Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወቅቱ ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እይታ

0 377

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወቅቱ ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እይታ

                                                                                       ይልቃል ፍርዱ

ሰሞኑን በሀገራዊ ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ጋር  ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት በሀገሪቱ የሚያጋጥሙትን  ግጭቶች ለመፍታት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የሚከሰቱ  የሰላምና መረጋጋት ችግሮችን በአግባቡ  ለመፍታት ሕዝቡን በዋናነት በማሳተፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ይህም ተከታታይ የሕዝብ ውይይቶችን እንደሚያጠቃልል ነው የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልል የፀጥታ አካላት በተቀናጀ ሁኔታ ያለአግባብ መጠቀም የሚፈልጉ የጸረ ሰላም  አካላትን ከዚህ ድርጊታቸው ለማስቆምና በዘላቂነት ይህን ድርጊት ለማጥፋት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ስራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ በ100ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ግብረኃይል ተመስርቶ በቀናት ውስጥ ስራውን እንደሚጀምር ጠቁመው በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች  ተከስተው  የነበሩት ግጭቶች ቆመው  ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን  አረጋግጠዋል፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ከተፈጠረ በኋላ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች መካከል መስማማቶች የሉም ልዩነቶች ይስተዋላሉ የሚል ጥያቄ  የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየታየ ያለው ችግር በፓርቲዎች መካከል ሳይሆን አመራሩ ላይ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል የፀጥታ አካላት ማስከበር ያለባቸው ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን ሆኖ ሳለ ጥቂት የፀጥታ አካላት በደምና በጎሳ ለይቶ ሕዝብን የማየት አዝማሚያ እንደተስተዋለባቸው፤ አንዳንድ የፀጥታ አካላትም በግጭት ውስጥ ተሳትፈው በመገኘታቸው እርምጃ መወሰዱን  ሰላምን በማደፍረስ ተግባር  ላይ  የተገኙትን አካላት ተጠያቂ ማድረጉ ተከታታይ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ነው ጠቅላይ  ሚኒስትሩ የገለፁት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢሕአዴግ ውስጥ ይፋ ስለማይደረግ እንጂ ቀድሞም የሀሳብ ትግል መኖሩን ሁሌም ግን ያሸነፈው ኃሳብ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም መረጃን ከመስጠት አንፃር በመንግስት በኩል ያለው ክፍተት ችግር ሕዝቡን በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ለሚናፈስ አሉባልታና የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እንዳጋለጠው አምነዋል፡፡

በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ልዩነት ይታያል ለሚለው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ አባል ድርጅቶቹ ያደረጉትን ኮንፍረንስ በማሳያነት በማቅረብ የተለያየ ፓርቲ እንዴት በተለያየ ኮንፍረንስ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ያንፀባርቃል? በሚለው ጥያቄያቸው መልስ ሰጥተዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልሎች ከፌደራል መንግስቱ ይልቅ ጠንክረው እየወጡ ነው፤ ይህ እንዴት ይታያል? ለሚለው ጥያቄ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ይህ ደስታችን ነው  የሚል ሲሆን፤ ሕገ መንግስቱ የክልሎችንና የፌደራል መንግስትን ስልጣን ለይቶ ያስቀመጠ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ በፌደራል መንግስቱ ድጎማ የሚንቀሳቀሱት ክልሎች በሚፈለገው ደረጃ ጠንክረው አለመውጣታቸውንም እንደዛው።

