Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግድቡን ከዳር የማድረስ ጥረት

0 299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግድቡን ከዳር የማድረስ ጥረት

ዳዊት ምትኩ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከፍጻሜው ለማድረስ ህዝቡ ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ህዝቡ እያደረገ ባለው ያላሰለሰ ጥረት የህዳሴው ግድብ ኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨትም አቅሙም ይሁን ሰራተኖችን ከወቅታዊ የግድቡ ሁኔታዎች ጋር አቅቦ ከማሰራት አኳያ በተፈለገው መጠን እንዲጓዝ ማድረግ ችሏል። ይህ ህዝባዊ ጥረት ወደፊትም ተጠናክሮ በመቀጠል የግድቡን ግንባታ ከዳር እንደሚያደርስ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

የአገራችን ህዝቦች የፀረ-ድህነት ዘመቻ ከዚህ ቀደም አስሮ የያዛቸውን የ“አይቻልም” መንፈስን የሰበሩበት ታላቅ የልማት ፕሮጀክት አንዱና ዋነኛው የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ስራውን ከተጀመረ ከስድስት ዓመት በላይ ሆኖታል። የህዳሴያችን መደላድል ፈጣሪ ከሆኑት የልማት ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ ፕሮጀክት፤ የዚህ ትውልድ አሻራ በመሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ የልማት ተቋም ነው።

ከዘመናት በፊት ያለፈው ትውልድ ለእኛ አወርሶን የሄዱው የአክሱምና የላሊበላ ስልጣኔ- ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ጥበብ በመሆኑ በኩራት ለቱሪስት መስህብነት እየተጠቀምንበት ያን ትውልድ እያስታወስነው ነው። የእኛው ትውልድም ይህን ታላቅ የልማት ፕሮጀክት ዕውን አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በአዲስ ምዕራፍ ደማቅ የዕድገት ታሪክ ለመፃፍ ሌት ተቀን እየሰራ ነው።

ይህም ለመጪው ትውልድ ልማትንና ብልፅግናን እንጂ ልመናን ያለማውረስ ራዕይን የሰነቀ ነው።

የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በመነሳሳት ለግንባታው አጋርነታቸውን መግለፃቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ዛሬም መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ርብርብ ከማድረግ አለተቆጠቡም፡፡ ግድቡ ክድህነት መውጣት እንደሚችሉ አንድ መገለጫ በመሆኑ ህዝቦች በቦንድ ግዥና የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በየአካባቢው ሲዞር ተገቢውን እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህም በአሁኑ ወቅት ግድቡ ለሚገኝበት ከ60 በመቶ በላይ የግንባታ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዘመናት በማንም ሳይደፈር የቆየውን የዓባይ ወንዝን በመድፈር ለሀገር ልማት እንዲውል መደረጉ ሁሉንም ዜጋ በአንድ ልቦና ያስተሳሰረ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በዕውቀቱ ለመደገፍ የገባውን ቃል አሁንም ቀጥሏል፡፡ በዚህም ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ሃይሎች የፈለጉትንና ያሻቸውን ቢያወሩም ዛሬም ድረስ ለአንድ ሰከንድ እንኳን አልተቋረጠም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለግንባታው ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚል መንግስት ያዘጋጀውን ቦንድ በመግዛት የበኩሉን ተወጥቷል፤ እየተወጣም ነው፡፡ የቦንድ ግዥውን እያከናወኑ ያሉት የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ናቸው።

የኢፌዴሪ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የትኛውም የሀገራችን ቀደምት መንግስታት ደፍረው የማያውቁትን በአባይ ወንዝን የመጠቀም መብታችንን ካወጀ ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ እጅና ጓንት ሆኖ በተገኘው የልማት አጋጣሚ ያለ ዕረፍት እየሰራ ነው። ወትሮም ቢሆን ይህ ድህነት ያንገሸገሸው ህዝብ ‘እንስራና ሀገራችንን በጋራ እንገንባ’ የሚል መንግስት አጥቶ እንጂ፤ በተፈጥሮው ስንፍና ኖሮበት አይደለም፡፡ ስለሆነም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በውጭ ሀገር ያሉት ወገኖቻችን ጭምር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉት ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከምንም በላይ ህዝቦች በተፈጥሮ ሃብታቸው ማልማት እንዲችሉና ድህነትን ታሪክ በማድረግ ዘመቻ ላይ በጋራ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያነሳሳ ነው፡፡ በእኔ እምነት ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የሰንደቅ ዓላማችን ፕሮጀክት ሆኗል። ለዚህም አንድም ግድቡ ሲጠናቀቅ ሊሰጠው የሚችለው ጠቀሜታ እኛን ብቻ ሳይሆን ከዓባይ ጋር የተቆራኙ ሃገሮችን የሚጠቅም መሆኑ፣ ሁለትም ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶቻችን አቅማቸውን በመገንባት እንደገና ለተጨማሪ ታሪክ እንድንዘጋጅ አዲስ ምዕራፍ ሊከፍት የሚችል ማሳያ መሆኑ በምክንያትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡

የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነ ጀምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተሳሰብ ለውጧል፡፡ ዜጎች ዛሬ ላይ ሆነው የዚህን ታሪካዊ ግድብ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ግድቡ አልቆ ነገ ለሚወልዷቸው ልጆች ክስተቱን በታሪክነት የመናገር ጉጉታቸውን ጫፍ ላይ ያደረሰ ግድብ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

የአገራችን ህዝቦች ለስኬታማነቱ ህዝባዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ሲነሱም የማንንም ጉትጎታ ያለመሻታቸው ለድህነት ካላቸው ከፍተኛ ጥላቻ የመነጨ መሆኑም ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ እናም ይህ አቋማችን መቼም አይቀየርም። አይለወጥም። የትናንቱም ሆነ የዛሬው ብሎም የነገም አቋማችን አንድ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ ዋነኛ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ትውልድ ደግሞ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚያምን ነው። የትውልዱ ይህ አስተሳሰብ በመንግስታችን ፖሊሲም ላይ ዕውን እየሆነ ነው።

የየትኛውንም ወገን ጥቅም ሳንነካ በጋራ ተጠቃሚነት ብሎት ሁሉም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑበትን መንገድ የሚከተል ነው። እናም ትውልዳችን ይህን ፍትሐዊና ትክክለኛ አቋሙን የሚቀይርበት አንዳችም ዓይነት ምክንያት የለም።

ይህ አቋምም ሀገራችን በእኩልነትና በፍትሃዊነት እንድታምንና የምታካሂዳቸውን ማናቸውንም ፕሮጀክቶች ከዚህ አኳያ እንድትቃኛቸው አድርጓል። ስለሆነም በዓባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ይህን ዕውነታ መሰረት አድርጎ የሚከናወን በመሆኑ፤ ይህ የሀገራችን አቋም መቼም ቢሆን የሚቀየር አይሆንም።

አገራችን በህዳሴው ግድብ ላይ የምትከተለው አቋም የማንንም ጥቅም የማይነካ ፍትሃዊ ብቻ አይደለም። እውነታው ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትም ያለው ነው። በዚህም ሳቢያ ባለንበት አዲሱ ክፍለ ዘመን ይህን ሃሳብ ማራመዷ ሊያስመሰግናት ይገባል።

ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ግድቡን ከፍፃሜው ለማድረስ ሌት ተቀን እየሰሩ ነው። ይህንን ተግባራቸውን ማንም ሊያደናቅፍባቸው አይችልም። ግድቡ ለኢትዮጵያና ለህዝቦቸስ ታሪካዊ ነው። ቀደምት የተመጽዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ – ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የይቻላል መርህን በተግባር ማዋል ያስቻለ ብሎም ከራስ አልፎ በሚደረገው ሽያጭ የህዝቡን ውለታ በዕድገት የሚመልስ ነው። እናም አገራችንና ህዝቦቿ ይህን ለመፈፀም በቁርጠኝነት ተነስተዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy