Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያልተሰበሰቡት የኤርትራ መንግስት የጥፋት እጆች

0 632

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ያልተሰበሰቡት የኤርትራ መንግስት የጥፋት እጆች

                                                    ዘአማን በላይ

ከመሰንበቻው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራና ሶማሊያ ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘሙን ገልጿል። በመንግስታቱ ድርጅት የኤርትራና የሶማሊያ ጉዳይ አጣሪ ቡድን በኤርትራ መንግስት ላይ ባደረጋቸው የአራት የስራ ዘመኑ ጥናቶች በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራው የአስመራው መንግስት ዛሬም ቀጣናውን ከማተራመስ ተግባሩ ያልተቆጠበ መሆኑን አረጋግጧል።

አጣሪ ቡድኑ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው፤ የአስመራው የሁከት መንግስት አሁንም ኢትዮጵያንና ጅቡቲን የሚቃወሙ ታጣቂ ቡድኖችን ያሰለጥናል፤ ያስታጥቃል የሀገራቱን ሰላም ለማወክ አስርጎ ለማስገባት ይሞክራል። ሆኖም የአስመራው አስተዳደር ሀገራችንን ለማወክ አስመራ ውስጥ ሰብስቦ ያየያዛቸው አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ሃይሎች በሀገራቱ ላይ እዚህ ግባ የሚባል ተፅዕኖ መፍጠር የማይችሉ መሆናቸውን የቡድኑ ሪፖርት ያመለክታል። ያም ሆኖ ግን የኤርትራው መንግስት እያካሄደ ያለው ተግባር አሁንም ቢሆን ቀጣናውን ለማወክ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል። በዚህ ሪፖርት መነሻነትም የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ በአንድ ዓመት እንዲራዘም አድርጓል።

የፀጥታው ምክር ቤት በውሳኔ ቁጥሮች 751 (1992) እና 1907 (2009) መሰረት የጣላቸውን ሁለት ማዕቀቦች በተመለከተ ለአጣሪ ቡድኑ በኤርትራና በሶማሊያ ያለውን ሁኔታ እንዲያጣራና ማዕቀቦቹን ዳግም ለማየት በውሳኔ ቁጥር 2317 (2016) መሰረት ሃላፊነት ሰጥቶታል። ሆኖም አጣሪ ቡድኑ ለአምስተኛ የስራ ዘመኑም ኤርትራ ውስጥ ገብቶ ሁኔታዎችን ለማጣራት ከአስመራው አስተዳደር ፈቃድ አለማግኘቱን ገልጿል። ይህ ሁኔታም የኤርትራ መንግስት ለየትኛውም ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች የማይተባበርና ደንታ ቢስ መሆኑን ያረጋገጠ ነው።

በአስመራው አስተዳደር ላይ ቀደም ሲል የተጣሉት ሁለቱ ማዕቀቦች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የሚከተለውን ይመስላሉ።…ቀዳሚው ማዕቀብ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት “የኤርትራ መንግስት እያተረማመሰን ነው” በሚል ለመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ላይ የተመሰረተ ነው።

ታዲያ አቤቱታውን የተቀበለው የፀጥታ ምክር ቤት የአስመራውን አስተዳደር ተግባሮች በራሱ የቅኝት መንገድ አጣሪ ቡድን መድቦ በጥብቅ ተከታትሎታል። በዚህ መሰረትም  የኤርትራ መንግስት “ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት አደገኛ ነው” በማለት የመሳሪያና የባለስልጣናት ዝውውር ዕገዳን ያካተተ የመጀመሪያውን ማዕቀብ ለመጣል ተገድዷል። ይህ ማዕቀብ የሚነሳው የአስመራው መንግስት ባህሪ ላይ ተመርኩዞ መሆኑንም በወቅቱ ገልፆ ነበር።

ዳሩ ግን የኤርትራ መንግስት እንኳንስ የባህሪ ለውጥ ሊያመጣ ቀርቶ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ማሸበሩን ቀጠለበት። እናም የፀጥታው ምክር ቤት አሁንም የአጣሪ ቡድኑን ሪፖርት ተንተርሶ በኤርትራ መንግስት ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ማዕቀብ ጥሎበታል።  ምክንያቱ ደግሞ የኤርትራ መንግስት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 1907 (2009)ን በመተላለፍ፤ የጂቡቲ፣ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የኡጋንዳ ታጣቂ ተቃዋሚ ኃይሎችን እና አሸባሪዎችን በማሰልጠን፣ የገንዘብና የሎጀስቲክስ ድጋፍ ማድረጉ በተጨባጭ ጥናት በመረጋገጡ ነው።

ሁለተኛው ማዕቀብም በአስመራው መንግስት ላይ ቀደም ሲል ከተጣለበት ማዕቀብ በተጨማሪ የባለስልጣናትና የገንዘብ ዝውውር ዕገዳን ብሎም ሻዕቢያ ለመሳሪያ ግዥ የሚጠቀምበትንና ውጭ ካሉት ዜጎቹ የሚሰበስበውን የሁለት በመቶ ቀረጥ ሀገራት እንዲከለክሉ የሚያደርግ ነው። ሆኖም ሻዕቢያ እነዚህ ማዕቀቦች መደራረባቸው እንደ ኩታ የሞቁት ይመስላል። አሁንም የዛሬ ዓመት ገደማ አጣሪ ቡድኑ ሁኔታውን እንዲገመግም ወደ ኤርትራ እንዲገባ ጥያቄ ቢያቀርብለትም አሻፈረኝ ብሎ መልሶታል።

እናም ከሰሞኑ ለፀጥታ ምክር ቤቱ የቀረበው የቡድኑ ሪፖርት፤ የአስመራው አስተዳደር ለኢትዮጵያንና ለጂቡቲ አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ሃይሎችን ድጋፍ በመስጠት የሀገራቱን ሰላም ለማወክ እንደሚጥር ያስረዳል። በተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎቹ አማካኝነት በተለይ ራሳቸውን “አርበኞች ግንቦት ሰባት”፣ “የቤኒሻንጉል ህዝቦች የነፃነት እንቅስቃሴ” እና “የትግራይ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ” የተሰኙ የታጠቁ ሃይሎችን እየደረገ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ይገልፃል።

ከዚህ በተጨማሪም በጂቡቲው ራስ ዱሜራ ኮረብታዎችና ሃይቆች አካባቢዎች የኳታር ወታደሮች ቦታውን ለቀው ሲወጡ በወረራ የያዘውና እሰጥ-አገባ ላይ የሚገኘው የኤርትራ መንግስት፤ የጂቡቲ አማፂ የሆነውንና ራሱን “ውህደት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ” በማለት የሰየመን ታጣቂ ቡድን በሁሉም መስኮች እየደገፈ መሆኑን የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ምን ይህ ብቻ! የአስመራው አስተዳደር የፀጥታው ምክር ቤት የጣለበትን የመሳሪያ እገዳ ተላልፎ ተገኝቷል። በአሁኑ ወቅት የውጭ ሃይሎች ለኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ቀጥተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል። በአሰብ ወደብ አቅራቢያ የሰፈረችው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ወታደራዊ ይዞታዋን በማስፋፋት ላይ ከመገኘቷም በላይ፤ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ከውጭ ለኤርትራ እያስተላለፈች ነው። እንዲሁም የኤርትራ መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ ላይ ትገኛለች። ይህም የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ መተላለፍ መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል።

እናም በእነዚህ ዛሬም ባልተሰበሰቡት የኤርትራ መንግስት የጥፋት እጆች ሳቢያ ቀደም ሲል ተጥሎ የነበሩት ማዕቀቦች ለአንድ ዓመት እንዲራዘሙ ተደርገዋል። ማዕቀቦቹ የሚነሱት የኤርትራ መንግስት አካባቢውን ከማተራመስ ከተቆጠበና የተጣለበትን ማዕቀቦች አክብሮ ከተንቀሳቀሰ ነው። ይሁንና በእኔ እምነት ይህ የሚሆን አይመስለኝም። ምክንያቱም “ጠብ-አጫሪነት” የአስመራው አስተዳደር አብሮት ያደገ ባህሪው ስለሆነ ነው።

የኤርትራ መንግስት ባህሪውን ሊቀይር የሚችል ነው ተብሎ አይታሰብም። በእኔ እምነት፤ ሰሞኑን ህዝባዊ ቁጣ የተቀሰቀሰባቸው የአስመራው አስተዳደር ጥቂት ሹማምንቶች በተሳሳተ የትናንት ስሌት እየተመሩ ነው። ሁሌም አሸናፊ የሚሆኑ ይመስላቸዋል። ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ መናቅ ዋጋ የሚያስከፍላቸው መሆኑን እንኳን አልተረዱም። አሊያም ራሳቸውን በሌለ ዕውነታ ላይ ኮፍሰው ተቀምጠዋል።

የአስመራው መንግስት መሪዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች የአንዲት ትንሽ፣ ከተመሰረተች ሁለት አስርታትን በቅርቡ የዘለለችና በጦርነት የተጎዳች ድሃ ሀገር መሪዎች መሆናቸውን እንኳን የዘነጉ ይመስለኛል። የተጣለባቸው ማዕቀብ “ይራዘም” በተባለ ማግስት ራሳቸውን ከመፈተሽ ይልቅ “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” ብለው ጣታቸውን በሌሎች ላይ ይቀስራሉ። ከፍ ሲል ከልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ጋር በእኩል ስሜት ጎን ለጎን ሆነው ለመገዳደር ይዳዳቸዋል። ወይም በምጣኔ ሃብት፣ በዴሞክራሲና በዲፕሎማሲ እንዲሁም በሰላም ወዳድነት ረገድ፣ ፈፅሞ ከማይገናኟት ኢትዮጵያ ጋር ያለ አንዳች ሃፍረት ራሳቸውን ያመዛዝናሉ። ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ ችግር ፖለቲካዊም ይሁን ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ሊኖረው ባይችልም፤ የሻዕቢያ አመራሮች ራሳቸውን ወደ ውስጥ በመመልከት የራስ በራስ ህክምና ሊያደርጉ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። ይህም ህክምና ያልተሰበሰቡትን የጥፋት እጆቻቸውን መሰብሰብ ብቻ መሆኑንም እንዲሁ። ያኔን ከዓለም አቀፉ ውግዘት ሊድኑ ይችላሉ።

ርግጥ የአስመራው አስተዳደር እምባገነን አመራሮች የችግራቸውን መንስኤ ለማወቅ ባይሹም፤ ራሳቸው በራሳቸው ከፈጠሩት ችግር ለመውጣት መፍትሔው ያለው በእጃቸው ብቻ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የተጣሉባቸው ማዕቀቦች ከሌሎች ሀገሮች የተላከባቸው ልክፍት አሊያም ወረርሽኝ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። የእነ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን በማዕቀብ ላይ ማዕቀብ ችግር የምዕራቡ ዓለም ወይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የፈጠሩባቸው አይደለም። የችግሩ አልፋና ኦሜጋ እነርሱው ብቻ ናቸው። ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።

እናም ለትክክለኛው መፍትሔ ከእነርሱ በላይ ለአሳር ስለሆነ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ያፈጠጠውንና ያገጠጠውን የአጣሪ ቡድኑን ሪፖርት “ፈጠራ ነው፣ የእነገሌ ሴራ ነው…ምንትስ” ማለት ከማለት የጥፋት እጆቻቸውን በመሰብሰብ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይሁን ከቀጣናው ሀገራት ጋር ለሰላም መስራት ይገባቸዋል እላለሁ። ይህን ሳያደርጉ ቀርተው ዛሬም እንደ ሳህል ተራራ ዘመናቸው በጦረኝነት አባዜ እየተመሩ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ለማናናቅ ከከጀሉ ግን፤ ምርጫው የእነርሱ ብቻ ይመስለኛል— “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…” እንዲል ብሂሉ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy