Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የግብርና ልማት ለትራንስፎርሜሽን ስኬት

0 1,059

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የግብርና ልማት ለትራንስፎርሜሽን ስኬት

ኢብሳ ነመራ

ኢትዮጵያ የአርሶና የአርብቶ አደሮች ሀገር ነች። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ በእርሻና በእንስሳት እርባታ የሚተዳደር ነው። በአሁኑ ወቅት ግብርና ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ውስጥ 36 ነጥብ 3 በመቶ ገደማ ድርሻ አለው። የኢንደስትሪው ዘርፍ 25 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ ሲኖረው የአገልግሎት ዘርፉ ድርሻ ደግሞ 39 ነጥብ 3 በመቶ ነው። ባለፉት አስራ እምሰት ዓመታት ኢኮኖሚው ተከታታይ እድገት ሲያስመዘግብ በዚህ ውስጥ ግብርና ትልቁን ድርሻ ይዞ ቆይቷል። በቅርቡ የአገልግሎት ዘርፉ ድርሻ የበላይነት እስከያዘበት ጊዜ ድረስ የግብርናው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ቀዳሚ ነበር። ይህ መዋቅራዊ ለውጥ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ውጤት ነው። የግብርናው ዘርፍ በሀገሪቱ የወጪ ንግድ ውስጥ ያለው ድርሻ አሁንም በጉልህ ከፍተኛ ነው። ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና የቁም ከብት የመሳሰሉት የግብርና ምርቶች 80 በመቶ የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ይሸፍናሉ።

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ግብ አጠቃላይ ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፎች ማሳደግ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢንዱስትሪውን የበለጠ በማሳደግ በሀገሪቱ ኢኪኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ቀዳሚ ማድረግ ነው። ይህ ግብ ውጤት እየታየበት ይገኛል። በ2017 የማምረቻ ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ቀዳሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የግብርናው ዘርፍ አሁንም በያዘው የሰው ሃይልና በወጪ ንግድ ድርሻ ቀዳሚ ነው። በመሆኑም በሀገሪቱ የዜጎችን ህይወት የማሻሻልና ለሌሎች ዘርፎች መጎልበት የሚያግዝ የካፒታል ክምችት በመፍጠር ውስጥ ግብርና የማይተካ ሚና አለው። በመሆኑም አሁንም የግብርና ዘርፍ ልማት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።

የግብርናው ዘርፍ በ2008 ዓ.ም. ከባለፉት ዓመታት አነስተኛ እድገት ያሳየበት ዓመት ነበር። በተጠቀሰው ዓመትም ግብርና የ8 ነጥብ 2 እድገት ያስመዘግባል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ያደገው ግን በ2 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ነበር። ይህ የሆነው በ2007 ዓ.ም. በልግና ክረምት በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢዎች በኤል ኒኖ ሳቢያ በተፈጠረ ድርቅ ሰበብ ነው። በ2009 ዓ.ም. የግብርናው ዘርፍ እድገት ማገገም አሳይቷል። በ2009 ዓ.ም. የግብርናው ዘርፍ በ8 በመቶ ያድጋል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ የ6 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል። በያዝነው በ2010 በጀት ዓመትም የግብርናው ዘርፍ በ8 በመቶ ያድጋል ተብሎይጠበቃል።

በ2009 መኸር 12 ነጥበ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ተሸፍኗል። ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባለው የመስመር እርሻ የለማ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዘንድሮው የመኸር ወቅት በአጠቃላይ 345 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት እንደሚጠበቅም የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታውቋል። ይህ ሰብል ገና ተሰብስቦ አልገባም። የሀገሪቱ መኸር አብቃይ አከባቢዎች የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት ስለነበረ በማሳ ላይ ጥሩ ቡቃያ መኖሩን መነሻ በማድረግ ነው 345 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ይሰበሰባል መሚል የተተነበየው፤ በማሳ ላይ ያለው ሰብል የትንበያውን ያህል ምርት እንዲሰጥ አርሶ አደሩ በእሸት ደርጃ ያሉ ምርቶችን በአግባቡ እንዲጠብቅ፤ በየጊዜው ማሳውን እንዲፈትሽ፤ ሰብሉ በአረም እንዳይጠቃ እንዲቆጣጠር ክትትል እየተደረገ  መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በ2010 በጀት ዓመት የግብርናን ምርት ለማሳደግ፤ በተመረጠ የግብርና መሰረተ ልማት ላይ ያተኮረ የግብርና እድገት ፕሮግራም ተግባራዊ ይደረጋል። የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ ፕሮግራሙ በእርሻ ላይ ብቻ ሳይሆን የእንስሳ ልማትንም የሚያካትት ነው። ለዚህ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ሶስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት መመደቡንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ከመንግስትና ከልማት አጋሮች በተገኘው በጀት የሚካሄደው ይህ ፕሮግራም የሀገሪቱን የግብርና እድገት ለማፋጠን ያግዛል ተብሎ ታምኖበታል። ፕሮግራሙ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሀረሪ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር  ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል።   

በእነዚህ አካባቢዎች በዓመቱ ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የአንድ ሺህ 161 አነስተኛ መስኖና 671 መለስተኛ የእጅ ጉድጓድ ግንባታዎች ይገኙበታል። እንዲሁም፤ የውኃ ማቆሪያ፣ መሳቢያና ውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ማሰራጨት፣ የአራት የፈሳሽ ናይትሮጂን ማምረቻ ተቋማትና የ338 የእንሰሳት ህክምና በረቶች ግንባታ ስራ ይከናወናል። በፕሮግራሙ የ20 ሺህ 500 የአንድ ቀን እድሜ ያላቸው የዶሮ ጫጩቶች ግዥና ስርጭት ይካሄዳል። የከብት አባለዘርና አባላዘሩ ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያደርገውን ፈሳሽ ናይትሮጂን አቅርቦት ተደራሽ  ለማድረግም ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች፤ አባለዘርና ፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻ ማዕከላት ይቋቋማሉ። የንግሥት ንብ ማራቢያና የአሳ ዕንቁላል መፈልፈያ፤ የሰብልና የእንስሳት የመጀመሪያ ደረጃ ገበያ፤ የወተትና የማር ግብይትና የማቀነባበሪያ ማዕከላት እንደሚገነቡም ይጠበቃል።

የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ እድገት የማይዋዥቅና አስተማማኝ ለማድረግ አሁን ከሚገኝበት የዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ማለት የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ማለት ነው። በዚህ ረገድ እስካሁን ተስፋ ሰጪ ጅምር ስራዎች ታይተዋል። በቀጣይም ዘርፉ ጉልህ እድገት ማስመዝገብ እንዲችል የሚያግዙ ተግባራት እንደሚከናወኑ የሚያመለክቱ አስረጂዎች አሉ።

በያዝነው የ2010 በጀት ዓመትም  በመስኖ ልማት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማቃለል ከ450 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቋል። ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጨምሮ እንዳስታወቀው፤ በተያዘው በጀት ዓመት በመስኖ ልማት ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ የስነምግብ ፕሮግራም እውን የማድረግ ግብም ተቀምጦ እየተሰራ ነው።

በ2010 በጀት ዓመት የመኸር እርሻ የዝናብ እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች፤ በተለይም በትግራይ ምስራቃዊ ዞን፣ በምስራቅ አማራ፣ በቦረና፣ በጉጂ፣ በምስራቅና ምዕራብ ሐራርጌ፣ በሃዲያ፣ በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ሊኖር የሚችለውን የምርት መቀነስ በመስኖ ምርት ለማካካስ የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ከሚኒስቴሩ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገሪቱ በመስኖ ከለማው 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ370 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል። በዚህም 7 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ችለዋል። በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ሃብት ለማከማቸት ዳዴ የጀመሩም አሉ። በ2010 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማትና ከ450 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒትሰቴር መረጃ ያመለክታል። በመስኖ ልማቱ  ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ ታቅዷል።

በሌላ በኩል፤ በተያዘው በጀት ዓመት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ  ሰባት የመስኖና የግድብ ፕሮጄክቶች ወደ ልማት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ  የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቋል። ባለፈው በጀት ዓመትና ቀደም ብሎ  የተጠናቀቁት እነዚህ የመስኖና ግድብ ፕሮጀክቶች በተንዳሆ፣ በከሰም፣ በርብ፣ በአልዌሮ፣ በቆጋ፣ በመገጭና በጎዴ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው። ወደ ልማት እየገቡ ያሉት ፕሮጀክቶች በተለይ  ለስኳር ልማት የሚውሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በየአካባቢዎቹ የሚገኙትን አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ከዝናብ ጥገኝነት ያላቅቃል። ከዚህ ባለፈ ለበጋ ወራት የእርሻ ስራ፤ እንዲሁም የመጠጥ  ውሃ  ፍላጎት የማሟላት አቅም አላቸው።

በአጠቃለይ ከላይ የሰፈሩት መረጃዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሀገሪቱ የሰው ሃይል የተሰማራበትና የአብዛኛውን ዜጋ ህይወት ለማሻሻል ወሳኝ የሆነው የግብርና ዘርፍ ቀጣይ የእድገት አቅጣጫ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን ያመለክታሉ። የሀገሪቱ ግብርና እድገት የአብዛኛውን ዜጋ ህይወት ከማሻሻል ባሻገር ሀገራዊ የካፒታል ክምችት በመፍጠር ረገድ ጉልህ ድርሻ ስላላው ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካትም ወሳኝ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy