Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፅንፈኛውና ጥቃቅን ግጭቶችን የማጦዝ ተግባሩ

0 299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፅንፈኛውና ጥቃቅን ግጭቶችን የማጦዝ ተግባሩ

ዳዊት ምትኩ

በአገራችን ላይ በማመሟረት የሚታወቀው ፅንፈኛው ኃይል የሚከሰቱ ጥቃቅን ችግሮችን በማጦዝ የችግሮቹ ምንጭ ፌዴራላዊ ስርዓቱ እንደሆነ አስመስሎ በማቅረብ ህዝብን እያደናገረ መሆኑን ሁሉም ኢትዮ;ጵያዊ የሚገነዘበው ይመስለኛል። ይህ የሁከት ሃይል እዚህም ሆነ እዚያ የሚፈጠሩ ችግሮች ስርዓቱ የፈጠራቸው በማስመሰል እያጎነ ህዝቡን እየሳሳተ ነው። ይሁንና የአገራችን ስርዓት በአሁኑ ወቅት ለተገኙት ውጤቶች መሰረት ነው። ሥርዓቱ በምንም መልኩ የችግሮች ምክንያት ሊሆን አይችልም።

ኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት እውን ያደረገችው የፌዴራሊዝም አወቃቀር ህዝቡን በልማት ተጠቃሚ ያደረገ ነው። የህዝቡን አጠቃላይ መብቶችንም ያስጠበቀ ነው። ሆኖም ፅንፈኛው ሃይል ይህን እውነታ ያወቀ ሊናገረው አይችልም። ምክንያቱም ሥርዓቱን ትክክለኛ ባልሆነ ገፅታ በማሳየት የተከናወኑትን ተግባሮች ሁሉ የመካድ ግብን አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ስለሆነ ነው።

ፅንፈኞቹ ሀገራችን ውስጥ አንድ ክስተት በተፈጠረ ወቅት የሚያካሂዱት ተመሳሳይ ዝማሬ እዚህ ሀገር ውስጥ ሆኖ ሁኔታውን በገለልተኝነት ለሚከታተል ሰው አስቂኝ ነው። አገር ቤት የተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ምንም ይሁን ምን ፅንፈኞቹ ሁከት ቀስቃሽ አሉባልታዎቻቸውን ሰንቀውና የነገር ካራቸውን ስለው በየሚዲያዎቹ ሲያቅራሩ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

አንዳንዶቹ ገንዘብ ተከፍሏቸው አሊያም ያለፈውን ማንነታቸውን በእዝነ ልቦና እያስታወሱ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋማቸውን ስለሚያንፀባርቁ ሃፍረት የሚባል ነገር የሚነካካቸው አይደሉም። አንዳንዶቹ ደግሞ በጥራዝ ነጠቅነት ሲያሻቸው ከምዕራቡ በል ሲላቸው ደግሞ ከምስራቁ ጎራ እየጠቀሱ መለፈፍን ስራዬ ብለው የያዙ ናቸው።

በተለይም እንደ ማንኛውም አገር ኢትዮጰያ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን በሥርዓቱ ላይ በማላከክ መጥፎ ገፅታን ለመፍጠር ይሯሯጣል። ሆኖም ሥርዓቱ የህዝቦችን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥ የቻለ ነው።

ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡

ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል፡፡ መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው፡፡

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡

የተገነባው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ያሰገኘ ነው፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅሙንና አስቸጋሪውን የትግል ምዕራፍ በድል አድራጊነት በቋጩ ማግስት በጋራ ተወያይተውና አምነው ያጸደቁት ህገ – መንግስት የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የመለሰ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይ ለሚያካሄዷቸው የጋራ አጀንዳዎች ዘላቂነትና ውጤታማነት ዋስትና የሰጠ ነው፡፡

ስለሆነም የመላው ህዝባችንን ጥያቄዎች የፈታውና ለዘላቂ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ዋስትና የሰጠው የኢፌዴሪ ህገ – መንግስት የፀደቀበት ዕለት በታላቅ ድምቀትና በልዩ ሁኔታ በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል፡፡

እርግጥ የሀገራችን ህዝቦች ከህገ – መንግስቱ ጋር በብዙ መልኩ እጅግ የጠበቀ ቁርኝት አላቸው፡፡ አዎ! የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህገ መንግስቱ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ህዝቡ ህገ- መንግስቱን ያቋቋመና የመንግስትንም አወቃቀር በፈቃዱ የነደፈ ነው። ይህም በህገ – መንግስቱ ላይ በግልጽ እንደሰፍር አድርገዋል፡፡

እንደሚታወሰው ያለፉት ሥርዓቶች የራሳቸው ህገ-መንግስት  የነበሯቸው ቢሆንም፤ ህዝባዊ መሰረት ግን አልነበራቸውም፡፡ ይህ የሆነው ባለፉት ሥርዓቶች በሀገራችን ህገ-መንግሥት የማይታወቅ በመሆኑ አልነበረም፡፡ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ በሀገራችን ሦስት የተጻፉ ህገ-መንግሥቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

ሆኖም በሃይለ ሥላሴ የአገዛዝ ዘመን የነበሩት ሁለት ህገ-መንግሥቶችም ሆኑ በደርግ ህገ-መንግሥት ወቅት ዘግይቶ የተረቀቀው ህገ-መንግስት የየሥርዓቶቹን ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ሥልጣን ማስጠበቂያ ብቻ ናቸው፡፡ ዋነኛ ዓላማቸው የገዢዎችን ሥልጣን ማራዘምና ሥርዓታቸውን ዘለዓለማዊ ማድረግ ነው፡፡

ያለፉት ሥርዓቶች ህዝባዊ አለመሆን በህገ-መንግሥታቸው ካሰፈሯቸው እውነታዎች በግልጽ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በህገ-መንግሥቶቹ ላይ ለህዝብ የሚጠቅሙ መሠረታዊ ጉዳዮች ካለመስፈራቸውም ባሻገር፤ የሰፈሩትም ቢሆን ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ተፈጻሚ የሆኑ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ገዢዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ህገ-መንግስቱን እንደ መጠቀሚያ ከመጠቀም ባለፈ፤ ተጨባጭ ተልዕኮው ምን እንደሆነ የሚያውቀው ጉዳይ አልነበረውም፡፡

በሀገራችን አዲስ ሥርዓት ዕውን ከሆነ በኋላ ህገ – መንግስቱ ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ሀገራችንና ህዝቦቿ በተለያዩ መስኮች እጅግ ውጤታማ  ተግባር አከናውነዋል፡፡ እነዚህን ውጤቶች አቅቦ ከመጓዝና ለአዳዲስ ድሎች ከመብቃት አኳያም፤ በአሁኑ ወቅት መንግስትና መላው ህዝብ በላቀ ቁርጠኝነት እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሀገራችን የድህነትና ኋላቀርነት ገጽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመለወጥ ላይ ይገኛል፤ ሂደቱም እጅግ በተጋጋለ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡

እርግጥ እዚህ ላይ በሀገራችን በሁሉም ዘርፎች የሚመዘገበው ዕድገት ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የህዝቡን ተጠቃሚነት ደግሞ የሀገራችንን ዕድገት የሚያፋጥን መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው፡፡

በአጠቃላይ በህዝቦች ሁለንተናዊ ፈቃድ ዕውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለፈውን መጥፎ ታሪክ የሻረ ከመሆኑም በላይ፤ መጻዒ ዕድላቸው ብሩህ እንዲሆን አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር ልማትን እውን በማድረግ ህዝባዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው፡፡

ይህ ነባራዊ እውነታ ግን በፅንፈኞቹ ሆን ተብሎ የተካደ ነው፡፡ የፅንፈኛው ሃይል ዓላማ እዚህ አገር ውስጥ ያለውን ሃቅ ማጣጣል ብቻ አይደለም፡፡ የህዝቡን ሰላም በመቀማት ለሁከትና ለአላስፈላጊ ብጥብጥ እየዳረገም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም ህዝቡ የፅንፈኛውን ፍላጎት በመረዳት ሊያወግዛቸውና ከተግባራቸውም እንዲቆጠቡ ሊያደርጋቸው ይገባል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy