Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሀገርን ከማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት መከላከል

0 522

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሀገርን ከማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት መከላከል

                                                                                 

                                                                                       መዝገቡ ዋኘው

የትኛውም አይነት ሚዲያ ቢሆን ትልቅ አቅምና ጉልበት አለው፡፡ በብዙ መልኩ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ይሆናል፡፡ በአንድ ሀገር የሀገርነት ሕልውና ውስጥ ሚዲያው የሚያበረክተው፤ መረጃን ለሕብረተሰቡ በፍጥነት ከማድረስ ተግባር አንፃር፣ አገልግሎቱ   ግዙፍ ነው፡፡ የሚዲያው ነጻነት መኖርና ማደግ ለሕብረተሰብም ሆነ ለመንግስት ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲዳብር በመንግስታዊ አሰራሮችም ረገድ ያሉትን ሕጸጾች ነቅሶ በማውጣትና በማሳየት እርምት እንዲወሰድባቸው በማድረግ ረገድ ሚዲያው የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡

ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዳይሰፍን የሚፈልጉ፣ በሕዝብ ውክልናና ተመራጭነት ስም ተቀምጠው  ለማን እንደሚሰሩ የረሱና የዘነጉ ክፍሎች ሚዲያው እኩይ ስራዎቻችንን ያጋልጥብናል ብለው ስለሚሰጉና ስለሚፈሩ የሚዲያውን ነጻነትና መረጃ የማግኘት መብት አያከብሩም፡፡ የሚዲያ ነጻነት በሀገሪቱ ሕገመንግስት የተከበረ ሕጋዊ እውቅና ያለው መሆኑንንም እስከመዘንጋት ይደርሳሉ፡፡ በቃል ብቻ ስለሚዲያ ነጻነትና መብት ደግመው ደጋግመው ሲናገሩ ለሰሚውም ለአድማጩም ግር  የሚያሰኝ ክስተት ነው፡፡

በሕትመቱም ሆነ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ዘርፍ ለሀገር ሰላም ልማት እድገት የሚከሰቱትንም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የራሳቸውን ጉልህ ድርሻ የሚወጡ መሆኑ ቢታወቅም ፈጣን ተደራሽነት ያለው ማሕበራዊ ሚዲያው የተዛቡ፣ በስሜታዊነትና በጥላቻ የተሞሉ፣ መሰረት የሌላቸው፣ በስሜታዊነት የታጀሉ ወሬዎችን በማሰራጨት ሀገራዊ ችግር የሆነበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡

የሕዝብን አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር የቆየ ባህልን ለመናድና እርስ በእርስ ለማናከስ ሌት ከቀን መስራት ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት የጎደለው የከፋ ጸረ ሀገርና ጸረ ሕዝብ ድርጊት ነው፡፡ በሀገር መጥፋት በሕዝብ መተላለቅ የሚገኝ ትርፍ የለም። በዚህ አይነቱ ነውረኛ ድርጊት ተጠቃሚ የሚሆኑት የኢትዮጵያን መጥፋት አጥብቀው የሚመኙት ጠላቶችዋ ብቻ ናቸው፡፡

ማሕበራዊ ሚዲያ መልካምና በጎ ጠቀሜታ ያለው የመሆኑን ያህል እጅግ የከፋ አደጋም ያስከትላል፡፡ ፈጣን የመረጃ ተደራሽነቱ ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍል በቀዳሚነት የሚይዝ ሲሆን በተሳሳቱ መረጃዎች፣ በፈጠራ ወሬዎች፣ በስም ማጥፋት ዘመቻዎች ወዘተ ያልሆነውን ሆነ፤ ያልተደረገውን ተደረገ ብሎ ያለበቂ መረጃ የሚያሰራጭ ሕግና ስርአት የማይገዛው፣ ድንበርና ወሰን አልባ በመሆኑ ሰላምን ያናጋል፤ ጥላቻን ያስፋፋል፡፡ የሕዝብን አብሮነት ያፋልሳል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ያጋጫል፤ ቁጣን በመቀስቀስ ያልተጠበቀ አደጋ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ለሰዎች ሕይወት እልፈት፣ ለሀብትና ንብረት መውደም፣ ከቀኤያቸውም ለመፈናቀልና ለመሰደድም ምክንያት ይሆናል፡፡

አይደለም እኛን በመሰለ ታዳጊ ሀገራት ሶሻልሚዲያው በእውቀትና በቴክኒዮሎጂ አድገናል ላሉትም የበለጸጉ ሀገራት ከባድ ችግር ሁኖ ፈተና ደቅኖባቸዋል፡፡ አንደኛውና በቀላሉ ለመዛመትና ለመድረስ የሚችልበት ምክንያት ማንኛውም የፌስቡክ ተጠቃሚ በሳንቲም  ቤቶች ውስጥ የተጻፉትን በጎም ይሁን መጥፎ ነገሮች በርካሽ ዋጋ ሊያገኘው ስለሚችል በቀላሉ ምርኮኛና ሰለባ ያደርጉታል፡፡ ቅብብሎሹና የስርጭት አድማሱ የሚሰፋው አንዱ ወደሌላው የሚያሸጋግረው በቀላሉ “ላይክ” እና “ሼር” በማድረግ ነው፡፡

በዚህም መልኩ በቀላሉ የትም ቦታ በከተማም ሆነ በገጠር መድረስ ይችላል፡፡ የሚገድበው ወይንም መልእክቱን ከመሰራጨት የሚያስቀረው ነገር አይኖርም፡፡ ስርጭቱ በኢንተርኔት በመሆኑ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች የተሳሳተና መርዘኛ የሆነ ሕብረተሰብን የሚያጋጭ መልእክት ማስተላለፊያ ዋነኛ መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ አደጋውም የከፋነው፡፡ እብሮነትን፣ ማሕበራዊ መስተጋብርን ያናጋል፡፡ ፍቅርን ወደጥላቻ ይለውጣል፤ በበቀል የተሞላ ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

የዛኑም ያህል ለመልካም ነገሮች አብሮነትን ፍቅርን ሰላምን ተቻችሎ መኖርን መከባበርን ሊያስተላልፉበት ይችሉነበር፡፡ ይቻላልም፡፡ ሀገርን ማጥፊያ ሰላም ማወኪያ ሕዝብን እርስ በእርስ ለማጋጨት መሳሪያ ሁኖ ማገልገል ግን የለበትም፡፡በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡የማሕበራዊ ሚዲያው አደጋነትና አሳሳቢነት የተለየ ትኩረትን የሚጠይቅነው፡፡

ሰሞኑን በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ ነገሪ ሌንጮና በሚኒስትር ዲኤታዋ ፍሬሕይወት አያሌው የተመራውና በአዋሳ ሲመክር የከረመው የፌደራልና የክልሎች የሕዝብ ግንኙነቶች መድረክ የማሕበራዊ ሚዲያው በደቀናቸው ወቅታዊ ፈተናዎች ላይ በሰፊው መክሮበት በስርአቱ ካልተመራና ካልተመከተ ሀገራዊ አደጋ ሊሆን እንደሚችል አስምሮበታል፡፡

በዚሁ የምክክር መድረክ የኮሚዩኒኬሽን መዋቅሮች የማሕበራዊ ሚዲያን አሉታዊ ጫና ለመቋቋምና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ወጥነት ያለው የአሰራርና የመረጃ አቅርቦት ስርኣት ዘርግተው መንቀሳቀስ ወሳኝና ቀዳሚ ተግባር መሆኑ በተሳታፊው በስፋት ተገልፇል፤ የጋራ መግባባት ላይም ተደርሷል፡፡

በዚሁ በሀዋሳ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን የጋራ ፎረም  ላይ በየደረጃው ያሉ የሀገራችን የኮሙኒኬሽን መዋቅሮች ከሀገራዊ አጀንዳ ቀረጻ ጀምሮ ፈጣን፣ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ማሕበራዊ ሚዲያው በሕብረተሰቡ ዘንድ እየፈጠረ ያለውን ውዥንብርና አሉታዊ ጫና ለመቋቋም የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው ተገልጾአል፡፡

ከልምድ እንዳየነው ማሕበራዊ ሚዲያው ለሰፊ አገልግሎቶች አመቺ ነው፡፡ ለአሉታዊ ገጽታዎች መበራከትም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ትኩረት የሚጠይቀውም በዚህ መሰረታዊ ምክንያትነው፡፡ ማሕበራዊ ሚዲያውን የኮሙኒኬሽን መሳሪያና ዋነኛ ተደራሽ የመገናኛ ዘዴ አድርጎ ለመጠቀም ወጥነት ያለው አሰራር በመዘርጋት ለግጭቶች መንስኤ የመሆን እድሉን ማጥበብና በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ በመግለጽ የፎረሙ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በስፋት አንሸራሽረዋል፡፡

ምንም እንኳን ማሕበራዊ ሚዲያው በርካታ አወንታዊ ሚናዎች ቢኖሩትም ጠባብነት፣ ትምክሕትና አክራሪነትን ሲያስፋፋ እየተመለከትን ነው፤ ምንጫቸው የማይታወቁ መረጃዎችን ያሰራጫል፤ የባእድ ባሕል ወረራን ያዛምታል፤ በዚህም ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍል ሰለባ ያደርጋል፡፡ አሉታዊ ጎናቸው የሚያመዝኑ መልእክቶችን በማስተላለፍ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ይጥሳል፤ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና መቃቃርን ያነግሳል፤ በተለይም ሕዝብና መንግስትን ለመለያየት በማያባራ ሁኔታ ይሰራል፡፡ በነዚህ ተግባራቱ መነሻነት ከተደራሽነቱ አንጻር የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ መሆኑ በውይይቱ ላይ በስፋት አወያይቷል፤ አነጋግሯል፤ ወደጋራ ውሳነ አድርሷል። “ሚዲያው”ለሀገራችን አዲስ ቢሆንም ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ በውይይቱ ወቅት ተሳታፊው አስምሮበታል፡፡ መድረኩ በተለይም በጋራ ሀገራዊ መልእክትና አጀንዳ ላይ ትኩረት በማድረግ በአስተሳሰብ ቀረጻና በቀውስ አያያዝ እንዲሁም በጠንካራ የመረጃ ፍሰት ላይ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መዋቅሩ በተደራጀ መንገድ  መስራት እንደሚገባው የተገለጸበትም መድረክ ነው፡፡

የኮሚኒኬሽን ዘርፉ የተጣለበትን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማስፈንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ የጋራ አገራዊ አመለካከት የማስረጽ ተልእኮውን መወጣት እንደሚገባው ተሳታፊዎች በስፋት የገለፁ ሲሆን፤ በተንሸራሸሩት አስተያየቶች ላይ ምላሽ የሰጡት የኤፌዴሪ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ ነገሪ ሌንጮ ዘርፉ ለጋራ ሀገራዊ ዓላማ ተገዥ ሆኖ የሚዲያና ኮሚኒዩኬሽን ተልእኮዎችን በአግባቡ የማወቅና የመተግበር ኃላፊነት አለበት፤ ግጭቶችን በመሰረታዊነት ለማስወገድ፤ ችግሮችን በያሉበት ነባራዊ ሁኔታ እውነታን መሰረት አድርጎ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ለዚህ ስኬትም የሕዝቦች የቆዩ የግንኙነቶችና የጋራ እሴቶች መጎልበት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡ 

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌው በበኩላቸው ተመጋጋቢና ፍሰታቸውን የጠበቁ እንዲሁም የሚናበቡ መረጃዎችን በማሰራጨትና የቀውስ ጊዜ አደረጃጀት በመፍጠር የማሕበራዊ ሚዲያውን ጫናም ሆነ ግጭቶችን ማስወገድ እንደሚገባ ለዚህ ደግሞ ወሳኙ ጉዳይ የዘርፉ ባለሙያ የአስተሳሰብ አንድነትን መፍጠር ብዥታ፣ የጎራ መቀላቀልና ስሜታዊነትን ማስወገድ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ ለአዎንታዊና አሉታዊ ጉዳዮች ተመጣጣኝ የሆነ ሽፋን መስጠት እንደሚገባም በውይይቱ ሂደት ተጠቅሶአል፡፡

ባጠቃላይ፣ አቅጣጫ የሳተና ከመንገዱ የወጣ ኮሚኒኬሽን የቀውስ ምንጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ፤ በእቅድ የሚመራ የቀውስ ወቅት ኮሚዩኒኬሽንን የማጠናከር ተግባር፤ ከሁሉም በላይ ሀገርን ከማህበራዊ ሚዲያ ጥቃት መከላከል ትኩረትን የሚሹ አበይት ጉዳዮች ናቸውና መደረግ ያለበት ሁሉ ከወዲሁ መደረግ ያለበት ሲሆን፤ ለዚህም በጉባኤው ላይ እንደተገላፀው፣ በሚዲያና ኮሚዩኒኬሽኑ ዘርፍ ያሉትን አካላት የጋራ ርብርብ ይፈልጋልና ከወዲሁ ለታሰብበት ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy