Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹የግብፅን የዓባይ የውኃ ድርሻ ማንም እንደማይነካው ለግብፃዊያን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ›› አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት

0 660

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • በህዳሴ ግድቡ ላይ ስምምነት መፍጠር እንዳልተቻለ ግብፅ ለአሜሪካ ማሳወቋ ተጠቁሟል

የግብፅን የዓባይ የውኃ ‹‹ለአገሪቱ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው›› ያሉት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቁ ነው የተባለው የዓሳ ማምረቻ ከቀናት በፊት በተመረቀበትና በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፣ ‹‹የግብፅን የዓባይ የውኃ ድርሻ ማንም እንደማይነካው ለግብፃዊያን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያና ለሱዳን የግብፅን የዓባይ የውኃ ድርሻ ማንም ሊነካው እንደማይችል እንዳሳወቁ የተናገሩት አልሲሲ፣ ከህዳሴ ግድቡ ግንባታ ጀርባ ያለውን የኢትዮጵያን የመልማት ግብ እንደሚረዱ ገልጸው፣ ይህ የኢትዮጵያ የመልማት ግብ ግን ለግብፅ ‹‹የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የግብፅ ባለሥልጣናት በህዳሴ ግድቡ የተፅዕኖ ግምገማና የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጥናት መዘግየት ሥጋት እንደገባቸውና የተፅዕኖ ግምገማው መነሻ እ.ኤ.አ. የ1959 የቅኝ ግዛት ስምምነት እንዲሆን ያቀረቡት ጥያቄ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ በቀጣዩ ወር ለመምከር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዳሳለኝና የግብፅ ፕሬዚዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ ቀጠሮ መያዛቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ኃላፊዎች ሪፖርተር ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ግን፣ በቅኝ ግዛት ስምምነት ላይ የተመሠረተ ምንም ዓይነት ድርድር ለማካሄድ ኢትዮጵያ ፍላጎት የላትም፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ ኮሚቴ 16ኛውን ስብሰባውን ከማካሄዱ በፊት፣ የአገሮቹ የውኃ ሚኒስትሮች የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ የግብፅ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ (ዶ/ር) የግድቡ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት በመዘግየቱ ሥጋት እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

የግብፅ ሚዲያዎች ሚኒስትሩ በግድቡ ግንባታ ዕድገት ምክንያት የሦስትዮሽ የቴክኒክ ውይይቱ ትርጉም አልባ ነው የሚል እምነት መያዛቸውን ዘግበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ድርድሩን በራሷ ተነሳሽነት የጀመረችው መተማመንን ለማዳበር እንጂ በፕሮጀክቱ ላይ ሌሎች አገሮች ውሳኔ እንዲያሳልፉ አለመሆኑን በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የህዳሴ ግድቡ ለተፋሰሱ አገሮች ጭምር የሚጠቅም ፕሮጀክት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ግብፅ ግን ግድቡ በውኃ ድርሻዬ ላይ መሠረታዊ ጉዳት ያመጣል በማለት ትከራከራለች፡፡ ግድቡ ምንም ዓይነት ጉዳት አያመጣም ሳይሆን፣ የታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ መሠረታዊ ጉዳት አያስከትልም በማለት ኢትዮጵያ ትሞግታለች፡፡

ግድቡ ለግብፅ የሚሰጣቸውን ጠቀሜታዎችም ትዘረዝራለች፡፡ የአፈር ዝቅጠትን መከላከሉ፣ የውኃውን ፍሰት መቆጣጠሩ፣ ከድርቅና ከጎርፍ የታችኛውን የተፋሰስ አገሮች መጠበቁ፣ ውኃ ማከማቸቱ፣ እንዲሁም ኃይል ማመንጨቱና በርካሽ ዋጋ ማቅረቡ ከጠቀሜታዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ከአሜሪካ አቻቸው ሬክስ ቲለርሰን ጋር እሑድ ኅዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ በህዳሴ ግድቡ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር ሊንቀሳቀስ እንዳልቻለ እንዳስታወቁ የግብፅ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ይህ ጥረት በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ለማሳደር ያለመ ቢሆንም፣ የሪፖርተር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች ግን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ መርህ የሆነውን ‹‹ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል መርህ›› በመከተል ከመሥራት ባሻገር የጣሰችው መርህም ሆነ ሕግ እንደሌለ፣ ሌሎች አገሮች በግድቡ ላይ የተፈጠረ አዲስ ነገር የማያገኙ በመሆኑና ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስምምነትን ትቀበል ሊሉ የሚችሉበት ዕድልም ስለማይኖር፣ ይህን መሰል ዘገባዎች የግብፅ ዜጎችን ከማምታታት የተረፈ ጠቀሜታ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy