Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌደራላዊ ስርአቱን እንደስርአት የሚኮንን አለ?? ካለ . . .

0 403

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌደራላዊ ስርአቱን እንደስርአት የሚኮንን አለ?? ካለ . . .

ዮናስ

 

ኢህአዴግ ሃገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ባዋቀረው የሽግግር መንግስትና ዘመን የብሔር ጭቆናን በማስወገድ በዴሞክራሲ መሰረት ላይ የተዋቀረ አንድነት ለመገንባት ሽር ጉዱን ቢጀምርም፤ የአገሪቱ መበታተን አይቀሬ ይሆናል የሚል ስጋት የገባቸው ትንሽ ያልነበሩ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በተለይ ደግሞ የኤርትራ ነፃነት ከመከበሩ ጋር ተያይዞ “ሌላውም የኢትዮጵያ ክፍል አንድ አንድ እያለ ወደዚሁ አቅጣጫ ያመራ ይሆናል” የሚሉና አንድነቱ ለአደጋ ባይጋለጥ እንኳ የአንድ ብሔር የበላይነት መፈጠሩ አይቀርም ብለው የሚሰጉ ምሁራንም ብዙ የነበሩ መሆኑም አይዘነጋም።  

የኢህአዴግ መንግስት፣ በኢትዮጵያ ብዙኅነትን ከቀደምት አስተዳደሮች በተለየ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለመያዝና ለማስተዳደር እንደሚፈልግ ባሳወቀ ጊዜም ሆነ በተግባር እያረጋገጠ መሆኑ በታየበት ሰአት፣ ሰፋ ያለው የከተማ ማህበረሰብ በተለይ ደግሞ የአገሪቱ ልሂቃን አቅጣጫውን በከፍተኛ ጥርጣሬ ከመመልከት አልፈው ጥርጣሬያቸውን ከወደቀው ስርአት ርዝራዦች ጋር ግንባር ፈጥረው ሲያራግቡና መረጋጋት እንዳይኖር ሲተጉ የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ሆና እንድትቀጥል ከፍተኛ  ፍላጎት ያላቸው በማስመሰል በመሰረቱ የነበረው ኢትዮጵያዊነት ብዙህነትን የማያስተናግድ የነበረ መሆኑን ምክንያት በማድረግ ይህን ጥያቄ የሚመልሰውን አዲሱን አቅጣጫ አደጋ የሚጋርጥ አስመስለው  በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ግራ መጋባቶች ፈጥረው የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ የማይዘነጋ ነው፡፡ አሁንም በየቦታው ለምናየው ሁከትና አመጻ ምክንያቱ ፌደራላዊ ስርአቱ ነው የሚሉት ወገኖች እነዚሁ ናቸው። እነዚህ ሃይሎች ደግሞ ወይ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው አልያም አክራሪዎች። ጉዳዩን በምክንያት እናጠይቅ።

መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊወስዱ እንደማይችሉ በተግባር መታየቱን ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ መከበሩ የመበታተንን ነገር ያበቃለት እንዲሆን አድርጎታል። በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ አስችሏል። መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን ደግሞ በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ እገዛ አድርጓል እያደረገም ነው። በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ ታዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓል እያደረገም ነው። ይህ በሆነበት አግባብ ለሚነሱ ግጭቶች ምክንያት ሊሆን የሚችለው ስርአቱ ሳይሆን ኪራይ ሰብሳቢነት አልያም አክራሪነት ብቻ ነው።   

አገሪቱን ከጫፍ ጫፍ የሚያስተሳስር የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት ተስፋፍቷል። ይህንንም በተናጠል ሳይሆን በጋራ ለመጠቀም የሚቻልበት እድል ተፈጥሯል። በዴሞክራሲ ላይ የተመሰረተውን አገራዊ ገመድ በጠንካራ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አውታር ለማወፈር ተችሏል። ይህ በሆነበት አግባብ ለሚነሱ ግጭቶች ምክንያት ሊሆን የሚችለው ስርአቱ ሳይሆን ኪራይ ሰብሳቢነት አልያም አክራሪነት ብቻ ነው።   

በአገራችን ህዝቦች ዘንድ በልዩ ልዩ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል። ህገ መንግስቱ የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትህና የእኩልነት ዋስትና እንደሆነ መግባባት ተደርሷል። እየተገነባ የሚገኘው ሥርዓት የገበያ መሆን እንዳለበትና ሰዎች በሰሩት ልክ የመጠቀም ህጋዊ ዋስትና ያገኙ በመሆናቸውም ላይ ተመሳሳይ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ ይህ ማለት ግን የዚህ ስርአት ቀበኛ የሆኑ ጸረ ዴሞክራሲ ሃይሎች በስርአቱ ውስጥ የሉም ማለት አይደለም። እንዲያውም ከነዚህ ሁከቶች በስተጀርባም ስለመኖራቸው አሁን ተረጋግጧል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ኮንትሮባንዲስቶች ሲሉ በተደጋጋሚ እና በምሬት ሲገልጿቸው የነበረው እነዚህኑ ነው።  

በዚሁም ላይ ከፈጣኑ እድገት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ነባርም ሆኑ አዳዲስ የስርዓቱ ችግሮችም እንደዚሁ ከሞላ ጎደል የጋራ ስምምነት ተይዞባቸዋል። በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑ አሁንም የመዋለልና ወደፊትና ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች እየታዩ ነው።በዚህች ሃገር ኢህአዴግ የአገሪቱን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነቷን የማስጠበቅ ችሎታ ጭምር እንዳለው የሚጠራጠሩ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ነው።  ስለምን ሲባል ከአፈጻጸም ችግሮች በላይ በስተጀርባ ኪራይ ሰብሳቢዎችና አክራሪዎች ስለሚፈነጩ ነው።ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በቶሎ መሬት ላይ ያለማውረድ ችግሮች ደግሞ የሚያስከፍሉት ዋጋ ከባድ ነው።ኦሮሚያን እና ፊንፊኔን የተመለከተው ጉዳይ ሲንከባለል ቆይቶ ባሳለፍነው አመት ያስከፈለን ዋጋ አይረሳም። አሁንም አንድ ያልተመለሰ አጀንዳ ታቅፈን እየተጓዝን ስለመሆኑ ስንቶች ያውቁ እንደሆን አላውቅም። ሁሉም ባለስልጣንና ምሁር እየተነሳ በ9ኙ ክልሎችና በ2ቱ የከተማ አስተዳደሮች ይለናል።ድሬደዋን ግን ህገ መንግስቱ አያውቃትም። ስለሆነም ነገ ተነስቶ የይገባኛል የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሚመዝ ብሄር ሊመጣ እንደሚችል መገመት አይከብድም።ድሬደዋ ለአክራሪውና ኪራይ ሰብሳቢው አሪፍ የብጥብጥ አጀንዳ ከመሆኗ አስቀድሞ እልባቱን ማበጀት ያስፈልጋል።

በጥቅሉ ቀደም ሲል በአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ካላግባብ የተያዙበት መንገድ ለግጭትና የእርስ በርእስ ለዘመናት ጦርነት መንስዔ እንደነበር በመገንዘብ አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ብዝሃነትን በማወቅና በመቀበል እንዲሁም በአግባቡ በማስተዳደር ላይ እንዲመሰረት ተደርጓል፡፡ ፌዴራላዊ  ስርዓቱ  ኢትዮጵያ የብዙ ህዝቦች አገር የመሆኗን እውነታ ያለማቅማማት የሚቀበል ስርአት ነው፡፡ ግን ደግሞ ፍትሃዊ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎችን፤ ያለአንዳች ማቅማማት ስርአቱ የተቀበላቸውን ጥያቄዎች በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ባለመደረጉ በአንዳንድ አካባቢዎች ለግጭት መንስኤ ሆኖ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡

እዚህ ጋር አሁንም ሊሰመርበት የሚገባው አንድ ነጥብ አለ። እሱም አንዳንድ ወገኖች ግጭቱ የተቀሰቀሰው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ በራሱ የግጭት መንስዔ ስለሆነ ነው የሚሉት ነጥብ ነው። ያም ሆኖ ግን ፌዴራላዊ ስርአቱ በመሰረታዊ ባህሪው የማህበረሰቦችን ማንነት ማክበር በመሆኑ ችግር ፈች እንጅ ችግር ፈጣሪ ወይም አባባሽ ሊሆን አይችልም፡፡  ይህም አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሃገራችን በዘመናዊ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ምዕተ ዓመት የሞላው ረዥም የሰላም ዘመን እንድትኖር፣  ህዝቦቿ ለሃያ ስድስት ዓመታት በሰላም፣ በፍቅርና በመካባበር እንዲኖሩ ያስቻለን በመሆኑ የሚረጋገጥ ነው። ይህን የሚክዱ ካሉ ደግሞ ወይ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው፤ አልያም አክራሪዎች።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy