Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራላዊ ሥርዓትን ስንመርጥ ለምን?

0 392

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራላዊ ሥርዓትን ስንመርጥ ለምን?

ወንድይራድ ኃብተየስ

በዓለማችን ዛሬ ላይ በርካታ አገሮች ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓትን ይከተላሉ። አገሮቹ ይህን ሲመርጡ ከየአገሮቻቸው ነባራዊ ሁኔታ፣ ታሪክ፣ ወግ፣ ባህልና ከየህዝቦቻቸው ፍላጎት በመነሳት ነው። በቅድሚያ የፌዴራላዊ ሥርዓት ምንነትን በጥቂቱ እንዳስስ። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዝሃነት ለሚያስተናግዱ አገራት ፌዴራላዊ ሥርዓት ሊሰጥ የሚችለውን ጠቀሜታ መፈተሽ ተገቢነት አለው። ፌዴራላዊ ሥርዓት በማንኛውም ወቅት የሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮችን መፍታት የሚችልበት የፖለቲካ ምህዳር አለው። የሥርዓቱን ጥቅሞች እስከመጨረሻው ድረስ አሟጥጦ መጠቀም ከተቻለም በሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በቀላሉ ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሄ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።  

ፌዴራሊዝም የመንግሥት ሥልጣንና ተግባራት በፌዴራል የመንግሥት መስተዳድር እና በክልል መንግሥታት መካከል በሕገ መንግሥት በግልፅ የሚከፋፈልበት ሥርዓት ነው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ደግሞ የመንግሥት ሥልጣን፣ ኃላፊነት፣ አስተዳደር፣ ግብር የመሰብሰብና የፋይናንስ ሀብት የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት በአንድ ማዕከል ወይም ቦታ ብቻ አይጠራቀሙም፤ እንዲከማቹም አይደረጉም። በተለያዩ የሥልጣን ማዕከላት ወይም እርከኖች ይከፋፈላሉ። ይህም የፌዴራል ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ ያልተማከለ የመንግሥት ሥልጣን፣ ኃላፊነት፣ አስተዳደር እና የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት እንዳለው ያመላክታል።

የፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ውስጥ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ የመንግሥት መስተዳድሮችን በአንድነት ያዋቀረ ነው። ለተወሰኑ ጉዳዮች በጋራ መስተዳድር አማካይነት የራስ አስተዳደርን የሚያቋቁም የሥርዓት ዓይነት ነው። በዚህ ዓይነት የሥርዓት አወቃቀር የፌዴራሉ እና የክልል መስተዳድሮች የበላይና የበታች ግንኙነት ብሎ ነገር የላቸውም።

ምንም እንኳን በህገ መንግሥቱ ተለይተው ለየራሳቸው በተሰጣቸው ጉዳዮች እያንዳንዳቸው ያላቸው ሥልጣን የተለያየና የየራሳቸው ነፃነት ቢጠበቅም የመንግሥት አስተዳደር ሥራና ሂደት በሁለቱ አካላት መካከል የመደጋገፍና የመቆራኘት ሥራን የግድ ማለቱ አይቀሬ ነው። በመሆኑም በሁለቱ መስተዳድሮች የተወሰነ የኃላፊነት መደራረቦች እና መደጋገፍ እንደሚኖር ይጠበቃል። ይህም ሁኔታ ሁሉንም የፌዴራል ሥርዓቶች የሚያጋሯቸው  የወል ባህሪቸው ነው።

ሌላው ዐቢይ ጉዳይ የፌዴራል የፖለቲካ ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች የተፃፈ ህገ መንግሥት ያላቸው መሆኑ ነው። ከዚህ ሌላም ይህንኑ የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች በተለየ አግባብ ለህገ መንግሥት የበላይነት መረጋገጥ ልዩ ትኩረት መስጠታቸው ነው። ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የፌዴራል ሕገ መንግሥት የፌዴራል የፖለቲካ ማኅበረሰብ ከመገንባትና ሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆናቸውን መሠረት ከማድረግ አንጻር ነው።

የመንግሥትን ሥልጣን በሁለት ወይም ከዚያም በላይ ባሉ የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት መካከል ያከፋፈሉበት፣ ሥልጣንና ተግባር የወሰኑበት፣ ጥቅሞችን ማቻቻል መደራደርና ሥልጣንን ያደላደሉበት፣ የፌዴራል ሥርዓታቸውን ያዋቀሩበት፣ ያደራጁበትና ስለ አሠራሩ የደነገጉበት የበላይ ህግ መሆኑ ሌላው ቁምነገር ነው። የአገራቸው አጠቃላይ የማህበራዊ፣ የምጣኔ ሀብታዊ፣ የፖለቲካዊና የህግ ሥርዓት የሚመረኮዝበትና የሚገነባበት ዋና የህግ ማዕቀፍ መሆኑም ሌላው ጉዳይ ነው።

ህገ መንግሥት በአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ውስጥ በጋራ ጉዳዮቻቸው የጋራ የመንግሥት መስተዳድር ተቋማትን ለማቋቋም፣ ለየራሳቸው ለሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ከሌላው የራስ መንግሥት መስተዳድርን ለማቋቋም ፈቃድና ፍላጎታቸውን የገለፁበት ከፍተኛ የህግና የፖለቲካ ቃል ኪዳን ሰነድ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም የፌዴራል ሥርዓቱ  መስተዳድሮቹ ለህገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ግዴታ እንዳለባቸው ያስገድዳል።

በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከህገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ወይም የሚጋጭ ተግባር በህግ ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም የህገ መንግሥት የበላይነትን መቀበል ለፌዴራል ሥርዓት መተግበርና ስኬታማነት ቁልፉና ወሣኙ ነጥብ ማለት ይቻላል። የፌዴራል ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች ህገ መንግሥትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት መሬት የመውረዱን  ተገቢነት የሚያረጋግጠው የፌዴራሉ እና አባል ክልላዊ መስተዳድሮች ማንነትና ህልውና የሚመነጨው እንዲሁም የሚመረኮዘው በህገ መንግሥቱ በመሆኑ ምክንያት ጭምር ነው።

በፌዴሬሽኖች መካከል እንደ ምሣሌነት ከላይ የተጠቀሱት የጋራ ባህሪያት ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው። ይህም ሲባል ግን ሁሉም ፌዴሬሽኖች አንድ ዓይነት አወቃቀርን ይከተላሉ ማለት አይደለም።

በየአገራቱ ያሉ የፌዴሬሽን ሥርዓቶች ተመሣሣይ ባህሪ እንዳላቸው ሁሉ ልዩነቶቻቸውም የገዘፈ ነው። ለምን ቢባል አገራቱ የፌዴራል ሥርዓትን እንዲመርጡ ያስገደዳቸው የየራሳቸው የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የምጣኔ ሀብታዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የተለያዩ መሆናቸው ጭምር ነው።

ብዙዎች ምሁራን እንደሚስማሙት የአንድ አገርን ፌዴሬሽን ከሌላው የሚለየው በባህላዊ ብሔራዊ ልዩነት መጠንና ይህን ለማጣጣም በሚደረግ ሙከራ፣ በአባላቱ ብዛት፣ አንፃራዊ መጠንና ተመሳሳይነት፣ በመንግሥታት መካከል ባለው ህግ የማውጣትና የአስተዳደር ኃላፊነት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ግብር የመሰብሰብ ሥልጣን እና የፋይናንስ ሀብት ድልድል፣ የመማከልና ያለመማከል መጠን እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ውህደት መጠን፣ የማዕከላዊ ተቋማት ዓይነትና ይዘት፣ በመንግሥት መስተዳድሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት እና በመካከላቸው የሥራ ትብብርን ለማቀላጠፍ የሚጠቀሟቸው ተቋማትና ሂደቶች ብሎም የፌዴራልና የክልል መስተዳድሮች በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ የሚኖራቸው ሚና ወሣኝ ጉዳይ ናቸው በማለት ምሁራኑ ለማስረዳት ይሞክራሉ። ይህም የተለያዩ አገራት የተለያዩ የፌዴራል አወቃቀር ሂደትን እንደሚከተሉ የሚያሳይ ተጨባጭ ሁኔታዎች ይሆናሉ።

የፌዴራሊዝም ሥርዓት በተለያዩ የፖለቲካ ክፍሎች ሥር የሚኖር፣ ነገር ግን የጋራ ቋንቋና ባህል ያለውን ህዝብ ወይም በጋራ የፖለቲካ ክፍሎች ውስጥ በአባልነት የመሳተፍን ጥቅም የሚፈልግ ነገር ግን በቋንቋና በባህል የሚለያይ ህዝብን አንድ ለማድረግ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በፌዴራሊዝም ሥርዓት የሚፈጠረው የአንድነት ውጤት በፌዴሬሽኑ የተካተቱ የአባል መንግሥታት መስተዳድሮችን የተለየ መሆን የሚያዋህድ ወይም የሚያጠፋ ሆኖ መወሰድ አይኖርበትም።

የፌዴራሊዝም ሥርዓት አንድነት የሚያራምደው ፌዴሬሽኑን ያቋቋሙትን አካላት የተለየ ማንነት የራሳቸው ለሆኑ ጉዳዮች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን ብሎም ለጋራ ጉዳዮቻቸው በጋራ መስተዳድራቸው የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚወከሉበትንና የሚሳተፉበትን ተቋማዊ ማዕቀፍ በህገ መንግሥት ዋስትና የሚሰጥ የሥርዓት አወቃቀር ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ፌዴራሊዝም የሚያልመው በአንድና በተመሳሳይ ጊዜ አንድነትንና ህብራዊነትን በመጠበቅና በመኮትኮት ዓላማ ያለው መሆኑ ነው። በዚህም የተነሳ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ የጋራ እሴቶችን እና ሁሉ አቀፍ ማንነትን መገንባት ይቻላል።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ቁልፍ ተግባር የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከውጭ የሚመጣ ወታደራዊ ጥቃትን ወይም የጦርነት ሥጋትን በመከላከል ሠላም እና ደህንነት እንዲረጋጥ ይረዳል። ይህ ጉዳይ በተሳካላቸው አገሮች የፌዴራሊም ሥርዓትን በተመሠረቱበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ይህ ጥቃትንና ሥጋትን በጋራ የመከላከል እሴት ይስተዋላል። ለአብነት በአሜሪካ የውጭ ጥቃትን ወይም የጦርነት ሥጋትን በጋራ የመመከትና ሠላምና ፀጥታን ማስፈን ዓይነተኛ የፌዴራሊዝም እሴት ሆኖ እያገለገ ይገኛል። በአሜሪካ ኮንፌዴሬሽን ውስጥ ያሉት መንግሥታት ፌዴሬሽንን ያቋቋሙት አንዱ ዐቢይ ምክንያታቸው ከውጭ ሊቃጣባቸው የሚችሉ ጦርነቶችን እና የጦርነት ሥጋቶችን ለማምከንና ለመከላከል ጠንካራ የመከላከያ አቅም ለመፍጠር በማቀዳቸው ነው።

እነዚህ አገራት አገራቱ ፌዴራሊዝምን ለመምረጥ የተገደዱበት ሌለኛው ምክንያት  ከውስጣቸው በተፈጠሩት ኃይሎች አማካይነት አንድነታቸው እንዳይሸረሸርና እንዳይጠፋ ለመከላከል በማሰብ ነው። ያም ሆነ ይህ ግን በሁለቱም አብነቶች የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለተጠቀሱት እሴቶች ማራመጃ ሁነኛ መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግል የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን ለማወቅ ብዙ ትንታኔን መስጠት አያሻም።  

በዚህ ረገድ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ነፃነትን እና ዴሞክራሲን በማጠናከር በኩል ቁልፍ ሚና አለው። የመንግሥትን ሥልጣን እንደተለመደው ወደ ጎን በማለት በህግ አውጪው፣ በህግ አስፈፃሚውና በዳኝነት አካላት መካከል ብቻ በማከፋፈል ሳይሆን ፌዴራሊዝም የመንግሥትን ሥልጣን በአግድሞሽ በፌዴራል መስተዳድሩና በአባል ክልል መንግሥታት መካከል በማከፋፈል ሥልጣን ላይ ተጨማሪ ገደቦችን በመጣል ለግለሰቦችና ለማኅበረሰቦች የተግባር ነፃነትን እና የፖለቲካ ሥልጣን ምህዳርን ያሰፍናል። ከዚህም አልፎ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የማኅበረሰብንም ሆነ የግል ነፃነቶችን ለመጠበቅ የሚያገለግል ጠቃሚ የመንግሥት አወቃቀር መሆኑን ለመመልከት ይቻላል።  ለዚህም ሲባል ነው የፌዴራል ሥርዓት ተመራጭ የሚሆንባቸው ምክንያቶች።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy