Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዜጎች የመንቀሳቀስና ሃብት የማፍራት መብቶች ሊገደቡ አይችሉም!

0 528

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዜጎች የመንቀሳቀስና ሃብት የማፍራት መብቶች ሊገደቡ አይችሉም!

                                                     ደስታ ኃይሉ

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በህግ መንግስቱ ተረጋግጧል። ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው የመኖር እንዲሀም ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ያላቸው መሆኑም ጭምር። ይህ መብታቸው ህገ መንግስታዊ በመሆኑ ማንም ሊሸረሽረው አይችልም። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሁሉም ህዝቦች የጋራ ቤት ናት። ህዝቦች ይህችን የጋራ ቤታቸውን ለማልማት በሚያደርጉት ሂደት ውስጥ እንቅስቃሴያቸው ሊገደብ አይችልም።

በአገራችን እየተገነባ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያና ለህዝባችን አንድነት፣ ሰላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው። ይህ እውነታም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተመሰከረለት ነው።

በመገንባት ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ያሰገኘ ነው።

የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓቱ አባል መንግሥታት የተደራጁት በመሠረቱ በብሔር ብሔረሰብ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ባለፈው ታሪክ ማንነቶች የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች በህገ መንግስት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚችሉት ይህንኑ አወቃቀር በመከተል ስለሆነ ነው።

ማንነቶች የተዛባውን ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሣሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት አንዱ ልዩ ባህሪ ተደርጎ የሚወሰደው አንዱ ይህ ነው። ባደጉት አገራት በተለምዶ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ተደርገው የሚወሰዱት ህዝቦች ናቸው። ይህ አስተሳሰብ የቡድን መብቶችን ወደ ጎን መተውን ብዙዎች ምሁራን ይስማሙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል። በምስረታው ወቅት የገቡትን ቃል በአፈፃፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ወስደዋል። የዚህ ድንጋጌ ቁልፍ ትርጉም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ የመኖር ስምምነት ነው።

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የግል መብቶችን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ይገልፃል፡፡ ብዙ ፀሐፊዎች የቡድን መብቶች ከግል መብቶች ተለይተው መገደብ የሌለባቸው እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡

የግል መብቶችን በማረጋገጥ ብቻ የቡድን መብቶችን ማረጋገጥ እንደማይችል፣ የቡድን መብቶችን የሚከለክል ስርዓት የግለሰብ መብቶችን ብቻ በማስከበር የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊሆን እንደማይችል የሚገልፁም አሉ።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ያደጉ የዴሞክራሲ አገሮች የቡድን መብቶችን በተሟላ መልኩ ባለመረጋገጣቸው ምክንያት የቡድን መብት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ የአገራቱን ውስጣዊ ስላም በማናጋት ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እሥር ቤት ልትሆን የቻለችው የቡድን ማንነቶች ማፈን ዋነኛ የጭቆና መገለጫ ስለነበር ነው።

በፌዴራላዊ ስርዓቱ ከተደነገጉ የህዝብ መብቶች ውስጥ አንዱ የሃይማኖት እኩልነትና የእምነት ነፃነት ነው። መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን፤ ሁሉም ሰዎች በመካከላቸው የዘር፣ የብሔር፣ የብሔረሰብ፣ የጾታ፣ የኃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የህግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው፣ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊናና የኃይማኖት ነፃነት፣ የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት ለብቻው ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን የማምለክ፣ የማስተማርና የመግለፅ መብት አለው።

ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሁሉም አካባቢዎች የመንቀሳቀስና ሃብት የማፍራት መብትንም ያካትታል። በህገ መንግስቱ ላይም እነዚህ መብቶች ተደንግገዋል። ኢትዮጵያዊያን አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት በህገ መንገስቱ ላይ ቃል ኪዳን ያሰሩ በመሆናቸው በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው የመስራት መብት አላቸው።

ይህ መብታቸው በየትኛውም ወገን እንዲቀር የሚደረግ አይደለም፤ ህገ መንግስተቱን መፃረር ስለሆነ። እናም የኢትዮጵያ ህዝቦች ይህንን መብታቸውን በክልላቸውም ይሁን ከክልላቸው ውጭ በሆነ ሁኔታ መተግበር እንደሚችሉ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።

ዜጎች በሌላ ጉዳይ በህግ ክልከላ ካልተደረገባቸው አሊያም የሌሎችን የመልማት መብት እስካልተቃወሙ ድረስ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ሃብት የማፍራትና ንብረትየመያያዝ ህገ መንግስታዊ ዋስትና አላቸው። የአንድ አገር ጠቅላላ ምጣኔ ሃበት እድገት የሚለካው በዜጎች የመልማትና ሀብት አፍርቶ የማደግ አቅም በመሆኑ ይህ መብታቸው ከአጠቃላይ አገራዊ እድገት አኳያ የሚታይ በመሆኑ ሊከበርላቸው ይገባል።

የስርዓቱ መሰረት የሆነው ህገ መንግስት ለእነዚህ ድንጋጌዎች ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው የኃይማኖቶች እኩልነትና የእምነት ነጻነት ሳይረጋገጥ ያለፈውን የተዛባ ግንኙነት ማስተካከል አይቻልም ከሚል መሠረታዊ አስተሳሰብ በመነሳት ነው።

አዲስ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የመገንባት ጉዳይም ከእነዚህ መብቶች ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። ለህዝብ የሚገደብ መብት መኖር የለበትም የሚል መሠረታዊ እምነት ፌዴራላዊ ስርዓቱ ስለሚያምነበት ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች በግልም ይሁን በቡድን የመረጡትን እምነት የመከተል መብታቸውን ማረጋገጥ የህዝብ ልዕልና አንድ አካል ነው።

ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ የተለያዩ መብት አስጠባቂ ተቋማትን በማቋቋም የተለያዩ ርምጃዎችን ወስዷል በመውሰድ ላይ ይገኛል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት…ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው።

እነዚህ ተቋማት ህብረተሰቡ በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት አፈፃፀም ሳቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳዩችን ጥያቄ ሲቀርብላቸውና በራሳቸው ተነሳሽነትም ይመረምራሉ፣ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሃሳቦችን በማቅረብም ተግባራዊነታቸውን ይከታተላሉ። በዚህ ተግራቸውም በስርዓቱ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ሚዛናዊ ጉዳዩች እውን እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ተቋማቱ የዜጎችን የመንቀሳቀስና ሃብት የማፍራት መብቶች መጣስና አለመጣሳቸውን በመቃኘት ህገ መንግስታዊ መብቶችን ማስከበር ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy