Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌዴራል ሥርዓቱ የክልሎች ድምር ውጤት ነው!

0 332

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌዴራል ሥርዓቱ የክልሎች ድምር ውጤት ነው!

                                                        ደስታ ኃይሉ

አገራችን ውስጥ እውን በመሆን ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት የክልሎች በጋራ እንዲቆም ያደረጉት ነው። ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የፈጠረው የክልሎች ድምር ውጤት ነው። ይህም በክልሎች ውስጥ ችግር ሲፈጠር፣ ችግሩ የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ጭምር መሆኑ የማይቀር መሆኑን ያረጋግጣል። ሥርዓቱ የተረጋጋና በህገ መንግስቱ የቆመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ክልሎች ሰላማቸው የተረጋጋጠ መሆን ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የቃል ኪዳን ማሰሪያ ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ -መንግስት ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ ወዲህ ሀገራችን ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ ይዛ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በድል ለመረማመድ በቅታለች፡፡ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት እስከመባል ደርሳ የነበረችው ሀገራችን፤ የህዝቦቿ መብት የተረጋገጠባት፣ የዕድገትና ልማት ብሩህ ተስፋን የሰነቀች፣ የእኩልነትና የፍትህ አምባ ለመሆን ችላለች፡፡

በመሆኑም የአፈና አገዛዝ፣ የግፍ ቀንበር ተጭኖት የኋላቀርነትና የበታችነት ተምሳሌት ተደርጎ ይታይ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦቿ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ የህዝቦቿ መኩሪያና መከበሪያ፣ የሀገራችን መድመቂያ ጌጥና የመልካም ገጽታዋ መገለጫ ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡

የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ በመዳበር ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፎ ለፈጣን ልማት ስራዎቻችን የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት ወደ ሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡

ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል፡፡ መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመገንት በሕገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ውስጥ የህዝቦች የሰበብ አስባብ ግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። የጋራ ወግ፣ ባህልና ትውፊት ያላቸው፣ በዘመናት አብሮነት ገመድ የተሳሰሩ፣ በተለይም አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ገንብተው የማየት ራዕይ አላቸው።

የሁሉም ክልል ህዝቦች በጥቂቶች ፍላጎት እንዲህ በቀላሉ ሊለያይ የሚችል አይደለም። በፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውስጥ አገራዊ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታን ለማስረፅ ከ23 ዓመታት በላይ አብረው በመፈቃቀድ ኖረውና በአገራችን ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ የራሳቸውን አሻራ በማኖር ላይ ያሉት ወንድምና እህት ህዝቦች በጥቂት ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ፍላጎትና ሴራ ከሰላማዊ ጉዟቸው አይችሉም።

አገራችን ሰላም ሆና በህዝቦቿ ተሳትፎ እንዳታድግና ወደ ህዳሴዋ እንዳትግሰግስ የማይሹ ፅንፈኛ ኃይሎችና የውጭ አጋሮቻቸው ሰለባ ላለመሆንም የየክልል አመራሮች ከህዝባቸው ጋር በመሆን ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በመሆኑም የሁሉም ክልሎች አመራሮች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቅድሚያ የህዝቡን ድምፅ መስማት፣ ለጥቆም ቁርጠኛና አሳታፊ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበትን አካሄድ መከተል ይኖርባቸዋል።

አገራችን የምትከተለው ፌደራላዊ ሥርዓት አወቃቀር አብዝሃነትን እንደ ውበት አድርጎ የሚነሳ ነው። በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን በማጠናከር የመቻቻል መንፈስ እንዲዳብር ተደርጎ በህዝቦች የተዋቀረም ሥርዓት ነው። እናም አገራችን ውስጥ ለግጭት የሚሆን ስፍራ እንደሌለ ግጭት አራጋቢዎቹ እንዲያውቁት ማድረግ ያስፈልጋል። ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች የሚቀር የልማት ጉዞ ሊኖር እንደማይችል ሁሉም ወገን እንዲገነዘበው ማድረግ ተገቢ ነው።

ግጭትን የሚያራግቡ ሃይሎች ለልማት በመትጋት ላይ በሚገኘው ወጣት እጅ እሳት ለመጨበጥ በሞከር የሚያረጉት ሴራ አንድ ቦታ ላይ መቆም ይኖርበታል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የበላይነት መያዝ ያለበት የልማታዊ አስተሳሰብ እንጂ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል አኮኖሚ የበላይነት ባለመሆኑ ነው።

 

በኮንትሮባንዲስቶችና በኪራይ ሰብሳቢዎች አሉባልታ እንደ ቦይ ውሃ የሚነዳ ህዝብም ሆነ መንግስት አለመኖሩን መግለፅ ያስፈልጋል። ህዝብም ሆነ መንግስት የየትኛውም ዓይነት አሉባልታ ማድመቂያ ሊሆኑ አይችሉም። እርግጥ የፀረ ሰላም ኃይሎቹ አሉባልታ የሰላም ወዳዶቹ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አጀንዳ አይደለም።

 

የሁሉም ክልሎች ህዝቦች አጀንዳ በጋራ የመልማት፣ ከአጎራባች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ብሎም በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩት መብቶቹ ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩላቸው መሻት ነው።

ግጭት አራጋቢዊቹ አገራዊና ክልላዊ ተጠቃሚነት ለማደናቀፍ እንዲሁም የየክልሉ ህዝቦች በትግሏቸው ያገኟቸውንና እያጎለበቷቸው የሚገኙትን ሁለንተናዊ ህገ መንግስታዊ መብቶቹን ለመሸርሸር ብሎም ህዝቡ ተረጋግቶ በልማት ስራው ላይ እንዳያተኩር ለማድረግ የታለመ ነው።

እንደሚታወቀው የሁሉም ክልል ህዝቦች ባለፉት ዓመታት በተጎናጸፏቸው የልማትና የዕድገት ዕድሎች በብቃት በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል። በእነርሱ ይሁንታ የተመሰረተው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በህዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ መገንባት ከጀመረበት ወዲህ በሁሉም መስኮች እየታየ ያለው ለውጥ ከፍተኛ ነው።

ከለውጦቹ መካከል በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በተመዘገቡ ለውጦች አጠቃላይ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት በሁለት አሃዝ እንዲያድግ አስችሏል። በዚህ ሂደት ውሰጥ የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊነትና ባለቤትነት ነበር። ያለ ህዝቡ ይሁንታና ፈቃድ የተከናወነ ነገር የለም፤ ሊኖርም አይችልም።

ይሁን እንጂ፤ የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ግጭት አራጋቢዎች ሁሌም በክልሉ ላይ በማተኮርና በሽብርተኝነት ከተፈረጁት እንደ ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት ሰባት ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና በጸረ ሰላም ሚዲያዎች የሐሰት ወሬ በመንዛት ሁከት ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። የሰው ህይወትም አጥፍተዋል።

እነዚህ ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲሁም ሽብርተኞች ቀደም ባሉት ጊዜያት በፈጠሩት እኩይ ሴራ አንድም ስንዝር መራመድ ያቃታቸው ናቸው። በዘመናት የትስስር ድር የተጋመዱት ህዝቦችን የአእምሮ ዕድገትና የፈጠራ ክህሎት እንዳይዳብር፣ ተወዳዳሪነታቸው እንዲደናቀፍና ድህነትና ኋላቀርነት በክልሉ ስር ሰዶ እንዲቆይ ያላቸውን ክፉ ምኞት ለመተግበር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሆኖም ጊዜያዊ ችግር ከመፍጠር በዘለለ ሌላ ያሳኩት ነገር የለም።

የሁሉም ክልል ህዝቦችህዝቦች በተፈጥሮ በተቸራቸው ቋንቋ የመጠቀም መብታቸው ለዘመናት ተነፍጎ ከኖረበት ሁኔታ ራሳቸውን በማላቀቅ ዛሬ ላይ ቋንቋቸው የሳይንስ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የእድገት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገቡ ናቸው። በውጤቱም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ይህ ሁኔታም የሀገራችም ህዝቦች ለሁከት ፈጣሪዎች ምንም ዓይነት ቦታ የማይሰጡ መሆኑን የሚያስረዳ ነው።

 

በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ጥቅማችን ሊነካ ይችላል በሚል ስጋት ግጭትን በማቀጣጠል ስራ ላይ የተጠመዱት እነዚህ ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች የህዝቡ ፍላጎት ያልሆነን አጀንዳ በመምዘዝ በሁለቱም ክልሎች ውስጥ የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ቢያደርጉም ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በግጭቱ የተጎዱት የሀገሩ ዜጎች መሆናቸውን ተገንዝቦ ድጋፉን በመቸር ላይ ይገኛል።

ይህ ኢትዮጵያዊ መተሳሰብ በእነዚህ ወገኖች እኩይ ሴራ የሚፈታ አለመሆኑም የተፈጠሩት ክስተቶች አመላካች ሆነው አልፈዋል። ይህን ሁኔታ በመማርና ለወደፊት እንደ ተሞክሮ በመቀመር አንድነትንና መቻቻልን ማጠናከር ይገባል። ምክንያቱም በክልሎች ውስጥየሚፈጠር ማንኛውም ችግር በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ ጥሎ ስለሚያልፍ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy