ዴሞክራሲ፣ የህግ የበላይነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት
ዳዊት ምትኩ
በአዲሷ ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የህግ የበላይነትና የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መቼም ቢሆን ለድርድር የማይቀርቡ ጉዳዩች ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህን ጉዳዩች እውን ማድረግ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው። መንግሥት ታዲያ እነዚህን ጉዳዩች እውን ለማድረግ በርካታ ተግባሮችን አከናውኖ ውጤት ማምጣት ችሏል።
መንግስት ባለፉት ዓመታት ባደረገው ጥረት የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከማጎልበትና ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው።
በተለይ ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረው ድርድርና ክርክር ተጠቃሽ መሆኑን በማመላከት ሂደቱ በመቻቻል፣ በመደማመጥና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ በመመስረት ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጠናከር የበኩሉን ሚና እያበረከተ ነው።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጋር የተደረጉ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ዴሞክራሲያዊ ባህልን ከማጎልበት አንጻር ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል።
በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የመደራጀት መብት ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመስርተው ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።
በተለይም የሽግግር መንግስቱን ተከትሎ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነ በኋላ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ እስከተካሄደው ምርጫ ድረስ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው ለአምስት ጊዜያት በተካሄዱት ምርጫዎች እንዲወዳደሩ ተደርጓል።
መንግስት አምና ላይ የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህገ መንግስቱን እስከማሻሻል ጭምር ድረስ በመሄድ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን በመከተል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበትን ሁኔታ በመፍጠር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል ገብቷል። እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከሚከተል እንዲሁም ዴሞክራሲን እንደ ሞትና ሽረት ጉዳይ አድርጎ ከሚመለከት ፓርቲና መንግስት የሚጠበቅ ነው።
ከህግ የበላይነት አኳያም መንግስት በርካታ ተግባሮችን ከውኗል። እንደሚታወቀው በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም።
የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። የመኖር ዋስትና በሌለበት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የሚደረስ ይደረሳል።
መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየደረጋቸው ከመጣው መንገድ መውጣት የለበትም።
መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በህጉ አግባብ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የተጎጂዎችን እምባ ማበስ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ የተመሰረተውን ስርዓት በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም።
ይህ የመንግስት የህግን ልዕልና የማረጋገጥ እርምጃ በህዝቦች ደም ስልጣን ላይ ለመውጣት ለሚሹ አሸባሪዎች፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ፅንፈኞች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ እነርሱ የሚመኙት ዓይነት ምህዳርና ህዝብ አለመኖሩን እንዲገነዘቡ ያስችላል።
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንጂ፤ በደማቸው ፍላፃነትና በአጥንታቸው ወጋግራነት የገነቧት ሀገራቸው እነርሱ እንደሚመኙት ዓይነት በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህገ-ወጦችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ከተያያዙት ድህነትን ድል የመንሳት ትግል አንድም ስንዝር ቢሆን ፈቀቅ ሊሉ የሚያደርጋቸው አይደለም።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው።
ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት አኳያም መንግስት ረጅም ርቀት ተጉዞ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ደንግጓል።
በደርግ ሥርዓት ወቅት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ሃብት ባለቤት የመሆን መብት በመሠረቱ ተንዷል። ዛሬ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ ተረጋግጦለታል።
የአገራችን ህገ መንግሥት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል። ይህም በመሬት ስሪት ጉዳይ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በፅኑ መሠረት ላይ ለመጣል አስችሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬቱ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አለው።
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦላቸዋል። በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረትም ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። እነዚህ እውነታዎች የሚያሳዩት ነገር ቢኖር ዴሞክራሲ፣ የህግ የበላይነትና የህዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በአገራችን ውስጥ የሞት ሽረት ጉዳይ ሆነው በፅናት እየተተገበሩ መሆናቸውን ነው።