) የወጭ ንግዱን ከማጠናከር አኳያም የራሳቸውን ሚና በመጫወት በዕቅዱ ላይ የተቀመጠውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ማረጋገጥ የሚችሉ ናቸው። ይህም በተለይ የማምረቻ ኢንዱስትሪው የአህጉሪቱ የስበት ማዕከል እንዲሆን ያስችለዋል።
በዕቅዱ ላይ እንደተገለፀው ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጡን ለማስጀመር የማምረቻ ኢንዱስትሪው በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። በዚህም በ2012 ዓ.ም የማምረቻ ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል። ይህም የማምረቻ ኢንዱስትሪው ድርሻ አሁን ካለበት በአራት እጥፍ በማሳደግ በ2ዐ17 ዓ.ም ወደ 18 በመቶ እንዲደርስ ምቹ መደላድል ይፈጥራል።
የማምረቻ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚና ከፍተኛ ነው። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የዘርፉ ምርቶች ጠቅላላ የኤክስፖርት ገቢ ያላቸው ድርሻ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ ከ1ዐ በመቶ የማይበልጥ ነው። ሆኖም በዕቅዱ መሰረት በ2012 ላይ ወደ አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ ታስቧል። ይህ ድርሻም ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግና በ2017 ዓ.ም 40 በመቶ ለማድረስ ግዙፍ ዕቅድ ተቀምጧል።
ሌላው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡ አመላካች የሚሆነው በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የሚደረገው የሰው ሃይል ሽግሽግ ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት በመካከለኛና በከፍተኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የተሰማራውና ከ350 ሺህ የማይበልጠውን የሰው ሃይል በቀጣዩቹ አስር ዓመታት በአራት እጥፍ እንዲጨምር ለማድረግ ታስቧል። ይህም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዩን ዜጎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር ነው። እነዚህን የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ልማታዊ ፋይዳዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ብርቱ ርብርብ እያደረገ ነው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው።
ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።
በአገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። እርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በአገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በአገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። ይህ ሁኔታም የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፤ የአገርን ሃብት በአገር ዜጋ የማፍራት ሁኔታን ይፈጥራል።
ታዲያ ይህን ውጥን ዕውን ለማድረግ ርብርብ ማድረጉ አጠያያቂ አይሆንም—በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በማሳተፍና በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የዕቅዱን ገቢራዊነት ማረጋገጥ መቻሉ አጠያያቂ የሚሆን አይመስለኝም። እርግጥ መንግስት የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከወዲሁ እያከናወና ያለውና በዕቅድ ደረጃ የያዛቸው የተለያያዩ የተጠቃሚነት ማዕቀፎች ሃቁን የሚያሳዩ በመሆናቸው በቀሪው የልማት ዕቅዱ ዘመን ተጠናክረው ከቀጠሉ ስኬቱን ማረጋገጥ ይቻላል።
እርግጥ በዕቅዱ ላይ በዘርፉ የተጠቀሱትን ስኬቶች እውን ለማድረግ በሁለት ዘርፎች ትልሞች ተይዘዋል—በጥቃቅንና አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ለመስጠት። ይህ ሁኔታም በሁለቱም ዘርፎች ውስጥ ኤክስፖርት መር የኢንዱስትሪ አቅጣጫን ለመከተልና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ በሚደረገው ሽግግር ውሰጥ የራሱን ሚና ይጫወታል።
እንደሚታወቀው በሀገራችን ውስጥ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰረቱ ይህን ያህል የሚያስመካ አይደለም—ጠባብ ነው። ያም ሆኖ ግን ሀገራችን በዘርፉ ለውጥ እንድታመጣ በዋነኛነት ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ይኖርባታል። በተለይም በማደግ ላይ የሚገኘው የሀገራችን ባለሃብት የለውጡ ተሳታፊ እንዲሆን እንዲሁም በተመረጡ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተግባሩ እንዲከናወን ማድረግ ያስፈልጋል። እናም ከሀገር ውስጡ ባለሃብት በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚኖራቸው የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተሳታፊነት የማይናቅ ቦታ ይኖረዋል። ይህም የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ጉልህ ሚና አለው።
ይህን መሰረታዊ ዕውነታ በመመርኮዝም በዕቅድ ዘመኑ በሁሉም ዘርፎች ጥንቃቄ በተሞላው ሁኔታ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብርቱ ጥረት ይደረጋል። በተለይም ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት እንዲሁም በአፈፃፀማቸው ጥሩ ስምና ዝና ያላቸውን የውጭ ኩባንያዎች በመመልመልና የማግባባት ስራ በማከናወን የዘርፉን ዕድገት እንዲያሳድጉት ማድረግ እንዲገባ ተጠቅሷል። ባለሃብቶቹን ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች ላይ በማሰማራት ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ ውጥን ተይዟል።
እርግጥ ሀገራችን የውጭ ባለሃብቶች ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ ዘርፎች ውስጥ እንዲካተቱ ስታደርግ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ምንም ዓይነት ቦታ ሳትሰጥ ነው ማለት አይደለም። የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በዘርፉ እንዲያፈሱ ይደረጋል። በተለይም በማደግ ላይ የሚገኙት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ተመልምለው በቂ ድጋፍ እንደሚሰጣቸውና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ገቢ ምርቶችን በሚተኩ ዘርፎች ጭምር እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ዕቅዱ ያብራራል።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል።
ታዲያ ይህን ዕውን ለማድረግም በአሁኑ ወቅት ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። ይህ ሁኔታም መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለመፍጠር ዓይነተኛ ሚና ያበረክታል።