በአጎራባች ክልሎች መካከል እየተካሄደ ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ኮንፍረንስ በክልሎች ብቻ ሳይሆን በፌደራል መንግስት እቅድ ውስጥ የነበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኦሮሞና አማራ ሕዝቦች መካከል የተጀመረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ይህ በሁሉም ተጎራባች ክልሎች መካከል እንደሚቀጥልና በመጨረሻ ወደ ሀገርአቀፍ ኮንፍረንስነት እንደሚመጣ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ የነበሩትን የተሐድሶ ሂደቶች በማስታወስ ጥገኛው ባለሐብት በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ተጣብቆ የመበልፀግ ፍላጎት የታየበትን አካሄድ ለማረም የታለፈባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አሁን ላይ ግን የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጥቅሙን ለማስከበር ሕዝብን ከሕዝብ እስከማጋጨት መድረሱን ለዚህም በቅርቡ አወዳይ ላይ የነበረውን ሁኔታ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ አካባቢ ላይ የነበረው ግጭት መነሻ ቦታው ጫት በዋነኛነት የሚመረትበት በመሆኑ ከዚህ ምርት አምራቹ እንዳይጠቀም በመፈለጋቸው ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጠቃላይ ምንም እንኳ ኢኮኖሚው ቢያድግም አብሮት ያረገዘው ችግር አለ፤ ይህም ችግር ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑን አስምረውበታል፡፡ የልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የበላይነቱን እስከሚያረጋግጥ ድረስ ኢሕአዴግ የጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ሂደት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳዑዲ አረቢያ ከሙስና ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ካዋለቻቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቢሊየነር ሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲንን በተመለከተ መንግስት በዲፕሎማሲያዊ መልኩ ጉዳዩን አስመልክቶ መረጃውን እየተከታተለ መሆኑን፤ ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ባለው የእሳቸው ኢንቨስትመንት ላይ እክል ይፈጠራል ብሎ መንግስት እንደማያምን ነው የገለፁት፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሳዑዲ አረቢያ ሉዓላዊ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሌላ ሊሰራ የሚችል ነገር እንደሌለ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ለመድረሱ እጃቸው አለበት የተባሉ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች አካላትን ለሕግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑም ተገልጾአል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከብሔራዊና  ከክልል ደህንነት ምክር ቤቶች፤ ርእሳነ መስተዳድሮች፤ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር በአገሪቷ ሠላምና ፀጥታ ዙሪያ መክረው በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ያለውን የሠላምና ፀጥታ ሁኔታ በመገምገም ግጭቶች ዳግም እንዳይከሰቱ መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አስታውቀዋል፡፡

የብሔራዊ ደሕንነት ምክር ቤት ኃላፊና የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ የምክር ቤቱን የ2010 ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ክልሎችም በሠላምና ፀጥታ ዙሪያ እቅዶቻቸውን አዘጋጅተው በቅንጅትና በተደራጀ መልኩ በጋራ እንዲሰሩ አቅጣጫዎች ተለይተው ወደስራ የተገባበት ሁኔታ መኖሩን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሚኒስትሩ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ በየአካባቢው በአውራ መንገዶችና ኬላዎች የሚከሰቱ ግጭቶች በሕዝቦች እንቅስቃሴና ወደውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ጫና እየፈጠሩ በመሆኑ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

“ተመሳሳይ ግጭቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ ሁሉም የፀጥታ ኃይሎቻችን በቅንጅት ተናበው ሰላማዊ ማድረግ ይገባቸዋል፤ የታየው ችግር መደገም የለበትም።” በማለት የጋራ አቋም መያዙን ጠቅሰዋል፡፡ በአገሪቷ በርካታ ቦታዎች ሕገ-ወጥ ሰልፎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን የአሸባሪ ባንዲራዎችን ጭምር በመያዝ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን በቀጣይ ሕገ-ወጥ ሰልፎችን ለማስቀረት የተሳሳቱ አካላትን በማስተማር ትክክለኛ ግንዛቤ ይዘው እንዲሄዱ መሥራት እንደሚገባ በምክር ቤቱ የሕግ የበላይነትን የማስከበር እቅድ ውስጥ መካተቱን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ከመንግሥት አመራር እስከ ታችኛው አካል የፀጥታ አካልም ሆነ ሌሎች በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ አካላት ተለይተው የሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ከኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በእቅድ ዝርዝር ጉዳዩ ታይቶ እያንዳንዱ ክልል ያለው የዝግጅት ሁኔታ ተገምግሞ በፍጥነት እንዲመለሱ ከመግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy