Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፈንዱ ስራ አጥነትን እየቀረፈ ነው!

0 550

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፈንዱ ስራ አጥነትን እየቀረፈ ነው!

                                                     ታዬ ከበደ

መንግስት ለወጣቶች የመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር የሚቀርፍ፣ የገቢ ምንጫቸውን የሚያዳብርና ራሳቸውንና አገራቸውን የሚጠቅም መሆኑን ፈንዱ ወደ ክልሎች ከተለቀቀ በኋላ የታየ ለውጥ ነው። በአሁኑ ሰዓት ወጣቶች በየክልሉ እያከናወኑ ያሉትን ስራ ፈጠራ ከፈንዱ ጋር ያያይዛል።

ይህ ሁኔታ ወጣቶች መስራት የሚችሉበት ሁኔታዎች ከተሟሉላቸው ያሉባቸው መሰረታዊ ችግሮች ሊቀረፉ እእንደሚችሉ የሚያሳይ ነው። ተስፋን የሚያጭርም ነው። ወጣቶች ከመንግስት በተሰጣቸው ፈንድ ራሳቸውን እየቻሉ ነው። እንዲያውም ከራሳቸው አለፈው ቤተሰቦቻቸውንም እየጠቀሙ ነው። ስራ አጥነትን በመዋጋት ሰራ ፈጣሪ ሆነው ለአምሳያዎቻቸው አርአያም እየሆኑ ነው።

ዛሬ ወጣቱ ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር መንግስት እንደሚፈታው ተገንዝቧል ማለት ይቻላል። እንደ ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች ውስጥ ማልማት ካልቻሉ ባለሃብቶች ቦታ በመቀማት ጭምር ወጣቱን ወደ ስራ የማስገባት ተግባር እያከናወነ ነው። ይህ ሁኔታም መንግስት ምን ያህል ለወጣቱ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያረጋግጣል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ትኩረት የመስጠት ተግባሮች እውን እየሆኑ ነው።

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ላለፉት 26 ዓመታት በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል።

ከ26 ዓመት በፊት በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው እንዲሁም ከአፈና የብሔራዊ ውትድርና በመሸሽ ይሰደድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በገዛ አገሩ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው። ለዚህ አባባል ማሳያ የሆን ዘንድ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። በመሆኑም ወጣቱ በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም መንግስት ጋር በጋራ መስራት ይኖርበታል።

ወጣቱ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ እየተገበረችው ያለችው የልማት ዕቅድ ሶስተኛው ዓመት ላይ እንደሆነ ያውቃል። ስኬትም እየተመዘገበ ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የዕቅዱ ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ፤ በተለይም ወጣቱ ክፍል ለዚህ ስኬት የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል። ወጣቱ በእነዚህ የልማት ዕቅዱ ዓመታት የስራ ባህሉንና ተነሳሽነቱን እንዲሁም የቁጠባ ባህሉን አዳብሯል። በቀጣዩ ዓመት ተስፋው ከመንግስት ጋር ስለሆነ ስራውን ሁሉ ከእርሱ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሊከውን ይገባል።

የህብረተሰቡ የስራ ሃይል የሆነው ይህ ወጣት የስራ ባህልንና ተነሳሽነትን ማዳበርና ማጎልበት ለሌላ ጊዜ የሚተወው ጉዳይ አይደለም። ለነገሩ ታታሪውና ሰራተኛው ወጣት በዚህ አይታማም። ይሁንና የበለጠ ለማደግና የድህነት ካባችንን አውልቀን ለመጣል የስራ ተነሳሽነቱንና ባህሉን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው መንግስት የ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቀቃሽ ፈንድ በቅርቡ በመንግስት ከፀደቀ በኋላ ወደ ስራ ለመግባት ተችሏል። በፌዴራል ደረጃ ከተያዘው ከዚህ ተንቀሳቃሽ ፈንድ በተጨማሪ ክልሎች የራሳቸውን በጀት በማከል የወጣቱን የስራ አጥነት ሁኔታ ለመቀነስ ርብርብ ተደርጓል። ይህም ሁሌም በየዓመተ የሚቀጥል ተግባር እንደሆነ መንግስት ቃል ገብቷል። ይህ ፈንድ የወጣቱን ስራ አጥነት እየቀረፈ ነው።

ወጣቶች የዚህች አገር ገንቢዎች ናቸው። አገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ አገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።

እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ሁለት ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። ለዚህም ነው መንግስት ፈንድ አዘጋጅቶ ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ያደረገው።

ወጣቱ ከመንግስት የሚሻው ነገር ተጠቃሚነትን ነው። ይህን ለመከወንም መንግስት ለወጣቱ ስራ ፈጠራ ሊውል የሚችል ቢሊዮኖችን መድቧል። ወጣቱም ወደ ስራ ገብቷል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እያስመዘገበም ነው። የአገሩ ተስፋ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ደማቅ የተጠቃሚነት መንገዶችን እየተጓዘ ነው።

እርግጥ የወጣቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በልማቱ ልክ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ሆኗል ማለት አይቻልም። ያም ሆኖ ግን ዛሬም ከትናንቱ በተሻለ ሁኔታ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሩህ ተስፋዎች ተወጥነዋል። እንዳልኩት ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንደመሆናቸው በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ለመስራት ታቅዷል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

የሀገራችን ወጣቶች አካበባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መረጃዎች ያስረዳሉ። በዚህም በተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ፣ ወጣቶች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት የብድርና ቁጣባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቧል።

በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክ ሥልጠና ማዕከላት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የወደፊት የሀገራችን ተስፋ በሆኑ አምራች ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ በኢንዱስትሪዎችና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው የወደፊት የሀገራችን ልማታዊ ባለሃብቶች መፍለቂያ እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በመንግስት የስልጣን መዋቅር ውስጥ በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ወጣቱን ከተጠቃሚነት ጎራ ያፈናቀለውና በተገቢው መንገድም ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳላደረገው ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት አገራችን ውስጥ ለወጣቱ አዲስ መድረክ ተፈጥሯል። የወጣቱ ስራ ፈላጊ ድምፅ ይበልጥ ሰሚ፣ ይበልጥ ተደማጭ ሆኖ ገንዘብም ተመድቦለት ወደ ስራ ገብቷል። ይህ መድረክ የስራ አጥነት ችግርን በሂደት እየቀረፈ ነው። ስራ ፈጠራንም እያጎለበተ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ወጣቱ ማንኛውንም ስራ ባለመናቅ የፈንዱን አቅርቦት በተገቢው መንገድ ሊጠቀምበት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy