Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጥላቻ ንግግር የኪራይ ሰብሳቢው ምሽግ ሆኗል

0 639

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጥላቻ ንግግር የኪራይ ሰብሳቢው ምሽግ ሆኗል

አሜን ተፈሪ

ኢትዮጵያ አንድ ትልቅ ድሱት ቤተሰብ በመሆን ዘመናትን ኖራለች ማለት አይቻልም፡፡ በዚሁ አንፃር በኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መካከል አስደናቂ ግንኙነት እና የአብሮ መኖር ጥበብ መኖሩንም መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ጉዳይ ለህዝብ ግንኙነት ሥራ ተብሎ ፖለቲከኞች የሚጠቅሱት አይደለም፡፡ አሁንም በግልፅ የሚታይ እና በተጨባጭ የሚዳሰስ እውነታ ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን ኢትዮጵያን የማየት ዕድል ያገኘ እንግዳ ሊመሰክረው የሚችለው ሐቅ ነው፡፡ ሆኖም ዛሬ ይህ አኩሪ የታሪክ ቅርስ በጥላቻ ንግግር ‹‹ወታደሮች›› ፈተና ተጋርጦበታል፡፡  

በ1959 ዓ.ም በታተመ አንድ ጥናቱ፤ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ትኩረት የሚስብ መልካም ግንኙነት መኖሩንና ይህም ለቀሪው ዓለም ሞዴል ሊሆን እንደሚችል የሚገልጸው ሴዝትሎው ጄስማን (Czestlaw Jesman)፤ የሩሲያ ዛሩ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በጉዳዩ ላይ ጥናት ማካሄዱን ጠቅሷል፡፡ ሩሲያ የራሷን ችግር ለመፍታት በማሰብ እና ከኢትዮጵያ ልምድ ለመቅሰም፤ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩነቱን አቻችሎ እንዲህ በሰላም ለመኖር የቻለው እንዴት ነው?›› የሚል ጥናት ማካሄዷን ስንመለከት፤ ኢትዮጵያውን ምን ያህል አኩሪ የአብሮ መኖር ታሪክ አንዳለን ለማሰብ እንገደዳለን፡፡  

በኢትዮጵያውያን መካከል አልፎ አልፎ ግጭቶች መታየታቸው ባይቀርም፤ ‹‹ግፍ የሚችል›› እና ችግርን ጥበብ በተሞላ አካሄድ መሻገር የሚችል ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር መቻላቸው እውነት ነው፡፡ ከፍ ሲል የጠቀስኩት ጄስማን ባካሄደው ጥናት በ1959 አካባቢ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን ይወቅሳል፡፡ ምሁራኑ (intelligentia) ይህን የኢትዮጵያን ህዝብ ‹‹ልዩ ችሎታ ወይም ደመ ነፍስ›› የማጣጣል፤ ትኩረት ሊቸረው የሚገባ ጉዳይ አድርጎ ያለማየት እና እንዲያውም የአስከፊው ዘውዳዊ አገዛዝ ትውፊት የሆነ አሳፋሪ ነገር አድርጎ የማየት ዝንባሌ አላቸው ሲል ይተቻል፡፡

ምናልባት የጄስማን አስተያየት ሁላችንንም ላያስማማን ይችላል፡፡ ሆኖም በዚህ በማንስማማበት አስተያየቱ ውስጥ የተቀመጠው ቀልብ ሳቢ ቁም ነገር፤ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹ልዩ አብሮ የመኖር ችሎታ ወይም ደመ ነፍስ›› የተናገረው ነው፡፡     

የሐገሪቱ ግዛት በተደጋጋሚ ሲጠብብ እና ሲሰፋ ቢቆይም፤ ኢትዮጵያ የተባለች ሐገር ዘመናትን መሻገር የቻለችው በሕዝቦች መካከል ባለው ልዩ የአብሮ መኖር ባህል የተነሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንድ ጸሐፊ በአንድ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ግዛት ሲጠብብ እና ሲሰፋ ቢታይም ህልውናዋ ሳይከስም ለረጅም ዘመን የመዝለቋ ነገር አስገራሚ መሆኑን፤ ግራ ቀኝ እየተመላለሰ የብዙዎችን ህይወት ባጠፋ የፈረንሳይ አብዮት ሰይፍ ሳይበላ በተአምር ከተረፈ አንድ ፖለቲከኛ ህይወት ጋር አነጻጽሮ ገልጾት ነበር፡፡ ከዚያ ሁሉ መከራ በተአምር ተርፎ ታሪክ ለመናገር እንደበቃው የፈረንሳይ ፖለቲካኛ፤ በርካታ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎችን በማለፍ፤ ግራ ቀኝ እየተምዘገዘገ ብዙ የአፍሪካ ሐገራትን የቅኝ ግዛት ሰለባ ካደረገው ‹‹የበርሊኑ ሰይፍ›› ያመለጠችው ኢትዮጵያ፤ እንደ ፈረንሳዩ ፖለቲከኛ ብዙ አደጋዎችን ተሻግራ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን መድረሷ አስገራሚ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህ እንቆቅልሽ ሊፈታ የሚችለው ‹‹ግፍ ቻይ›› በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩ የአብሮ መኖር ባህል ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሺህ ዘመናትን ባስቆጠረ የመንግስትነት ታሪክ የታለፈው ውጣ ውረድ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ሂደት በኢትዮጵያ የዳበረ ልዩ የብሔራዊ ማንነት (ብሔርተኝነት ስሜት) ተፈጥሯል፡፡ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንዳለው፤ ኢትዮጵያዊነት ተረት እና ስሜት አይደለም፡፡ በራሱ ምክንያት ጸንቶ የሚቆም እና በቀላሉ በነፋስ የማይወሰድ ማህበራዊ እውነታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በየጊዜው እየተፈተነ፤ በበርካታ ምዕተ ዓመታት ጉዞ የተለያዩ ተግዳሮቶችን እያለፈ የተጓዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ህልውና የሚፈታተን ከባድ ችግር በተከሰተ ቁጥር ኢትዮጵያውያን በጠንካራ ስሜት አደጋውን ለመከላከል ሲነሱ ታይቷል፡፡ በግዛት ወረራ ፍላጎት በተደጋጋሚ የገጠማቸውን የውጭ ኃይል ጥቃት በብቃት በመመለስ ድንቅ ገድል የተገነባ በኢትዮጵያዊነት የመኩራት ጥልቅ ስሜት ተፈጥሯል፡፡ በ1579 የኦቶማን ቱርክን፤ በ1898 አጼ ዮሐንስ አራተኛ የግብጽን ወራሪ ኃይል ጉራዕ ላይ አሳፍረው በመመለሳቸው፤ አጼ ምኒልክ በ1896 በአድዋ ጦርነት የጣሊያንን ጦር ድል በመንሳታቸው የተፈጠረ እና በአይበገሬነት ስሜት ላይ የታነጸ የኢትዮጵያዊነት ስሜት አለ፡፡

ብሔርተኝነት፤ እሙናዊ ወይም ምናባዊ በሆነ ባህል እና ታሪክ ላይ የሚመሠረት፤ የርዕዮተ ዓለማዊ እና የፖለቲዊ አስተሳሰብ ወይም እምነት መገለጫ ነው፡፡ ብሔርተኝነት ዓለም ዓቀፍ ክስተት ሲሆን ከተለያዩ ወገኖች የተናጠል ልምድ እና ገጠመኝ ውህደት የሚፈጠር የቡድን ማንነት መገለጫ ነው፡፡ የተለያዩ ህዝቦች የወል ህሊና ወይም አስተሳሰብ የሚፈጥሩበት እና የተለየ መገለጫ የሚሆን ልዩ ባህርይ ያለው ነው፡፡ አካባቢያዊ፣ ብሔረሰባዊ እና ክልላዊ ቁርኝትን ተሻግሮ የሚሄድ የጋራ ማንነት ነው፡፡ ብሔራዊ ስሜት ከኔሽን-ስቴት ጋር የተቆራኘ እና የጋራ ማንነት አስተሳሰብ ማዳወሪያ እና የሁሉንም ዜጎች ፍጹም ታማኝነት የሚጠይቅ ክስተት ነው፡፡

ሆኖም ማቅማማትን የማይፈቅድ ፍጹም ታማኝነትን የመፍጠር ፍላጎት ሲኖር፤ ልዩነቶችን ጨፍልቆ በኃይል አንድ የማድረግ ስህተትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከብሔራዊ ስሜት ጉያ ሊደበቅ የሚችል፤ ሁሉንም አንድ የማድረግ ጠንካራ ምኞት ከባህል ብዙነት ጋር ግጭት እንዲገባ ያደርገዋል፡፡ አንድነት የመፍጠር ፍላጎቱ፤ አንድ ወጥ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማ የያዘ ፖሊሲ የመከተል ዝንባሌ ሊስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ የሚነሳው ግጭትም የፖለቲካ ህብረቱን አደጋ ላይ ከሚጥል ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡ ችግሩ ከዚህ ደረጃ ሲደርስ ‹‹በጠቅላይ ግዛቱ›› መጨፍለቅ የማይሹ ቡድኖችን ሊፈጥር እና ይህን ድምጽ በኃይል የማፈን እርምጃ ሊጋብዝ ይችላል፡፡ በዚህ ሳቢያ የሚከሰተው የፖለቲካ ግጭትም ለብሔራዊ ስሜት ግንባታ መሠረታዊ ስንቅ ሊሆን የሚችለውን ሐብት እየሸረሸረ፤ በመጨረሻ የብሔርተኝነት ስሜቱን አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡  በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ችግር ታይቷል፡፡ ዘመናዊውን የኢትዮጵያ የሐገረ-መንግስት (nation-state) ግንባታ ታሪክ መመልከት፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ህብረት ውስብስብነት ለመረዳት ከማስቻሉም በላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ህብረት አፈጣጠር የሐገሪቱ የጥንካሬ እና የችግር ምንጭ መሆኑንም ያስገነዝባል፡፡

ይህ ፈተና በኢትዮጵያ ብቻ የወደቀ አይደለም፡፡ የመንግስት እና የብሄር ቡድኖች ውስብስብ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ የብሔር ቡድኖች፣ መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ ማንነታቸውን የሚጎዳ ሲመስላቸው በተለያየ መንገድ ተቃውሞአቸውን ይገልጻሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ያየነው ማንነትን ለማስከበር የተደረገው ትግልም ምንጩ ይኸው ነው፡፡ በመሆኑም፤ በሐገር ግንባታ ጥረቶች ላይ ሁሌም የሚደቀነው ችግር፤ የብሔርን ማንነት ሳያጠፉ አንድነትን መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ታዲያ ኢትዮጵያ በውስጧ የሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ልዩነት በመዘንጋት ወይም እንደ ነገሩ በመያዝ ለችግር ብትዳረግም፤ የዳር እና የመሐል ሥፍራ የተሰጠው ባህል ይዛ ባደረገችው ያልተሳካ ጉዞ ውስጣዊ ሰላም ብታጣም፤ እንደ ሐገር የመቆየት ጥበብን ማዳበር እና አሁን ለተፈጠረው ፌዴራል ህብረት መሠረት ሊሆን የቻለውን የህዝቦች ግንኙነት መፍጠር ችላለች፡፡ ፈተናዋ ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡

ለዘመናት የዘለቀውን የኢትዮጵያ ህዝቦች በሰላም አብሮ የመኖር፣ የመከባበር እና የመቻቻል አኩሪ ባህል ወይም ታሪክ የሚጎዳ አንድ ወቅታዊ ፈተና ሆኖ የመጣው የጥላቻ ንግግር ነው፡፡ የኢንዱስትሪ አደረጃጀትን የመሰለ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በርግጥ ህዝብን በህዝብ ላይ የማነሳሳት ግብ ያላቸው የጥላቻ ንግግሮች በሐገራችን ከንግግር እና ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት መከበር ጋር አብረው አደባባይ የወጡ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሐገራችን ከተስፋፋው የኢንተርኔት አገልግሎት እና ከማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር መበራከት ጋር ተያይዞ፤ የጥላቻ ንግግር ተጽዕኖ መጠናከሩ ይታያል፡፡ በሐገራችን የጥላቻ ንግግር እና ሕዝብን ከህዝብ ሊያጋጩ የሚችሉ መልዕክቶች በሰፊው የሚታዩ መሆናቸውን ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ አንዳንድ ጥናቶችም ያመለክታሉ፡፡

የፕሬስ ነጻነት መብት በተከበረ ማግስት የግል ፕሬስ ባለቤቶች የመሆን ዕድል ያገኙት የደርግ ስርዓት የሳንሱር ክፍል ሹሞች እና አፈ ቀላጤዎች፤ የሐገራችንን የግል ፕሬስ ሥነ ምግባራዊ እና ሙያዊ አሰራር የሚጎዳ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደራቸውም በላይ፤ በጥላቻ ንግግር ቀለም በተሞላ እና በተሸናፊነት ስሜት በታመመ ብዕራቸው፤ በአንዳንድ ወገኖች ላይ የተዛባ አመለካከት በመፍጠር ረገድ ጉልህ ጥረት አድርገዋል፡፡

አዲሱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በነጻነት የማሰር፣ የመግደል፣ የመዝረፍ ወዘተመብት ስለነፈጋቸው በስርዓቱ ላይ የከረረ ጥላቻ ነበራቸው፡፡ ለስርዓቱ ያላቸውን ይህን ጥላቻ ሲገልጹም፤ ከአዲሱ ሥርዓት ጋር የተለየ ቁርኝት አላቸው ብለው በሚያስቧቸው ህወሓት እና በትግራይ ህዝብ ላይ በማትኮር ነበር፡፡ ይህም በ17ቱ የደርግ የስልጣን ዘመናት ሲያደርጉት የቆዩት እና በፕሬስ ነጻነት ማግስት የቅርጽ ለውጥ በማድረግ ያስቀጠሉት፤ ጥርሳቸውን የነቀሉበት የዘወትር የፕሮፓጋንዳ ፊደላቸው ነው፡፡ ይህ በተደጋጋሚ የተገለጸ እና ከአርባ ዓመታት በላይ የቆየ ዕድሜ ያለው በሰፊው የሚታወቅ ችግር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የተዛባ አመለካከት ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ቀደም ሲል እንደ ተገለጸው የማህበራዊ ሚዲያ ልዩ ባህርይ ለችግሩ መጠናከር የበኩሉን ድርሻ ተጫውቷል ማለት ይቻላል፡፡  

ከግርግሩ ወጣ ብለን ስንመለከት በግልጽ የምንመለከተው፤ በዘር እና በነገድ የማይወሰነው የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር እና አመለካከት ሐገሪቱን እያመሰ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ችግር የስርዓቱ አደጋ ከመሆን የደረሰ ችግር ነው፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት ሐብት ያፈሩ እና በተለያየ ደረጃ ሐገራችንን በቀውስ እንደትታመስ እያደረጉ ያሉ ሰዎች በተለያዩ የሐገራችን ባሉ ከተሞች ውርውር ይላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የወላይታ፣ የሲዳማ ወዘተ ተወላጆች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል በመንግስት እና በድርጅት የታቀፈ ወይም ከዚያ ውጭ ሆኖ የሚንቀሳቀስ ሊሆን ይችላል፡፡ የሐገራችን እና የህዝቧ እውነተኛ ጠላት ይህ ኃይል ነው፡፡ የየትኛውንም ብሔር ካባ ለብሶ ቢመጣ ይህን ኃይል አምርረን ልታገለው ይገባል፡፡ ይህ ኃይል በጥላቻ ንግግር ውስጥ የመሸገ ኃይል ነው፡፡ በዚህም እውነተኛውን ጠላታችንን ለይተን እንዳንታገለው ጨለማ ይፈጥርብናል፡፡ ጨለማውን ተጠቅሞ ህገ ወጥ የግል ጥቅሙን ለማራመድ ጥረት ያደርጋል፡፡ በመሆኑም፤ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግላችን ውጤታማ እንዲሆን፤ ራሳችንን ከማናቸውም የጥላቻ ንግግር በማራቅ ትግል ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይህን በማድረግ አንድነታችንን አጠናክረን፤ ዓለም የሚቀናበትን የአብሮ መኖር ቅርሳችንን ከአደጋ አንጠብቅ፡፡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አንድነት መሰረቱ የህዝቦች የአስተሳሰብ አንድነት በመሆኑ፤ ሕገ መንግስታችን በቆመላቸው አላማዎች፣ መርሆዎች፣ እሴቶችና እምነቶች በልዩነታችን የደመቀ አንድነታችንን በማጠናከር፤ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ተልዕኮችንን ለማሳካት በአንድነት እንረባረብ፡፡   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy